«በአየነው ነገር በጣም እየተገርም ነው። በሶማሌ ክልል የእርሻ ሥራ አልተለመደም። አብዛኛው ሕዝብ አርብቶ አደር ነው። ከብት፣ ፍየልና ግመል እያረባ ነው የሚተዳደረው። በዚህ አካባቢ ያማረ የስንዴ ልማት ማየታችን እያስገረመን ነው፤ ለካ እንዲህም ማልማት ይቻላል፤ በምግብ ራስን ለመቻል መሥራት እንዳለብን በተግባር ያሳየን ሥራ ነው» ይላሉ በሱማሌ ክልል ፋፈን ዞን ቱሉጉሌት ወረዳ ኩሉሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሱልጣን አብዲ።
አቶ ሱልጣን በቀበሌያቸው የክልሉ መንግሥት ባካሄደው የስንዴ ልማት ተደስተዋል፤ ሥራውንም እንዲማሩበት ያስቻለ ውጤታማ ሥራ ብለውታል። በቀላሉ ማምረት እንደሚቻል በተግባር አይተንበታል ያሉት አቶ ሱልጣን፣ እኛም ስንዴ እንድናለማ መነሳሳትን ፈጥሮብናል ይላሉ። ከአሁን በኋላ በእንስሳት እርባታ በመተማመን ብቻ አንተኛም፤ በዘንድሮም ስንዴ፣ በቆሎና ማሽላ ለማምረት ተዘጋጅተናል ሲሉ ገልጸውልናል።
በሱማሌ ክልል ቱሉጉሌት ወረዳ ለጥ ባለው ማሳ አረንጓዴ ምንጣፍ የሚመስለው የስንዴ ሰብል ሲያዩት ያምራል፣ ቀልብን ይማርካል። የሰብሉ ቁመና የስንዴ አዝመራውን ፍሬያማነት በአደባባይ ይመሰክራል። በሱማሌ ክልል ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቀው የስንዴ ልማት በአካባቢው ነዋሪዎችም ዘንድ አግራሞትን ፈጥሯል። መነሳሳትን አጭሯል። ተስፋንም ሰንቋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከልም አንዱ አቶ ሱልጣን አብዲ ናቸው።
ከመንግሥት ድጋፍ የምንፈልገው በብድር ትራክተር እንዲሰጠንና የመስኖ ውሃ እንዲያሟላልን ብቻ ነው የሚሉት አቶ ሱልጣን አብዲ፤ ራሳችን ለመለወጥና ከድርቅ አደጋ ስጋት በዘላቂነት ለመላቀቅ ሌት ተቀን ጥረንና ሠርተን እንለወጣለን ሲሉ ቃል ገብተዋል።
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በሶማሌ ክልል ዝናብ መጣል ባለመቻሉ በክልሉ በሚገኙ 11 ዞኖች ድርቅ ተከስቷል። በድርቁ ምክንያትም ከሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች በላይ ለአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ተጋልጠዋል፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንስሳት መሞታቸውን የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቢሮ መረጃ ያመለክታል። ለዚህም ነው ክልሉ የድርቅ አደጋን በዘላቂነት ለመቋቋም ለመስኖ ልማት ትኩረት እንደሰጠ የሚጠቀሰው።
የድርቅ አደጋን በዘላቂነት ለመቅረፍም ክልሉ ለአነስተኛና መካከለኛ መስኖ ልማት ትኩረት እንደሰጠና አርብቶ አደሩንም ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቢሮ ያስረዳል።
የሱማሌ ክልል ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ አራት ወንዞችና ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት አለው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ክልሉ ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተመቸ መሆኑም ይገለጻል። በ2012 ዓ.ም በተደረገ ሙከራም ከሦስት ሺህ ሄክታር በላይ የበጋ ስንዴ ልማት ተካሂዶ አበረታች ውጤት መገኘቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህንኑ መሠረት በማድረግም በክልሉ በስፋት የቆላ ስንዴ ለማልማት ዕቅድ መያዙ ተመልክቷል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት የተከሰተው ድርቅ በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳስከተለ ይታወሳል። 85 በመቶ የሚሆነውን የክልሉን አርብቶ አደር ወደ ከፊል አርሶ አደርነት የመቀየር ሥራ እንደሚከናወንና ለዚህም በዋነኝነት አርብቶ አደሩን ከመስኖ ልማት ጋር በማስተዋወቅ በግብርና ሥራ ላይ እንዲያተኩር እንደሚደረግም የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቢሮ መረጃ ይጠቁማል።
ቀደም ሲል የሱማሌ ክልል ሲነሣ ከግጭትና ከድርቅ ጋር ተቆራኝቶ ነበር የሚሉት የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ፤ ባለፈው ዓመት በተከሰተው አስከፊ ድርቅ ከሕዝባችን ብዙ ጊዜ ‹‹ድርቅን ሁልጊዜ ዕርዳታ እየጠበቅን መከላከል እስከመቼ ይቀጥላል? በክልሉ ወቅት እየጠበቀ የሚከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት ለመከላከል ምን እየሠራችሁ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሱ ነበር ሲሉ ያስታውሳሉ።
ለእነዚህ ጥያቄዎች ዋናው መልስም በሶማሌ ክልል መንግሥት ባለፈው ዓመት የተጀመረውና በሚቀጥሉት ዓመታት ተስፋፍቶ መቀጠል ያለበት የስንዴ ልማት ሥራ መሆኑን ይገልጻሉ። የስንዴ ልማቱ እየተሠራ ያለው ድርቅንና በምግብ ራስን ለመቻል ብቻ እንዳልሆነም ነው የተናሩት። ድርቅን ሁልጊዜ በዕርዳታ ስንዴ መቋቋም የለብንም በሚል የጀመርነው የስንዴ ልማት አመርቂ ውጤት አግኝተንበታል ያሉት አቶ ሙስጠፌ፣ የስንዴ ልማቱ የዋጋ ንረትንና ድርቅን በዘላቂነት ከማርገብ አኳያ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ይገልጻሉ።
ባለፈው ዓመት በሱማሌ ክልል 847 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ልማት መሸፈኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህም በክልሉ ሊለማ ከሚችለው መሬት 10 በመቶ ብቻ ነው ይላሉ። ዘንድሮ ደግሞ የሚለማውን መሬት ለመጨመርና ምርታማነትን ለማሳደግ ዝግጅት አድርገናል። አገራችን ስንዴን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በያዘችው ዕቅድም ሁለት ሚሊዮን ኩንታል አስተዋጽኦ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንገኛለን ነው ያሉት።
እንደ ርእሰ መስተዳድሩ ገለጻ፤ በአራት ወንዞች የቦይና የመስኖ መሠረተ ልማቶችን የመዘርጋት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፤ ውሃ በማቆርና መስኖ መሠረተ ልማት ዝርጋት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ከተሠራው እጥፍ መሥራት ታቅዷል። ለዚህም የሶማሌ ክልል ዝግጅት እያደረገ ነው። ይህም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከማስቻሉም በላይ ለኢኮኖሚያችን ማነቆ የሆኑ የዋጋ ንረትን የመሰሉ አደጋዎችን ለመቆጣጠር አመቺ ሁኔታ ይፈጥርልናል ይላሉ።
በሶማሌ ክልል የታየው የስንዴ ልማት ተሞክሮ በሌሎች የአገራችን ቆላማ እና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎችም ሊሰፋ እና ሊያድግ እንደሚገባው የሚናገሩት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን፤ ለተግባራዊነቱም ሁሉም የሚመለከተው አካል የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አሳስበዋል።
እንደ ግብርና ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ባለፈው ዓመትም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 24 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተገኝቷል። ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት በበጋ ስንዴ ልማት ለተገኘው አመርቂ ውጤትም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከፍተኛ የአመራር ቁርጠኝነት፣ የተቀናጀ የፋይናንስ ድጋፍና አገራዊ የስንዴ የመስኖ ፕሮጀክት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት መዘርጋቱ ከፍተኛ ሚና አበርክተዋል።
በ2015ዓ.ም የበጋ መስኖ ስንዴ ፕሮግራም ከተነሳበት ከውጭ የሚገባን ስንዴ በአገር ውስጥ የመተካት እቅድ በተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠርና በቂ ምርት ለግብርና ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃ ማቅረብን ዓላማ ያደረገ ነው። እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ገቢን ማሳደግንም ታሳቢ አድርጓል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 52 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት ዕቅድ ተይዟል። ይህም የአገርን ፍጆታ ሙሉ ለሙሉ ከማሟላት ባለፈ ለውጭ ንግድ ማቅረብ እንደሚያስችል ሚኒስትሩ ያስረዳሉ።
የክልሎችን መረጃ መሠረት አድርገው ሚኒስትሩ ሲገልጹ፣ ከዘንድሮው የመኸር ምርት ዘመን 101 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ ከበጋ ስንዴ ልማት ጋር ሲደመር 153 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። አገራዊ ዓመታዊ የስንዴ ምርት ፍላጎት 107 ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም የአገር ውስጥ ፍጆታን ሙሉ ለሙሉ ከማሟላት ባለፈ ለውጪ ንግድ ለማቅረብ ያስችላል ነው ያሉት። በመስኖ ከሚለማው 52 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ምርት ውስጥ ቢያንስ 26 ሚሊዮን ኩንታሉን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ትርፍ ምርት መኖሩንም ጠቅሰዋል።
ይህን የበጋ ስንዴ ልማት ለማሳካት የሚሠራው በአብዛኛው በአነስተኛ ይዞታ የመስኖ ልማት ነው። ዕቅዱን ለማሳካትም ተጨማሪ 75ሺህ የውሃ መሳቢያ ሞተር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ለዚህም ሁለት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል። ወጪውም በክልልና በፌዴራል መንግሥት በጀት ድጋፍ የሚሸፈን መሆኑን ይገልጻሉ።
ሶማሌ ክልል ውስጥ ለጥ ባለው መስክና ልምላሜ በሄክታር ከ40 ኩንታል በላይ ስንዴ የሚገኝበት ማሳ ማየት የአምናውን ድርቅና ችግር ላየ ሰው ይህ የስንዴ ልማት ተአምር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ በአሁኑ ጊዜ አመራር እየሰጠን ያለን ሰዎች የምንናገርና የምንጀምር ብቻ ሳይሆን የምንጨርስና ቃላችንን በተግባር የምናሳይ መሆናችንን ሕዝብ እየተገነዘበ መጥቷል ነው ያሉት።
በበጋ ስንዴም የምናገኘው ምርት ከአምናው እጥፍ መሆን አለበት ሲሉ ጠቅሰው፣ ለምሳሌ የሶማሌ ክልል ባለፈው ክረምት በሠራው ሥራ ቢያንስ ከስድስት እስከ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል እንደሚያመርት ይጠበቃል ብለዋል። በረሃውን ለም ካደረጉ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ስንዴ ማምረት አይከብዳቸውም። ይህንንም ይተገብሩታል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በስንዴ ምርት የተመዘገበው ስኬት ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርታማነቷን በማሳደግ ከድህነት መውጣት እንደምትችል በግልጽ እንደሚያመላክትም አስታውቀዋል። በሁሉም መስክ በትብብርና ቁርጠኝነት መሥራት ከተቻለ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደምትለወጥ ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።
እንደ አገር ድህነትን ለመቀነስ ለምናደርገው እንቅስቃሴ በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አካባቢ የሚደረጉ መሰል የግብርና ሥራዎች እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን በሱማሌ ክልል ፋፈን ዞን ቱሉጉሌት ወረዳ ኩሉሌ ቀበሌ በመገኘት አገራዊ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሲያስጀምሩ እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ እንኳን ለራሷ ለሌሎች የሚተርፍ ስንዴ ማምረት ትችላለች። እያንዳንዱን ፈተና ወደ ዕድል በመቀየርና ለእያንዳንዱ ችግር ዘላቂ መፍትሄ በመተግበር የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን ለራሳችን ለሌሎች የሚተርፍ ስንዴ ማልማት እንችላለን፣ ይህን መንገዱን ጀምረነዋል ሲሉ ገልጸው፣ ለዚህ ትልቁ ማሳያ ሱማሌ ክልል ነው ብለዋል። በክልሉ በአሁኑ ጊዜ በሄክታር ከ40 ኩንታል በላይ ማምረት የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩንም ተናግረዋል።
ዘንድሮ በሚሊዮኖች ኩንታል የሚቆጠር ስንዴ ለውጭ ገበያ እናቀርባለን ያሉት ዶክተር ዐቢይ፣ ለዚህ ስኬታማነትም አመራሩን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከተው አካል ርብርብ ማድረግ እንደሚኖበት አሳስበዋል። እኛ ኢትዮጵያውያን ሰፊ መሬት፣ ታታሪ አርሶ አደርና ለም መሬት አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከስንዴ ጋር የተያያዘውን ችግር ሙሉ ለሙሉ በመፍታት አዲስ ታሪክ መጻፍ ይኖርብናል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን አጥግበን ለሌሎች ለመትረፍ የዘንድሮው በጋ ወቅት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ 2015ዓ ም የብዙ ድሎችና መሻገሮች ዓመት እንደሚሆን ገልጸዋል።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም