ህሙማኑ ህፃናት ብቻ ሳይሆኑ ወላጆችም የልጆቻቸውን ጭንቀት በሚጋሩበት የህፃናት የልብ ሕክምና ቀደምቱና አንቱ የተባሉ ናቸው።ዛሬ ላይ በሀገራችን የልብ ማዕከል በመከፈቱ ብቻ ሳይሆን እሳቸውና መሰሎቻቸው ባፈሯቸው በርካታ የህፃናት የልብ ሐኪሞች ርብርብ ከአምስት ዓመትና ከዛ በታች ያሉ የህፃናት ሞት በእጅጉ ቀንሷል። ህፃናትም ለሕክምና ወደ ውጭ ሀገር መላካቸው እየቀነሰ ነው።ወላጅም ህፃናት ልጆቹን ውጪ ልኮ የሚያሳክምበት ጥሪትና የሀገር ውስጥ ሕክምና በማጣት መጨነቁና መሳቀቁ እየቀነሰ ነው። በሀገር ውስጥ የህጻናትን ሞት ለመቀነስ አስተዋጸኦ የነበራቸውን ልዩ ልዩ የጤና መርሐ ግብሮች በመዘርጋት ኢትዮጵያ በተለይም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጤናው ምርምር ረገድ ላሣዩት እመርታ የጎላ ድርሻ አላቸው።በኤች አይቪና በኮቪድ ጊዜ እጃቸውን አጣጥፈው ሳይቀመጡ ውጤታማ ታሪኮችን ሰርተዋል። የጤና ባለሙያዎች በተለያዩ መርሀ ግብሮች ከማሰልጠን ባለፈ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህፃናት ህክምና ክፍል ተቀጥረው ከአሥር ዓመት በላይ በመምህርነት አገልግለዋል።እስከ አሁንም እያስተማሩም ይገኛሉ።ለበርካታ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት የጤና መርሐ ግብሮቹ ያመጡትን ለውጥም በመገምገምና በማሻሻል ለረዥም ዓመታት ተሳትፈዋል። ሐኪም፣ አስተማሪ፣ ሜዲካል ሳይንቲስት ናቸው።የኮሚቴና የማኔጅመንት ሥራዎችንም ይሰራሉ።ለማስተማር የሚደረግ ዝግጅት ጨምሮ አብዛኞቹን አካዳሚክ ሥራዎችን እቤት ከሄዱ በኋላ ሌሊት ነው የሚሰሩት። ምክንያቱም ቀን ሕሙማንን ማስተናገድ፤የልብ ሕክምናውን መስራት፡ በተለያየ ደረጃ ላሉ የህክምና ተማሪዎችን ሌክቸር መስጠት አለ ። የተለያየ ምርመራና ቀዶ ጥገና የተደረገላቸውን መከታተል ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ በራሱ ቀላል አይደለምና ነው።በዚህ መካከልም በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በሀገር ውስጥና በውጪ ማሳተም ችለዋል።በወጣትነታቸው ዘመን የኪነት ቡድንን ተቀላቅለው ባማረ ቅላፄ ሲዘፍኑ የሚያውቋቸው የሕክምና ሙያ መቀላቀላቸውን ባያምኑም ተግተው በማጥናት እጅግ ከፍተኛ ውጤት አምጥተው በህፃንነታቸው ሲመኙት የነበረውን ሙያ የራሳቸው ማድረግ ችለዋል።በሙያቸውም በገጠር የሚኖረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ለስምንት ዓመታት ተዘዋውረውም እንደተመኙት አገልግለዋል።የዛሬ እንግዳችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተባባሪ ፕሮፌሰር ታምራት ሞገስ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ አስተዋጽኦ ጨምሮ የበርካታ ህፃናትን ሕይወት ከሞት መታደግ የቻሉበትን ተሞክሯቸውን እንድትጋሩልን እንጋብዛለን።
ትውልድና እድገት
ኢሉባቦር ሊሙገነት የሚባል ከተማ ነው የተወለዱት። ምክንያታቸው ወላጅ አባታቸው ከመሀል አዲስ አበባ ተነስስተው ሊሙ ገነት ከተማ ውስጥ ኢትዮጵያና አሜሪካ በጋራ ይሰሩበት ወደ ነበረ የቡና ልማት ኩባንያ ተቀጥረው ሲሰሩ ከእናታቸው ጋር የተዋወቁበት አጋጣሚ ነው። ሆኖም ወላጆቻቸው በትምህርት ደረጃ በመበላለጣቸው እሣቸው ከተወለዱ በኋላ ወላጆቻቸው አብረው መቀጠል አልቻሉም። አባታቸው ወደ አዲስ አበባ ይዘዋቸው በመመለስ ለአያቶቻቸው ሰጧቸው። አያቶቻቸው ከአዲስ አበባ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ መናገሻ ኮሎቦ በምትባል ስፍራ ላይ ነበርና የሚኖሩት እነሱ ጋር ወስደው አሳደጓቸው።
አያቶቻቸው እንደነገሯቸው ታድያ በህፃንነታቸው እጅግ ታማሚ ነበሩ። ምክንያቱም በተወለዱበት ዘመን ስለ ልጅ አስተዳደግ ለእናቶች የሚሰጥ ትምህርት አልነበረም። ክትባት፤የተመጣጠነ የህፃናት አመጋገብ፤ ኦ አር ኤስ የለም።በመሆኑም እሳቸውን ጨምሮ የዚያን ዘመን ህፃናት በመጣው በሽታ ሁሉ እየታመሙ ነው ያደጉት።‹በተለይ ኩፍኝ የታመምኩበትን ወቅት አልዘነጋውም› የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ አያቶቻቸው የሰው ጥላ እንዳያገኛቸው ከማድረግ ጀምሮ እንዴት አድርገው ሲያስታምሟቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።‹‹ታናሽ እህቴ በሰባት ዓመቷ በኩፍኝ በሽታ ታማ መሞቷም አሁንም ከሆዴ ያልወጣ ቁጭት አሳድሮብኛል››ይላሉ።ወደ ሕክምና ሙያ እንዲገቡ ያደረጓቸውም እነዚሁ ሁኔታዎች ነበሩ። ‹‹ምክንያቶቹ በትንሹ ልቤ ውስጥ በህፃናት ሕክምና ዙሪያ የቀረ ጉዳይ አለ ብዬ እያሰብኩ እንድኖርና እንድሰራም አድርገውኛል›ሲሉም ይገልፃሉ።
የትምህርት ቤት ቆይታ
የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መናገሻ ኮሎቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማሩት።የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በቀጥታ አባታቸው ጋር አዲስ አበባ ነው የመጡት።የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኮልፌ ኮምፒሬሲቭ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀዋል።ሁለተኛ ምርጫቸው አርቲክቸር ቢሆንም ከፍተኛ ውጤት ስላመጡ በመረጡት የሕክምና ሙያ ህክምና እንዲያጠኑ ተደረገ። ‹በኔ ህመምና በእህቴ ሞት ከልጅነቴ ጀምሬ ሐኪም ብሆን ችግሩን መቅረፍ እችላለሁ››እያሉ ይመኙት የነበረው ትክክለኛው ቦታቸው ሕክምና ነበርና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሚገኘው ሜዲካል ኮሌጅ አንድ ሙሉ ሐኪም ሲመረቅ ጄነራል ፓርቲሽነር በሚያሰኘው የመጀመሪያ የዶክተሬት ዲግሪ ተመረቁ።
የሥራ አሀዱ
የያኔ ወጣቶች ከአዲስ አበባ ውጪ ሥራ አንሰራም የሚባል ነገር አያውቁም። ትኩረታቸው በሙያቸው ያስተማራቸውን ወገናቸውን ማገልገል እንጂ ምቾት ፍለጋ ብቻ አልነበረም። አካባቢው የማይመቻቸውና መሰረተ ልማት የሌለው ቢሆንም የሚፈልጉት በሕክምና እጦት የሚቸገረውን የገጠሩን ሕብረተሰብ ማገልገል በመሆኑ ሳያቅማሙና ሰበብ ሳያበዙ የተመደቡበት ቦታ ይሄዳሉ።አዲስ አበባ ሥራ የመቀጠር ዕድል ቢኖራቸውም እንኳን ክልል መርጠው የሚሄዱ ብዙ ሐኪሞች እንደነበሩም ያስታውሳሉ። ታድያ እሳቸውም በ1982 ዓ.ም ቤንሻንጉል ክልል ውስጥ በሚገኘው የመተከል ጠቅላላ ሆስፒታል ተመደቡና የሥራ ዓለምን አሀዱ ብለው ተቀላቀሉ። በሕክምናው ዘርፍ አንድ ሙሉ ሐኪም ሲመረቅ ጄነራል ፓርቲሽነር እንደመባሉም በዚህ ደረጃ ከተመረቁ በኋላ በጀነራል ፕራክቲሽንነት ለሦስት ዓመታት ሕዝቡን ሲያገለግሉም ቆዩ። ተመልሰው ለስፔሻላይዜሽን ወደ አዲስ አበባ መጡ። በሕክምና ሙያ አንድ ሐኪም የተወሰነ ዓመት ከሰራ በኋላ በአንድ የሕክምና መስክ ስፔሻላይዝድ ማድረግ የግድ ይጠበቅበታል።እንግዳችን እንደሚሉት ለምሳሌ፦ በስፔሻላይዜሽን ደረጃ የህፃናት፤የውስጥ ደዌ፤ የቀዶ ጥገና፤የዓይን ሕክምና ስፔሻላይዝድ ሊያደርግ ይችላል።እሳቸውም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በሕፃናት ሕክምና ትምህርታቸውን በመከታተል ስፔሻላይዝድ አደረጉ። ስፔሻላይዝድ ካደረጉ በኋላ ዳግም አሁንም የገጠሩን ወገናቸውን ለማገልገል አርባ ምንጭ ሆስፒታል ተመደቡ።በሆስፒታሉ ቆይታቸው በሕፃናት ሐኪምነት፤ በሕፃናት ሕክምና ክፍል ኃላፊነት እንዲሁም በሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተርነት በተለያዩ ደረጃዎች ለአራት ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።ከዚህ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመዛወር ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ለሰባት ዓመታት በሕፃናት ሕክምና ክፍል በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።በተለይ ዘውዲቱ ሆስፒታል ተመድበው ሲሰሩ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ማህበር መርጃ ድርጅት ግቢ ውስጥ ነበር የሚገኘው።ወደ እዚህ ድርጅት በርካታ ከልብ ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸው ህፃናት ከአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ይመጡ ነበር።ድርጅቱ በፊናው እነዚህን ህፃናቶች ተቀብሎ ከውጪ አገር ሕክምና ተቋም ጋር እየተፃፃፈ ለሕክምና ይልክ ነበር። እናም ድርጅቱ በዘውዲቱ ሆስፒታል እያሉ ለአንዳንድ ምርመራዎች ህፃናቱን ወደ እሳቸው ይልካቸው ነበር። በተለይ ዘውዲቱ ሆስፒታል ተመድበው በሚሰሩበት ጊዜ የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ማህበር መርጃ ድርጅት ጽሕፈት ቤት ዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ መሆኑ የልባቸውን ሀሳብ ለመተግበር ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል። በነዚህ ልጆች ዙሪያ እየሰሩም እዛው ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ እራሱን የቻለ የልብ ሕክምና ክትትል ማካሄጃ ክሊኒክ አቋቋሙ። በሦስተኛው ዓመትም በርካታ የልብ ታማሚ ህፃናት ዳታ ሰብስበው የምርምር ጥናት አደረጉ። ጥናቱንም አሳተሙት። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሙያቸውን ወደ ትልቁ የሕክምና ሙያ ሰብ ስፔሻላይዝድ የማሻገር ራዕያቸውን ሰንቀው ነበር። አንድ ዕለት ማታ ከባለቤታቸው ጋር የታመመ ሰው ሊጠይቁ በሄዱበት አጋጣሚ ታድያ ድንገት አንድ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ በጆሯቸው ጥልቅ አለ። ሙያቸውን ወደ ሰብ ስፔሻላይዜሽን ከፍ በማድረግ በአጠኑት ጥናት መሰረት የልብ ህሙማን ህፃናት ለመታደግ የሚያስችል ሥራ የሚያስጀምራቸው የስልጠና ዕድል ነበር።
‹‹ማስታወቂያውን ድንገት ስሰማ ውስጤ “የአንተ ዕድል ነው አለኝ” ።ለዚህ ነው በዕምነት የተወዳደርኩት››ሲሉ ያስታውሱታል ተባባሪ ፕሮፌሰር ታምራት።ገና ለጥየቃ ከሄዱበት ቤት ውስጥ ተሰናብተው ሳይወጡ ነው ለፕሮፌሰሩ አለቃቸው ዕድሉን ማግኘታቸውን የደወሉለት። ሪኮመንዴሽን ደብዳቤ ይፅፍላቸው እንደሆን ጠይቀውትም በሥራው ጉብዝናቸውን የሚያውቀው አለቃቸው ሳያቅማማ ነበር እንደሚፅፍላቸው የነገራቸው። እናም በማግስቱ ቢሮ ሄደው የፃፈላቸውን ደብዳቤ ተቀብለው እንግሊዝ ሀገር የሚገኘውና ቼይን ኦፍ ሆፕ የተሰኘው ድርጅት ወደ አወጣው ማስታወቂያ ሄዱ። በዕምነት ተወዳድረው አላፈሩም። ከአንድም ሁለቴ የወሰዱትን ኢንተርቪው ከነማጣሪያው በአጥጋቢ ውጤት አልፈው በቼይን ኦፍ ሆፕ ድርጅት አማካኝነት ለህጻናት ሰብ ስፔሻላይዜሽን ትምህርት ስልጠና እንግሊዝ ሀገር ሄዱ። የእንግሊዝ ሁለተኛ ከተማ በሆነችው በርሚንግሀም በተሰኘችው የልዕልት ዲያና የህጻናት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥም የመጀመሪያውን የውጭ ሀገር ስፔሻላይዝድ ስልጠና ለመውሰድ በቁ። ተባባሪ ፕሮፌሰር ታምራት ከህፃናት ልብ ህክምና ሰብ ስፔሻላይዜሽን ሙያ ጋር በተያያዘ በእንግሊዙ በርሚንግሀም ከተማ ብቻ ሳይሆን በበርካታ የውጭ ሀገራት ትምህርት ቀስመዋል። ለአብነት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልኳቸው በህንድ ሀገር ክርስቲያን ሜዲካል ኮሌጅ የተሰኘ ትምህርት ቤት ተምረዋል።በተጨማሪም አሁንም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልኳቸው ግብጽ ሀገር በሚገኘው ካይሮ ናሽናል ኀርት ኢንስቲትዩት የተሰኘ ትልቅ የልብ ህክምና ማዕከል የቀሰሙትም ተጠቃሽ ነው። በኦስትሪያ ሣልዝብርግ እንዲሁ በሙያው የመሰልጠን ዕድል አግኝተዋል ። እንግዳችን እንዳወጉን አንድ የሕፃናት ሐኪም ስፔሻላይዝድ ያደረግንበትን አጠቃላይ የህፃናት ሕክምና ይሰራል። እሳቸው የልብ ችግር ያለባቸውን ጨምሮ ሌሎችን ጨቅላ ህፃናትንም ያክማሉ። በመሆኑም እሳቸው ሙያቸው የልብ ህክምናይሁን እንጂ ሳንባ ምቺ፣ወባ፣ አጣዳፊ ተቅማጥና ተውከት፣ማጅራት ገትር ሌሎችንም ሲያክሙ ቆይተዋል።ሆኖም በልብ ሕክምናው መስክ ማንኛውንም ምክር መስጠት የሚችሉት እሳቸው ናቸው። ለምሳሌ፦ በልብ በሽታ ላይ ከነርብ ሐኪሙ ይልቅ የእሳቸው ምክር የበለጠ ይደመጥና ዋጋ አለው። ከዚህ ተሞክሮ ተነስተው እንግዳችን እንደሚናገሩት በተለይ ህፃናት ላይ አብዛኛው የልብ ችግር አብሮ ነው የሚወለደው። ስለዚህም ገና እንደተወለዱ በልብ ህመም ችግር የሚጠረጠሩ በጣም ቡዙ ህፃናትን ያያሉ።ይሄም ከሥራቸው አንዱ ክፍል ነበር።በህፃናት ልብ ህመም ዙሪያ ብዙ ምርምሮችን ሰርተው አሳትመዋል።በዚሁ ዙሪያ ከፃፏቸው ሌሎች በርካታ ጽሑፎች ጋር በአጠቃላይ የሕፃናት ሕክምና ዘርፍ ወደ 23 ፐብሊኬሽን በውጭ አገር እና በአገር ውስጥ ታዋቂ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል። እነዚህ ጆርናሎች በሙያው በጣም የበቁ ሰዎች ተቀባይነት የሰጧቸው (አፕሩቭ ያደረጓቸው) በህፃናት የልብ ችግሮች የሚያተኩሩና ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሳይንስ አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው።
እንግዳችን ጥናታዊ ህትመቶችን መሰረት አድርገው እንደሚናገሩት የሕፃናት ልብ ችግር ሁለት ዓይነት ሲሆን አንዱ ከተወለዱ በኋላ የሚከሰት ነው። ሌላኛው ገና ሳይወለዱ በእናት ማህፀን ውስጥ ይፈጠራል። በእናት ማህፀን ውስጥ ከሚከሰተው የልብ ህመም 85 በመቶው ምክንያቱ አይታወቅም። 15 በመቶው የህፃናቱ እናቶች በእርግዝና ወቅት የተለያዩ መድሃኒቶች የሚወስዱ ከሆነ ይከሰታል። በተለይ ከሚጥል በሽታ ጋር በተያያዘ የሚወሰዱ ወይም የአእምሮ በሽታ መድሃኒቶች በአጠቃላይ ቶክሲክ የሆኑ መድሃኒቶች በምትወስድበት ጊዜ በእናቱ ማህፀን ውስጥ ህፃኑ ሊጎዳ ይችላል ። ለምሣሌ ሩቤላ እንደሚባል ዓይነት ኢንፌክሽን ካጋጠመው ወይም ኤች አይቪ ኢንፌክሽን የልብ ችግር ሊያመጣ ይችላል። በተጨማሪም በዘር የሚተላለፍ የዘረመል (የክሮሞዞም) ችግርም ህፃኑ ከልብ ችግር ጋር አብሮ እንዲወለድ ያደርጋል። ሖርሞኖችን መውሰድ እንዲሁ ህፃናትን ለልብ ሕመም ያጋልጣሉ። ከወሊድ በኋላ ለምሳሌ የደም ካንሰር መድሃኒት የሚወሰዱ ህፃናት የልብ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል።
ከተወለዱ በኋላ የሚከሰተው የልብ ችግር በአብዛኛው ከኢንፌክሽን ጋር በተያያዘ ነው። ለምሳሌ በተደጋጋሚ በባክቴሪያ ቶንሲል የሚታመሙ ህፃናት በወቅቱና በአግባቡ ካልታከሙት ወደ ልብ ችግር እንደሚለወጥም ያወሳሉ። ካልታከሙ ወደ ሦስት በመቶው በልብ በሽታ ሊያዙ ይችላሉ። በቫይረስ ምክንያት የሚመጡ ብዙ የልብ ህመሞች አሉ። ሆኖም አብዛኛው በኑሮ መሻሻል ሊቀንስ የሚችል ነው። የህፃናት የልብ በሽታ የህፃን በሽታ ብቻ አይደለም። በተጽዕኖው የቤተሰብም በሽታ ነው።
በቅርብ የሚያማክሩት ሐኪም እንዳጠናው ጥናት አንድ ታማሚ ህፃን በወላጆች ኢኮኖሚ፤ በቤተሰብ ማህበራዊ ኑርም ላይ ጫና ይፈጥራል። ቤተሰብ ሲጨነቅ፣ ፍቅራቸው ሲቀዛቀዝና ሲጠፋ ትዳር ሲፈርስ የሚታይበትም ጊዜ ብዙ ነው። በሽታውን በመከላከልና ህክምናውን በማስፋፋት ማህበራዊ ተጽዕኖውን መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይ የጨቅላ ህፃናት የጤና ችግር በአብዛኛው የልብ ህመም ቀዶ ጥገና ይፈልጋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሕክምናው ይሰጥ የነበረው ከውጭ በሚመጡ ባለሙያዎች በሚሰጡት እርዳታ ነው ። ህፃናት ለቀዶ ጥገናው በብዛት የሚላኩትም ህንድ ነበር።ይህም የሆነው ቀለል ያለው የቀዶ ሕክምና ዋጋ ህንድ ስለሆነ ነው። ከኮቪድ በፊት ከ200 ሺህ እስከ 250 ሺህ ብር ይወስድ እንደነበር ይገልፃሉ። የሕክምናው ዋጋ ከኮቪድ በኋላና በጦርነቱ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ይጠቅሳሉ። በዚያን ጊዜ ወላጆች 8ሺህ ዶላር ይጠየቁ እንደነበርም ያስታውሳሉ። የልብ ቀዶ ሕክምና ውድ በመሆኑ ምክንያት ብዙዎች ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሳከም ውጪ አገር ዘመድ ያላቸው መሆን አለባቸው። አለበለዚያ ቤትና መኪና ሸጠው ነው የሚያሳክሙት። አሁን ላይ እሳቸውና ሌሎች ባልደረቦቻቸው ከተመረቁና እሳቸው ያስተማሯቸው የሕፃናት የልብ ሀኪሞች በመመረቅ ላይ በመሆናቸው ችግሩ መቀረፍ ጀምሯል። ዛሬ ላይ እሳቸው ያፈሯቸው ሐኪሞች በቅዱስ ጳውሎስ፡ በየካቲት 12ና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች እንዲሁም በተለያየ ሕክምና ተቋማት ይሰራሉ።ሆኖም አሥር ዋና ዋና የጨቅላ ህፃናት የጤና ችግሮች ከመኖራቸው አንፃር ብዙ ተደራሽነት ይቀራል።በተለይ ከ10ሩ አንዱ የሆነው ኢንፌክሽንን በእኛ አገር ደረጃ በጣም ትልቅ የጨቅላ ህፃናት የጤና ችግር ቢሆንም ልንከላከለው እንችላለን። ነገር ግን የአንድ አገር ኢኮኖሚን፣ እውቀትና ስልጠና እንዲሁም የተለያዩ አስፈላጊ ግብዓቶች ይጠይቃል። ከፍተኛ የሰው ኃይልም ይፈልጋል።ለምሳሌ በሰለጠነው ዓለም ሲሰራበት እንደሚታየው አንድ ነርስ ለአንድ ጨቅላ ሕፃን ነው የምትመደበው።ነርሷ ይሄን አንድ ጨቅላ ህፃን ብቻ ስትንከባከብ ነው የምትውለው። ይሄን የምትንከባከበውን ጨቅላ ህፃንም በምንም ታምር ሌላ ሰው መጥቶ አይነካውም።በመሆኑም ህፃኑ ከኢንፌክሽን በጣም የተጠበቀ ነው። እያንዳንዱ ጨቅላ ህፃን የተከለለበት ቦታም አለ።እዛ ቦታ ላይ ማንም ዝም ብሎ አይገባም። ሲገቡም ደግሞ ሙሉ በሙሉ ኢንፌክሽን የሚከላከል ልብስ ለብሰው ነው። እናም በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ እንክብካቤና ጥንቃቄ በሚደረግላቸው ህፃናት ላይ ኢንፌክሽን ለመድረስ በጣም አይችልም።ሆኖም ይሄ ሁሉ ኢኮኖሚ፣የተለያዩ ግብዓቶች፣የሰው ኃይል በመጠየቁ እዚህ በኛ አገር ደረጃ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያወጣው ስታንዳርድ አንድ ነርስ ለአምስት ጨቅላ ህፃናት ነው።ነገር ግን በአንድ ወቅት እንደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ይሄን የሰው ኃይል ማሟላት ስላልተቻለና ከኢኮኖሚ አንፃር እንደ ሀገር የአቅም ውሱንነት ስለነበረ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንድ ነርስ ከስምንት እስከ ዘጠኝ የሚደርሱ ህፃናትን ይዛ ስትንከባከብ ይታያል ። ይሄ ማለት ደግሞ ነርሷ ጨቅላ ህፃን ኤን ነክታ ወደ ጨቅላ ህፃን ቢ ስትሄድ የጨቅላ ህፃን ኤን ኢንፌክሽን ወደ ቢ እና ሌላው ልታስተላልፍ ትችላለች።
ከዚህ ዓይነቱ የሥራ መደራረብ አንፃር ‹‹እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎቹም የስራ ባልደረቦቼ በርካታ ኃላፊነቶችን ተሸክመን ነው እየሰራን ያለነው››ሲሉም ጫናውን ይገልፁታል። ቀን ቀን በዚህ ሁኔታ ሌክቸር ላዘጋጅ ቢሉ አይታሰብም።ለተማሪዎቻቸው ሌክቸሮችንና ፈተናዎች የሚያዘጋጁት፣የተለያዩ ጽሑፎች የሚጽፉትና ጥናትና ምርምሮችን የሚያካሂዱት ከልጆቻቸውና ከባለቤታቸው ጊዜ ቆርሰው ሌሊት በቤት ውስጥ ነው። በርካታ ጥናቶችንም በዚህ ሁኔታ ነው ያሳተሙት። ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር እራት አብረው ይበላሉ። ቅዳሜና እሁድ ትንሽ ጊዜ ከልጆቻቸው ጋር አብረው ያሳልፋሉ።በተለይ እሁድ አብረው ቤተክርስቲያን ይሄዳሉ።ከዚህ ውጪ አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉት በሥራቸው ላይ ነው።
‹‹ቀን ላይ በሥራ ሰዓት እነዚህ ሥራዎችን ልሥራ ብል አልችልም››ሲሉም ከአራት ሰዓት በላይ እንደማይተኙ ያስረዳሉ።ሌሎች ሐኪሞችም ውጤታማ የሆኑት ከዚህ በላይ ተኝተው ነው የሚል ዕምነት እንደሌላቸውም ይናገራሉ።በዚህ ሥራ ጫና ውስጥ ሆነውም ቢሆን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ስለሚወጡና ጥሩ የተካበተ ልምድ ስላላቸው በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ በአስተዳደር ውስጥ ያስገቧቸዋል።ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ይገኛሉ።አብዛኞቹ ያከሟቸው ህፃናት ወላጆች በሰርግ፣በለቅሶ፣በመንገድ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያገኝዋቸው የልጄ አባት ይሏቸዋል። ታካሚ ህፃናቶች በፊናቸው ትልቅ ሰው ሆነውና ሥራ ይዘው እሳቸው እንዳከሟቸውና ለቁም ነገር እንደደረሱ ሲነግሯቸው ደስ ይላቸዋል። እንግዳችን ከነዚሁ ከህፃናትና ወላጆቻቸው ጋርም የነበራቸውን የሕክምና ገጠመኝ አጫውተውናል።
በዚህ አገልግሎታቸው ውስጥ በርካታ የሚያስገርሙ ገጠመኞች አሏቸው። ወጣት ሐኪም ሆነው በፓዊ ሆስፒታል(ቤንሻንጉል ክልል) ሲያገለግሉ አንድ የሶስት ሳምንት ህፃን ከፓዊ 250 ኪሎ ሜትር ከሚርቅ ቦታ ወደሳቸው ይላካል። ችግሩ ዲሃይድሬሽን (የሰውንት ድርቀት) ነበር። ከተወለደ ጀምሮ ያስመልሰዋል። እዛም ያሉት ሐኪሞች በኦ አር ኤስ ፤በኤይ ቪ ጉልኮዝ አከሙት። ግን ሊያድኑት አልቻሉም።ሬዚስታንት ዲሃይድሬሽን ብለው ላኩት። ልብሱን አስወልቀው ሲመረምሩት ሆዱ ላይ ከግራ የሆዱ ክፍል ወደ ቀኙ የሚሄድ እብጠት ይመለከታሉም። ይሄ ሕፃን በሽታው አንጀቱ ድፍን የመሆን ጉዳይ መሆኑን ግልጽ አደረገላቸው። አንጀቱ የሚበላና የሚጠጣውን አያሳልፍም። እናቱን አጥቢው ብለዋት ስታጠባውና ሲያስመልሰው እብጠቱ ይጠፋል። ሕክምናው ቀዶ ጥገና ብቻ ነበር።
በወቅቱ በሆስፒታሉ ቀዶ ጥገና የሚያደርገው ጣሊያናዊ ሀኪም ነበር።ሆኖም በዛ ሰዓት ሀኪሙ ለዕረፍት ወደ ሀገሩ ሔዶ ነበር። በወቅቱ ሰመመን የሚሰጠውም ሰው አልነበረም። ስለዚህ ወላጆቹ ህፃኑን ጎንደር ወይም አዲስ አበባ ይዘውት እንዲሄዱ ተነገራቸው። ገንዘብ ስለሌለን 10 ኪሎ ሜትርም መሄድ አንችልም አሉ።የተማሩ አይደሉም።ጎስቋሎች ነበሩ።እና በጣም ተስፋ ስለቆረጡ ስቅስቅ ብለው በማልቀስ ሆስፒታሉን ለቅሶ ቤት አስመሰሉት። በስተመጨረሻ ወስደነው እቤት ይሙት ብለው ሲነሱ ግራ ገባቸው። ከዛ በፊት እንደዚያ ዓይነት ሰርጀሪ ሰርተው ባያውቁም መጽሐፍ አንብበውና ዶክተር ደሴ ከሚባልና ባልደረባቸው የሰመመን ህክምና ዝንባሌ የነበረው አንድ ጓደኛቸው ሰመመን እንዲሰጥላቸው አድርገው ለሦስት ሳምንቱ ህፃን ቀዶ ጥገና ሰሩለት። ህጻኑ አንጀቱ ተከፍቶ ምግብ ማስተላለፍ ጀመረ ። እናቱ በሦስት ሳምንቱ ልጇን ስታይው አላመነችም።ወፍሮ ልዩ ሆኖ ወላጆቹ ይዘውት ወደ ሀገራቸው ሄዱ። የሚያስገርመው የዚህ ልጅ ወላጅ አባት ከአራት ወር በኋላ ፓዊ ሆስፒታል ውስጥ ዶክተር ታምራት የሚባል ሐኪም አለ። ልጅህን እሱ ነው የሚያድንልህ ብሎ ዲዳና ደንቆሮ ልጅ ላከላቸው። ከሩቅ ቦታ ገንዘብ አውጥቶ ነው ይዞ የመጣው። ይሄን ሰው መርዳት ባለመቻላቸው ደግሞ ህፃኑን ሲያድኑ የተደሰቱትን ያህል እጅግ ያዘኑበት ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር።
‹‹ሰርግ ቤት ዶክተር ታምራት እርሶ ኖት? አለኝ አንድ ወጣት።እናም እናቴ ሁልጊዜ ትሞት ነበር ከሞት ያዳኑህ ዶክተር ታምራት ናቸው እያለች ትነግረኝ ነበር።አሁን እሳቸው ናቸው ብላ እሷ ስታሳየኝ ነው ልተዋወቆት የመጣሁት አለኝ። እናቱ መጥታ ጥቁር አንበሳ እኮ ልጄን ያዳኑልኝ እርሶ ኖት። እሳቸው ባይደርሱልህ ኖሮ ትሞት ነበር እያልኩ ሁሌ እነግረዋለሁ አለችኝ››ሲሉ ትዝታቸውን ያወሳሉ።
አርባ ምንጭ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ተደወለላቸው።ደግነቱ እዛው ግቢ ውስጥ ነበር የሚኖሩትና ሮጠው ሲሄዱ ልጁ ፓራላይዝድ ሆኗል፡ ኮማ ውስጥ ነበር።በርካታ ሐኪሞች አይተውት ነበር ወደ እሳቸው የተላከው። ሊሞት እያጣጣረም ነበር። አምላኬ ሆይ ይሄንን ህጻን እርዳው ብለው ሲመረምሩት በቲቢ ቫክቴሪያ ምክንያት የሚመጣ ማጅራት ገትር በሽታ እንደሆነ ተገለጠላቸው ። ወዲያው የቲቪ መድሃኒት አስጀመሩት። ፓራላይዝ ያደረገው ለቀቀው፡ ከኮማም ነቃ።ይሄ ልጅ መዳኑን ያየ አንድ አስታማሚ ታድያ ከሐኪሞች ጋር ተሰብስበው ራወንድ ሲያደርጉ እየሮጠ መጥቶ እባክህ ና እና ለእኔም ልጅ ጸልይ ያለው አይረሳቸውም።
‹‹በህፃናት ሕክምና እግዚአብሄር ባርኮኛል››የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ታምራት ሞገስ፤ የሕክምና ሙያ ገጠመኝ ብዙ ነው። በኤች አይቪ ዘመን ወረርሽኝ በአገራችን በተከሰተ ጊዜ ሁሉ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ብዙ ታሪክ የማይረሳው ሥራ ሰርተዋል።የሕክምና አገልግሎቱን ክፍል የሚመሩት እሳቸው ነበሩ። ያኔ እሳቸው የሚሰሩት ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሲሆኑ የኤች አይቪ ታማሚዎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚታከሙበት ዋና ቦታ ነበር። በርካታ ህፃናት ኤች አይቪ ታመው ሰውነታቸው እንደ ቅርፊት እየተቀረፈ ተቅማጥ፤ መግልና ብዙ ፈሳሾች እየወጧቸው በሚያሳዝን ሁኔታ በየኮሪደሩ ይሰቃዩ ነበር። ይሄኔ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ይሰራ የነበረ ዶክተር አቡበከር በድሪ የሚባል አንድ አስተማሪያቸው የኤች አይ ቪ መድሀኒት ኪኒን እየሰበረ ለኤች አይቪ ታማሚዎች ህጻናት ሲሰጥ ማየታቸው ትዝ አላቸው።ለመጀመሪያ ጊዜ ይሄን ልምድ መሰረት አድርገው ዘውዲቱ ሆስፒታል ላሉ ህፃናት የአዋቂ ኪኒን እየሰበሩ መስጠት ጀመሩ። በጣም ይሻላቸው ነበር። ብዙዎች እንዴት ያልተመጠነ የአዋቂ መድሃኒት ለሕፃናት ታዛለህ በሚል የሚቃወሟቸውም ነበሩ። እንደዛ ዓይነት ልምምድ ሲያደርጉ ከዛሬ ነገ ተከሰስኩ የሚል ፍርሃትም ነበራቸው። ግን በጣም ብዙ ህፃናት የህፃናት መድሃኒት እስኪመጣ ከሞት እንዲተርፉ አስችለውበታል።በዚህ ሁኔታ ወደ ህፃናት መድሃኒት ያዛወሯቸው ልጆች በርካታ እንደነበሩም ያነሳሉ።ይሄን መሰረት አድርገውም 214 በኤች አይቪ የታመሙ ህፃናት ላይ የሰሩት ሪሰርች በውጭ አገር ጆርናል ታትሟል።እንግዳችን ተባባሪ ፕሮፌሰር ታምራት ሞገስ በኮቪድም ዘመን እጃቸውን አጣጥፈው ቁጭ አላሉም። በዚህ ዘመን የሥራ ባልደረቦቻቸውን በማስተባበር ፕሮጀክት ቀርፀው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፈቀደላቸው በጀት ተላላፊ የኮቪድ በሽታ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሕክምና አሰጣጥ ላይ ያስከተለው ተጽዕኖ ምንድነው? የሚልም ትልቅ ጥናት አካሂደዋል።
በተለይ በስኳር፣ ካንሰርና የደም ብዛት በሽታ ሕክምና አሰጣጥ ላይ ያስከተለው ችግር ምንድነው የሚለውን ጥናት ያካሄዱት 600 የሚሆኑ ተላላፊ ያልሆነ በሽታ ያላቸውን ቤተሰቦች በስልክ በማነጋገር ነበር። ጥናቶቹ ሁለት ሲሆኑ፤ አንዱን በውጪ አገር ሌላውን ደግሞ በሀገር ውስጥ ጆርናል አሳትመውታል።እንግዳችን ተባባሪ ፕሮፌሰር ታምራት ሞገስ አሁን ላይ ሰባቲካል እረፍት ላይ ሲሆኑ እኛም ያገኘናቸው በእረፍት ሰዓታቸው ለትርፍ ባልተቋቋመው ለደግ የእናቶችና የሕፃናት ኮሌጅ ውስጥ ሙያዊ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ነው። አሁን ላይ ግማሽ ቀኑን እዚህ ኮሌጅ ግማሹን ቀን ደግሞ ሌሎች የምርምር ሥራዎች እየሰሩ ይገኛሉ። በቅርቡም ወደ ዋናው የማስተማር ሥራቸው ይመለሳሉ። መልካም የሥራ ዘመን!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም