ጥበብ ምርቶችን ዘመናዊ የፋሽን አልባሳት ማድረግ ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል። አልባሳቶቻችንን ልዩ መልክ በመስጠትና ገበያ ተኮር በማድረግ በአገር ውስጥ ተወዳጅነቱ ይበልጥ እንዲጠነክር ብሎም በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ እንዲሆንም ብዙ እየተሰራ ይገኛል።
ለልዩ ልዩ ክብረበዓላት ተውበንና አምረን የምንታይበት የሀገር ባህል ልብሳችን ጥበባቱ ብዙዎችንም የሚያስደምም ብቻ ሳይሆን የሚያስደነግጥም ነው። ምንም የሳይንስ ውጤት ሳይታከልበት፣ ዘመናዊ መሳሪያ ሳይጎበኘው በእኛው የጥበብ ባለሙያዎች ጉልበት እና እጅ ድንቅ ድንቅ ጥበቦችን ለብሰናል። ማለቴ ቻይና መጣሹ ሳያስቸግረን በፊት። ዛሬም ቢሆን ግን የቻይና ምርት ያልበገራቸው የባህል ልብሶቻችን ደረጃቸውን እንደጠበቁ አሉ። ለዚህም በዋናነት የሚነሳው የባህላዊ ጫማ ምርቶቻችን ናቸው። ጊዜ፣ ውጪና ቴክኖሎጂው አይፈትናቸውም። ሰው እንደሚፈልገውና እንደሚወደው በተለያየ ዲዛይን በሀገረ ባህል አልባሳቱ ተመሳስለው ይሰራሉ።
ለእይታም ቢሆን አይሰለቹም፤ ሁልጊዜ የክት ሆነው ይለበሳሉ። ባህላዊ ጫማ ለምን የሰርክ እስከመሆን አልዘለቀም? ተወዳጅነቱስ ምን ድረስ ነው? ስንል በሥራው ላይ የተሰማሩትን ሽሮሜዳ አካባቢ የሚገኙ ሙያተኞቹን አነጋግረናል።
«የባህል ልብሶቻችን ተመሳሳይ ጫማ ሳይኖራቸውና ከውጭ አገር በመጡ ጫማዎች ሲደረጉ በእጅጉ እናደድ ነበር። ለምን በተመሳሳይ ባህል ማስጌጥ አልተቻለም የሚለውም የሁልጊዜ ጥያቄዬ ነው» ያለን «የእኛ ጫማ» በሚል የንግድ ስምና «ቤዛዊት፣ ሜሮንና ጓደኞቻቸው» በሚል የንግድ ፈቃድ ስም የሚጠራው ማህበር መስራችና ዲዛይነር ዳንኤል ግርማ ነው።
ዳንኤል ከልጅነቱ ጀምሮ ዲዛይነር እንደሚሆን ያምን ነበር። በዚህም የሚገዛለትን ልብስ ሳይቀር እየቆራረጠ የተለያየ የልብስ ዲዛይን ይፈጥራል። አባቱ ደግሞ የልብስ ሰፊ ስለነበሩ ይህንን ጥበቡን በእጅጉ ያግዙት እንደነበር ያስታውሳል። እናም ይህ ልምዱ ዛሬ ላይ ወደዚህ ሙያ የሚገባበትን መንገድ አመቻችቶለታል።
ዛሬ በባህልም ሆነ በቆዳ ውጤቶች ላይ የተለያዩ ዲዛይኖችን በመስራት ባህልን ወደማስተዋወቁ እንደገባ የሚናገረው ዳንኤል፤ ኢትዮጵያውያን ዓይን የሚስብ ቀለም ባለቤቶች ናቸው። በዚህም ለዲዛይን ሥራ ከእነርሱ የሚቀርብ የለም። በየጊዜው አዲስና ዘመናዊ የጥበብ ሥራዎችን በጫማዎች ላይ እንዲያዩ ዕድል ያገኛሉ። ህብረ ቀለማት የታከለበት ሥራ ደግሞ የማይሰለች ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። በዚህም ነው በዲዛይነርነቴ በባህላዊ መንገድ ጫማን ወደመስራት ተግባር የገባሁት ይላል።
ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው በርካታ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች መካከል አልባሳት፤ ጌጣጌጥና መገልገያ ቁሳቁሶች ተጠቃሽ ናቸው የሚለው ዲዛይነር ዳንኤል፤ ባህል ማለት የአንድ ማህበረሰብ ማንነት የሚገለጥበት ነው። በዚህም በብሔር ብሔረሰቦች የአልባሳት ዲዛይን ሁሉ ጫማዎችን አስውቦ ሳይሰለቹ እንዲለበሱ ማድረግ እንደሚቻል ይናገራል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንስ ምሩቅ እንደሆነ የሚገልጸው ዲዛይነር ዳንኤል፤ ሸማኔዎች በሚያቀርቡለት ጥበቦች ጫማና ቦርሳ ይሰራል። ወደ ባህላዊ የጫማ ሥራ የተሰማራው ደግሞ በተመረቀበት የትምህርት መስክ መስራቱ እርካታን ስላልሰጠው የሚያስደስተውን ሥራ ለመስራት በመወሰኑ መሆኑን ይናገራል።
ዲዛይነር ዳንኤል፤ ውስጣዊ ፍላጎቱን በዘመናዊ እውቀት የተደገፈ ለማድረግም አለ የዲዛይንና ጥበብ ሥራ ትምህርት ቤት የተለያዩ የዲዛይን ትምህርቶችን ተምሯል። በተጨማሪም በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በጫማ ሥራ ከዛሬ የሥራ አጋሮቹ ጋር መሰልጠኑን ይገልጻል። ወደዚህ እንዲገባ ያደረገውም የባህል ጫማዎች ከባህልም ሆነ ባህላዊ ካልሆኑ ልብሶች ጋር ሲለበሱ ሳቢነታቸው በእጅጉ የሚያስደምም መሆኑ ነው። ሥራው ሲጀመር ብዙም ተመራጭ እንደማይሆን ቢያምንም ሲለመዱ ግን ከምንም በላይ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉት ያስባልና ይህንን አልሞ እንደገባበት ይናገራል።
መጀመሪያ ለዓይን ቅርብ የሆነው ጫማ ነው። ወደ ባህላዊ ጫማ ስንመጣ ደግሞ ከሁሉም ቀድሞ የሚታየው እርሱ ይሆናል። ስለዚህም ለዘወትር ልብሶች እንኳን ሳይቀር ማድመቂያነት ከእርሱ ውጪ ተመራጭ አይኖርም። ዛሬም እየሆነ ያለው ይኸው ነው። ብዙዎች የዘወትር እያደረጉትም ይገኛል ይላል ዲዛይነር ዳንኤል።
ጫማ ማንነትን መግለጫ ነው። በቀላሉ ሞቃት፣ ቀዝቃዛና መካከለኛ የአየር ንብረት አካባቢ የሚኖሩ እንኳን እንደየአየር ንብረቱ ተለያይተው ይሰራሉ። ለአብነትም በሞቃታማ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች ሸበጥ በጥበብ ሊሰራ ይችላል። ቀዝቃዛ አካባቢ ለሚኖሩት ደግሞ ሽፍን በተለያየ ዘመናዊ ዲዛይን ይሰራላቸዋል። እናም ከዚህ አንጻር ማንነትን ሳይለቁ በባህላዊ የእጅ ጥበብ ውጤት ጫማዎች ይሰራሉ።
እንደ ዳንኤል ገለጻ፤ የእኛ ጫማ ከመስራቾቹ በተጨማሪ ለስድስት ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ሥራ በሚበዛበት ወቅትም ኮንትራት ሠራተኞችን ይቀጥራል። ሠራተኞቹን የሚያስደስታቸው አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር ምቾት ያለውና ዓይንን የሚስብ ባህላዊ ጫማ መስራት ነው።
«አዛውንቶች የቆየውን ዲዛይን ይፈልጉታል። ወጣቶች ደግሞ ፋሽን ነው የሚወዱት። ስለዚህም ይህንን ፍላጎት ለማጣጣም ሲባል በሁለቱም ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ጫማ ይሰራል። ባህላዊ ጫማዎች ሲሰሩ የእጅ ጥበቡና ዲዛይኑ ትልቅ ዋጋ አለው። ሁለቱን አጣጥሞ መስራት ከምንም በላይ ለባህል መጠበቅ የማይተካ ሚና ይኖረዋል። እናም ሥራውን በማስፋት ወጣቱን ባህል ወዳድ ማድረግ ላይ እንሰራለን »ይላል።
የባህል ጫማዎች ሲሰሩ ምንም አይነት ሌላ ጥሬ ዕቃ አይጨመርባቸውም። በሸማኔው የጥበብ ልክ የተሰሩ የእጅ ጥበቦች ነው እንዲዋብ የሚደረገው። የጫማው ዲዛይንን በመቀያየር ግን ዘመንኛና ከውጭ የሚመጡ ጫማዎችን የሚያስንቁ ማድረግ ይቻላል። ከዚያ ውጪ ከሆነ ግን ማንነቱን ሊቀይር ይችላልና ባህላዊ አይሆንም የምትለው ደግሞ «በእኛ ጫማ» ውስጥ የምትሰራው ሜሮን ግዛቸው ናት።
እርሷ እንደምትለው፤ የባህል ጫማዎች ምቾታቸው፤ የአገልግሎት ቆይታቸውና ጥራታቸው ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ነው የሚሰሩት። ልክ እንደማንኛውም ልብስ ዚፕና ቁልፍ እንደምንጠቀመው ሁሉ ጫማ ላይ የምንጠቀመው ቆዳ እንኳን ሳይቀር ባህላዊ ነው። ስለዚህም ሁሉም ባህላዊ ከሆነ ጥንካሬውም ልክ እንደባህሉ ይሆናል።
«ባህል ዲዛይን ነው፤ የሰው ልጅ ሲፈጠር ጀምሮ አብሮት የተፈጠረ ነው» የምትለው ሜሮን፤ ባህል በሚመቸውና በሚሆነው ልክ መስጠት ማለት ነው። ልኬት ሲኖር ደግሞ ዲዛይን ይኖራል። እናም የባህል ጫማ ላይም የሚመጥንና የሚበቃን ነገር ማስቀመጥ ነው። ሸማኔው ጥለቶችን በማሽን ሳይሆን በእጁ ልብስ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ከዚያ ዲዛይነሩ ደግሞ በምን መልኩ ቢሰሩ ይበልጥ ያምራሉ የሚለውን ሳይንስ ያክልበታል። ይህ የሁለቱ ውህደት ደግሞ ማንነትን በሚገባ እንዲያሳይ ዕድል ይፈጥርለታል። በዚህም ነው ከባህል የወጣ ሥራ አልተሰራም የሚባለው ትላለች።
ዲዛይን የሚመጣው ሰው ከሚያየው፤ ከሚኖርበትና ከአስተሳሰቡ እንዲሁም ከለመደው ነገር ነው። ለዚህ ደግሞ ባህላዊ ልምድ ያለው እጅጉን ቅርብ ነው። ከተማረው የሚለየው በሳይንሳዊ መንገድ እንዴት እንደሚሰራው ብቻ ነው። በዚህም በሚረዳበት ልክ ከመንገር ውጪ የተማረ ሰው ለባለልምዱ ሸማኔ አስፈላጊ አይደለም ትላለች። የእነርሱን ትክክለኛ ምልከታ በሳይንሱ ለመደገፍ ግን ከሸማኔዎች ጋር ተግባብቶ መስራት ያስፈልጋልና እኛ ይህንን እያደረግን ነውም ብላለች።
ዲዛይኖቹ አሁን የመጡ አይደሉም።ለዚህም ማሳያው ከዛሬ አርባና ሃምሳ ዓመት በፊት ሲያገቡ ያጠልቁት እንደነበር በፎቶ ጭምር አምጥተው እንደሚያሳዩዋቸው የገለጸችው ሜሮን፤ ይህ የሚያሳየውም ልምድ ያለው ሰው መሀል ላይ መጥፋቱን ነው። ስለዚህም ዳግመኛ የተነሳው የባህል ጫማ ሥራ ዳግም እንዳይጠፋ በጽሁፍና በተግባር ተደግፎ ተተኪዎችን እያፈራ መስራት እንደሚገባ ትናገራለች። ለዚህ ደግሞ እኔና መሰሎቼ ትልቅ ኃላፊነት አለብን፤ የበኩላችንን ማበርከትም ይገባናል ባይ ናት።
መንግሥትም ቢሆን ባህላዊ የጫማ ዲዛይን መማሪያ ተቋማትን መክፈት ይኖርበታል። ጠቅላላ አልባሳት ዲዛይን በሚል ብቻ መሰጠቱ ተፈላጊነቱን ያሳንሰዋልና ይህ ሊታሰብበት ይገባል ስትል ትገልጻለች።
የሜሮን እህት አንበሳ ጫማ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥራ ትሰራለች። ሜሮንም ጫማ መስራትን የለመደችው ከእርሷ ነው። ከዛም በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በደረጃ ሦስት የጫማ ዲዛይን ሥራን ተማረች። ሆኖም የጫማ ሥራ ብዙ ባለሙያ አለው ስለዚህም ተጠቃሚ አያደርገኝ ይሆናል ብላ በማሰብ ወደ ባህላዊ የጫማ ሥራ ገብታለች።
«ያደጉት አገራት በእጅ የሚሰራ ነገር ምን ያህል ከባድና አድካሚ እንደሚሆን ስለሚገነዘቡ ዋጋው ሲገለጽላቸው ይመጥነዋል ብለው ይቀበላሉ» የምትለው ዲዛይነር ሜሮን፤ በእኛ አገር ግን የባህላዊ ጫማዎች ዋጋ ውድ እንደሆነ ይታሰባል። ስለዚህ ብዙዎች ለመግዛት አይደፍሩትም።
ሜሮን የጫማ ሥራውን የጀመረችው በቴክኒክና ሙያ እየተማረች ሳለ ትቆጥብ በነበረው ገንዘብ መነሻ ላይ ተጨማሪ ከማህበሩ አባላት ጋር ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ብድር አገኙ። ስድስት ሆነው ማህበሩን ከመሠረቱት መካከል። አምስቱ ዛሬ ድረስ ሥራውን አጠንክረው ቀጥለዋል። መነሻቸው 12 ሺህ ብር ነበር። ዛሬ ብድራቸውን መልሰው በአራት ዓመት ውስጥ መቶ ሺህ ብር መድረሳቸውንም ነው የነገረችን። የባህል የጫማ ሥራው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ሲመጣ የአሰራር ጥበቡን እያዘመነው በመምጣቱ ሁሉም አካላት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። እነርሱም በቀን ከ30 ጫማ በላይ ሰርተው እያስረከቡ ናቸው ።
ቻይኖች ዛሬ ላይ ገበያውን ሁሉ የተቆጣጠሩት ያለምክንያት አይደለም።«የለም» የሚለውን ነገር በእነርሱ ዘንድ በመተዋቸው ነው። ስንት ነው ያለህ እንጂ የለም የሚል ምላሽ አይሰጡም። ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ባለው ገንዘብ ልክ ይሰራሉ። እኛም በባህል ጫማው ትርፋማ ለመሆን የለም ሳንል ከትንሽ ጀምሮ ለመስራት እንሞክራለን። ሃያ ብር ትርፍ ብናገኝ እንኳን እንሰራለን። አያዋጣም ብሎ የሚተው ሥራ የለም። ምክንያቱም ማስተዋወቅ፣ ማስለመድና ማስቀጠልን ስለምንፈልግ መስራት ላይ ትኩረታችንን አድርገናል ትላለች።
«ከቻይና የተወሰደብንን ብቻ ማቀንቀን አይገባንም ጥሩ ልምዷን ወስደን ከእርሷ የተሻለ ለመሆን መትጋት አለብን» የምትለው ሜሮን፤ ዛሬ ከጥራት አኳያ የቻይና ልብሶች ተትተው ማህበረሰቡ ወደ ራሱ ተመልሷል። ስለዚህም የራሱን እንዲያይ ለማድረግ ደግሞ እኛ በባህል ዘርፉ የምንሰራ ባለሙያዎች የለም ሳንል ባህል ወዳድ ማህበረሰብ መፍጠር ላይ ልንሰራ ይገባል መልዕክቷ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2011
ጽጌረዳ ጫንያለው