ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በተለይም በኢኮኖሚ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ከዚህ አኳያም አንዱ የሚጠቀሰው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ነው።
በፋይናንስ ዘርፍ ላይም እንዲሁ የሪፎርም ሥራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በሀገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ ያለው የካፒታል ገበያና የውጭ ባንኮች በሀገሪቱ የሚሰሩበት ሁኔታ መመቻቸቱም በዘርፉ የተካሄዱ ማሻሻያዎችን ተከትሎ በሀገራችን ሊተገበሩ የተቃረቡ ስራዎች ናቸው።
በአክሲዮን ገበያ አስፈላጊነት ላይ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ፋይዳውን በመዘርዘር ምክረ ሃሳቦችን ሲሰጡ ኖረዋል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፤ በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ የካፒታል ምንጭ በመሆን እንደሚያገለግል ይናገራሉ። የንግድ ድርጅት ለማቋቋም ወይም የተቋቋመ ድርጅትን ለማስፋፋት ሲያስፈልግ፣ የመጀመሪያው ጥያቄ ድርጅቱን ለማቋቋም ወይም ለማስፋፋት የሚያስፈልገው ካፒታል ከየትና እንዴት ይገኛል የሚል ጥያቄ ይነሳል የሚሉት ባለሙያዎቹ፣ ባሀብቶች መሠረተ ሰፊ የንግድ ድርጅቶችን ለማቋቋምና ለማስፋፋት በፈለጉ ጊዜ ከፍተኛ ካፒታል ለማሰባሰብ በበርካታ አገሮች ዘንድ የታወቀውና የተለመደው መንገድ የአክሲዮን ወይም ወደ ገንዘብ የሚቀየሩ ሰነዶች ገበያ እንደሆነ ያብራራሉ።
የአክሲዮን ገበያው ምንነትና ጥቅም ላይ ግንዛቤ ባለው ሕብረተሰብ ውስጥ የገበያው መሠረት ሕዝቡ እንደሚሆንም ነው የተጠቀሱት። ግብይቱ የማይነጥፍ የካፒታል ምንጭ በመሆን የሚጫወተው ሚና ትልቅ እንደሆነም ያስረዳሉ። የአክሲዮን ገበያ ሌላኛው ጠቀሜታ የኢንቨስትመንት አማራጭ መሆኑና የቁጠባ ባህልን ለማዳበር ማስቻሉ መሆኑንም ያመለክታሉ። ሕዝብ አሳታፊ መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል።
የአክሲዮን ገበያ በአንድ ኩባንያ ውስጥ አክሲዮን በመግዛት የኩባንያው የጋራ ባለሀብት ለመሆን ብሎም ከሚያስገኘው ትርፍ ተጠቃሚ ለመሆን ለሚፈልጉ ሁሉ ክፍት መሆኑን በመጥቀስም፣ ሁሉም እንዳቅሙ አክሲዮን እየገዛ የንግድ ድርጅት ባለንብረት እንዲሆን ያስችላል ይላሉ። ስለዚህ ጥቂት ከበርቴዎች ብቻ ኢኮኖሚውን እንዳይቆጣጠሩ ከመከላከሉም በላይ የሀብት ሥርጭትን እንደሚያሰፋ ጠቅሰው፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች መንግሥት የካፒታል ገበያው እንዲጀመር የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጦ እየሠራ መሆኑን በመልካም ጅምር ይጠቅሳሉ።
ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፤ በርካታ ዕድሎችንም ይከፍታል፤ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ተብሎ ትልቅ ግምት የተሰጠው የአክሲዮን ገበያን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመንግሥትና በግል ድርጅቶች አማካኝነት እየተሠሩ ይገኛሉ።
ይህ ተቋማዊ ሥርዓት የሚያስፈልገውና ሕዝብ የሚተማመንበት የገበያ ሥርዓትን የሚጠይቀው የአክሲዮን ገበያ በርካታ አገራት ኢኮኖሚያቸውን ከፍ ያደረጉበት ቢሆንም፣ ጥቂቶች ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ባለማሟላታቸው ሳቢያ ውጤታማ ሳያደርጋቸው እንደቀረ መረጃዎች ያመለክታሉ።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ እንደ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ካናዳ በመሳሰሉ አገራት የካፒታል /የአክሲዮን/ ገበያው የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት ለአኮኖሚያቸው አጋዥ ሞተር ሆኖ አገልግሏል። ታዲያ የአክሲዮን ገበያን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰናዳች ያለችው ኢትዮጵያም ከሌሎች አገራት ልምድ በመውሰድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቿን ከወዲሁ አጠናክራ መሥራት እንዳለባት ባለሙያዎች እየመከሩ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ወደ ካፒታል ገበያ ለመግባት እጅግ በመዘግየቷ ያጣቻቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ቢኖሩም፤ በተመሳሳይ ደግሞ ቀድመው ተግባራዊ ካደረጉና ከፍተኛ ልምድ ካካበቱ አገራት ልምድ በመውሰድ ውጤታማ መሆን የምትችልበት አጋጣሚ
ስለመኖሩ በማንሳት ዕድሉን በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚገባ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ሞላ አለማየሁ፤ የአክሲዮን ገበያ ሲመሰረት ሰፋፊ መሰረተ ልማቶች የሚያስፈልጉት እንደሆነ በማንሳት መሠረተ ልማቱም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እንደሚጠይቅ ያስገነዝባሉ። እንደሳቸው ገለጻ፤ ከመገበያያው ሕንፃ ጀምሮ አስፈላጊ የሆኑ የቢሮና የመረጃ ቁሳቁስ ማሟላት፣ የጥበቃና ደህንነት ግብዓቶች፣ ዘመኑ የደረሰበትን ዕድገት የሚመጥን የመረጃ መረብ መዘርጋትና ለዚህ ሥራ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ማፍራት ያስፈልጋል።
ዶክተር ሞላ ስቶክ ማርኬት ወይም የአክሲዮን ገበያ ለኢኮኖሚው ዘርፍ የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን በመጥቀስም አጠቃላይ ሊገጥመው ይችላል ያሉትን ችግርና መወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ አስረድተዋል። የአክሲዮን ገበያ በኢትዮጵያ እንዲጀመር ከፍተኛ ግፊት ሲደረግና ብዙ ሲባልለት የነበረ መሆኑን አስታውሰው፣ በተለይም የካፒታል ማርኬቱን የሚያሳልጥ ስለመሆኑ ያላቸውን እምነት ያመለክታሉ።
‹‹የአክሲዮን ገበያ በዋናነት ከፍተኛ የካፒታል አቅም በመፍጠር ለግሉ ዘርፍ ምጣኔ ሀብት የገንዘብ ፍሰትን የሚያሻሽል፣ በቀላሉ ወደ ገንዘብ ሊለወጥ የሚችል ሀብትን መፍጠር የሚችልና ባለሀብቱና ባለድርሻው ትርፍም ሆነ ኪሳራቸውን በጋራ እንዲጋሩ የሚያስችል ሥርዓት እንደመሆኑ በኢኮኖሚው ላይ በጎ ተጽእኖ ያመጣል›› የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ ከፍተኛ ግምት የተሰጠውን ይህን የአክሲዮን ገበያ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።
የአክሲዮን ገበያ ከመፈጠሩ አስቀድሞ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት የግድ እንደሆነ በማንሳት በተለይም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማብቃት ረገድ ለአብነትም ኦዲተሮችን፣ የሂሳብ ባለሙያዎችን፣ የስቶክ ብሮከሮችንና የአክሲዮን ጠበቆችን ማሰልጠን የሚችሉ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ቀዳሚ ሥራ መሆኑ ይታመናል። ይህንኑ ለማሟላትም እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው አይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ተጠቃሽ ነው።
ኢንስቲትዩቱ ከሰሞኑ ከናይሮቢ ሴክዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ጋር በመተባባር ለአክሲዮን ገበያው ውጤታማነት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ተገልጿል። የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ገመቹ ዋቅቶላ ጉዳዩን አስመልክቶ በተዘጋጀ መድረክ ላይ የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ መጀመሩ ብቻ ሳይሆን እንዴት ውጤታማ ሊሆን ይችላል? የዘርፉ ተዋናዮችስ እነማን ናቸው? የሚለውን መለየትና አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በሌሎች አገራት ተሞክሮ የአክሲዮን ገበያ ውጤታማ የሆነባቸው አራት መሰረታዊ ነገሮች ስለመኖራቸው የጠቀሱት ዶ/ር ዋቅቶላ፣ ከእነዚህ አራት መሰረታዊ ነገሮች መካከልም ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ እየተሠሩ እንደሆነ ነው ያመለከቱት። አንደኛው የመሰረተ ልማት ግንባታ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ መሰረተ ልማት በሚገባ መልማት እንዳለበት አንስተዋል። ሁለተኛው የገበያ ልማት እንደሆነ ተናግረው፣ ይህ ማለት ደግሞ የሚሸጠው ነገር ሲሆን ለአብነትም ቦንድና ሼር መሸጥ መለወጥ የሚችሉት ተጠቃሽ ሲሆኑ ሶስተኛው የፖሊሲና የቁጥጥር ሥርዓቶች ናቸው። እነዚህም እየተሠራባቸው ሲሆን፤ አራተኛውና ቁልፍ ጉዳይ የአቅም ግንባታ እንደሆነም ያብራራሉ። አቅም ግንባታ ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን የሚይዝ እንደሆነ በመግለጽ አንደኛው የሰው ኃይል ግንባታ፣ ሁለተኛው ደግሞ ተቋማዊ አቅሞችን መገንባት እንደሆነ አስረድተዋል።
የሰው ኃይል ግንባታና ተቋማዊ አቅሞችን መገንባት ለካፒታል ገበያው ውጤታማነት ቁልፍ ተግባራት እንደሆኑ አስታውቀው፣ ከሌሎች አገራት ልምድ በመውሰድ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ልማትን ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ዶ/ር ዋቅቶላ ይጠቁማሉ። ለዚህም ድርጅታቸው አይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ለዘርፉ ቁልፍ ሚና ያላቸውን ሥራዎች እየሠራ እንደሆነም አስረድተዋል። ከሥራዎቹ መካከልም አቅም በመገንባትና ልምድ ካካበቱ በተለይም ጎረቤት ከሆኑ አገራት ጋር በመሆን በተግባር የሚታየውን የአክሲዮን ገበያ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት እንዴት እንደሚሠራ ሥልጠና መስጠት የሚለው ይገኝበታል ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የካፒታል ገበያ እንደማንኛውም ሸቀጥ ሻጭና ገዢ ሕግና ሥርዓት ባለው መንገድ ተገናኝተው መገበያየት እንዲችሉ የሚያደርግ ነው፤ በርካታ ጠቀሜታዎችም አሉት። መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመስራት ሲያስብ ገንዘቡን ማግኘት ይቸገራል። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ በካፒታል ገበያ ውስጥ ተሳታፊ በመሆን ፕሮጀክቱ ገንዘብ ማመንጨት እንዲችል ይሆናል። ይህ አንድ ፋይዳው ነው። አክሲዮን በመግዛት ትርፍ ማግኘት ማስቻሉ ነው። ሁለተኛው ፋይዳው ደግሞ መንግሥት በእጁ ያሉትን ተቋማት ወደ ግለሰቦች ማዘዋወር ሲፈልግ ወደ ካፒታል ገበያ ማውጣት ያስችለዋል። በዚህ ጊዜ ማንኛውም ሰው ኢንቨስት የማድረግ ዕድል ይኖረዋል።
ይህ የካፒታል ገበያ በትክክል ተግባራዊ እንዲሆን አይ ካፒታል ኢንስቲትዩት በዋናነት አጠቃላይ የገበያው ሲስተም አቅም፣ ዕውቀትና ልምድ ባላቸው አካላት እንዲደገፍ ያመቻቻል። ለዚህም የመንግሥት አካላትን ጨምሮ የፖሊሲ ሰዎችን የዘርፉ ቁልፍ ተዋናይ ለሆኑ ባለሙያዎችና ተቋማት ልምድ ባላቸው አካላት አቅማቸውን መገንባት፣ የምክር ሃሳብ መስጠት፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን መስጠትና ዕድሎችን ማመቻቸት ነው።
የአክሲዮን ገበያን በኢትዮጵያ ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ የመጀመሪያ አጋር የሆነው የኬንያው ናይሮቢ ሴክዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ሲሆን፤ በዘርፉ ከ70 ዓመት በላይ የዳበረ ልምድ ያለው ነው። ተቋሙ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ገብቶ አዲስ የሚመሰረተውን የአክሲዮን ገበያ የማገዝ ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ስለመሆኑም ያስረዱት ዶክተር ዋቅቶላ፤ ጎረቤት አገር ከሆነችውና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ካካበተችው ኬንያ ጋር በመሥራት ልምዳቸውን በመጠቀም የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ ልማት ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ነው ያስገነዘቡት።
አይ ካፒታል ኢንስቲትዩት በአክሲዮን ገበያ ከፍተኛ ልምድ ካለው የኬንያ ናይሮቢ ሴክዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ጋር በመተባበር ተጨባጭ በሆነ መንገድ የካፒታል ገበያ ልማት ውጤታማ እንዲሆን ይሠራል። የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን ውጤታማ ለማድረግ ጽኑ ፍላጎት ያላት ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር የሚመሳሰል ማህበረ ኢኮኖሚ ያላት በመሆኑ የተፈጠረው አጋርነት ውጤታማ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት በመግለጽ፤ የእነሱ ተሞክሮም የአክሲዮን ገበያው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ሊተገበር እንደሚችል፣ አቅም በመገንባትና በጋራ እንዴት መሥራት እንደሚቻል የምክር አገልግሎቶችን ማግኘት ዋናው ጉዳይ ይሆናል ይላሉ።
ሁለቱ ድርጅቶች በገቡት የውል ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ በካፒታል ገበያ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ድርጅቶችና ቡድኖች የማማከርና የሥልጠና አገልግሎቶችን፣ በገበያው አመሰራረት ዙሪያ ለኢትዮጵያ መንግሥት ተሞክሮን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ ድጋፎችን እንዲሁም የድርጅቶችን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን በጋራ የሚሰጡም ይሆናል። በአሁኑ ወቅትም ለአክሲዮን ገበያው ዋና ቁልፍ የሆኑ ተዋናዮችን ከተለያዩ ባንኮች በማሰባሰብ የመጀመሪያውን ዙር ሥልጠና በመስጠት የጋራ ሥ ራቸውን ጀምረዋል።
በመጀመሪያው ዙር የተሰጠው ሥልጠናም የተሳካና ውጤታማ እንደነበር ያነሱት ዶክተር ዋቅቶላ፤ ሥልጠናው ቀጣይነት ያለውና አቅም መፍጠር የሚችል እንደሆነ ተናግረዋል። ከሥልጠናው ባሻገር የካፒታል ገበያን በኢትዮጵያ ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም ሰው በአገር ደረጃ ስለጉዳዩ ምንነት መረዳት፣ እንዴት መጠቀምና መሳተፍ እንደሚችል ማወቅ ይኖርበታል። ይህን ማድረግ ሲቻል ካፒታል ገበያን ውጤታማ ማድረግ ይቻላልም ነው የሚሉት።
የናይሮቢ ሴክዩሪቲስ ኤክስቸንጅ ሥራ አስኪያጅ ዴቪድ ዋኔይና ደግሞ፤ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ምስረታ ቢዘገይም፣ የድርጅታቸውን ልምድና የአገሪቱን የህዝብ ቁጥር በመጠቀም ስኬታማ የካፒታል ገበያ ልማት መመስረት ይቻላል ሲሉ ይገልጻሉ። በስምምነቱ መሰረትም የመጀመሪያ የሆነው፣ ከፋይናንስ ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች በካፒታል ገበያ ባለድርሻዎችና ከገበያው ጋር ተያይዘው ስለሚመጡ የሥራ እድሎች የሁለት ቀናት ሥልጠና በሳፋየር አዲስ ሆቴል የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይም መሰል ሥልጠናዎች በመስጠት ቀጣይነት ያለውና ውጤታማ የሆነ ግንኙነት እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።
አይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ከተመሰረተ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ የምስራቅ አፍሪካ ዓመታዊ የፋይናንስ ጉባኤን ለተከታታይ አምስት ዓመታት በማዘጋጀት ይታወቃል። ከዚህም በተጨማሪ በፋይናንስ ዘርፉም ሆነ ከፋይናንስ ዘርፍ ውጭ የሰው ኃይል ግንባታ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ድርጅት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9 ቀን 2015 ዓም