እኔ ምላችሁ ….አዲስ አበባ ላይ አሁን ላይ በእግር መሄድ እኮ በጣም አስጊ እየሆነ ነው። በተለይ በሥራ መውጫ ሰዓት እና በሥራ መግቢያ ሰዓት በሰላም መንቀሳቀስ ችግር እየሆነ ነው።
እስኪ ተመልከቱ ጠዋት እና ማታ ያለውን የጎዳና ላይ ትርምስ። በተለይ መገናኛ፣ ሜክሲኮ፣ አራት ኪሎ ምናምን ያለውን … ባለፈው ለምሳሌ እዚሁ አራት ኪሎ ላይ በሰላም እየተጓዝኩ እያለሁ ደንብ አስከባሪዎች ያባረሩት አንድ የልብስ ነጋዴ ገፍትሮ ከጥቅም ውጪ አድርጎኝ ነበር። እርግጥ በወቅቱ በደረሰብኝ የመገፍተር አደጋ ካደረሰብኝ አካላዊ ጉዳይ በላይ የደረሰብኝ ድንጋጤ በጣሙን የበለጠ ነበር። የልብስ ነጋዴው ክንዴን ገንጥሎ ከበረረ በኋላ የመጀመሪያ ሥራዬ ያደረግኩት የትከሻዬን ደህንነት ማረጋገጥ ሳይሆን እንደ ማንኛውም የአዲስ አበባ ነዋሪ ስልኬ በኪሴ ውስጥ መኖር አለመኖሩን ማጣራት ነበር። በወቅቱ ስልኬ ከእኔው ጋር እንዳለ ሳውቅ የተነፈስኩት የእፎይታ ትንፋሽ በፊት ለፊቴ የምትገኘውን እየተራመደች የነበረችውን እንስት ገፍቶ እርምጃዋን እንድታፈጥን አድርጓት ነበር።
ከዚያን ጊዜ በኋላ እኔ ራሱ በመንገድ ላይ ስሄድ ከነጋዴዎቹ ባልተናነሰ ሁኔታ ደንብ አስከባሪዎችን መኖር አለመኖራቸውን እያጣራሁ ነው የምጓዘው። ምክንያቱም የእነሱን መኖር አለመኖር ማወቅ ግርግሩ የሚጀመርበትን ዕድል ለማወቅ ስለሚረዳኝ ነው። የመንገድ ላይ ልብስ ነጋዴዎችን ስታልፍ፤ ሙዝ እና አፕል ነጋዴዎች፣ ቻርጀር ነጋዴዎች፣ የአይጥ እና በረሮ መርዝ ነጋዴዎች፣ ዳቦ ግዛልኝ የሚሉ ሕፃናት፣ እኔ ነኝ ደራሽ ለወገኔን የሚያዘፍኑ የበጎ አድራጎት ሠራተኞች እና ሌሎችም በተራ በተራ ይጠብቁሃል። እነዚህን ሁሉ አልፈህ ነው እንግዲህ ታክሲ የምታገኘው።
የሆነ ሆኖ የዛሬው ዋና ጉዳይ ስለ መንገድ ላይ ልመና፤ ንግድ እና ወይም ደንብ አስከባሪዎች ለማውራት አይደለም። የዕለቱ ዋነኛ ጉዳይ በየመንገዱ አላስኬድ ስላሉኝ የባንክ ቤት ሠራተኞች መናገር ነው። በስማም ብዛታቸው። መልካቸውን አሳምረው፤ በሱፋቸው ዝንጥ ብለው፤ ፈገግ ብለው ሲጠጉ ራሱ የሆነ ደስ የሚል ነገር አላቸው። ከዚያ አካውንት በመክፈቴ ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሚሆን ሲያስረዱኝም እኔም በጥሞና ፈገግ ብዬ እሰማቸዋለሁ። ግን እዚህ ጋር ብዙ ችግር አለ። አንደኛ ነገር እንኳን በየባንኩ በአንድ ባንክም የሚቀመጥ ገንዘብ የለኝም። ይህ ደግሞ የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሕዝብ ችግር ነው። በተለይም አሁን ያለው የኑሮ ውድነት እንኳን በየባንኩ የምናስቀምጠው ኪሳችን ውስጥ ራሱ የምንይዘውን ሊያሳጣን ቆርጦ የተነሳ ነው። ስለዚህ የባንክ ሰዎች አካውንት መክፈትን አስፍተው እና አብዝተው እንደሚወተውቱን አካውንት ውስጥ የምናስገባው ገንዘብ ከየት ልናመጣ እንደምንችልም አብረው ሊነግሩን ይገባል ባይ ነኝ። አልያም ግን የባንክ ሰዎች ገንዘብ የለንም የሚለውን ቃል ትርጉም ቢረዱልን እና የግድ ባይሉን ጥሩ ነው። ግን ደግሞ በእነሱም አይፈረድም። እነሱም ሥራ ሆኖባቸው ነው።
ሁለተኛ ጉዳይ የባንክ ሰዎች መንገድ ላይ ቆመው ወጥረው አካውንት ክፈት የሚል ምክር ሲመክሩን እነሱ ሥራቸውን እየሠሩ ነው። ነገር ግን ሌላው ሰው ሰዓት እየረፈደበት እንደሆነም መረዳት አለባቸው። አሁን ላይ የባንክ ሠራተኞችን ለማለፍ ስል ወደ ግራ ወደ ቀኝ እየተጠማዘዝኩ ነው የምሄደው። በዚህም የተነሳ ተጨማሪ ደቂቃዎች እያባከንኩ ነው። ከዚያ ደግሞ እንደዚህ ወዲያ ወዲህ ብዬ ሦስቱን ባንኮች እንዳለፍኩ አራተኛው እጅ ላይ እወድቃለሁ። ያ ዕድለኛ የባንክ ሠራተኛ እጁ ላይ የወደቅኩትን እኔን ለማሳመን የአካውንት መክፈትን ያብራራልኛል። ሰምቼ ስጨርስ አልፈልግም እለዋለሁ። የነገረኝን ነገር በሌላ ቋንቋ ደግሞ ይነግረኛል። እንዲህ እያለ ስለ አካውንት መክፈት አምስቴ ይነግረኛል። ከዚያም እኔ ይሉኝታ ይዞኝ እሺ እለዋለሁ። እሱ የወጣበትን አላማ አሳክቶ ይሄዳል እኔ ግን ያለ እቅዴ የአካውንት መክፈቻ 50 ብር አውጥቼ ጊዜዬንም አቃጥዬ አልፋለሁ።
ሦስተኛ ጉዳይ የባንክ ሰዎች አካውንት ሲያስከፍቱን የሚያሳዩትን ትህትና እና ፍቅር አካውንት ከከፈትን በኋላ አገልግሎት ፍለጋ ስንሄድም ቢደግሙት በእውነቱ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ይሆን ነበር። አካውንት ስንከፍት የምትሰጡን ፍቅር እኮ የትም የማይገኝ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን አገልግሎት ፍለጋ ስንሄድ ያ ትህትናችሁ አልቆ የገዛ ገንዘባችንን ልንወስድ ሳይሆን ከኪሳችሁ ልንበደር የመጣን ያህል ነው የምትቆናጠሩብን። በእውነት ይህ ነገራችሁ መስተካከል አለበት…
ከዚያ ደግሞ የባንክ ሰዎች አካውንት ክፈቱ ቆጥቡ ስትሉን እንቆጥባለን፤ ነገር ግን ቆጥቡ የምትሉንን ያህል ብድር ውሰዱ አትሉንም። ለምን አገሪቱ ውስጥ የባንክ አካውንት ያለው እና የሚቆጥበው ሰው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ነው። የተቆጠበው ገንዘብም በትሪሊዮን ደርሷል። በየአመቱ አበደርን የምትሉትም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ነው። የሚበደረው እና የሚሠራው ሰው ግን ገና በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብቻ ነው። ለምን ምክንያቱማ ገንዘባችንን አምነን እንድንሰጣቸው የሚወተውቱንን ያህል ተበድረን ሥራ እንድንሠራ ስለማትፈልጉ ነዋ። አካውንት ለመክፈት ሲሆን ስም እና ፎቶአችን ብቻ ነው የሚፈለገው። ብድር ለመውሰድ ግን ምን የማንጠየቀው ነገር አለ። የምትጠይቁንን ነገር ቢኖረን እኮ መጀመሪያውኑም ብድር ላንበደር ሁሉ እንችል ነበር። ስለዚህ አካውንት ስታስከፍቱልን ነገሮችን ሁሉ ቀላል እንደምታደርጉልን ሁሉ ብድር መውሰድም ላይ አሠራራችሁን ቀለል አድርጉልን።
ለማጠቃለል፤ ውድ ባንኮች ሆይ፤ ገንዘብ እንድንቆጥብ የምታደርጉት ጥረት እና የምታሳዩን ትህትና በጣም አሪፍ ነው። ነገር ግን አካውንት ማስከፈት ላይ ያሳያችሁንን ትህትና እና ፍቅር አካውንት ከከፈትንም በኋላ አሳዩን። ገንዘባችንን ስትወስዱ የምታሳዩንን ቀናነት ብድር ልንወስድ ስንፈልግም አሳዩን።
አቤል ገ/ኪዳን