አ ዲስ አበባ፣ በወንጀል ተግባር ተሳታፊ ሆነው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ህፃናት አያያዝ እና የህግ አተገባበር ጉዳይ እንዳሳሰበው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ። ፍርድ ቤቱ በወንጀል ፖሊሲው ዙሪያ ህፃናቱ ከአዋቂዎች በተለየ በፍትህ ተቋማት የሚዳኙበት እና እርማት የሚያገኙበትን መንገድ በተመለከተ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ትናንት በቦሌ ፍሬንድ ሺፕ ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ እንዳሉት፤ በወንጀል ነክ ጉዳይ ተሳትፈው የተገኙ ህፃናት ተገቢውን የእርማትና የተሃድሶ አገልግሎት አግኝተው ወደ አምራች ዜጋነት ከመሸጋገር ይልቅ ወደ ከፋ ችግር ውስጥ እየገቡ ነው።
‹‹ዛሬ በወንጀል ተግባር የገቡ ህፃናት ተገቢውን ትኩረት እና እንክብካቤ ካልተደረገላቸው ነገ አገሪቷ የማትወጣው ችግር ውስጥ እንደምትዘፈቅ በማጤን የህፃናትን ሰብዓዊ መብት በተሻለ ለማክበር መረባረብ ይኖርብናል›› ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ የብሄራዊ ህፃናት ፖሊሲው በፍትህ ሥርዓትና በወንጀል ነክ ጉዳይ የሚያልፉ ህፃናት እንዲሁም በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙትን ጨምሮ በልዩ ትኩረት መያዝ እንደሚኖርበት ገልፀዋል።
ለበርካታ ዓመታት በህፃናት ጉዳይ ላይ የሠሩትና በእለቱ የፖሊሲ እና የህግ ጉዳዮችን በተመለከተ ለውይይት መነሻ ጥናት ያቀረቡት ዳኛ ልኡልሰገድ ሊበን በበኩላቸው ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በወንጀል ነክ የተሰማሩ ህፃናት የሚታረሙበት አንድ ማቆያ በብቸኝነት በአዲስ አበባ ውስጥ ይገኛል። በዚህ የተነሳ ህፃናት ወደ አዋቂ ማረሚያ ቤት የሚላኩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይሄ በብሄራዊ ህግ እና አገሪቷ በዓለም አቀፍ ህግ የፈረመቻቸውን ስምምነት የሚጥስ ነው።
‹‹በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት የፍትህ፣ የማህበራዊ፣ የትምህርት እና የጤና ዘርፎች ተቀናጅተው የህፃናት ታራሚዎችን አስመልክቶ ልዩ ትኩረት ሰጥተው አዳዲስ ህጎችን መቅረፅ እና ተቋማትን መገንባት አለባቸው›› የሚሉት ዳኛ ልኡልሰገድ፤ አሁን ያለው ሁኔታ በጊዜ መፍትሄ ሊፈለግለት የሚገባ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው አዲስ በተሻሻለው የወንጀል ህግ መሰረት በልዩ ፍርድ ቤት በጥንቃቄ ጉዳያቸው የሚታይላቸው እና ‹‹ህፃናት›› የሚባሉት ከ9 እስከ 15 የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ናቸው። በፍርድ ሂደት ላይ ጉዳዩን የያዘው ዳኛ አሳማኝ መረጃ ካገኘ ከ15 እስከ 18 ያሉ ታዳጊዎች በልዩ ሁኔታ ጉዳያቸውን ይመለከታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2011
ዳግም ከበደ