ድስት ጠጋኙ አባ ጎሹ የአይኖቻቸውን እዳሪ በእጃቸው እያባበሱ የማለዳዋን ጀምበር ተከትለው ከቤት ወጡ።ለአንድም ቀን ከጎባጣ ጀርባቸው ላይ ወርዶ የማያውቀው አሮጌ ማዳበሪያ በስብርባሪ ብረታ ብረት ተሞልቶ ዛሬም እንደታዘለ ነው።የሁልጊዜም ጸሎታቸው የማዕድ ቤት ድስቶች ሁሉ ተሸንቁረው እሳቸውን እንዲጠብቁ ነው፡፡
አባ ጎሹ ቀይ ናቸው።ቀይነታቸው ግን አይታይም። ወይቧል። በውብ የሽማግሌ ፊታቸው ላይ እድሜ የተጫነው የደስ ደስ ይታያል። የእድሜያቸውን አሀዝ ባያውቁትም በነሉሲ ዘመን እንደነበሩ ግን ገጻቸው ምስክር ነበር። ቁመታቸው ረጅም ነው… ከለግላጋነታቸው የተነሳ ከእግዜር ጋር በቅርበት የሚነጋገሩ ብቸኛው ፍጡር አስመስሏቸዋል። የሰፈራቸውን አቧራማ መንገድ ጨርሰው …. ራቅ ካለ መንደር ደረሱ።…….ከጎዳናው ግራና ቀኝ ካለው ቤት ላይ አይኖቻቸውን እያንቀዋለሉ
“ቀዳዳ ድስት ያለው.. ቀዳዳ ድስት ያለው.. አሮጌ ድስት አዳሹ መጥቷል አባ ጎሹ። እያሉ ከአንዱ ሰፈር ወደ አንዱ ሰፈር ኳተኑ። እሳቸው የእለት ጎርሳቸውን የሚሸፍኑበትን አንድም የጥገና ስራ ሣያገኙ አብራቸው የወጣችው የማለዳ ጀንበር ጥላቸው ሸሸች።አባ ጎሹ በየመንገዱ የሚያገኙትን የሰው ቤት በቅልውጥና እያማተሩ” ቀዳዳ ድስት ያለው ….. ሰባራ ድስት ያለው አሮጌ ድስት አዳሹ መጥቷል አባ ጎሹ።በማለት እንደ እድር ለፋፊ ጉሮሮአቸው እስኪንጣጣ ጮሁ።ይህ የራሳቸው ግጥም ነው….. በእድሜ የተማሩት ….. በዘመን ያጠኑት የእንጀራ ገመድ።የደንበኞቻቸውን ቀልብ ለመሳብ የዘየዱት መላ፡፡
በሰፈሩ ውስጥ ድስትና ወይዘሮ የሌለ እስኪመስል ድረስ ጥሪያቸውን የሰማ አንድም ሰው አልነበረም።ሆዳቸውም መራቡን ሊያስታውቅ እንደ ሰኔ ሰማይ አጉረመረመ።እውነት ለመናገር የዘመናቸውን ገሚሱን ያሳለፉት በጾም ነው።ሁሉም ቀን ለእሳቸው የጾም ቀን ነው።…የድህነት ጾም።አሁንም አልበሉም።ትላንት የባቄላ አሹቅ እንደቀመሱ ነው።ሁሌም ጾመኛ ሁሌም ምኞተኛ ናቸው…. ሽማግሌው አባ ጎሹ፡፡
በአዋጃቸው መሃል አንድ የተስፋ ድምጽ ሰሙ።አንዲት ወይዘሮ ሴት ‹‹ወዲህ ይግቡ›› ስትል ጠራቻቸው። ከመግባታቸው ወስፋት የሚቀሰቅስ የምግብ ሽታ ተቀበላቸው።በአምሮት ወስፋታቸው ተንጫጫ፡፡
ወይዘሮዋ ከወደማዕድ ቤት በኩል ሁለት እኩል መጠን ያላቸውን መናኛ ድስቶች ይዛ ተመለሰች፡፡
“ይሄውሎት በደንብ አድርገው ይስሩት” ስትል አቀበለቻቸው።ብዙም ጎልማሳነት ባልሸሻቸው አይኖቿ ስታያቸው ቆይታ ካጠገባቸው እብስ አለች። ስትራመድ ዳሌዋ ይደንሳል….. ወጣትነት ከድቶት በጉልምስና እድሜ ላይ ቢሆንም ወንድ ልጅ ለማነሁለል ሀይል ነበረው፡፡
አባ ጎሹ ሁለቱን ድስቶች አገላብጠው ካዩ በኋላ ከማዳበሪያው ውስጥ መዶሻና መጠገኛ ብረት በማውጣት መቀጥቀጥ ጀመሩ።ቀጥቅጠው ካቆነጇቸው መንትያ ድስቶች የሚያገኟትን አስር ብር በምን እንደሚያጠፏት በልባቸው እቅድ ጀመሩ።እንዲህ በደከማቸውና ሕይወት ባስመረረቻቸው ሰዓት የመጠጣት… ጠጥቶም የመስከር አመል አለባቸው። በዚህም በሚያገኟት አስር ብር ሊጎነጩ እቅድ ያዙ። ቀጥቅጠው ያሳመሩትን አሮጌ ድስት ለወይዘሮዋ ሊሰጡ… ድምጽ አሰሙ ……… እሜቴ የሚል፡፡
የጥሪ ድምጽ የሰማቸው ወይዘሮ ከለስላሳ ጸጉሯ ላይ የተንሸራተተ ሻሽዋን በእጆቿ እያጠበቀች ወደ ውጪ ወጣች።
“ይሄውልሽ ኩችም አድርጌ አበጅቼልሻለሁ። የፈለግሽውን ነገር ልታበስይበት ትችያለሽ” ሲሉ አቀበሏት።
ወይዘሮዋ የድስቶቹን ቂጥና ሆድ ካየች በኋላ ስንት ነው? ስትል ጠየቀች፡፡
‹አስር ብር ይበቃኛል› መለሱላት፡፡
በሻሿ ጠቅልላ ጆሮ ግንዷ ስር የደበቀችውን አስር ብር አውጥታ ሰጠቻቸው፡፡
አባ ጎሹ ብርቅ የሆነችባቸውን አስር ብር ሰባት ጊዜ አጣጥፈው ከሱሪያቸው ስር ካለ ሌላ ኪስ ውስጥ በመክተት ወይዘሮዋን አመስግነው ሄዱ።ቀዳዳ ድስት ያለው፣ አሮጌ ድስት አዳሹ መጥቷል አባ ጎሹ ከማለታቸው ከወጡበት ቤት ቀጥሎ ካለው ሶስተኛው ግቢ ውስጥ ጥሪ ሰምተው ወደዛው አመሩ።የጎረቤት ሰዎች እርስ በእርስ እየተጠራሩ ለአባ ጎሹ የገቢ ምንጭ ሆኑ።ጀምበር ከጠለቀች ጀምሮ አባ ጎሹ አምስት አሮጌ ድስቶችን አደሱ።እንዳሰቡት ርሀብና ድካማቸውን ሊረሱ ቀን ሙሉ ተንከራተው ያገኟትን ሃያ አምስት ብር ጨብጠው ብረት የሞላውን አሮጌ ማዳበሪያ እንደተሸከሙ ወደ መሸታ ቤት አቀኑ። ገና በር ከመድረሳቸው የአረቄው ሽታ ሰነፈጣቸው። የጀርባቸውን ሸክም ሰዋራ ቦታ ደብቀው ወደ ውስጥ ገቡ። ሃያ አምስት ብሯን ዳግመኛ ቆጥረው ለማውጣት እንዲመቻቸው በማሰብ ከደረት ኪሳቸው ውስጥ ከተቱት፡፡
ከፊት ለፊታቸው አንድ ወጣት ጨለምለም ካለ ቦታ ላይ ተቀምጦ እያያቸው እንደሆነ አልተረዱም ነበር።ወጣቱ የጎፈረ ጸጉሩን በእጁ እያፍተለተለ የአባ ጎሹን ሃያ አምስት ብር እንዴት መውሰድ እንዳለበት ሲያሰላስል ነበር፡፡
አባ ጎሹ ገና ቂጣቸው መሬት ከመንካቱ አረቄ አዘዙ። የናፈቁትን መጠጥ በአንድ ትንፋሽ ጨለጡት። ሆዳቸው ቅጥል፣ አንጀታቸው እርር አለ።ደግመው ጠረጴዛውን ቆረቆሩ እስከ አፍጢሙ ተሞላላቸው።አባ ጎሹ ያለወትሯቸው ቶሎ ሰከሩ።ደክመው የለ?……ተርበው የለ?
ወጣቱ ከዚህ በላይ ጊዜ ማጥፋት አልፈለገም።የአባ ጎሹ ስካር የፈለገውን እንዲያደርግ እድል ስለሰጠው ከተቀመጠበት ተነሳ።በዘየደው መላ የደረት ኪሳቸውን ፍራንክ ሊወስድባቸው የቅርብ ዘመዱን ያገኘ ያህል ደስ በሚል ፈገግታ ተንደርድሮ አቀፋቸው ።‹እንዴት ኖት?…..ሰላም ኖት ? ጠፉ እኮ.. በሰላም ነው ? ሰላምታው ማብቂያ አልነበረውም።ወጣት ትከሻውን ስንት ነገር የተሸከመ አዛውንት ትከሻቸው ላይ እያጋጨ የሰላምታ መአት አወረደባቸው፡፡
አባ ጎሹ በወጣቱ ሰላምታ ተደስተው አቅፈው አገላብጠው ሳሙት።ቢያውቀኝ ነው እንጂ በሚል የደግነት ስሜት ሣያውቁት አጻፋቸውን መለሱለት፡፡
ወጣቱ እንዳሰበው የአባ ጎሹን ሃያ አምስት ብር ከደረት ኪሳቸው ውስጥ ሞጭልፎ ተሰወረ። ደማቸውን፣ የሽማግሌ ወዘናቸውን ነጥቆ እብስ አለ።አባ ጎሹ አገር ሰላም ብለው አረቄያቸውን ይኮመኩማሉ። በአንድ ትንፋሽ ጭልጥ፣ ሌላ ሙልት እሱንም ፉት.. ጭልጥ.. ጠረጴዛ መቆርቆር።አፍና ብርጭቆአቸው ሳይለያይ ሰዓቱ ነጎደ።ፈጣኖቹ አስተናጋጅ ከአባ ጎሹ ፊት ሣይሸሹ በአፍ..በአፉ ይሞሉላቸዋል።አባ ጎሹ የደረታቸውን ሃያ አምስት ብር ተማምነው ዶሮ እስኪጮህ ድረስ ጠጡ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምተ 11 ቀን 2015 ዓም