ኢትዮጵያ የቡና ዕትብቱ የተቀበረባት ሀገር ናት ።የቡና ሥርና ምድር (መሠረት) እንዲሁም ባህል መገኛ ።በአፋን ኦሮሞ ቡነ ይባላል ።የደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ቡና የታወቀ ተክል የእንጨት ስም፤ ፍሬው ተቆልቶና ተወቅጦ ፈልቶ የሚጠጣ ።አንዳንድ ሰዎች ቡኖ በሚባል ቦታ ስለተገኘ (ኢሉ አባቦራ) ቡና /ቡነ ይሉታል፤ ፈረንጆቹ ግን በከፋ ስላገኙት ካፌ (ከፋዊ) ይሉታል ሲል ይፈታዋል ።በኢትዮጵያ ሀገረኛ የሆነው ቡና ንቁ ሆኖ ለመዋል እና ጊዜ ለማሳለፍ የሚጠጣ ብቻ አይደለም።ሥራን በንቃት፣ በትጋት ለመሥራት ፤ በእረፍት ዕለታት ለመዝናናት፣ ለማውጋት በማኅበራዊ ውይይት ችግርን ለመፍታት ይጠቀሙበታል ።
በኢትዮጵያ ቡና ላይ የተለያየ ጥናት ያካዱት መልካሙ ዓለማየሁ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ Ethiopian Highlands: home for Arabica coffee (September 2015) ባወጡት ጥናት በኢትዮጵያ የተረጋጋ የቡና ግብርና የተጀመረው ከ2ሺህ ዓመታት በፊት ነው ።ቡና ከባህር ወለል በላይ 550-2750 ከፍታ የሚበቅል ሲሆን፤የአረቢካ ቡና ግን ከ1500-2500mm ባለው ከፍታ ይበቅላል ።ኢትዮጵያ ከብራዚል ፣ቪየትናም፣ ኮሎምቢያና ኢንዶኔዥያ ቀጥሎ በቡና ምርት አምስተኛ ደረጃ ላይ ስትሆን በአፍሪካ ደግሞ ፊታውራሪ ነች ።
በሀገሪቱ አራት የቡና ምርት ዓይነቶች አሉ ።የጫካ፣ ከፊል የጫካ፣የጓሮ እና የእርሻ ቡና ናቸው ።የጫካ ቡና፤በደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በተለይ ባሌ፣ ምእራብ ወለጋ፣ ቤንች ማጂ፣ ከፊቾ ሸኪቾ፣ መቱና ጅማ ይገኛል ። የጫካ ቡና የአረቢካ ቡና ማዕከል ሲሆን፤ ከሀገሪቱ የቡና ምርት 10 በመቶ ይሆናል ።ከፊል የጫካ እና የጓሮ ቡና እያንዳንዳቸው የሀገሪቱን የቡና ምርት 35 በመቶ ይደርሳሉ ።የእርሻ ቡና ደግሞ በመንግሥት እና በባለሀብቶች የተያዙ ናቸው ።የመንግሥት 5 በመቶ ፣ጥቃቅን እርሻዎች 15 በመቶ ይደርሳሉ ።በነዚህ ከሚመረቱት 95 በመቶው ኦርጋኒክ ናቸው ።
በንግዱ የሚታወቁት ዋና የቡና ዝርያዎች አረቢካና ሮቡስታ ናቸው ።ሊበሪካ እና ኤክሴላ ቡና ተብለው የሚታወቁ ንዑስ ዝርያዎችም አሉ ።በቃናቸውና መዓዛቸው የሚወደዱ በሽታን ለመቋቋም ለመድኃኒትነት የሚጠቀሙበት የሚችሉ ከፍተኛ ጄኔቲክ የሆኑ፤ ከፍተኛ ምርትና ጥራት ያላቸው ቡናዎች አሉ ሲሉ መልካሙ ዓለማየሁ በጥናታቸው ጠቁመዋል ።
ቡና በዓለም በጣም ተፈላጊ የእርሻ ምርት ነው። በዓመት እስከ 14 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል ።ኢትዮጵያን ጨምሮ 121 ሀገሮች ቡና ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ ወይም ገዝተው ዳግም ይሸጣሉ፤ከ165 በላይ ሀገሮች ምርቱን የሚገዙ ናቸው ።በማደግ ላይ ካሉ ሀገሮች 50ዎቹ በቡና ንግድ ላይ ያሉ ሲሆን፤ ከአፍሪካ 25 ሀገሮች በቡና ውጭ ንግድ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ይመራሉ ።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ሕይወት ቡና ላይ የተንጠለጠለ ነው ።በዓመት በአማካይ ከ200ሺህ እስከ ሩብ ሚሊዮን ቶን የሚደርስ ምርት ሲመረት፤ከዚህ ውስጥ ግማሹ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ይውላል። ቡና መጠጣት ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ሕይወትን መጋራት ነው ።ቡና ከሌላው ጋር መጠጣት ማለት ሰላም ናችሁ ማለት ነው፤ ሲሉ መልካሙ ዓለማየሁ ባወጡት ጥናት ጠቁመዋል።
መሰንበት ገረመው ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ባወጡት ጥናትም በኦሮሚያ ቡና ለቃና ብቻ ሳይሆን ለጤናም ተብሎ ይፈላ ነበር ።በብዛት ለራስ ምታት ሕመም ማገገሚያና ማከሚያ ይጠቀሙበታል ።በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል፤ ለሚያስቀምጣቸው ሰዎች እንዲሻላቸው ቡና በማር ተደርጎ ይሰጣቸዋል ።የቡና ሥነሥርዓቱ ልዩ ሚናው ለኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አብሮነትን በመፍጠር ማሳደጉ ነው ።በቡና ሥርዓት መሳተፍ የበጎ ዕድል ተምሳሌት፤ ሥርዓቱ የሃይማኖትና የብሔር ድንበር ሳይገድበው የማኅበረሰብ አብሮነትን ለመፍጠር ይረዳል ሲል ጥናታዊ ጽሑፉ ያስረዳል ።
መታሰቢያ ዮሴፍ ከአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ ለሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ (A CULTURE OF COFFEE: TRANSMEDIATING THE ETHIOPIAN COFFEE CEREMONY April 26th, 2013) በሚል ርዕስ ባካሄዱት ጥናትም ፤ የቡና ሥርዓቱ የማኅበረሰብ አብሮነትን በመፍጠር ያለውን ሚና ጠቅሰዋል።‹‹ …የማኅበራዊ ሕይወት ማዕከላቸው ነው፤…እየታየ ያለው የጎጠኝነት ውጥረቱ እንዳለ ሆኖ፤ የጋራ የሆነው ባህላዊ የጀበና ቡና ሥርዓታቸው ብሔራዊ መለያቸው ነው።በማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤት የምታገኙት ። በገጠራማ ጎጆ፣ በከተሞች ዘመናዊ ቤቶች።የቋንቋ፣ የእምነት፣ የአለባበስ ልዩነት ካልሆነ፤ በሁሉም ብሔር የምታገኙት ሥርዓት ነው።›› ይላሉ። ፓንክረስት ደግሞ በተለይ በኢትዮጵያ ባህል ውስጥ ከዓለም አቀፍ ውስብስብ ታሪካዊ ንግድ ጋር የተቆራኘ ፖለቲካዊና ሰብዓዊ መስተጋብር ያለው ነው ይሉታል ።
ዶን ሴማን አሜሪካን ኢትኖሎጂስት Coffee and moral order 2015 በሚል ባወጡት ጥናት ባህላዊው የቡና አፈላል ሥርዓቱ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ነው፤ በእሥራኤል ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አይሁዶችም (ፈላሻ) ቡና ከማነቃቂያ፣ ባህላዊ መለያና እንዲሁም ከማኅበራዊ መዋቢያ (social lubricant) በላይ ነው። ግጭቶችን የሚፈቱበት፣ ሥርዓትን የሚያሲዙበት ሞራል የሚገነቡበት መድረክ ነው ሲሉ ያስረዳሉ ።
ዲያስፖራውም አንዳች የሚሰበሰብበት ሁኔታ ካለና አመቺ ቦታ ካገኘ፤ ቡና በጀበና አፍልቶ፣ ጠጥቶ፣ ተጨዋውቶ ይሰነባበታል ።በዓረብ ሀገር ፣ በምዕራባውያን ያሉ ኢትዮጵያውያን ይህ የተለመደ ነው ።በለንደን ኢትዮጵያውያን ቡና አፍልተው ጭሳጭሱን እያጨሱ ሲጠጡ ሲጨዋወቱ ፖሊስ ጭሱን አይቶ በፍጥነት በአምቡላንስ መጣ፤ የሚቃጠል ነገር ያለ መስሏቸው ነው ።የኢትዮጵያ ባህል መሆኑን ተረድተው ተረጋግተው መመለሳቸውን ከቡናና ሻይ ልማት ባለሥልጣን ያገኘሁት መረጃ ያስረዳል ።እርግጠኛ ነኝ ቡና ጠጡና ሂዱ መባላቸውና ፖሊሶቹም መጠጣታቸው የማይቀር ነው፤ በሰው ሀገር ቢሆንም የቡና ሥርዓቱ ሀገርኛ ባህላቸው ነዋ።
ኢትዮጵያን የሠራት የቡና ሥርዓታችን ነው የሚለው ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፤ ባንድ ወቅት ስለዚሁ ሲናገር ቡና የአንድነታችን ምስጢር የአብሮነታችን መሠረት ነው።ቡና ለሀገራችን ከሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በላይ ኢትዮጵያን በኅብረት በመተሳሰብ ላይ አርጎ የገነባበት አስተዋፅኦ ይበልጣል ።ስለዚህ ዛሬ የምናወራለት ማኅበራዊ ሕይወታችን አብሮነታችን መደጋገፋችን ማገር ሆኖ ያቆየው ያጠናከረው አሁን የያዘውን ቅርፅ የሰጠው ቡና እና የቡና አጠጣጥ ሥርዓታችን ነው ብሎ ነበር ።
ቡና የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት ነው። ሀገርኛ ተወዳጅ ባህላዊ ሥርዓት። በዓልም ሲሆን አክብረው በልተው ጠጥተው ሲያበቁ፤ በቤቱ ቡና ካላፈሉ በዓሉ በዓል የማይመስላቸው ብዙዎች ናቸው ። ጎረቤት እንኳን አደረሰህ/ሽ ተባብሎ በዓሉን የሚያደምቀው ቡና በጋራ በመጠጣት ባህሉ ነው ።የቡና ሥርዓት ሐረር ብትሔዱ ጎንደር፣ ባሌ ብትሔዱ ቦሌ፣ ላሊበላ ብትሔዱ ጋምቤላ፣አሳይታ ብትሔዱ ወላይታ ፣ሰላሌ ብትሔዱ ሶማሌ፣ ሆሳዕና ብትሔዱ ቦረና ፤ ሲዳማ ብትሉ አዳማ፣አስመራም በሉት ሰመራ አይታጣም ።የቡና ሥርዓቱ የሚከናወንበት መንገድ በኢትዮጵያ በብዛት ተመሳሳይ ነው ።
እንግዳ ሲመጣ ማስተናገጃው ማጫወቻው ቡና ነው። የትም ብትሄዱ ፤ ‹ግቡና ቡና ጠጡ ›ነው የምትባሉት። ቡና እንግዶች የሚስተናገዱበት ትልቁ ግብዣ ነው። ሰዎችም በገጠር አካባቢ ሲያልፉ የሚተዋወቁ ከሆነ ሰላም ይባባላሉ፤ሰላም የተባለው ‹‹ ጎራ በሉና ቡና ጠጡና ትሄዳላችሁ ›› የሚል ግብዣ ይቀርብለታል ። በአፋን ኦሮሞም ጎርተኒ ቡነ ዱጋቲ ዴማካ? (ማል ኢንጎርተኒ? ቡነ ዱግተኒ ኢንደምተኒ? ) ፍቺው ምነው ጎራ አትሉም? ቡና ጠጥታችሁ አትሄዱም እንዴ? ማለት ነው ።መንገደኛም በራፍ ላይ አረፍ ብሎ ቡና ጠጥቶ ይሄዳል ። ሁሉም በፍትሐዊነት በዴሞክራሲያዊነት የሚስተናገድበት ሀገርኛ ሥርዓት ።
ቡና ሲፈላ አቦል ፣ቶና (ሁለተኛ )፤ ሦስተኛ (በረካ) በየቤቱ የተለመደ ነው ።ጎረቤት ተሰብስቦ ማኅበራዊ ጉዳዩን ይወያይበታል ።ቤት ማሞቂያና ማድመቂያም ነው ።ሴቶች የቤት ሥራን የሚለማመዱት ቡና በማፍላት ነው ።በኢትዮጵያውያን ቢያንስ በቀን አንዴ እንኳ ቡና የማፍላት ልማድ አለ ።ሥርዓቱ ጊዜ ቢወስድም ፤ ሥነ ጥበባዊ ፣ ባህላዊ ነው ።የባህል መስተጋብር የሚፈጥር የብሔር፣ የጎሳ፣ የእምነት ድንበር የሌለበት ።
የቡና ዛፍ ተተክሎ ፍሬው ሲደርስ እሸቱ ተለቅሞ ከነገለፈቱ ተቆልቶ፤ በአንዳንድ ቦታዎችም የደረሰው ቡና ደርቆ ከነገለፈቱ ተቆልቶ ይጠጣል ።ቡና እጥረት ባለበት ቦታ ከገብስ ጋር ቀላቅለው ፤ቆልተው፤ ወቅጠው፤ አፍልተው መጠጣት የተለመደ ነው ።ቡና በቅቤ አፍልተው የሚጠጡም አሉ ።በተለይ በገጠር፤ ይህ ግን በዓል ሲሆን አልያም ግብዣ ሲኖር የሚደረግ ነው ።የቅቤ አጠቃቀም ሥርዓቱ ከቦታ ቦታ ይለያያል።አንዳንዶች ቅቤውን ሲኒ ላይ አድርገው ለታዳሚው ሲቀዱ ይታያል።የተነጠረውን ቅቤ እየፈላ ባለው ቡና ላይ በጀበና ጨምረው የሚጠቀሙም አሉ ።ይህ ግን ለወደዱት ቡናውን በቅቤ ሞላ ጎላ አድርገው ሲሰጡት፤ ላልፈለጉት ደግሞ በጀበና አጠቃቀም ዘያቸው ለስሙ ቅቤ የተደረገበት እንዲመስል አድርገው ይቀዱለታል።
በዓል ሲሆን ደግሞ ቡና በተደጋጋሚ ማፍላት የተለመደ ነው ።በዚህም ጎረቤት ተጠራርቶ ቡና በማፍላት እንግዶችን ማስተናገድ አለ ።ከቡናው ጋራ የቡና ቁርስ እንዳቅሚቲ ይቀርባል ።ዳቦ፣ ቂጣ፣ አምባሻ፣ ፈንዲሻ፣ ህብስት፣ አነባበሮ፤አልያም ቆሎ ወይም ንፍሮ ይዘጋጃል ።ካልሆነም እንጀራ ተቆርሶ በሚጥሚጣ ተደርጎ ለእድምተኛው ይቀርባል ።በዚህም የወግ የወጋቸውን ያወጋሉ ።በማወደስም ሆነ በመውቀስ ስለ አካባቢያቸው ሀገራቸው ጉዳዮች ያወራሉ ይጨዋወታሉ ።በኢትዮጵያ ቡናን በስኳር መጠጣት የከተሞች ልምድ ነው ።ወደ ገጠር ብትሔዱ ቡና ባዶው አልያም በጨው ይጠጣሉ፤እንጂ በስኳር የመጠጣት ፍላጎት እምብዛም የላቸውም ።ቡና በጨው፣በቅቤ እንዲሁም ከነገለፈቱ መጠጣታችን በሌላ ሀገር የለሌ ሀገርኛ ልምድ ነው ።
የጀበና ቡናችን አደባባይ እየወጣ ሴቶች ቡና እያፈሉ የሚውሉበት እየሆነ ነው ።አሁን አሁን በማሽን የተፈላ ቡና ሰው አታሰየኝ ያለ ይመስላል ።ሰው የማሽን ቡና የመጠጣት ስሜትም ሆነ ፍላጎቱ እየሳሳ ነው ።በዚህም ምግብ ቤቶች ሻይ ቤቶችና ቡና ቤቶች በረከቦታቸው ሲኒውን ደርድረው የጀበና ቡና ከሰል ላይ ጥደው የሚያፈሉበት ወቅት ላይ ደርሰናል ።ሰው የጀበና ቡና ዙሪያ ተኮልኩሎ ቡናውን ጠጥቶ ተጫውቶ ይሄዳል ።
እንደ እኛ ቡና አጠጣጥ ቢሆን ኖሮ፤ ያመረትነው ቡና እንኳን ወደ ውጭ ሀገር ልከን ልንሸጠው ለራሳችንም አይበቃንም ነበር ብዬ አስባለሁ ።አንድ ቡና አፍልተን እስከ ሦስተኛ ዙር የመጠጣት ባህላችን ቡናውን ቆጥበንም ለውጭ ምንዛሪ እንድናተርፍ የበጀን ይመስለኛል።መሰንበት ገረመው ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በጥናታቸው በኢትዮጵያ ቡና በጣም እንደሚጠጣ ሲጠቅሱ (…ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገሮች ኢትዮጵያ በጣም ቡና ተጠቃሚ ከሆኑት ቀዳሚዋ ሀገሮች አንዱዋ ናት ።ከሚመረተው ቡና ግማሽ የሚጠጋው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ነው ።…) ይላሉ ።እንደውም ከተቻለ ዙሩን እናክረውና እንጨምረው ።በሌሎች ሀገሮች እንዲህ ዓይነት ልማድ የለም ።ወደ ምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች ግን ሻይን እንደ ኢትዮጵያው ቡና አንድ ጊዜ ጥደው ሦስት ዙር አፍልተው የመጠጣት ልምድ እንዳላቸው አንብቤያለሁ።የሩቅ ምሥራቅ ሀገራት ሻይ አፈላል ሥርዓታቸው ልክ እንደ ኢትዮጵያ ይመስላል በተለይ የጃፓን ።
የኢትዮጵያ ሴቶች በትውፊታዊ (Tradition) ዘዬ ይህን የቡና ሥርዓት ከቤተሰቦቻቸው ተቀብለውታል።ቡና በዓለም ብዙዎች ሊጠጡት የሚሹት ብቻ ሳይሆን የሚጠጡት ነው ።የብዙዎችን ልብና ቀልብ የሚስብ በዓለም ገበያም ሁነኛ ሚና ያለው ሲሆን ሀገራችንም ትልቁ የውጭ ምንዛሪ ምንጭዋ ነው ።(የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ባለሥልጣን ሰሞኑን ያወጣው መረጃ ፤ ሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በቡና የውጭ ንግድ ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ገቢ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች፤ በጥራቱ አንደኛ ነጥብ ያመጣ አንዱ ኪሎ የኢትዮጵያ ቡና 884 ዶላር ተሸጧል) ።ይህም ቡና በባህልና በምጣኔ ሀብት በሀገራችን ያለውን ሚና ፤በዓለም በብዙዎች ሕይወት ውስጥ እንዴት ልዩ ቦታ እንዳለውም ጭምር ያሳያል ።
በርግጥም በሠርግ እንግዶች ተስተናግደው ተሰናብተው ሲያበቁ ፤ዘመድ አዝማድ ጎረቤቱ የደስታቸው ማሟሻ የሚያደርጉት ቡና ሲጠጡና ሲያወጉ ነው ። ኃዘንም ሲያጋጥምም ሰውን ቡና ማጠጣት በከተሞች ጭምር የተለመደ ባህል ነው ።ይህም የሚያሳየን በባህላችን ቡና ለደስታ መዝናኛ፣ ለችግርም ደግሞ መጽናኛ ሆኖ የሚያገለግለን ትልቅ ዕሴት መሆኑን ነው ። እናም ቡና በደስታም በኃዘንም ከየቤቱ የማይወጣ፣ የማይታጣ ሀገርኛ ሥርዓት ነው ።
ቡና ሲቆላ ምጣዱን፣ ሲፈላ ደግሞ ጀበናውን፣ሲቀዳ ረከቦቱንና ሲኒውን ስታዩት የሚሰጠው ስሜት አለ።ምንም ቡና ስሜት የለኝም ያለኝ አንድ ጎልማሳ ፤ ቡና ተፈልቶ ሲኒው ረከቦቱ ላይ ተደርድሮ ሳየው ቤቱ ሞቅ ደመቅ ያለ ይመስለኛል ደስ ይለኛል ብሎኛል ።በርግጥም የቡና ቁርሱ በቤቱ ውስጥና ረከቦቱ ዙሪያ የሚጎዘጎዘው ጉዝጓዝ (ቄጠማ፤ ሳር የመሳሰሉት) ቤቱን ጥሩ አድርገው እንዲያውዱ ጣል ጣል የሚደረጉት አሪቲና ጠጅ ሣር ፤ በር ላይ የሚጤሰው ዕጣንና ወይራ የቤቱን ግርማ ሞገስ የሚጨምሩ ጥሩ ጠረንና መዓዛ የሚፈጥሩ የቡናውን ታዳሚ ሐሴት የሚያጭሩ ናቸው ።ይህ የኢትዮጵያዊ ሁሉ ባህል ነው ።እንደቄጠማ የመሳሰሉ እርጥብ ነገሮች የሚጎዘጎዙት ለምለም ነገሮች ከመመኘት በመነጨ ነው ።
በአንዳንድ ቦታዎችም ቡናውን ከጠጡ በኋላ ከሲኒው ላይ የቀረውን አተላ አፍሰው የሕይወታቸውን ዕጣ ፈንታ በመገመት ይዝናኑበታል ።ቡና በሀገሪቱ ውስጥ የዕለት ተዕለት ኑሮ አካል እና ሕዝቦች በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ በአኗኗራቸው፣ በአቋማቸው ወይም በልማዳቸው ቢለያዩም ወደ አንድነት በማምጣት ተወዳጅነት ያለው ነው። ለሀገሪቱ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ቡናን በኢትዮጵያ ውስጥ ሁነኛ ሚና ያለው ያደርገዋል።
ቡና የአካባቢ ነጋዴዎችን መተዳደሪያ ከመደገፉ ባሻገር የኢትዮጵያ ሕዝብ የማኅበራዊ ትስስር ዋና አካል ነው። ከላይ እንደገለጽነው የቡና ሥርዓት በኢትዮጵያ ዘወትር የሚከወን ነው ።ሰው በምድጃው ዙሪያ ተሰባስቦ ቡናውን እየጠጣ ማኅበራዊ፣ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ይወያያል፤ ይቀላለዳል፣ ወግ ያወጋል፣ በሽሙጥም ይዋጋል፣ሥራው፣ጤናውን ሁሉ ያወራል፤ ችግሮችን ይፈታበታል ።የተጣሉን ያስታርቅበታል እንግዳን ይጋብዝበታል ፤ዜናዎችንና መረጃዎችን ይጋራል ።
አንዳንድ መረጃዎች የቡናው ሥነ-ሥርዓታችን ሙሉ የስሜት ህዋሳት ተሞክሮ የሚያካትት ነው ይላሉ ።ማየት፣ መስማት፣ መዳሰስ፣ መቅመስ፣ እና መስማት የሚባሉት አምስቱ የስሜት ሕዋሳት የሚታይበት መጠጥ ቡና ነው ።የሚባለው በሀገራችን ባህል ቡናው ተቆልቶ ሲጨስና እንዲሁም በሙቀጫ ሲወቀጥ በጀበና ሲፈላ ጠስ ጠስ ሲል ስንሰማው ሲቆላ ስናየውና ስንዳስሰው፣ የቡናው መዓዛ በሽታው ሲያውደን ፣ ተፈልቶ ቀምሰን እየጠጣን ቃናውን ስናጣጥመው ነው ።
ከላይ እንደገለፅነው ሀገርኛው የቡና ሥርዓት የሰርክ ክስተት ነው ።የምጣኔ ሀብቱን የአንበሳ ድርሻ የያዘ ነው ።በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል እንደሚባለው ግን ትኩረት የተሰጠው አይመስልም፤ የቡና ሥርዓታችን ለብቻው የቱሪስት መስህብ ነው።ቱሪዝም ኮሚሽን ፖስተር በሚያሳትምበት ጊዜ የወለጋዋ ውቢት ኢትዮጵያ ጥበብዋን ለብሳ ቡና በጀበና እያፈላች የሚያሳይ ፎቶ አስታውሳለሁ።በሀገር ውስጥም ለገበሬው ለነጋዴው ለወዛደሩ ለሹፌሩ የገቢ ምንጭ ነው ።እናም ‹ምሉዕ በኩልሄ› ግልጋሎት ለሚሰጠን ቡና ትኩረት እንስጠው፤ገበሬው ቡና በማምረት ላይ እንዲተጋ ይደረግ፤በገቢው እየተበረታታ የበለጠ እያመረተ ምንዛሪ ያምጣልን ።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/ 2015 ዓ.ም