ከአዲስ አበባና ከሀዋሳ የተሰባሰቡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችንና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ተዋናዮችን ያካተተው የጎብኚዎች ቡድን የደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖችን የቱሪዝም መስህቦች ጉብኝቱን ጅማሬ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጌዲኦ ዞን ለማድረግ በዞኑ ከተማ ዲላ ምሽት ገብቶ አዳሩንም በዚያ አርጎ ማለዳ ተነስቷል፡፡የጉብኝቱን አሀዱ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የእጽዋት ጥበቃ እና የኢኮ ቱሪዝም ማእከል በማድረግ በቡና ምርቷ በእጅጉ ወደ ምትታወቀው ይርጋ ጨፌ ወረዳ ማቅናት ጀመረ፡፡
በዲላም እስከ ይርጋ ጨፌ ባለው መንገድም የዞኑ የተፈጥሮ ገጽታ ይታያል ።ዲላ በጫካ ውስጥ የተመሰረተች ከተማ ትመስላለች፡፡በዛፎች ተሸፍናለች፤ ዛፎቹ ብቻቸውን የቆሙ አይደሉም፤ ከስራቸው እንሰቱ፣ ሙዙ፣ ቡናው፣ ሸንኮራው፣ ወዘተ. በስፋት ይታያል። ከከተማዋ መግቢያ አንስቶ በመላ ከተማዋ ዛፎችን መመልከት ፣ ከተተንተራሰችው ተራራማ አካባቢም እንዲሁ ዛፎችን እና በስራቸው የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸውን እጽዋትን መመልከት የከተማዋ በአጠቃላይ የአካባቢው መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
ወደ ሞያሌ የሚወስደውን አውራ ጎዳና ይዘን ወደ ይርጋጨፌ ስንጓዝ በግራም በቀኝም ከፊትም የደን ሽፋኑ ይበልጥ ጎልቶ ይታያል፤ የተፈጥሮና የሰው ልጅ ትስስር የተጠበቀበት በሚል የሚታወቀው የጌዲኦ ዞን ወረዳዎች አንዷ ከሆነችው ይርጋ ጨፌ ከተማ ደርስን። ከዲላ ይርጋጨፌ 37 ኪሎ ሜትር አካባቢ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ ።በከተማዋ በስተግራ አድርገን ቁልቁለቶችን፣ ዳገቶችን ፣ ሸለቆዎችን እየተጠማዘዝን ስንወጣም ዛፎችና በስራቸው ያሉትን ልዩ ልዩ ተክሎችንና ወንዞችን እንመለከታለን፤ ሁሉም የአካባቢው የተፈጥሮ በረከቶችና መስህቦች ናቸው፡፡ገና ከጥብቁ ደን ሳልደርስ ከጉዞውና ስለጌዲኦ ዞን ከተሰጡ መግለጫዎች የተረዳሁትን መሬት ላይ ማግኘት ችያለሁ፡፡
ዞኑ የጥምር እርሻ /የአግሮ ፎረስተሪ/ አካባቢ መባሉንም ከጉዞው መረዳት ይቻላል፡፡በእዚህ አካባቢ ግዙፍ ዛፎች በትናንሾቹ ላይ ጠፈጠፍ በማሳረፍ አይጎዷቸውም፤ በጥላቸውም ጸሀይ አይከለክሏቸውም፤ በስሮቻቸውም ምግብና ውሃ አይሻሟቸውም ፤ይልቁንም ከሀሩር ይጠብቋቸዋል፤ በቅጠሎቻቸው ማዳበሪያ ይለግሷቸዋል፤ ሁሉም እጽዋት አምሮባቸው መታየታቸውም ከዚህ የመነጨ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ከይርጋ ጨፌ 34 ኪሎ ሜትር ከተጓዝን በኋላ በርካታ ሰዎች ከተሰባሰቡበት ስፍራ ደረስን፡፡መዳረሻችን መሆን አለበት፤ የተሰበሰበው ህዝብ እኛን የሚጠብቅ መሆን አለበት ስል አሰብኩ፡፡የጌዲኦ ባህላዊ አልባሳት የለበሱ ወጣቶች በጌዲኦኛ እያዜሙና እየተወዛወዙ ናቸው፡፡በአካባቢው ባለው ጎጆ ፊት ለፊት ደግሞ ሌላ አንድ ስነስርአት ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል፤ በዚህም ስፍራ የጌዲኦ አባቶች ዝግጅታቸውን አቅርበው ወደ ጎጆ ቤቱ በመግባት ሌላ ስነስርአት ማካሄዳቸውን ቀጠሉ፡፡
በስፍራው ስንደርስ ስለተካሄዱት ስነስርአቶች የጠየቅናቸው የጌዲኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ማሩ እንዳሉት፤ የደረስንበት አካባቢ ወግድ አምባ ይባላል፤ ወግድ አምባ በዩኔስኮ በሚዳሰስ ቅርስነት በቅርቡ እንደሚመዘገብ የሚጠበቀው የጌዲኦ ጥብቅ ደን የሚገኝበት ቀበሌ ነው፡፡ከዲላ እስከ ወግድ አምባ ያለው ስፍራም በጥምር ግብርና ስፍራነቱ /በመልካ ምድሩ/ እና ጥብቅ ደን ያለበት በመሆኑ በዩኔስኮ በአለም ቅርስነት ሊመዘገብ የታጨ ነው ።የጌዲኦ ህዝብ አንድ ባህላዊ ዜማ/ አንተም/ አለው ያሉት አቶ ዮሴፍ፣ በሁሉቃ እንግዳ ሲመጣ አቀባበል እንደሚያደርግ ይገልጻሉ፡፡በዚህም ሁሉቃ በማካሄድ እንግዶቹን መቀበሉን ነው የተናገሩት፡፡
ወጣቶቹም ‹‹እኛ /ጌዲኦ ህዝብ/ እዚህ ቦታ መጣን፤ ለእዚህ ደረስን፤ ይህን አካባቢ አለማን፤ እውቃታችንን ደግሞ ለሚቀጥለው ትውልድ እናስተላልፋለን›› የሚል መልእክት በዜማ እያስተላለፉ ምስጋና ማቅረባቸውንና ‹‹እናንተም ሾልካችሁ ውጡ፤ ክፉ አይንካችሁ›› ማለታቸውን አቶ ዮሴፍ አብራሩልን ።
የቆምንበት ያለው ጎጆ፣ ከፊት ለፊቱ መሹለኪያ በርና ከአጠገቧ ጦርና ጋሻዎች የተቀመጡበት፣ የእንሰት ቀጥል ከበሩ አንስቶ ጎጆው ድረስ የተነጠፈበት ስፍራ ይታያል፡፡ ይህ ስፍራ ባህላዊ ስርአት የሚካሄድበት ሶንጎ በመባል የሚጠራ መሆኑን አቶ ዮሴፍ ይናገራሉ፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ በሶንጎ ባህላዊ ዳኝነት ይካሄድበታል፤ በጌዲኦ ማህበረሰብ ከአምስት መቶ በላይ ሶንጎዎች ይገኛሉ፤ በእያንዳንዱ ሶንጎ የማስታረቅ ስራና ሌሎች በርካታ ስነስርአቶች ይካሄዳሉ፡፡ለምሳሌ ዝናብ ሊጠፋ ወይም ያለወቅቱም ሊጥል እንደሚችል ጠቅሰው፣ ይህ ችግር እንዲወገድ ህዝቡ ይህን በመሳሰሉት ሶንጎዎች ወጥቶ ፈጣሪውን የመለማመን ስርአት ይፈፀማል፡፡
እንደ አቶ ዮሴፍ ገለጻ፤ ሶንጎ ከዘመናዊው የዳኝነት ስርአት ይለያል፤ ሁሉቃም ሶንጎ ነው፡፡ትልቅ ዛፍ ስር ነው ሁሉም የሚከወኑት፤ በጌዲኦ ዛፍ ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡ያ ቦታ ቅዱስ ነው፤ ዛፍ ስር ነው የሚጸለየው፤ ችግር ያለበት ሰው እዚያ ይሄዳል፡፡ችግሩን ሽማግሌዎች ይፈታሉ ።ሰው ወደ ፍርድ ቤት ከመሄድ ይልቅ ወደዚያ ነው የሚሮጠው፤ ፍርድ ቤት ቢሮክራሲ አለ፤ ይህ ግን ቢሮክራቲክ አይደለም፤ ሰው አየኝ አላየኝ ብሎ ነገር የለም፤ መረጃ የሌላቸው ወንጀሎች እዚህ ነው የሚታዩት፡፡
ጌዲኦዎች ሶስት ቦታ ላይ ለዛፎች ጥበቃ ያደርጋሉ፡፡ አንዱ ጥብቅ ደን ላይ ነው፤ ጥብቅ ደን ጨርሶ አይነካም ፤ ሁለተኛው ደግሞ ጥምር እርሻ /አግሮ ፎረስትሪ/ ላይ ነው፡፡እዚህ ጌዲኦ መልካምድር ላይ ዛፍ አይቆረጥም፤ ይጠበቃል እንጂ፤ ሌላኛው መንገድ ዳር ያሉ እንዲሁም ለደን በተለዩ ቦታዎች ያሉ ደኖችም እንዲሁ ዛፍ አይቆረጥባቸውም ፡፡
በዞኑ ወደ ስምንት የሚደርሱ ስፍራዎች /ሳይቶች/ በዩኔስኮ ተከልለው ለመመዝገብ መታጨታቸውን ጠቅሰው፤ ዩኔስኮ በቅርቡ በሚያካሂደው ኮንፈረንስ ጥብቅ ደኑ በሚዳሰስ ቅርስነት ይመዘግበዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ዮሴፍ ይጠቁማሉ፡፡
ጥብቅ ደኑን የምንጎበኝበት ወቅት ደርሷል፤ ጎብኚዎችና በስፍራው የተገኘው ህዝብ ለጉብኝቱ ሲንቀሳቀስ መኪና ወደ አካባቢው እንደማይገባና ጉዞው በእግር እንደሆነ ማሳሰቢያ ተሰጠ ።ጎብኚዎች እንዲቆሙ የተደረገው የጌዲኦ ሽማግሌዎች ወደ ጥብቅ ደኑ እንዲገቡ እስከሚፈቅዱ ድረስ ነበር፤ ከካሜራ ማኖችና ጋዜጠኞች ውጪ ሌሎቻችሁ ቁሙ ሲባል እኔም አልፌ ፎቶ ማንሳት ጀመርኩ፡፡ሽማግሌዎቹ ፈቃዳቸው ሆነናም ጉዞው በእግር ተጀመረ፡፡
መንገዱ ቁልቁለታማ፣ ቀጭንና ሊያንሸራትት የሚችል አይነት ነው፤ ብዙም ጭቃ ባይሆንም፣ ፈጥኖ መጓዝ አያስችልም፤ በመንገዱ በስተግራ በኩል ግዙፍ ዛፎችና ጥቅጥቅ ያለ ደን ይታያል፡፡ ብዙ ተጉዘን አሁንም እንድንቆም ተደረገ፡ ፡ለካስ ጥብቅ ደኑ ጋ ደርሰናል፡፡
አቶ ገረመው ደንቦባ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው፡፡በጌዲኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ ወግዳ አምባ የተፈጥሮ ደን ይሄ ነው ሲሉ በእጃቸው እያመለከቱ ስለደኑ ማብራራት ጀመሩ፡፡አምባ ስለሚለው ቃልም ያብራሩልን ጀመር፡፡አምባ የጌዲኦ ቃል ነው፤ ትርጉሙም ስውር፣ ምስጢር፣ ዋሻ፣ ከለላ፣ ምሽግ ማለት ነው ሲሉ አብራሩ፡፡አምባ ተብሎ ለምን እንደተሰየምም ሲያብራሩ፤ ጌዲኦ ለም የቡና መሬት አለው፡፡በዚያው ልክም ብዙ ጠላቶች ነበሩበት፡፡እነዚህ ጠላቶቹ ይህን ለም መሬት ሊወስዱ ብዙ ደክመዋል አሉን፡፡
ሌሎች መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ደግሞ ጌዲኦን ከእነዚህ ጠላቶቹ የታደገው ይህ ደን ነው፤ እናም ህዝቡ ለደን ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው አንድም ከዚህ በመነሳት ነው፡፡
አቶ ገረመው ‹‹ እዚህ ጥብቅ ደን ውስጥ የዱር አራዊት አሉ፤ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡እዚህ ደን ውስጥ ቀይ ቡራቡሬ ነብር አለ ፤ ነብሩ ቢተናኮል እኔ የለሁበትም፤ ከእንግዶቹ ውጪ ማለቴ ነው፡፡ጅብ ተናዶ ቢወጣ እኔ የለሁበትም፣ እንግዶቼ በምርቃት ስለመጣችሁ እናንተን እንዳይነካብኝ የጸጥታ ሀይሎች ጠበቁልኝ፤… ሲሉ አሳሰቡ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ የጌዲኦ ህብረተሰብ የሰው ነፍስ አያጠፋም፤ ከገደለም ይኮነናል፤ ይገለላል፤ እንስሳትን አይገድልም፤ አድኖም ከገደለ እንዲሁ ይኮነናል፤ ሰባት ቤት ድረስ ያልቅበታል ።የጌዲኦ መንፈስ እዚህ ድረስ ይዘልቃል ።ዛፍ አይቆርጥም፤ ለእዚህ ምስክሩም ጥብቅ ደኑ ነው፡፡ይህ አካባቢ ድንግል መሬት ነው፤ ዶማና ማረሻ አላየውም፤ የጌዲኦ ቀደምት አባቶች በቃል ብቻ ያጸኑት ቦታ ነው፡፡
ያለ አካባቢው አባቶች ፈቃድ እዚህ አይገባም ይላሉ፡፡ከሌላ ቦታ የዱር እንስሳት ተሰደው ወደ እዚህ ደን እየመጡ መሆናቸውንም ነው አቶ ገረመው የጠቆሙት፤ በድርቅ ምክንያት ከተመናመነው ጂጎ ደን አራዊት ወደ ዚህ ደን እየመጡ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡
ቁልቁለቱ፣ የመንገዱ ጥበትና ምናልባትም ዝናብ ቢጥል ለመውጣት ሊፈጠር የሚችለውን ችግር በማሰብ አብዛኛው ሰው መመለስ ቢጀምርም፣ ካሜራ ማኖች፣ጋዜጠኞች ግን ደኑን በደንብ ማየት ወደሚያስችለው ስፍራ መሄዳቸውን ቀጭኑን መንገድ ይዘው ቁልቁል መውረዳቸውን ቀጥለዋል፡፡በመጨረሻም የደኑን አጠቃላይ ገጽታ በድሮን ማንሳት መጀመሩ ስለተነገረ መመለስ ግድ ሆነ፡፡
ስለደኑና ባህላዊ ስርአቱ ያነጋገርናቸው የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ይህን ደን የጠበቀው የብሄረሰቡ ስርአት መሆኑን ይገልጻሉ ።አንድም ጎብኚ የብሄረሰቡን ሽማግሌዎች ሳያስፈቅድ ወደ ደኑ እንደማይገባም ጠቅሰው፣ ዩኔስኮ ጥብቅ ደኑን ብቻ ሳይሆን ይህንን ባህላዊ ስርአት ጭምር ለመመዝገብ እያየው መሆኑን ይናገራሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በሀገሪቱ የግብርና አሰራር ከፍተኛ ቦታዎች የመሬት አቀማመጥ 30 በመቶው ብቻ ነው ለግብርና ስራ የሚፈቀደው። በጌዲኦ ግን ይህ አይሰራም፤ ሁሉም ቦታ ይመረትበታል፤ በዞኑ ተራራማ ቦታ ላይ እንሰት፣ ቡና፣ ወዘተ. ለምቶ ይገኛል፤ ክፍት ቦታ የለም፤ አካባቢው ሲታይ አግሮ ፎረስትሪ አይመስልም፤ ደን ነው የሚመስለው፤ ሰው ውስጡ ያለ አይመስልም፤ ብዙ ሰው ግን አለበት፡፡ከፍተኛ የሕዝብ ጥግግት ያለበት አካባቢ ነው፤፡ በአንድ ስኩየር ኪሎ ሜትር ላይ ወደ አንድ ሺ ሶስት መቶ ሰዎች ይኖራሉ፤ ይህን ህዝብ የተሸከመው ይህ ስርአት ነው፡፡ደኑ ውስጥ ያለው ምግብ ነው፤ እንሰት፣ ጎመን፣ ፍራፍሬ ፣ ወዘተ አለ ። ይህ ደግሞ በትምህርት የተገኘ አይደለም፤ በሀገር በቀልና ከትውልድ ወደ ትውልድ በተላለፈ እውቀት ነው፡፡
ይህን አካባቢ ካልቸራል ላንድ ስኬፕ ብሎ በሚዳሰስ ቅርስነት ለመመዝገብ ዩኔስኮ ከልሎት ያለው ጥብቅ ደኑን ብቻ አይደለም፤ ይህን ሀገር በቀል እውቀትና ትክል ድንጋዮችን ጭምር ነው ።እዚህ አካባቢ አግሮ ፎረስትሪና ትክል ድንጋዮች አሉ፡፡በአፍሪካ ደረጃ በተካሄደ ጥናት በአህጉሪቱ ወደ አስር ሺ ትክል ድንጋዮች ይገኛሉ፤ ከዚህ ውስጥ ከስድስት ሺ በላይ ትክል ድንጋይ የሚገኘው በጌዲኦ ዞን ነው፡፡እነዚህ ትክል ድንጋዮች በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ቢገኙም በዩኔስኮ አምስቱ ስፍራዎች ናቸው ለምርጫ የቀረቡት፡፡ይህን ካየን በኋላ በየቦታው ያሉትን ትክል ድንጋዮች ለማስመዝገብ ደግሞ እንሰራለን ሲሉ አቶ ዮሴፍ ይገልጻሉ፡፡
አቶ ዮሴፍ እንደሚሉት፤ ይህን የጌዲኦ ዞን መስህብ ለማልማት እየተሰራ ነው፡፡ቀጥሎ የሚመጣው ማስተዋወቅ ነው፡፡የዚህ ጉብኝት አንዱ አላማም ይሄው ነው፡፡ መንገዱ ወደ መስህቡ እንደልብ አያስገባም ነበር፤ ይህን መገንባት ተችሏል፤ ሳይቶቹ ተከልለዋል፤ ጥበቃ አለ፡፡
ይህ አካባቢ በዘመናዊ እውቀት አይደለም እየተጠበቀ ያለው ፤በሀገር በቀል እውቀት ነው፤ ይሄ ማህበረሰብ እያከናወነ ያለው ተግባር በሚገባ ከተዋወቀ ከቱሪዝም ዘርፉ ብቻ ሳይሆን ከካርቦን ገበያም ተጠቃሚ መሆን ይቻላል፡፡ይህ ስራ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንዲሁም ከዘመናዊ እውቀት ጋር ቢቀናጅ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻልም ይናገራሉ፡፡ተመጋጋቢነት እንዳለም ነው የሚናገሩት፡፡በጌዲኦ ዞን የማይዳሰሰው የህብረተሰቡ የደን መጠበቂያ ስርአት፣ የሚዳሰሰውን አግሮ ፎረስትሪ እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚያው ልክም አግሮ ፎረስትሪው የማይዳሰሰውን የህብረተሰቡን ስርአት እየጠበቀው ይገኛል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ጉብኝቱን ያዘጋጀው የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፍሬህይወት ዱባለ በጉብኝቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡ እሳቸው እንደተናገሩት፤ የጉብኝቱ አላማ አዳዲስ የቱሪስት መስህቦችን በማስተዋወቅ ወደ ቱሪዝም ገበያው ማስገባት ነው፡፡ክልሉ በርካታ የቱሪዝም ሀብቶች አሉት፤ መስህቦቹ ግን በሚገባ እንዲተዋወቁ ባለመደረጉ ወደ ቱሪዝም ገበያው በሚፈለገው ልክ አልገቡም፡፡
በአንጻራዊነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የደቡብ ክልል በቱሪዝሙ ዘርፍ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዳለው ጠቅሰው፤ አሁንም ቢሆን ቱሪስቱ የሚፈለገውን ያህል እየገባ አይደለም ይላሉ፡፡ለዚህ አንደኛው ምክንያት ኮቪድ መሆኑን ገልጸው፣ ሁለተኛው እንደ ሀገር ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ያለው ችግር በሀገር ገጽታ ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተጽእኖ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡መስህቦችን በማስተዋወቅ ቱሪስቱን የበለጠ ለመሳብ እየተሰራ መሆንም ተናግረው፤ ጉብኝቱም የዚህ አካል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እየተካሄዱ ያሉ ስራዎችን ተከትሎ በቅርቡም ወደ ጋሞ ዞን የሚሄዱ 34 የሚጠጉ የውጭ ዜጎች ወደ ሀገሪቱ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የደቡብ ክልል ቱሪዝም ፓርኮችንም ያካተተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ክልሉ በሚያስተዳድራቸው ብሄራዊ ፓርኮችና የአርባ ምንጭ አዞ ራንች ላይ የመዳረሻ ልማቶችን እንደሚያካሂድ ይገልጻሉ፣ ሌሎቹን ዞኖች በራሳቸው እያለሙ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ጌዲኦ በአግሮ ፎረስትሪ፣ በክልሉ ከቡና ጋር በተያያዘ የሚታወቅ መሆኑን ተናግረው፤ በአለም ቅርስነት ሊመዘገብ የደረሰ ያለቀለት ጥብቅ ደን ሀብት በዞኑ እንደሚገኝም ይጠቅሳሉ፡፡
ይህን ሀብት በባህላዊ እሴቱ ጠብቆ ያቆየው የጌዲኦ ማህበረሰብ መሆኑንም አመልክተው፤ ጥብቅ ደኑን የጎበኘነው የጌዲኦ አባቶች ፈቅደውልን መርቀውን ነው፤ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶቻችን ጠብቀን መጓዝ ያለብን ስለመሆኑ ከጌዲኦ ህዝብ ብዙ ተምረናል ነው ያሉት፡፡
በዞኑ የሚገኙ ትክል ድንጋዮች፣ በዩኔስኮ ሊመዘገብ የተቃረበው ጥብቅ ደን፣ ህዝቡ ደኑን የጠበቀበት ባህላዊ ስርአት፣ በጉብኝቱ ወቅት የተመለከትናቸውና ያጣጣምናቸው ባህላዊ ምግቦቹ፣ የጎጆ ቤት አሰራሩና ሌሎች ባህላዊ ስርአቶቹ በእርግጥም ዞኑን የቱሪስት መስህብ ያደርጉታል፡፡እነዚህን መስህቦች በማስተዋወቅ መስህቦቹ ለገበያ እንዲውሉ እየተደረገ ያለው ጥረት ሊበረታታ የሚገባውና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው፡፡
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም