የመንግሥት መመሪያ በተገቢው መንገድ ባለመተግበሩ በደል ተፈፅሞብናል ሲሉ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ቁጥራቸው 27 የሚሆኑ መምህራን ቅሬታቸውን ለማሰማት ወደ ዝግጅት ክፍላችን መጥተዋል። ጥያቄ አቅራቢዎቹ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል በየደረጃው ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም ተገቢውን ምላሽ የሰጣቸው እንደሌለ በመግለጽ በደላችንን ሕዝብና መንግሥት ይወቀው ሲሉ የቅሬታቸው ምንጭ የሆነውን ጉዳይ ነግረውናል። ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል መምህር መንግሥቱ ቱፋ አንዱ ናቸው:: መምህር መንግሥቱ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በፍሬሕይወት ቁጥር 2 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማስተማር ላይ ይገኛሉ:: መምህሩ እንደሚናገሩት፤ በ2009 ዓ.ም በኪራይ መልክ ለአምስት ሺህ መምህራን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲሰጥ እርሳቸውም የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል:: በዚህ ምክንያት ከአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ ጋር የኪራይ ውል ተዋውለዋል:: እስከ 2011 ዓ.ም በውሉ ተመሥርተው ኪራዩን እየከፈሉ ቆይተዋል::
በ2011 ዓ.ም ደግሞ ሌላ አዲስ ዕድል አጋጠማቸው :: ይሄውም በ1997 ዓ.ም የተመዘገቡት የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ዕድለኛ ሆኑ:: 13ኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ሲወጣ የቤት ዕጣ ዕድለኛ ሲሆኑ ሁለት የጋራ መኖሪያ ቤት በእርሳቸው ስም ሊመዘገብ ሆነ:: በእርግጥ አንዱ ማለትም (የመምህራኑ ቤት) በኪራይ ስም ነው:: 2ኛው የ2011 ዓ.ም ደግሞ በስማቸው የወጣው የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ግን በግዢ ወደ እርሳቸው የሚተላለፍ ነው::
ቀድመው በኪራይ መልክ የተዋዋሉት ውሉ ሲፈፀም፤ በወጣው መመሪያ ቤት ከደረሳቸው ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው ተቀምጧል:: ስለዚህ ሪፖርት አደረጉ:: በጊዜው ማለትም በ2011 ዓ.ም በነበረው መመሪያ መሠረትም መምህሩ የቤት ኪራይ ተጠቃሚ ሆኖ መንግሥት በዘረጋው የቤት ልማት ፕሮግራም በራሱ ወይም በትዳር አጋሩ ስም የቤት ዕጣ ከደረሰው፤ ተመሳሳይ የቤት ዓይነት ከሆነና በኪራይ የያዙትን ቤት ከፈለጉ በወቅቱ በሚኖረው የቤት የማስተላለፊያ ዋጋ ግምት ተሰልቶ በረዥም ጊዜ ሽያጭ በስሙ እንዲተላለፍለት ይደረጋል የሚል በመሆኑ በረዥም ጊዜ ሽያጭ ቤቱን ለማግኘት ጥያቄ ማቅረብ መጀመራቸውን ይናገራሉ::
መምህር መንግሥቱ ‹‹ መጀመሪያ በ13ኛ ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች የቤቱ ዕጣ ሲወጣልኝ፤ በገባሁት የኪራይ ውል መሠረት ላለሁበት ወረዳ ቤቶች ኤጀንሲ ቅርንጫፍ ማሳወቅ ግዴታ ነበረብኝ:: ስለዚህ ‹እኔ መምህር ነኝ:: የመምህራን የኪራይ ቤት ተጠቃሚ ነኝ:: አሁን ደግሞ ቤት ደርሶኛል:: ስለዚህ የቤቱን ልዋጭ እፈልጋለሁኝ:: › በማለት ላለሁበት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 አመለከትኩኝ:: ›› ይላሉ::
ወደ ወረዳው ቤቶች ኤጀንሲ ቅርንጫፍ ሔደው ማመልከታቸውን ተከትሎ፤ የወረዳው ባለሞያ ቤቱን ለመረከብ የሚያስፈልገው እና መሞላት ያለበት ቅፅ 9ኝ ላይ ‹‹ የመምህራን ቤት ኪራይ ተጠቃሚ ናቸው›› በማለት ከፃፈ በኋላ አሽጎ ‹‹ይዘህ ቦሌ ክፍለ ከተማ ሂድ›› መባላቸውን ያስታውሳሉ::
የቦሌ ክፍለ ከተማ የቤት ዕድለኞችን የሚያስተናግደው በወረፋው ነው ተባሉ:: ታሽጎ የተሰጣቸውን ቅፅ 9ኝን ይዘው ለቀናት ተራቸውን ጠብቀው ወረፋቸው ሲደርሳቸው ሔዱ:: በሔዱበት ቀን ልክ እንደእርሳቸው አይነት ጉዳይ ያጋጠማቸው ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተገኙ መምህራኖች ነበሩ:: በጊዜው 27 የሚደርሱ ሲሆን፤ በ2011 ተሻሽሎ በወጣው የመምህራን ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የቤት መመሪያ ሰነድ መሠረት እንስተናገድ አሉ::
መመሪያው
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ለመምህራን በኪራይ ስለሚቀርብ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለማስተላለፍና ማስተዳደርን በተመለከተ የተዘጋጀ ላይ እንደሚያመለክተው በአንቀፅ 20 ልዩ የተከራይ መብት በሚለው ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ መምህሩ እንዴት ቤቱን በሽያጭ ማግኘት እንደሚችል ያትታል:: አንቀፅ 20 ንዑስ አንቀፅ 3 እንደሚያብራራው፤ መምህሩ የቤት ኪራይ ተጠቃሚ ሆኖ መንግሥት በዘረጋው የቤት ልማት ፕሮግራም በራሱ ወይም በትዳር አጋሩ ስም የቤት ዕጣ ከደረሰው፤ ተመሳሳይ የቤት ዓይነት ከሆነና በኪራይ የያዙትን ቤት ከፈለገ በወቅቱ በሚኖረው የቤት የማስተላለፊያ ዋጋ ግምት ተሰልቶ በረዥም ጊዜ ሽያጭ በስሙ እንዲተላለፍለት ይደረጋል ይላል::
በንዑስ አንቀፅ 4 ላይ ደግሞ ተከራይ በኪራይ የያዘውን ቤት በረዥም ጊዜ ሽያጭ በስሙ እንዲተላለፍለት ከተደረገ አከራይ ተመሳሳይ የቤት አይነት በተለዋጭ የሚተካ ይሆናል ይላል:: መምህር መንግሥቱም በሰነዱ መሠረት በአንቀፅ 20 ላይ ቤቱ አቻ ከሆነ መምህሩ ተለዋጭ ቤት ለማግኘት ውል መዋዋል ይችላል ስለሚል ቤቱ በሽያጭ ይተላለፍልኝ አሉ:: በዕጣ የደረሳቸውን ቤትም ለአከራይ ማለትም ለቤቶች ልማት ኤጀንሲ እንደሚለቁ አሳወቁ::
በተጨማሪ በአንቀፅ 20 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ ተከራይ ሙሉ ዕድሜውን በመምህርነት እስከ ጡረታ ካገለገለ እስከዚያ የከፈለው ኪራይ ታስቦ ባለው መደበኛ አሠራር የቀሪውን የቤቱን ዋጋ በወቅቱ በሚኖረው የቤት ማስተላለፊያ ዋጋ ግምት ተሰልቶ በረዥም ጊዜ ሽያጭ ቤቱ ይተላለፋል ይላል:: እዚህ ላይ የመምህራኑ ዋነኛ ጥያቄ በአንቀፅ 20 በንዑስ አንቀፅ 3 ላይም ሆነ በንዑስ አንቀፅ 1 ላይ ቤቱ መተላለፍ ያለበት በወቅቱ ዋጋ የሚለው በተለያየ መልኩ ተተግብሯል የሚል ነው::
አቻ ቤት ስለመግዛት
መምህር መንግሥቱ ንፋስ ስልክ ቤት የደረሳቸው ባለአንድ መኝታ የጋራ መኖሪያ ቤት ነው:: 13ኛው ዙር የቤት ዕጣ ሲወጣ ኮዬ ፈጬም የደረሳቸው በተመሳሳይ መልኩ ባለአንድ መኝታ የጋራ መኖሪያ ቤት ነው:: መመሪያው ደግሞ አቻ ቤት ከሆነ መምህሩ ከሁለት አንዱን መርጦ በወቅቱ ዋጋ ውል በመግባት መግዛት ይችላል ይላል:: ይህንን መሠረት በማድረግ ኮዬ ፈጬ የደረሳቸው ቤት 2ኛ ፎቅ ላይ ሆኖ፤ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማው ደግሞ 4ኛ ፎቅ ላይ ቢሆንም በመምህርነታቸው ጊዜ የተሰጣቸውን መርጠዋል:: ቤቱን መርጠው በ2009 ዓ.ም ዋጋ መሠረት ለመዋዋል ተዘጋጁ:: ነገር ግን ያ ሊሆን አልቻለም:: የአቤቱታቸው መነሻም ይኸው ነው::
መምህር መንግሥቱ እንደሚገልፁት፤ የግዢ ውል ከመፈፀማቸው ቀደም ብሎ በተጨባጭ አሁንም በሕይወት ያሉና መናገር የሚችሉ ጡረታ የወጡ ከአንድም ሁለት አንጋፋ መምህራንን አግኝተው አነጋግረዋል:: እርሳቸው በሽያጭ ከመግዛታቸው በፊት ጡረተኞች ቤቱን ሲገዙ የከፈሉት የቤት ኪራይ ተይዞላቸው ቤቱን ሲረከቡ የነበረው በ2009 ዓ.ም የዋጋ ተመን መሠረት ነበር:: ጡረተኞች በ2009 ማስተላለፊያ ዋጋ የተላለፈላቸው የከፈሉት ኪራይም ተቀንሶላቸው ነው:: ያ ተገቢ ነው:: ነገር ግን ለእነርሱ እንደጡረተኞቹ የከፈሉት የቤት ኪራይ ባይታሰብም፤ መመሪያው ላይ እንደተቀመጠው ነገር ግን ቤቱ ሊተላለፍላቸው ይገባ የነበረው በ2009 ዓ.ም ታሪፍ መሠረት መሆን ነበረበት ይላሉ::
መመሪያው ላይ ምንም እንኳ እነመምህር መንግሥቱ ጡረታ ባይወጡም በ2011 ዓ.ም የቤት ዕጣ የወጣላቸው በመሆኑ ለአቻው ቤት መክፈል ያለባቸው ልክ እንደጡረተኞቹ ሁሉ በወቅቱ ዋጋ መሆን እንዳለበት በግልፅ ተቀምጧል:: ነገር ግን የቤቶች ልማት ኤጀንሲ እነመምህር መንግሥቱን በዛ መንገድ አላስተናገዳቸውም:: ይልቁኑ በአምስት ቀን ውስጥ በአስቸኳይ ቤቱን ለማግኘት በ2011 ዓ.ም ዋጋ ተመን መሠረት እንዲከፍሉ ያዘዘ መሆኑን ያስረዳሉ::
እነመምህር መንግሥቱም ቤቱን እንዳያጡ በመስጋትና ነገ የሚመጣው አይታወቅም ብለው እንደምንም ተሯሩጠው ገሚሱ ቅድመ ክፍያውን ማለትም 20 በመቶውን፤ የቻለ ደግሞ ሙሉ ክፍያውን በ2011 ዓ.ም ዋጋ ተመን መሠረት ከፈሉ:: እንደርሳቸው ሁሉ ቀሪውን 80 በመቶ በባንክ ወለድ እየከፈሉ ያሉም አሉ:: መምህር መንግሥቱ በዚህ ምክንያት ምን ያህል እየተጎዱ እንደሆነ ሲያመለክቱ፤ ለምሳሌ በ2009 ውል ተዋውለው ቢሆን ኖሮ ክፍያው 187 ሺህ ብር ብቻ ይሆን ነበር:: ነገር ግን በ2011ዓ.ም ተመን ክፈል በመባላቸው 248 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ተገድደዋል::
ስለዚህ ከባንክ ጋር ሲዋዋሉ ወርሐዊ ክፍያው 420 ብር ነበር:: ከአንድ ዓመት ዕረፍት በኋላ ሲሔዱ ግን 2600 ብር ተደርጓል:: ወደ ፊትም ይጨምራል:: ይህ እርሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ መልኩ ቃሊቲ አካባቢ እንደርሳቸው ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠመው መምህር ለተመሳሳይ ቤት 2500 ብር እየከፈለ ነው:: አሁን በቅርቡ የተዋዋሉት ግን በ2009 ዓ.ም ተመን መሠረት የሚከፍሉ በመሆናቸው ልዩነቱ ብዙ ነው:: ስለዚህ በተመሳሳይ ሙያ ላይ እየሠሩ አቻ ቤት ገዝተው የሚከፍሉት ግን የተለያየ አንዳንዴም ድብልቅልቅ ያለ መሆኑን ይናገራሉ:: ስለዚህ ጥያቄያውን እስከ ካቢኔ ጽሕፈት ቤት ለማቅረብ ተነጋግረው ሲንገታገቱ ሌላ ነገር መጣ፡፤
በድጋሚ ጥያቄ
እንደመምህር መንግሥቱ ገለፃ፤ ቀደም ሲል የመምህራን የቤት ኪራይ የነበረው ሽያጭ የሚፈፀመው ለጡረተኞች ብቻ ነበር:: ተጨማሪ ደግሞ እንደርሳቸው አይነት የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኛ ለሆኑ ሰዎች በተለዋጭነት የደረሳቸውን ቤት ሰጥተው አቻውን ይገዙ ነበር:: አሁን በቅርቡ የተከራዩ መምህራኖች ቤቱን ይግዙ ሲባል ደግሞ ለ5ሺ መምህራኖች በ2009 ዓ.ም ታሪፍ መሠረት ቤቱ በሽያጭ ይተላለፍላቸው ተባለ:: እስከ ጡረታ በኪራይ እንዲኖሩ የነበረው ደንብም ሆነ መመሪያ እንዲሁም ውሉም በሙሉ ተጥሶ ሌላ ማስተላለፊያ ደንብ ተዘጋጀ:: ከዛ ውስጥ ጡረታ የወጡም ሆኖ እንደእነርሱ ዓይነት ቤቱን ጠቅልሎ በልዋጭ የገዛው (የወሰደው) ሳይለይ ሁሉም በ2009 ዓ.ም ዋጋ ቤቱን ይውሰድ ተባለ::
ስለዚህ አሁንም ድረስ በወለድ ለቤቱ ሽያጭ እየከፈሉ ያሉት እነመምህር መንግሥቱ ‹‹ይህ እኛን ይመለከተናል›› ብለው ጥያቄ አቀረቡ:: እንደሁሉም መምህራን ቤቱን በኪራይ መልክ የተዋዋሉት 2009 ዓ.ም ስለሆነ ለሽያጭም መዋዋል ያለባቸው በ2009 ዋጋ ተመን መሠረት መሆን ነበረበት ብለው ተከራከሩ:: ያንን መሠረት አድርገው የሚመለከተው እና መምህራንን ወክሎ ሊከራከርላቸው ይችላል ወደተባለው የሙያ ማኅበር ሄዱ:: እንዲሟገትላቸው ብዙ ጥረት አደረጉ::
መምህር መንግሥቱ እንደሚናገሩት፤ መጀመሪያ ቤቱ በኪራይ መልክ ሲሰጣቸው የመሰላቸው ትምህርት ቢሮ ቤቶቹን ገዝቶ ለመምህራን እንዳከፋፈለ ገምተው ነበር:: ስለዚህ ዋጋውን በሚመለከት ትክክለኛው አሠራር እንዲተገበር ሲሉ ትምህርት ቢሮ አመለከቱ:: ሆኖም አልሆነም:: ቤቱን ትምህርት ቢሮ ሳይሆን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ጉዳይ መሆኑን ሲያውቁ ይህንን መሠረት አድርገው በ12/08/2013 ተነጋግረው ግንቦት 2013 ላይ ለሙያ ማኅበሩ ደብዳቤ ፅፈው የሙያ ማኅበሩ ጥያቄውን እንዲያቀርብላቸው አመለከቱ:: በወቅቱ ለማኅበሩ ፕሬዚዳንት አስረድተው እና በደንብ ተናግረው ማመልከቻውን ሲያስገቡ፤ የማኅበሩ ፕሬዚዳንትም የሚመለከተውን አካል እንደሚያነጋግሩ ገለፁላቸው::
እንደመምህር መንግሥቱ ገለፃ፤ ለሙያ ማኅበሩ ብቻ ሳይሆን ለከተማው ቤቶች ልማት ኤጀንሲም መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም አመልክተዋል:: ሆኖም ምላሽ አላገኙም:: ቤቶች ኤጀንሲ በቃል የሰጠው ምላሽ ቢኖር ‹‹እኔ የሠራሁት በመመሪያው መሠረት ነው:: ምንም ዓይነት የጣስኩት መመሪያ የለም ›› የሚል ብቻ ነበር::
እነመምህር መንግሥቱ ደግሞ በበኩላቸው፡ ኤጀንሲው እነርሱን ያስተናገደበት መንገድ ፍትሐዊ አይደለም:: ነገር ግን ይሄ መንገድ ትክክል ከሆነ፤ አሁን ሌሎች በ2009 ዓ.ም ቤቶቹን ለተከራዩ መምህራን የተላለፈበት መንገድ ትክክል አይደለም:: ምክንያቱም መመሪያው በወቅቱ ስላለ ከእነርሱ በኋላ የሽያጭ ውል ለፈፀሙ መምህራን በ2009 ዓ.ም ዋጋ ማስተላለፋቸው ተገቢ አይደለም:: ስለዚህ አሠራሩ አንድ ዓይነት መሆን ነበረበት:: እነርሱ ላይ የተፈፀመው ትክክል ካልሆነ ማስተካከል ወይም የአሁኖቹን በአሁኑ ታሪፍ መሠረት ማዋዋል እና ሽያጭ መፈፀም ሲገባ የተለያየ ክፍያ መፈፀሙ ፍትሃዊነት የጎደለው ነው ባይ ናቸው::
እነመምህር መንግሥቱ ይህንን መሠረት በማድረግ እስከ መምህራን ማህበር ድረስ ሔደው መሟገት ጀመሩ:: በእርሳቸው በኩል ለክፍለ ከተማው መምህራን ማኅበርም ጥያቄያቸውን አቅርበዋል:: ነገር ግን ከአዲስ አበባ መምህራን ማኅበርም ያገኙት ምላሽ በቅድሚያ ሌሎቹ ውሉን ተዋውለው ይጨርሱ ከዛ የእናንተ ይቀጥላል መባላቸውን ይናገራሉ:: በኋላም እንደመምህር መንግሥቱ ተመሳሳይ ተበድለናል ያሉ መምህራን እርስ በእርስ ተነጋግረው፤ ሁላችንም ግር ብለን ከምንሔድ እና የመንግሥት ሥራ ከምንበድል የተመቸው ሰው እየመጣ ሒደቱን ይከታተል ተባብለው በዛ መሠረት መከታተል ጀመሩ::
በዛ መሠረት ምላሽ ሲያጡ በየካቲት 2014 ዓ.ም መምህራን ማኅበሩ ጋር በድጋሚ ሔደው ሲጠይቁ የተሰጣቸው ምላሽ ‹‹ለተወካያችሁ በቴሌግራም ጥሪ አቅርበን ነበር›› ተባሉ:: ነገር ግን በቴሌግራም ጥሪ የተደረገው ከ5ሺው መካከል ክፍያቸውን በተለያየ ምክንያት ያላከናወኑ እና ውል ያልተዋዋሉ መምህራን የጊዜ ይራዘምልን ጥያቄ አቅርበው ስለነበር እነርሱ ስለተፈቀደላቸው ለእነርሱ ጥሪ ቀርቧል:: ጥሪው እነርሱን እንጂ እነርሱን እንደማይጋብዝ መምህር መንግሥቱ ይናገራሉ::
‹‹ቀድሞም ቢሆን የወከልነው ሰው የለም:: የወከልነው ሰው ሳይኖር ለተወካያችሁ ጥሪ አስተላልፌያለሁ›› የሚል ምላሽን የመምህራን ማኅበሩ መስጠቱን ተከትሎ ሰዎች ተስፋ ቆርጠው መበታተናቸውን መምህር መንግሥቱ ያስረዳሉ:: ማኅበሩ እንደው በእውነት ተወካይ ለማነጋገር ከሞከረ ምንም እንኳ የተወከለ ባይኖርም የአንዱ ሰው ስልክ እምቢ ቢል ለሌላው ሰው መደወል ነበረበት:: ›› ሲሉ ያስረዳሉ::
እንደመምህር መንግሥቱ ገለፃ፤ በዚህ ምክንያት ቅሬታ ላላቸው መምህራን ስልክ እንኳ ሲደውሉ ፈቃደኛ የሚሆን ጠፋ፤ ሁሉም ተስፋ ቆረጡ:: ምክንያቱም ፍርድ ቤት ለመሔድ አቅም የለም:: ስለዚህ ቢያንስ ሕዝብ ይወቀው በማለት ወደ መገናኛ ብዙኃን መጥተዋል::
ሌላኛዋ አቤቱታ አቅራቢ መምህርት ዘውድነሽ መለስ በቀለመወርቅ ጥሩነህ ትምህርት ቤት ሾላ አዲሱ ገበያ አካባቢ በማስተማር ላይ ይገኛሉ:: መምህርት ዘውድነሽ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ እርሳቸውም ለመምህራን ቤት በኪራይ ሲሰጥ እንደመምህር መንግሥቱ ሁሉ ጀሞ አካባቢ ቤት አግኝተው ተከራይተው ሲኖሩ ነበር፡፤ በመሐል በ1997 ዓ.ም የተመዘገቡት የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ በ2011 በ13ኛው ዙር እንደወጣላቸው ሰሙ::
በዛ ጊዜ መምህራን የተከራዩትን ቤት እንዲገዙ አመራሩ ውይይት ቢያደርግም እነርሱ ግን ባለማወቃቸው በመመሪያው መሠረት የደረሳቸውን ቤት ወደ ኪራዩ ማዘዋወር መብታችሁ ነው በመባላቸው የደረሳቸውን ቤት ትተው የተከራዩትን ቤት ለመግዛት ለቤቶች ልማት ኤጀንሲ አሳወቁ::
‹‹እንደአንዳንድ ሰዎች ሁለት ቤት የምናገኝበት ሁኔታ ቢያጋጥመንም አጭበርብረን ለመሸጥ አላሰብንም፤ ምክንያቱም ጓደኞቻችን ሽንት ቤትና ማዕድቤት
ተከራይተው እየኖሩ እያየን የመሸጥ ሞራል ስላልነበረን አንዱን እናስረክብ አልን:: ›› የሚሉት መምህርቷ፤ በመመሪያው መሠረት አንዱን አስረክበው ሌላውን ሲወስዱ ቤቱን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ በቀድሞ ዋጋ ማለትም በ2009ዓ.ም ታሪፍ መሠረት ማስተላለፍ ሲገባው በአዲሱ ዋጋ እንዲወስዱ ማድረጉ ፍፁም ግፍ መሆኑን በምሬት ይናገራሉ::
‹‹ አቤቱታ ለማቅረብ ብንፈልግም የትም ቦታ ሔደን የሚያነጋግረን የለም:: ‹ቤቶች ኤጀንሲ የሠራነው በመመሪያው መሠረት ነው› አለ:: ሌላ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደለም:: ነገሩን ትምህርት ቢሮ፣ መምህራን ማኅበርም ሆነ ቤቶች ልማት ተገቢውን ምላሽ ሳይሰጥ፤ በመጨረሻ አሁን ደግሞ ሁሉም የተከራየው መምህር በ2009 ዓ.ም ታሪፍ መሠረት ቤቱን ይግዙ ተባለ ይላሉ::
በእነርሱ በኩል ‹‹ እኛም ጥያቄ እያቀረብን ነበር:: እኛም መስተናገድ ያለብን በ2009 ዓ.ም ዋጋ ነው›› ብለው ቢጠይቁም መምህራን ማኅበሩ ‹‹ቀድማችሁ መዋዋል አልነበረባችሁም፤ መተው ነበረባችሁ›› ያላቸው መሆኑን ይናገራሉ:: ጠበቃ ጋር ሲሔዱ ማሸነፍ እንደሚቻል ቢያሳይም ሁለት ዓመት ይፈጃል ሲባል ተጎጂ እሆናለሁ ብለው በመገመታቸው ጉዳዩን እንዳቆሙት ይጠቁማሉ::
እንደመምህርቷ ገለፃ፤ በወቅቱ የኪራይ ቤቱን የማግኘት ዕድል በዚህ መልኩ የሚከናወን ስላልመሰላቸው በዕጣ የደረሳቸውን 66 ካሬ ሜትር የጋራ መኖሪያ ቤት ትተው የወሰዱት 44 ካሬ ሜትር የሆነውን በኪራይ አግኝተውት የነበረውን ቤት ነው:: ነገር ግን አሁን ለ44 ካሬ ሜትር እየከፈሉ ያሉት ግን ለ66 ካሬው መሆን የሚችል ነበር::
