
በዛሬው እትማችን እንነጋገርበት ዘንድ አቅደን የመጣነው ስለ ”አገር በቀል እውቀት” ምንነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና ይዞታ ነውና አቻ ትርጉሙ Indigenous Knowledge የሚለው፤ በተለዋዋጭነትም Traditional Knowledge መሆኑን ከወዲሁ መግለፅ ተገቢ ይሆናል።
ብያኔውን በተመለከተ ከዚህ በፊት በተያያዥ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ በተለዋወጥንበት ወቅት ”አገር በቀል እውቀት ማለት …” ካልን በኋላ፤
አገር በቀል እውቀት ማለት በውስን አካባቢዎች ላይ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ገጽታዎች ዙሪያ ላሉ ክፍተቶች መፍትሄ ይሆኑ ዘንድ ባህላዊ በሆነ መንገድ በአንድ ወይም በተወሰኑ ሰዎች የሚመነጭና የሚተገበር እውቀት ነው፡፡ በእንግሊዘኛው በዋናነት “Indigenous knowledge” የሚለው የሚገልፀው ሲሆን “Traditional knowledge“ ወይም “Local knowledge” የሚሉትም ሊተኩት ይችላሉ፡፡
የማህበረሰብ እውቀት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ የህይወት ገፅታዎች የሚዳሰሱበትና መፍትሄ የሚሰጥበት የተገለፀና ያልተገለፀ እውቀትና ልምድን ያጠቃለለ ነው፡፡ በብዙ ዘመናት ልምድ የዳበረና በባህል ውስጥ ሰርፆ ከትውልድ ትውልድ በታሪክ፣ በዘፈን፣ በአባባል፣ በእምነት እና በሌሎች መንገዶች በአካባቢው ቋንቋ የሚተላለፍ እውቀት ነው፡፡ እውቀቶቹ በተገኙበት ቦታ ምንጭ ለሆኑት ግለሰብና ቤተሰብ የተሰጠ ልዩ ጥበብ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን በአብዛኛው ግን በጊዜ ሂደት በአካባቢው ማህበረሰብ እየተለመደና እየሰፋ ሲመጣ የማህበረሰቡ የጋራ ንብረት ይሆናል፡፡
እንደ አገራችን ባሉ በተፈጥሮ ሀብት በበለፀጉ አገራት በተለይ በግብርና፣ በጤና እና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች የአገር በቀል እውቀቶች እና ቴክኖሎጂዎች ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ በተጨማሪም በትራንስፖርት ዘርፉ የአገር በቀል እውቀቶች እና ቴክኖሎጂዎች ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ በግብርናው ዘርፍ የእፅዋትና አዝርእት ተከላ፣ መረጣና አሰባሰብ ሂደት፣ በእንስሳት እርባታና አያያዝ ስርዓት እና ለመሳሰሉት ተግባራት መሠረት የሚሆን በግለሰብና በማህብረሰብ ውስጥ የዳበሩ ብዙ እውቀቶች አሉ፡፡ በማለት አገራዊ ምንጮችን (ከወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያገኘነውን መረጃ) ጠቅሰን ማስቀመጣችን ይታወሳል።
እርግጥ ነው ከአንዳንድ የሙያና ጥናት ዘርፎች ህክምናና ቋንቋ ጥናት (medicine እና linguistics) አካባቢ ካልሆነ በስተቀር አገር በቀል እውቀት ይሁነኝ ተብሎ በትምህርት ተቋማት ውስጥ አይሰጥም። በእነዚህ የጥናት መስኮች ግን ለአገር ባህል እውቀቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራባቸዋል። ይህን ስንል ግን ሁሉም ጋ ማለታችን አይደለም፤ የነቁት ጋ እንጂ።
ባጭሩ አገር በቀል እውቀት (በነገራችን ላይ፣ እኛ አገር በቀል እውቀት እያልን እንነጋገር እንጂ በባለሙያዎች እይታ Indigenous knowledge, Traditional Indigenous knowledge; Indigenous Knowledge Systems and Practices (IKSPs) በሚል ተለያይተው የሚጠኑ ዘርፎች መኖራቸውን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል። ይህንን ስንል ግን የሚጋሯቸው ጉዳዮች ወይም ብያኔዎች የሉም ማለታችን አይደለም።)
ይህንን ስያሜ፣ ገነነ ብዙነህ ”ሀገረሰብ ትምህርት በኢትዮጵያ” በምትልና ምንም ብቀጥን ጠጅ ነኝ … አይነት ፈገግታን የምታሳየው ስራቸው ውስጥ ”አገርፈለቅ እውቀት” (2006 ዓ.ም) ማለታቸውን አክለን፤ ለዛሬውም ይኸው ብያኔ ይሰራልና በዚሁ አልፈነው ወደ ፋይዳና ይዞታው እንሂድ። ከአፍሪካም እንጀምር።
ኤፕሪል 2022 ለአደባባይ የበቃውና African Indigenous Knowledge Systems and the World የሚል ርእስ የተሰጠው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ አፍሪካ የሚያዋጣት የራሷን አህጉር በቀል እውቀቶች ይዛ ወደ ስራ መግባት እንጂ ሌላ አይደለም።
ናይጄሪያዊው ስመ ጥር ደራሲ ቹና አቼቤ በዝነኛ ስራው (Things Fall Apart, 1958) አጉልቶ ያሳየው ይህንኑ የናይጄሪን አገር በቀል እውቀቶች ሲሆን፣ ጊዜውን በተመለከተም በተለይ ቅድመ ቅኝ አገዛዝ የነበረውን በማሳየት ድህረ ቅኝ (በ19ኛው ክፍለ ዘመን) አገዛዝ የደረሰውም ውድመት ያመላከተ ስራ ነው።
ይህ መጽሐፍ በአቢይነት የሚያንፀባርቀው በቅድመ የአውሮፓውያን ቅኝ አገዛዝ የናይጄሪያው ቱባው አገር በቀል እውቀት ምን መልክ እንደነበረው፤ ማንነትን፣ ባህልን … ከመግለፅና ማንፀባረቅ አኳያ የነበረውን ጉልህ ሚና ሲሆን፤ በአውሮፓውያን ቅኝ አገዛዝ ዘመን ያንን ቱባ አገር በቀል እውቀት ከስሩ በመንቀል ናይጄሪያውያንን ከማንነታቸው የመነጠል ክፉ ስራ እየተሰራ እንደ ነበር፤ ይህ ደግሞ በፍፁም መሆንና መቀጠል እንደሌለበት አስረግጦ የሚሄድ ሆኖ፤ ይህም በኢቦ ማህበረሰብ (Igbo society)ና ከሱ በወጣው፣ በዋናው ገፀ ባህርይ Okonkwo አማካኝነት በሚገባ የተንፀባረቀ ሆኖ ታይቷል።
ይህ በልቦለድ መልክ የቀረበ፣ በአቀራረቡ ቀላል የሆነ፣ በናይጄሪያ የኢቦን ማህበረሰብ ባህልና አገር በቀል እውቀት ፍንትው አድርጎ ያሳየ …. መጽሐፍ ወደ እውነቱ ወይም ታሪካዊነቱ ያዘነበለ (allegorical or perhaps closer to historical fiction) ሆኖ እንጂ የተገኘው እንደማንኛውም ልቦለድ በፈጠራነቱ ብቻ የተፈረጀ ሆኖ አልታለፈም። በተለይ በቅድመ ቅኝ አገዛዝ ዘመን ሳይበረዝና ሳይከለስ የኖረው ቱባው የናይጄሪያውያን ባህል በቅኝ አገዛዝ ዘመን ምን ያህል እንደተደፈረ፣ እንደተበረዘና እንደ ተከለሰ፤ ይህም (በዋናው ገፀባህርይ Okonkwo አማካይነት ለማሳያት እንደ ተሞከረው) ምን ያህል ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የማንነት ቀውስን ሁሉ እንዳስከተለ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጠጉር እያብጠረጠረ ያሳየ መፅሀፍ ነው።
ይህንን እዚህ ማንሳት ምናልባትም በወካይነት ሁሉንም የአፍሪካን አገር በቀል እውቀቶችንና ቱባውን አፍሪካዊ ባህል ያሳያል በሚል ሲሆን፤ አገር በቀል እውቀትን በተመለከተ በአፍሪካ ደረጃ ተመሳሳይ ግንዛቤ እየተያዘ ይገኛል።
ይህ ተመሳሳይ ግንዛቤ በአፍሪካ ደረጃ መኖሩ በማንኛውም መልኩ ተቀባይነት ያለው ሲሆን፣ ምናልባት አስቀድመው ቅኝ ገዥ በነበሩት አሁንም ያ ለምን ይቆማል የሚል አስተሳሰብ ባላቸው ወገኖች ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል። ይህም የጥቅም ጉዳይ ነውና ቢኖር የማይገርም ሲሆን ዋናው ነገር ችግሩን በመሰረታዊነት ለመፍታት የአፍሪካውያን አንድነት አስፈላጊ የመሆኑ ጉዳይ አጠያያቂ መሆን የለበትም።
በቅርቡ የአፍሪካ ህብረት (ኤዩ) ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የአፍሪካ አገር በቀል እውቀቶች ከዚህ መለስ የሚባሉ እንዳልሆኑ፤ በቀኝ አገዛዝ ኃይሎች እንዲጠፉ የመደረግን ሙከራ ሁሉ ተቋቁመው እዚህ የደረሱ መሆናቸውን፤ እነዚህ ቱባ አፍሪካዊ እሴቶች ለአፍሪካውያን የማንነት መገለጫዎች መሆናቸውን፤ እነዚህን ወደ ልማትና እድገት መሳሪያነት መጠቀም እንደሚገባ … ወዘተ አብራርቶ አስፍሯል። (ለዝርዝሩ የድርጅቱን ድረ-ገጽ መመልከት ይቻላል።)
በአንዳንድ ልሂቃን ነን በሚሉ ሰዎች የኋላ ቀርነት መገለጫ ተደርጎ ሲወሰድ የነበረውን የአገር በቀል እውቀት (IK) መሰረታዊ ፋይዳ በተመለከተ በርካታ ጥናቶች ያሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት እየወጡ ያሉት፣ ሁሉም በሚባል ደረጃ እያመለከቱ የሚገኙት አገር በቀል እውቀት በተለይ ለአርሶ አደሩ ማህበረሰብ ስለ ተለያዩ ተግባራትና እንቅስቃሴዎች ውሳኔ ከመስጠት ጀምሮ በግብርናውና ትምህርቱ ዘርፍ ለህይወታቸው ተስማሚና የሚበጅ በሆነ መልኩ ስራ ላይ ያውሉት ዘንድ የሚያደርግ እውቀት ነው።
ይህ መደበኛ ያልሆነ የእውቀት ምንጭ በተለይ አገር በቀል እውቁቱ ባለበት አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች የሚሰጠው ጥቅም የዋዛ አይደለም። (በጥናቶች ”provides problem-solving strategies for local communities” እንደተባለው ማለት ነው።)
የአገር በቀል እውቀት ሚና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ጀምሮ የሰዎችንና እንስሳትን ጤንነት ለመጠበቅ፣ ከተፈጥሮ ጋር ያለን ትስስር ለማወቅና ለማጥበቅ፣ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም፣ እና ሌሎች በርካታ ወሳኝ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን፤ ብሎም ለመቆጣጠር ማስቻል ድረስ የዘለቀ ነው።
”እነዚህን አገር በቀል እውቀቶች እንዴት አድርጎ ከማጥፋት፣ ከመከለስና መበረዝ … መጠበቅ ይቻላል?” የሚል ጥያቄ ብዙውን ጊዜ ሲነሳ የሚሰማ ሲሆን፣ ለዚህ መልስ ይሆን ዘንድ የፊሊፒንስ መልካም ተሞክሮ መሰረት በማድረግ መልስ የሚሰጡ ሲሆን፤ እሱም የባለቤትነት መብትን በማስከበር፣ ምልክቶችን በማድረግ፣ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥን አመላካች ምልክቶችን መጠቀም፤ እውቅና መስጠት … የሚል ነው።
ሌላውና አገር በቀል እውቀቶችን እንዴት አድርጎ ከጥፋትና መጥፋት መታደግ ይቻላል ለሚለው የሚሰጠው መልስ ትልቁ የአገር በቀል እውቀት ጠላት ዝመና (Modernization) ሲሆን፣ ይህንን መከላከል እንኳን የማይቻል ቢሆንም የጥፋት እጁን ነባሩን ባህልና እሴት ማውደም ላይ እንዳያሳርፍ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ ሊደረግ ይገባል የሚል ነው።
ይህ መዘመንና ነባር ማንነትን የመንቀል ተግባር በአንድ አገር ወይም አህጉር ላይ የተወሰነ ሳይሆን አጠቃላይ ዓለምን ያጥለቀለቀ ችግር እንደ መሆኑ መጠን ለመፍትሄውም አጠቃላይ የዓለምን ንቅናቄና የመፍትሄ ርምጃ የሚፈልግ ይሆናል።
ዛሬ በመላው ዓለም በከፍተኛ ደረጃ እውቅናን ያገኘውና በየአውዱ ተዘውታሪነት ያለው አገር በቀል እውቀት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ይዞታ በእጅጉ የተለያየ ነው። ለምሳሌ በአፍሪካና ኤዥያ አካባቢ፣ ማለትም አልበለፀጉም የሚባሉት ስፍራዎች ያሉት አገር በቀል እውቀቶች ጭራሽም ያልተነኩና ልማትም ላይ ያልዋሉ (underutilized resources) ሲሆን፤ በአንፃሩ ደግሞ በምእራቡ አለምና አሜሪካ አካባቢ ቀድሞውንም የዳበረ ባህላዊ እሴቶች የሌላቸው መሆኑን ተከትሎ እዚህ ግባ የሚባል አገር በቀል እውቀት የለም።
ይህ አገር በቀል እውቀት ባለመኖሩም ምክንያት ወደ ፈጠራውና ሰው ሰራሽ ምርቶች (ሸቀጦች) በቀጥታ መግባት ጀመሩ። ይህ እየተስፋፋ ሄደ። በመሆኑም ያላደጉ አገራትን መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶች ኋላ ቀር (outdated) በማለት ለማፈራረስ ደፋ ቀና ማለትን ተያያዙት። የተሳካላቸው የመኖሩን ያህል ግን በአብዛኛው አልተሳካላቸውም።
ይሁን እንጂ ”ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን ጨምሮ፣ በበርካታ የአለማችን አገራት የአገር በቀል እውቀት እጅጉን ተፈላጊ እየሆነ መጥቷል። በተለይ ከተፈጥሮ አምርሮ እየተጣላ የሚገኘው የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር መልሶ ለመታረቅ፣ የአየር ንብረት ለውጥና የመሳሰሉትን ችግሮች ለመፍታት … መፍትሄው አገር በቀል እውቀቶችን ማወቅ፣ ማልማት፣ መጠበቅና በስራ ላይም ማዋል መተኪያ የሌለው መሆኑን እየተገነዘበ ያለ ይመስላል።
የትና መቼ
በተለያዩ መንገዶች እንደተረጋገጠው፣ አገር በቀል እውቀት የማይገባበት፣ የማያስፈልግበት ጊዜና ቦታ፤ ሙያና ዘርፍ … የለም። ለምሳሌ ያህል እንኳን በትምህርቱ ዘርፍ (ከላይ የህክምናውንና ሥነቋንቋን ጉዳይ በተመለከተ ያነሳነው እንዳለ ሆኖ) ያለውን ወስደን መመልከት እንችላለን።
ሁሌም፣ አገራችንን ጨምሮ (ለምሳሌ ያህል፣ በፈረንጆቹ በ1972 የወጣውን የትምህርት ሴክተር ሪቪው፣ በ1994 የወጣውን የኢትዮጵያ የትምህርት ስትራቴጂ ይመለከታል)፣ አገር በቀል እውቀት በትምህርቱ መስክ አስፈላጊነቱ አሻሚ ሆኖ አያውቅም። ችግሩ ስርአተ ትምህርቱ ውስጥ ማካተትና ወደ ተግባር ማሸጋገር አለመቻሉ ላይ ነው። ሁሉም፣ በተለይ ዘመናዊ ትምህርት ወደ አገራችን ገባ ከተባለ ወዲህ አገር በቀል እውቀትን እንደ ኋላ ቀር ቆጥሮ (በፈረንጆቹ ”ጠቃሚ” ምክር ምክንያት) ከስርአተ ትምህርቱ ውስጥ እስከ ማስወገድ ተዘለቀ። ይህም፣ ከትውልዶች የስነ ምግባር ጉድለት ጀምሮ ከፍተኛ ጉዳትን ማስከተሉ እየታየ ሲሆን፤ አሁንም መፍትሄው ፊትን ወደ አገር በቀል እውቀት ማዞርና እሱኑ በመፍትሄነት መጠቀም እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ነው እየተመከረ ያለው።
በቅርቡ፣ ጃንዋሪ 2022 ለንባብ የበቃ አንድ ዓለም አቀፍ የምርምር ውጤትም አገር በቀል እውቀት በትምህርቱ ዘርፍ የሚያስገኛቸውን መሰረታዊ ፋይዳዎች የዘረዘረ ሲሆን፤ በተማሪዎች መካከል አብሮነትን፣ ትብብርን፣ ልምድ ልውውጥን፣ አብሮ ማደግና መስራትን … ወዘተ ያሰርፃል። ትምህርትቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ይቀንሳል። የአካባቢያቸውን ባህል ይገነዘባሉ። ይህ በበኩሉ ወደ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲያቀኑም ያደርጋል።
አንድ ህብረተሰብ፣ ለረዥም ጊዜያት ከተፈጥሮ ጋር በነበረው ተራክብኦ መነሻነት ያዳበረው ግንዛቤ፣ ክህሎት፣ ፍልስፍና … መሆኑን በመረዳት ለአገር በቀል እውቀት(ቶች) ”the understandings, skills and philosophies developed by societies with long histories of interaction with their natural surroundings.” የሚል ብያኔን ያስቀመጠው ዩኔስኮ፣ አለማችን አሁን ለተጋረጠባት ችግር፣ ማለትም ኮቪድ-19፣ የአየር ንብረት ለውጥ … እና የመሳሰሉት ሁሉ መፍትሄው አገር በቀል እውቀትን ተግባራዊ ማድረግ ነው። (እንደ አንዳንድ ምሁራን ጥናት ኮቪድን ተከትሎ በአደጉት አገራት አማካኝነት ለአፍሪካ የታዘዙትና ተግባራዊ የተደረጉት (በሁሉም ባይሆን) ርምጃዎች (ለምሳሌ ፍፁም ከቤት አለመውጣት) የአፍሪካ አገር በቀል እውቀትን ያገናዘቡ ሳይሆኑ የፈረንጆቹን አፍሪካን ዳግም የማደህየት ስትራቴጂም መሰረት ያደረጉ ናቸው። ሌሎችም ብዙ አሉ።)
ባጠቃላይ፣ በአሁኑ ሰዓት ዓለም ፊቱን ወደ አገር በቀል እውቀት የመለሰበት ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው። የጥናትና መርምር ስራዎችና አጥኚዎቻቸውም ብእራቸውን ወደዚሁ ካደረጉ ቆዩ። በመሆኑም፣ በተለይም አፍሪካን የመሳሰሉና በአገር በቀል እውቀት የበለፀጉት አህጉራት ፊታቸውን ወደዚሁ ቱባና እምቅ ሀብታቸው በማዞር፣ የአፍሪካ ህብረት ”አጀንዳ 2063ን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው አገር በቀል እውቀትን ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ነው” እንዳለው ሁሉ፣ በአገራት ደረጃም (ከግለሰብ ጀምሮ) ይህንኑ ሊከተሉና እጃቸው ላይ ባለው ሀብት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይገባል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓም