በጥቅምት ወር ነፋስ ከወዲህ ወዲያ በሚገማሸረው የስንዴ ማሳ ጠርዝ ላይ ቆም ብለው ከአጋሮቻቸው ጋር ሲያወጉ ያገኘናቸው አርሶ አደር ፈይሳ ቡታ፣ ሁሌም ሲቆጨኝና ጥያቄ ሲያጭርብኝ የነበረው የዳቦ ቅርጫት እየተባለ የሚነገርላት ኢትዮጵያ ዳቦ ሊሆን የሚችለውን ስንዴ ከውጭ ስታስገባ ማየቴ ነው ይላሉ::
አርሶ አደር ፈይሳ ነዋሪነታቸው በአርሲ ዞን ሔጦሳ ወረዳ ሲሆን፣ የቡቺ ሐቤ ባዶሳ ቀበሌ የሕብረት ስራ ማህበር አባል ናቸው:: እኛ ኢትዮጵያውያን ስንዴን በስፋት አምርተን በቅርባችን ላሉ ለጎረቤት አገራት መላክ የሚያስችለን አቅሙ እያለን ከውጭ አገር ማስገባታችን ሳያንስ ለልመና እጃችንን መዘርጋታችን ሊያስቆጨን ይገባል ሲሉ ይገልጻሉ:: እስካሁን የመጡበት ይህ ሁኔታም ከእንግዲህ ወዲያ ሁሉም በቁጭት ተነሳስተው እንዲሰሩ ሊያደርጋቸው እንደሚገባም ያስገነዝባሉ::
በእነ አርሶ አደር ፈይሳ ክላስተር ያሉት አርሶ አደሮች ስንዴ አምርተው ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚችሉ ራሳቸውን አሳምነዋል ወደ ስራ ገብተዋል፤ በዚህ ስራ ላይ ማተኮርን ትልቁ ተግባራቸው አድርገው ተነስተዋል::
ሰሞኑን ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ከግብርናው ዘርፍ የተውጣጡ ታዳሚዎች በአርሲ ዞን በስንዴ አምራችነቷ ከምትታወቀው ሔጦሳ ወረዳ በሻቂ ሻራራ ቀበሌ ተገኝተው የልምድ ልውውጥ ባደረጉበት ወቅት እርሳቸውም ልምድ ካካፈሉ አርሶ አደር አንዱ ናቸው:: እኚህ አርሶ አደር፣ የቡቺ ሐቤ ባዶሳ ቀበሌ ህብረት ስራ ማህበር አባል ከመሆናቸው በተጨማሪ እርሻቸውን የሚያካሂዱት በክላስተር (ኩታ ገጠም) ነው፤ አርሶ አደሩ የክላስተሩ ተጠሪም ናቸው:: በቁርጠኝነት የሚሰሩ አርሶ አደር ከመሆናቸው የተነሳም በርካታ አርሶ አደሮችን ያቀፈው ክላስተር መጠሪያ ስሙ ‹‹ፈይሳ ክላስተር›› በመባል ለመታወቅ በቅቷል::
ክላስተሩ በብዙ እንግዶችም የተጎበኘ ነው:: በ‹ፈይሳ ክላስተር› የታቀፉ አርሶ አደሮች ስንዴ የሚያመርቱት በ506 ሔክታር መሬት ላይ ነው:: ከዚህ ውስጥ ደግሞ 100 ሔክታሩን ለዘር ማብዣ አውለውታል::
አርሶ አደር ፈይሳ፣ ሁልጊዜ መለመን አስነዋሪ ከመሆኑም በተጨማሪ አሳፋሪም ነው ይላሉ:: አሳፋሪና አስነዋሪ ነው ያሉበትንም ምክንያት ሲያብራሩ፤ ኢትዮጵያ የጎደላት ነገር ስለሌላት ነው ብለው ኮራ ብለው ይናገራሉ:: የሰጡትን የሚያበቅል ሰፊ መሬትና በውሃም ቢሆን የታደለች አገር መሆኗን ጠቅሰው፣ ካለፈው የአመራረት ዘዴ ዋጋ ከፍላም ቢሆን ልትወጣ እንደሚገባ ነው የሚገልጹት::
‹‹ራሳችንን የግድ በምግብ መቻል ብቻ ሳይሆን አሁን በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተጀመረውን ስንዴ ለውጭ ገበያም የማቅረብ እቅድ ለማሳካት በትኩረት መስራት አለብን ይላሉ:: ይህን ደግሞ ተግባራዊ ለማድረግ አቅማችንን ሁሉ አሟጠን በመረባረብ ላይ እንገኛለን ብለዋል:: ያለምንም ማጋነን በእኛ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች የ‹ይቻላል›ን መንፈስ ተላብሰናል ማለት እደፍራለሁ ሲሉም ገልጸዋል::
በክላስተሩ 130 አርሶ አደሮች ታቅፈዋል፤ እነርሱም ስንዴ ወደውጭ አገር በመላኩ ረገድ የመጀመሪያዎቹ እንዲሆኑ እድል የተሰጣቸው መሆናቸውን ነው አርሶ አደር ፈይሳ የተናገሩት:: ይህን የመጀመሪያ የሆነ እድላቸውንም በአግባቡ ሰርተው ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኞች ስለመሆናቸው ያመለክታሉ::
አርሶ አደሩ፣ ስንዴ ለውጭ ገበያ የማቅረቡን ጉዳይ እንደምናሳካው በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን፤ ይህ ብቻ አይደለም፤ ወደፊት ደግሞ ስንዴ ከውጭ ከመግዛት፣ ከድህነት ለመውጣት ቁርጠኝነቱ አለን:: በመሆኑም እያንዳንዱ ከእኛ ጋር የሚሰራ ባለድርሻ አካል ታች ድረስ ወርዶ መስራት ይጠበቅበታል:: እንደእሱ ከሆነ ደግሞ ታሪክ መቀየር የሚያስችለን ሀብት በእጃችን አለና እናሳካዋለን ብዬ አምናለሁ ሲሉ ገልጸው፣ እኛ ጠንክረን ከሰራን ድህነትን የማናጠፋበት፣ ራሳችንን በምግብ ከመቻል ባለፈ ቀሪውን ዓለም የማንመግብበት ምንም ምክንያት አይኖርም ብለዋል::
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ገና ያልተነካ ሀብት ባለቤት ናት፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችም አሏት:: ምንም እንኳ የግብርናው ስራ አብዛኛውን ጊዜ ለአርሶ አደሩ ተትቶ የቆየ ዘርፍ ቢሆንም፤ አሁን ግን የተማረውም ሆነ ያልተማረውም ወደስራ መግባት አለበት::
አንዳንዶች ለግብርና የሚሰጡት ትርጉም ዝቅተኛ እንደሆነም አርሶ አደሩ ጠቅሰው፣ ለግብርናው ሙሉ አቅማችንን አውለን በትጋት ከሰራን ከየትኛውም ዘርፍ ባልተናነሰ ውጤታማ መሆን እንችላለን ነው የሚሉት:: እሳቸው ኮምባይነር እና ትራክተር ለመግዛት ጠይቀዋል:: ይህን የሚያደርጉት ደግሞ ሌላ ገቢ ኖሯቸው አይደለም፤ በግብርናው ዘርፍ ተግተው መስራት በመቻላቸው ነው:: አርሶ አደር ፈይሳ በእርግጠኝነት በግብርና መለወጥ እንደሚቻል ያመለክታሉ:: በትጋት ሰርተን ማምረት ከቻልን ወደውጭ ገበያ የማንልክበት ምክንያት አይኖርም፤ እንዲያውም ለውጭ ገበያ ማቅረቡ በጣም ቀላሉ ነገር ነው ይላሉ::
የሔጦሳ ዩኒየን ዘር ከማቅረብ ጀምሮ የግብርና ምርቶችን እስከመረከብ ድረስ አብሯቸው የሚሰራ መሆኑን የተናገሩት አርሶ አደር ፈይሳ፣ ሔጦሳ ዩኒየን ማለት የእኛ ድምር ውጤት ነው ሲሉ ይገልጻሉ:: ኬምቴክስ የተባለ የእርሻ ግብዓቶች አስመጭ የግል ድርጅት አብሯቸው የሚሰራ ድርጅት መሆኑንም ጠቅሰው፤ ልክ እንደዚህ ድርጅት ሁሉም ለሚሰራው ስራ የተሻለ ነገር ማቅረብ ቢችል አገራችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሷን ከድህነት ማውጣት ይቻላል ብለዋል:: የዘንድሮው እንደ ጅማሬ ቢሳካ በቀጣይ ዓመት የሚላከውን ምርት ከማሳደጋችንም በተጨማሪ ተፎካካሪ እስከመሆን እንደርሳለን፤ ከዚህ ደግሞ የሚያግደን አይኖርም ሲሉ አስረድተዋል::
የሔጦሳ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዘሪሁን መኮንን በበኩላቸው የሔጦሳ ወረዳ በስንዴ አምራችነቷ ቀደም ሲልም እንደምትታወቅ ተናግረው፣ ኩታ ገጠም በስፋት የሚሰራበት ወረዳ መሆኗ የዘንድሮውን ለየት እንደሚያደርገው ይጠቁማሉ:: አጠቃላይ ወረዳዋ ካላት መሬት ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የተሰራው በኩታ ገጠም መሆኑና ወረዳው ከ95 በመቶ በላይ በሜካናይዜሽን መጠቀሙ መሆኑን ያብራራሉ::
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ወረዳው ካለው ኩታ ገጠም እርሻ 1 ሺ 390 ኩታ ገጠሞችን አንድ ላይ ሰብስቦ እየሰራ ነው:: ከ26 ሺ ሔክታር መሬት ውስጥ ወደ 24 ሺ ሔክታር የሚሆነው የተዘራው በኩታ ገጠም ነው:: ከዛ ውስጥ 15 ሺ 952 ሔክታሩ በስንዴ ዘር ተሸፍኗል:: በዚህ መልኩ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ስንዴ ነው:: በተለይም በወይና ደጋና ቆላማው አካባቢ ስንዴ በከፍተኛ ሁኔታ እየተመረተ ይገኛል::
ከዚህም የተነሳ ዘንድሮ ወደ 50 ሺ ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል:: እንደ ኦሮሚያ ክልል ወደ ሶስት ሚሊዮን እንደ ፌዴራል ደግሞ አስር ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ ለመላክ ዝግጅት መደረጉን መረጃዎችን ጠቅሰው ተናግረዋል:: ከፍተኛ መስኖም ባይኖረን በክረምቱ ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርገን እየሰራን ስለሆነ ይህን እናሳካዋለን ሲሉም ገልጸዋል::
በጠቅላይ ሚኒስትራችን ሲገለጽ የቆየው ጉዳይ በስራ እየተገለጠ ነው ወይስ አይደለም የሚለው በተግባር መሬት ላይ እየታየ ያለ ጉዳይ ነውና ተነሳሽነቱን ወስደን በመስራት ላይ እንገኛለን የሚሉት ደግሞ የሔጦሳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ሁሴን ናቸው:: ይህን እውነት የመገናኛ ብዙኃኑ መጥተው ማየት ይችላሉ ሲሉም አረጋግጠዋል::
እርሳቸው እንደሚሉት፤ በውጭ አገር መገናኛ ብዙኃኑ በኩል እንደሚወራው ኢትዮጵያ በጦርነት እየታመሰች ያለች አገር አይደለችም፤ ያጋጠማትና ተገዳ የገባችበትን ጦርነት ሕግን በማስከበር ረገድ ወደፍጻሜው ማምጣት ብቻ ሳይሆን በልማቱም በኩል በአግባቡ እየሰራች ስለመሆኗም ሊነገርላት ይገባል:: ይህንንም በማምረት እያሳየች ትገኛለች:: እየበለጸገች ያለች አገር እንጂ ድህነቷ ላይ የቆመች አለመሆኗን ትልልቅ ነን የሚሉ መገናኛ ብዙኃን ሊያጤኑት ይገባል::
በአሁኑ ወቅት ስንዴን ከራሳችን አልፈን ለውጭ ገበያ እናቀርባለን ስንል እየሰራን ያለውን ስራ ተማምነን ነው ሲሉ ይገልጻሉ:: በኩታ ገጠም (በክላስተር) መስራት በመጀመራችን ትልቅ ለውጥ እያመጣን እንድንሄድ አስችሎናል ሲሉ አቶ መሀመድ ይጠቁማሉ:: ኩታ ገጠም ደካማውን አርሶ አደር ወደ ብርቱው አርሶ አደር የሚስብ ስራ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ውጤት እንድናስመዘግብ እያደረገን ያለ ነው ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል::
በኩታ ገጠም የዘራነውን 3ሺ ሔክታር ስንዴ ለውጭ ገበያ ለማዋል አቅደናል የሚሉት አቶ መሐመድ፣ ይህ ደግሞ እንደሚሳካ መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ:: እንዲያውም ከዚህም በላይ እናሳካዋለን ብዬ አምናለሁ ብለዋል::
እኛ በወረዳችን ያሉ አርሶ አደሮቻችንን ግብርና ወደሜካናይዜሽን ለውጠናል ብለን እናምናለን:: በወረዳው በአሁኑ ወቅት በበሬ የሚያርስ አርሶ አደር እምብዛም አታዩም:: ሁሉም የሚያርሰው በትራክተር፣ ሁሉም የሚያጭደው በኮምባይነር ነው ማለት ያስደፍራል ብለዋል::
በእርግጥ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይቻልም ያሉት አቶ መሀመድ፣ ለምሳሌ ሙጃን የሚያጠፋልንን የአረም መድኃኒት ዛሬም ቢሆን እንሻለን ይላሉ:: ስንዴን መሬት ስላለን ብቻ ዘርተን መቀመጥ ማለት አይደለም፤ ልክ እንደ አንድ ህጻን ልጅ መንከባከብን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው:: እንክብካቤው እንደተጠበቀ ሆኖ ቴክኖሎጂውን በአግባቡ ተጠቅመን የምንሰራ ከሆነ ደግሞ ኦሮሚያን ሁሉ ይዘን መውጣት እንችላለን ሲሉ በእርግጠኝነት ተናግረዋል:: እጅ ለእጅ ተያይዞ በመስራት ኦሮሚያን ብሎም ኢትዮጵያን የበለጠ ማሳደግ እንደሚቻልም ነው ያመለከቱት::
የአርሲ ዞን የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሙዘይን አማን የዞኑን ሰፊውን እርሻ የሚሸፍነው ስንዴ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘንድሮ በመኸር ሰብል ከተሸፈነው 656 ሺ ሔክታር መሬት ውስጥ 281 ሺ ሔክታሩ የተሸፈነው በስንዴ ነው ይላሉ:: ከአንድ ወር በኋላ ለአጨዳ ብቁ የሚሆነው ስንዴ ደረጃውን ጠብቆ እንዲታይ ካደረገው ምክንያት አንዱ የአረም መድኃኒቶችን በአግባቡ መጠቀም በመቻሉ ነው ሲሉ ይናገራሉ:: በተለይ ኬምቴክስ በመባል የሚታወቀው ድርጅት ከአርሲ ዞን አርሶ አደርና ግብርና ባለሙያዎች ጋር በቅርበት ሆኖ ሰፋፊ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ይገልጻሉ:: አርሶ አደሩ ኬምቴክስ የሚያቀርባቸውን የአረም መድሃኒቶች እንደ ፓላስ፣ ሱፐር ፓላስና ሌሎች ኬሚካሎችን በስፋት መጠቀሙ ለምርታማነቱ ትልቁን ድርሻ ማበርከቱን አስረድተዋል::
ባለሙያው እንደሚሉት፤ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው:: ዘንድሮ ደግሞ ስንዴ ላይ በትኩረት እየሰራ ነው:: እንደዞንም በስንዴ ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል:: ዘንድሮ ብቻ 281 ሺ ሔክታር በዘር ተሸፍኗል፤ ከአንድ ወር በኋላ ወደ ሰብል ስብሰባው የሚገባ ይሆናል::
በአጠቃላይ ወደ አስራ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ከስንዴ ብቻ እንጠብቃለን ያሉት ባለሙያው፤ ከዚህ ውስጥ 60 በመቶው ለቤት ፍጆታ፣ 40 በመቶው ደግሞ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው ብለዋል:: ከዚህ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ስንዴ እንደ አርሲ ዞን ብቻ በአገር ደረጃ ለውጭ ገበያ ከታቀደው ትልቁን ድርሻ ለመሸፈን ዞናችን ሰፊ አቅም አለው ሲሉ አስረድተዋል::
እርሳቸው እንዳሉት፤ አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ የመቀበል ዝግጁነቱ ጥሩ ነው፤ አስፈላጊ የሆነውን ግብዓት በሰዓቱ በማቅረቡ ረገድ ግን ክፍተት አለ:: በጥቅሉ የግብዓት ችግር አለ፤ በዚህ ጉዳይ ሁሉም ባለድርሻ ቢተባበር መልካም ነው፤ ከዚህ በላይ ምርታማነትን ለመጨመር ግብዓት መሟላት ብሎም ሁሉም እንደየደረጃው መትጋት ይጠበቅበታል::
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በኦሮሚያ ክልል በዘር ለመሸፈን ከተዘጋጀው 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ እስከ አሁን በኩታ ገጠም የለማውን ጨምሮ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚሆነው በዘር ተሸፍኗል። በስንዴ ብቻ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ለማልማት ርብርብ እየተደረገ ሲሆን፣ በእስካሁኑ ሂደት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ልማት በስንዴ ብቻ መሸፈን ችሏል::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2015