አዲስ አበባ፣ ሀገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት የጥቁር ገበያውን መቆጣጠር፣ በግለሰቦች እጅ ላይ ያለ ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመጣ ማድረግ እና ዳያስፖራው በህጋዊ መንገድ ገንዘብ እንዲልክ ማበረታት አስፈላጊ መሆኑን ምሁራን ገልጸዋል።
ምሁራኑ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታ ወቁት፣ አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቋቋም በአጭር ጊዜ ሊሰሩ በሚገባቸው ስራዎች ላይ ማተኮር ይገባል።
የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የኢኮኖሚክስ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንዳፈራው ሙሉጌታ እንዳሉት፣ ህዝቡ በእጁ ላይ የሚገኘውን የውጭ ገንዘብ ወደ ባንኮች እንዲወስድ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ህዝቡን ማሳመን፣ የጥቁር ገበያውን እንቅስቃሴ መከታተልና ማስቆም፣ ከረጂ እና አበዳሪ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ያስፈልጋል።
«የውጭ ገንዘብ እንደ ልብስና ጫማ በየቦታው እየተሸጠ ይገኛል» ያሉት ዶክተር ወንዳፈራው፣ ይሄንን ወደ ህጋዊነት ማምጣት ከመንግስት የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁንም መንግስት የውጭ ምንዛሬ እያገኘ ያለው ከብድር፣ ከእርዳታ እና ከዳያስፖራ በሚላክ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይነትም ይህንን የማጠናከርና የወጪ እና የገቢ ሚዛኑ መጠበቅ ያስፈልጋል።
በረጅም ጊዜ ደግሞ የኤክስፖርት ምርቶችን ማሳደግና ማስፋት እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በሀገሪቱ ያለውን የማዕድን ሀብት በማጥናትና በመለየት ማዕድናትን መላክ፤ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ማድረግ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን የሚፈታ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
በቱሪዝም ዘርፍ ያልተጠቀምንበት ተፈጥሮአዊ መስህቦች በማሳየት የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ ሰላም መቅደም አለበት ብለዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የባንክ እና ፋይናንስ መምህር አቶ መስፍን ተስፋዬ በበኩላቸው፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለመቋቋም በአጭር ጊዜ መወሰድ ያለበት እርምጃ በግለሰቦች እጅ የሚንቀሳቀሰውን የጥቁር ገበያን መቆጣጠር እና የችግሩንም ምንጭ ለማድረቅ መሞከር መሆኑን ተናግረዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ከአዲስ አበባ ውጭም የጥቁር ገበያ እየተስፋፋ መሆን አስታውቀዋል።
በረጅም ሂደት ደግሞ አዲስ የተቋቋሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኤክስፖርት ስራውን እስከጀመሩ ድረስ ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን በአገር ውስጥ የመተካት ስራ እንደ አማራጭ መያዝ ይኖርበታል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ተክኤ አለሙ እንዳሉት፣ አሁን በባንኮች አለ የተባለው ሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ከዚህ ቀደም ለረጅም አመታት ከነበረው ጋር ሲነፃፃር ምንም አስጊ ሁኔታ እንደሌለ ጠቅሰዋል። ወደኋላ ረጅም አመት መለስ ብሎ ሲታይ ከዚህ በላይ በእጅ ላይ የውጭ ምንዛሬ ኖሮ አያውቅም። አንዳንዴ የሶስት ወር ሊኖር ይችላል ፤ አንዳንዴ ደግሞ የአንድ ወር ይሆናል። በመሆኑም አስጨናቂ አይደለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ደግሞ በስምንት ወራት ውስጥ 13 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ማስታወቁ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2011
አልማዝ አያሌው