በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ክፉኛ ተፈትኖ የነበረው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቅመማ ቅመሞችና ዕጽዋትን አካትቶ የያዘው የሆርቲካልቸር ዘርፍ፣ ወረርሽኙ ካሳደረበት ተፅዕኖ በመላቀቅ ባለፈው ዓመት ከእቅድ የበለጠ አፈፃፀም ማስመዝገቡን የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ። በ2014 ዓ.ም ከሆርቲካልቸር ዘርፍ የወጪ ንግድ 589 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 628 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። ከዚህም ውስጥ ኢትዮጵያ ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ የምትገኝበት የአበባ ልማት ከ541 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማስገኘት ቀዳሚው ሆኗል።
የሆርቲካልቸር ዘርፍ የ2014 ዓ.ም ውጤታማ አፈፃፀም
በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ መሪ አቶ አብደላ ነጋሽ በበጀት ዓመቱ ለሆርቲካልቸር ዘርፍ ልማት የተሰጡ ትኩረቶች ለአፈፃፀሙ መሻሻል አስተዋፅዖ እንዳደረጉ ይገልፃሉ። እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ከግብርና ሚኒስቴር በተጨማሪ የመሬት፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የትራንስፖርት፣ የኢንቨስትመንት ጉዳዮች የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች በጋራ ውይይት በማድረግ የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት የተደረጉት ጥረቶች፤ ሰፋፊ መሬቶችን ይዘው ውስን በሆነ አቅም ሲያለሙ የነበሩ ኩባንያዎች ሥራቸውን ማስፋታቸው፤ ያረጁና ተፈላጊ ያልሆኑ ዝርያዎችን በማስወገድ የተሻሉ ዝርያዎችን ማልማት መቻሉ እንዲሁም ኩባንያዎች ለምርት ሥራቸው የሚስፈልጓቸውን ግብዓቶች በፍጥነት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ቀልጣፋ አሠራሮች መተግበራቸው ዘርፉ በበጀት ዓመቱ የተሻለ ምርትና ምርታማነት እንዲያስመዘግብ አስችለዋል።
መንግሥት በየደረጃው በሚገኙ ተቋማት ሪፎርም ማካሄዱን ያስታወሱት አቶ አብደላ፤ ሪፎርሙ ለዘርፉ ውጤታማነት አወንታዊ ድርሻ እንደነበረው ይናገራሉ። ‹‹ሪፎርም ከተካሄደባቸው ዘርፎች አንዱ የግብርናው ዘርፍ ነው። በዚህም በተበታተነ መልኩ ሲሰጡ የነበሩ የሆርቲካልቸር ዘርፍ አገልግሎቶችን ወደ አንድ ቦታ በማምጣት ዘርፉን በተሻለ አፈፃፀም ለመምራትና የተጠናከረ ድጋፍ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው። እነዚህ ጥረቶችም በዘርፉ ለተመዘገበው ስኬት አስተዋፅዖ ነበራቸው›› ይላሉ።
የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው፤ በ2014 ዓ.ም በሆርቲካልቸር ዘርፍ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደተቻለና በበጀት ዓመቱ የተገኘው የውጭ ምንዛሬም ባለፉት ዓመታት ከተገኘው ገቢ የተሻለ እንደሆነ ይናገራሉ። በዘርፉ የነበረው ግብይት መጨመር፣ የባለሀብቶች የሎጂስቲክስ አቅም መጠናከር እና የተሻሉ ቅንጅታዊ ሥራዎች ለአፈፃፀሙ መሻሻል አስተዋፅዖ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በዋነኞቹ የገበያ መዳረሻዎች ላይ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሮ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ የእንቅስቃሴ ገደቦች እየላሉ ሲመጡ በመንግሥት እና በኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማኅበር በተከናወኑ ቅንጅታዊ ተግባራት ዘርፉ የተሻለ አፈፃፀም ማሳየት መቻሉንና የወረርሽኙን ተፅዕኖ ተቋቁሞ ለአገር ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረከተ ዘርፍ እንደሆነም ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ
ለአንድ አገር ዘላቂ እድገት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎና ድርሻ የማይተካ ሚና አለው። የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ጥያቄ ሊነሳበት የማይገባ ጉዳይ እንደሆነና ተጨባጭ ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ የምጣኔ ሀብት ሳይንስ ጥናት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ባለሀብቶቹ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ከሚኖራቸው ሚና ባሻገር ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ገቢ ምርቶችን በመተካት እና የወጪ ንግድን በመጨመር ትልቅ አስተዋፅዖ ስለሚኖራቸው ይህን ሚናቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ በመንግሥት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ባለሙያዎቹ ደጋግመው የሚናገሩት ምክረ ሃሳብ ነው።
ኢትዮጵያውያን የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎና ድርሻ በየጊዜው እየተሻሻለ እንደመጣ ባይካድም በቂ የሚባል ግን አይደለም። የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ተሳትፎና ድርሻ እንዲሁም ተወዳዳሪነት ላቅ ያለ እንዳይሆን የሚጠቀሱት ምክንያቶች ዓይነተ ብዙ ናቸው።
በሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያለው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ቴዎድሮስ፤ ባለሀብቶቹ በዘርፉ ያላቸው ድርሻ በሚጠበቀው ልክ እንዳልሆነ ይገልፃሉ። ‹‹የባለሀብቶቹ ተሳትፎና ድርሻ ዝቅተኛ እንዲሆን ዋነኛ ምክንያቶቹ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የግንዛቤ እጥረትና የሎጂስቲክስ ችግሮች ናቸው። ለዘርፉ የሚያስፈልገውን የፋይናንስ አቅርቦት በሚፈለገው ልክ ማግኘት ከባድ ነው። ባለሀብቶች ስለዘርፉ ያላቸው ግንዛቤ በቂ አይደለም። በተለይ በአትክልትና በፍራፍሬ ዘርፍ የሚስተዋለው የሎጂስቲክስ ችግር በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎም ሆነ በሆርቲካልቸር ዘርፍ አጠቃላይ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ መሰናክሎች ናቸው›› ይላሉ።
አቶ አብደላም በዘርፉ ያሉት አብዛኞቹ ባለሀብቶች የውጭ ኢንቨስተሮች መሆናቸውን ጠቁመው፤ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎም እየተሻሻለ እንደመጣ ያስረዳሉ። ‹‹ባለሀብቶች ከዚህ ቀደም ሲያነሷቸው የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ባለድርሻ አካላትን ወደ አንድ መድረክ በማምጣት ስለችግሮቹ ምክክር ይደረጋል። ይህም ለዘርፉ ችግሮች መፈታትና ለአፈፃፀም መሻሻል ትልቅ ሚና እንዳለው ማረጋገጥ ተችሏል›› በማለት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ይጠቅሳሉ።
ከዚህ በተጨማሪም የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በዘርፉ ያላቸውን ድርሻ ለማሳደግ የሚያስችሉ የማበረታቻ ሥርዓቶች እንዳሉ አቶ አብደላ ይናገራሉ። እንደርሳቸው ገለፃ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ሥራው ሲሰማሩ ማቅረብ የሚገባቸውን ፋይናንስ እንዲያቀርቡ የሚደረጉት በአገር ውስጥ ገንዘብ (በብር) ነው። የብድር አቅርቦትም ሌላው ማበረታቻ ነው። ባለሀብቶቹ የተወሰነውን ገንዘብ ማቅረብ ከቻሉ መንግሥት ከፍተኛውን ገንዘብ በብድር ያቀርባል።
የሆርቲካልቸር ዘርፍ ተግዳሮቶች
እንደሌሎቹ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በሆርቲ ካልቸር ዘርፍም የሚጠቀሱ ችግሮች አሉ። እንደ አቶ ቴዎድሮስ ማብራሪያ፤ የመሬት፣ የኃይል፣ የፋይናንስና የግብዓት አቅርቦት እጥረቶች እንዲሁም የቅንጅታዊ አሠራር ጉድለት ከሆርቲካልቸር ዘርፍ ተግዳሮቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ብዙ ኩባንያዎች ሥራቸውን ማስፋፋት ቢፈልጉም መሬት ለባለሀብቶች በሚፈለገው ልክ እየቀረበ አይደለም። ለምርት ሥራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች አቅርቦትም በቂ አይደለም። የኃይል መቆራረጥ ችግር በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች በሙሉ አቅማቸው እንዳይሠሩ አድርጓቸዋል። ከትምህርትና የምርምር ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነትና ትብብርም ዘርፉ ካለው አቅም አንፃር ሲመዘን አነስተኛ ነው።
አቶ ቴዎድሮስ ችግሮቹን ለመፍታት ከፌዴራልና የክልል መንግሥታት ጋር ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንና እየተካሄዱ እንደሚገኙም ጠቁመው፤ በግብርና ሚኒስቴር የሚመራና የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን ያቀፈው ወርሃዊ የምክክር መድረክ አንዳንዶቹ ችግሮች እልባት እንዲያገኙ ማስቻሉን ተናግረው፤ ሌሎቹ ችግሮችም በቀጣይ መፍትሄ እንደሚያገኙ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
አቶ አብደላ ስለሆርቲካልቸር ዘርፍ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ እርምጃዎች ሲያስረዱ፣ ‹‹የመሬት አቅርቦት ችግር ከሆርቲካልቸር ዘርፍ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ነው። ክልሎች ለኢንቨስትመንት የተለዩ ቦታዎችን መርጠው ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። የመሬቱን ደህንነት አስተማማኝ ማድረግና ባለሀብቱ ያለምንም እንቅፋት የሚያለማበትን መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ ከይዞታ ማስከበር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ። ለአብነት ያህል ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ እርሻዎቹ አካባቢ ሲደርስ የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ። አንዳንድ ጊዜ መሬቶቹ በከተማ ይዞታ ስር ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው። ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት ሥራዎቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች ከውጭ እንዲያስገቡና ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው›› በማለት ያብራራሉ።
ቀጣይ እቅዶች
በ2015 የበጀት ዓመት ከሆርቲካልቸር ዘርፍ ወጪ ንግድ ከ770 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዷል። ይህ እቅድ እንዲሳካ የዘርፉ ችግሮች ተብለው የተለዩት ተግዳሮቶች መፍትሄ እንደሚያሻቸው ግልጽ ነው። በግብርናው ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ የቆየው ለሌሎች ሰብሎች ስለነበር የሆርቲካልቸር ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት ሳያገኝ ተዘንግቶ ቆይቷል›› የሚሉት አቶ አብደላ፤ በአሁኑ ወቅት የሆርቲካልቸር ልማት የራሱ የሆነ ስትራቴጂና ፍኖተ ካርታ እንዲኖረው እና የዘርፉ ልማት በፖሊሲ የተደገፈ እንዲሆን እየተሠራ እንደሆነ ይገልፃሉ። እንደርሳቸው ገለፃ፣ በሆርቲካልቸር ዘርፍ በሥራ ላይ ተሰማርተው ከሚገኙ ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ በአበባ ልማት ላይ የሚሠሩ ናቸው። የአሠራር ሥርዓቱን በማሻሻልና ለዘርፉ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ከፍተኛ አቅም ካለው ከአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍም ተጠቃሚ ለመሆን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹መንግሥት በሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ የሪፎርም ሥራዎችን እየሠራና የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። ባለሀብቶችም ዕድሉን ተጠቅመው አገሪቱ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ዕድል መፍጠር ይገባል። በዘርፉ ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አደረጃጀት ስላለ ይህን ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል። ክልሎች ለኢንቨስትመንት በቂ የሆነ መሬት ማዘጋጀትና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ በላቀ ሁኔታ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ የሚሠሩበትን አሠራር መፍጠርና ማጎልበት ይገባል። ክልሎች የኢንቨስትመንት መሬት ለይተው የሚያቀርቡበት የተሻለ ምቹ ሁኔታ ቢፈጠር በርካታ ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ ከላይ ለመሰማራት ፍላጎት አላቸው። ይህን ማድረግ ከተቻለ ዘርፉ ለአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘቱም ባሻገር በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል›› ብለዋል።
አቶ ቴዎድሮስ በበኩላቸው፤ ‹‹መንግሥት ለሆርቲካልቸር ልማት የሚፈለገውን ግብዓት ማቅረብ ከቻለ፣ በሥራ ላይ የሚገኙት ባለሀብቶች ሥራቸውን ማስፋፋት፣ አዳዲስ ባለሀብቶች ደግሞ በዘርፉ ለመሰማራት ይፈልጋሉ። የተሻለ የመሬት አቅርቦት እና የድጋፍ ሥርዓት ከተዘረጋ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ ይቻላል። ስለሆነም የዘርፉን ውጤታማነት የሚያሳድጉ ግብዓቶችን ማሟላትና አሠራሮችንም መዘርጋት ይገባል›› ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅም ያላት አገር ናት። አገሪቱ ከዘርፉ እምቅ አቅም ተጠቃሚ እንድትሆንና የዘርፉን እድገት ዘላቂ ለማድረግ በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍ ተሳትፏቸውን ማጎልበትና ድርሻቸውንም ማሳደግ እጅግ አስፈላጊ ነው። የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ አገር በራሷ አምራቾች ላይ እንድትተማመን ያስችላል። ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ ምክንያት በሚፈጠሩ ችግሮች ከሚከሰት አደጋ ለመዳንም ይረዳል። ስለሆነም የሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በሚደረጉ ሁሉም ጥረቶች ውስጥ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ሊዘነጋ አይገባም።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም