የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2014 ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ በሱዳኑ አል ሂላል በደርሶ መልስ ውጤት ተሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ሳያልፍ መቅረቱን ተከትሎ ኢትዮጵያን በአፍሪካ መድረክ የሚወክለው የፋሲል ከነማ ብቻ ሆናል፡፡ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እየተሳተፉ የሚገኙት አፄዎቹ የመጀመሪያውን ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ አሸንፈው የሁለተኛውን ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታም ባለፈው እሁድ ባህርዳር ስታዲየም ላይ አድርገዋል፡፡
አፄዎቹ የቱኒዚያውን ክለብ ሴፋክሲያንን በሜዳቸው በገጠሙበት ያለፈው እሁድ ጨዋታ ካለ ምንም ግብ አቻ ቢለያዩም በመልሱ ጨዋታ ነገ ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያሳልፋቸውን ውጤት ለማስመዝገብ ከቀናት በፊት ወደ ቱኒዚያ አቅንተዋል፡፡ አፄዎቹ በሜዳቸው ያደረጉትን ጨዋታ ማሸነፍ ካለመቻላቸው በተጨማሪ ምንም ግብ አለማስቆጠራቸው ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ የሚያስችላቸውን እድል ያጠበበው ሲሆን በነገው ወሳኝ ፍልሚያም የማሸነፍ ወይም ግብ አስቆጥረው አቻ የመለያየት ግዴታ ውስጥ ገብተዋል፡፡ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽም ቡድናቸው በመጀመሪያው ጨዋታ የነበሩበትን ድክመቶች አስተካክሎ በነገው የመልስ ጨዋታ የሚፈለገውን ውጤት ይዘው ለመምጣት ጥረት እንደሚያደርጉ ከባህርዳሩ ጨዋታ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“በመልሱ ጨዋታ ያሉብንን ክፍተቶች አርመን የተሻለ ነገር ይዘን ለመምጣት እንጥራለን” ያሉት አሰልጣኙ የተጋጣሚያቸውን የጨዋታ ታክቲክ መሠረት ያደረገ ዝግጅት አድርገው ወደ ሜዳ ቢገቡም ቡድናቸው ያገኛቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብ መቀየር ባለመቻሉ ጨዋታው 0ለ0 እንደተጠናቀቀ ተናግረዋል፡፡
አፄዎቹ በሜዳቸው አሸንፈው የተሻለ ውጤት ይዘው ወደ መልሱ ጨዋታ ለመሄድ ጉጉት እንደነበራቸው ያስታወሱት አሰልጣኝ ኃይሉ፣ የነበራቸውን እድል ባለመጠቀማቸው በተጫዋቾች ስነልቦና ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሌለ ገልፀዋል፡፡
‹‹ብዙ ጊዜ ተጫዋቾች አሸንፈን እዚህ ጨርሰን እንሄዳለን የሚል ጉጉት ስለነበራቸው የማጥቃት ዕድሉ ላይ ትንሽ የመቻኮል ነገሮች ነበሩ፡፡ መጀመሪያም ጎል መሳት ያገኘነውን አጋጣሚ ያለመጠቀም ደግሞ ትንሽ እየወረድን እንድንመጣ አድርጎናል፡፡ እነዚህን ስህተቶች አርመን ለቀጣዩ ጨዋታ የተሻለ ነገር ይዘን እንቀርባለን ብለን እናስባለን›› ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የሴፋክሲያን አሰልጣኞች ቡድን አባል የሆነው የሱፍ ከሬይ ለሶከር ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጨዋታ በኋላ በሰጠው አስተያየትም፣ “ለቀጣዩ ጨዋታ ጥሩ ውጤት አግኝተናል፣ ጨዋታው ጥሩ ነበር ስፖርታዊ ጨዋነት የተሞላበት ጨዋታ የነበረ ሲሆን አቻ ወጥተናል። ለቀጣዩ ጨዋታ ጥሩ ውጤት አግኝተናል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ፉክክር የታየበት ፈታኝ ጨዋታ ነበር አቻም በቂ ውጤት ነው›› በማለት ተናግረዋል፡፡
አጼዎቹ ጠንካራ የቡድን ስብስብ እንዳላቸው የገለፁት የሱፍ ከሬይ በተለይ የባህርዳሩ ጨዋታ በሜዳቸውና በደጋፊው ፊት ፈታኝ እንደነበር በማስታወስ አፄዎቹ ላላቸው ብቃት ‹‹እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ›› ብለዋል፡፡
‹‹አስደናቂ ደጋፊዎች ናቸው። ሙሉ ደቂቃ ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ነበር ስታዲየሙ ውስጥ ጥሩ ነበሩ። ሜዳውም ተመችቶናል በጣም ደስ ይላል ለጨዋታ የሚመች ሜዳ ነው። ስታዲየሙ በጣም ደስ ይላል ጥሩ ብቃት ያየንበት ጨዋታም ነበር ፤ ያለው ነገር ደስ ይላል›› ሲሉም ለአፄዎቹ ደጋፊዎችና ለባህርዳር ስታድየም አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡ የሱፍ ከሬይ በባህርዳሩ ጨዋታ ውጤት ባይከፉም የነገው የመልስ ጨዋታ ቀላል እንደማይሆንም ተናግረዋል።
አጼዎቹ በእሁዱ ጨዋታ ወሳኝ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቻቸው ሱራፌል ዳኛቸው ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ በነገው የመልስ ጨዋታ እንደማይሰለፍና ከቡድኑም ጋር ወደ ቱኒዚያ አብሮ እንዳልተጓዘ ተረጋግጧል።
ሱራፌል በመጀመሪያው የእሁዱ ጨዋታ አስቀድሞ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት ለጨዋታው የመድረሱ ነገር ሲያጠራጥር ቢቆይም በ59ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በመግባት መጫወት ችሎ ነበር። ሜዳ ላይ መቆየት የቻለው ግን ሃያ ደቂቃ ብቻ ነበር። ቀኝ ታፋው ላይ ከባድ ያለ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ሊወጣ ችሏል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/ 2015 ዓ.ም