አዲስ አበባ፡- በአማራና ትግራይ ክልሎች መካከል ያለው የቃላት ጦርነት ለጊዜው ጋብ ቢልም ልዩነቱ በመሰረታዊነት መፈታት እንዳለበት ምሁራን አሳሰቡ።ችግሩ ቶሎ መፍትሄ ባለማግኘቱ ወደሌሎች ክልሎች እየሄደ መሆኑንም ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁሩ አቶ የማነ ካሳ እንደሚሉት በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የተፈጠረውን መካረር መፍታት የሚያስችል በቂ አሰራር ቢኖርም እስካሁን አለመፈታቱ ለችግሩ ተገቢው ትኩረት አለመሰጠቱን ያሳያል።
እንደ አቶ የማነ አገላለፅ ችግር እያስከተሉ ከሚገኙ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የሆነው የወሰን ጉዳይ ሲሆን፣ ይህንን በህገ-መንግሥቱ (አንቀፅ 48) መፍታት እየተቻለ ክልሎች በሱ እየተዳኙ አይደለም። ትግራይና አማራን የሚያስተዳደሩት ፓርቲዎች የአንድ ድርጅት አባል ሆነው ሳለ እርስ በእርስ መግለጫ እየተሰጣጡ ነው። ይህ ምን ያህል እንደተራራቁ ነው የሚያሳየው ብለዋል።
ለመሆኑ «በአሁኑ ሰዓት አገሪቱ መረጋጋት ላይ ባልሆነችበት ሰዓት ለምን በየቦታው ጥያቄዎችን ማንሳት አስፈለገ?» ሲሉ የሚጠይቁት አቶ የማነ «ይህ የሚሆነው ኃላፊዎች የቤት ሥራቸውን ባለመሥራታቸው ምክንያት ህዝብን ለማዘናጋት ሲሉ የሚያደርጉት ነው» ሲሉም እራሳቸው ይመልሱታል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር መምህር የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው እንደገለፁት በአማራና በትግራይ ክልል አመራሮች መካከል የተከሰተው መካረር መንስኤ ፓርቲዎቹ ችግሩን ተነጋግረው መፍታት ባለመቻላቸው የተፈጠረ ነው፡፡ ፓርቲዎቹ ቢስማሙ መፍታት አያቅታቸውም ነበር።
ምሁራኑ እንደሚሉት በአማራና ትግራይ ክልሎች መካከል ያለው መካረር ለጊዜው ጋብ ቢልም መንግሥት ችግሮችን መፍታት ችሎ ሳይሆን ችግሩ ወደሌሎች ክልሎች ስለሄደ ነው። ግጭቶቹ ከአማራና ትግራይ አልፈው ወደ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ከመቀጠላቸው በፊት ሊታሰብበት ይገባ ነበር። መንግሥት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅ ድረስ ህገመንግሥቱ መብት እየሰጠው ይህ ሁሉ ሲሆን ዝም ማለቱ ተገቢ አይደለምና ህግ ሊያስከብር ይገባል ይላሉ።
እንደ ምሁራኑ ገለፃ መንግሥት የህዝብን ስሜት፣ ፍላጎትና ጥያቄ ማድመጥ ይገባዋል። በራሱ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ልዩነትም በመነጋገርና በመወያየት ባስቸኳይ ሊፈታ የግድ ነው።
ምሁራኑ እንደገለፁት የአማራና የትግራይ ህዝቦች ለዘመናት አብረው የኖሩና ብዙ የጋራ ታሪክ እና ባህል ያላቸው ናቸው። የተፈጠረው መካረር የህዝቦች ሳይሆን በኢህአዴግ ፓርቲዎች መካከል ያለው የእርስ በእርስ አለመተማመንና እመራዋለሁ የሚሉትን ህዝብ በአግባቡ መምራት ባለመቻላቸው የተፈጠረ ነው። ፓርቲዎቹ አዲስ አበባ ላይ ይስማሙና ተመልሰው ወደየክልላቸው ሲሄዱ ይለያያሉ፤ በመካከላቸው ከፍተኛ የመጠራጠር ስሜት አለ። በዚህ የተነሳም ተግባብተው መምራት አልቻሉም። ይህ ሁኔታ ደግሞ አሁኑኑ መገታት አለበት፤ አንድ ሊሆኑና እንደ ኢህአዴግ ሊቆሙ ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድም ባለፈው ሳምንት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ በአማራና ትግራይ ክልሎች መካከል የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች ቢነሱም ለፀብና ግጭት የደረሰ አለመሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል ሱማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ወደ ግጭት ገብተው እንደነበር ይታወሳል፤ ከግጭቱ ግን ሁለቱም ክልሎች ያተረፉት ኪሳራ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ገሎ ምንም አይነት ጥያቄ መመለስ እንደማይቻል ሱማሌና ኦሮሚያ በተግባር አረጋግጠዋል፡፡ አማራና ትግራይ አንዱ ሌላውን በመውጋት ዘላቂ ሰላምን በሚያረጋግጥ መንገድ ምንም አይነት ጥያቄ መፍታት አይቻልም፤ የሁለቱ ክልል ህዝቦችም ይህንን ጉዳይ በደንብ ይገነዘባሉ ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2011
ግርማ መንግስቴ