‹‹የቤቶች ልማት ኤጀንሲ የ2011 መምህራን የቤት ዕድለኞችን ያለአግባብ ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ከ50ሺህ ብር ጀምሮ ተጨማሪ ዕዳ ከፋይ አድርጎናል:: ለእዚህም ማንንም ብንጠይቅም ኃላፊነት የሚወስድ የለም:: የአሁኑ ውሳኔ ደግሞ እኛንም ያማከለ ቢሆንም የሚያስተናግደን የለም:: በተለይ ቤቶች ኤጀንሲ መመሪያው አይመለከታችሁም እያለ ነው:: ሊያስተናግደን የወደደ ባለመኖሩ ተስፋ ቆርጠናል:: ›› ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል::
የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ምላሽ
የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ ከመምህራኑ የቀረበውን አቤቱታ አስመልክቶ ላነሳነው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ፤ መንግሥት በዝቅተኛ የቤት ኪራይ ዋጋ ለመምህራን በ2009 ዓ.ም ቤት ሰጥቷል:: ቤቱ ሲሰጥ አገልግሎትን መሠረት ያደረገ መስፈርት የነበረ ነው ። ከ16 ዓመት በላይ አገልግሎት የነበራቸው ቤት የሌላቸው ከ70 በመቶ በላይ መምህራን እንዲያገኙ ተደርጓል:: 30 በመቶ የሚሆነው ደግሞ የቤተሰብ ቁጥርን ማዕከል በማድረግ ከአራት ቤተሰብ በላይ ያላቸው ባለሁለት መኝታ፤ አንድ ልጅ ያላቸው ባለ ሶስት ቤተሰብ ባለአንድ መኝታ፤ ትዳር ያላደረጉ ስቱዲዮ እንዲከራዩ ተወስኖ ተሰጥቷል::
ከ2009 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 2013 ዓ.ም ድረስ በየቤት ዓይነቱ እንደየተመኑ ኪራዩን እየከፈሉ ኖረዋል የሚሉት አቶ ድንቃለም፤ ‹‹ ቀደም ሲል እኛ ጥያቄ እያቀረብን ነበር:: አንደኛው ጥያቄ ከአምስት ሺ ሌላ ለሌሎችም ቤቶች ሌሎች መምህራኖች ቤት ይሰጥ እያልን ነበር:: በተጨማሪ ‹5ሺው መምህራን ቤቱ በኪራይ ብቻ መሆኑ በቂ አይደለም:: ወደ እኛ መዘዋወር አለበት› የሚል ጥያቄ ነበራቸው:: ይህንን ተከትሎ በ2013 ዓ.ም ከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ ስብሰባ በማካሔድ መምህራን በኪራይ የያዟቸውን ቤቶች በግዢ ወደ ስማቸው እንዲያዞሩ ውሳኔ አስተላልፏል:: ›› ሲሉ ሂደቱን ያብራራሉ::
ትምህርት ቢሮ፣ መምህራን ማኅበር እና የከተማው ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ተገናኝተው የጋራ ሰነድ በማዘጋጀት ጥቅምት 2014 ዓ.ም ላይ ቤቱን ማስተላለፍ ተጀመረ:: ቤቶቹ ሲተላለፉ የወጡ 26ት አካባቢ መስፈርቶች እንደነበሩ በማስታወስ፤ በዛ መሠረት ቤቱን የማስተላለፍ ሥራውን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ያስረዳሉ::
መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ቤቱ ይተላለፍላቸው የሚል ብቻ ነበር:: ማኅበሩ ግን ለመምህራን ቤቱ መተላለፍ ያለበት በኪራይ ሲተላለፍላቸው በነበረበት ወቅት በነበረ የቤት ሽያጭ ዋጋ መሆን አለበት አለ:: ምክንያቱም መመሪያው ላይ በወቅቱ የሚል ቃል ስለነበረ ቤቱ አሁን ባለው የዋጋ ተመን ከተላለፈ መምህራንን የሚጎዳ በመሆኑ መተላለፍ ያለበት በ2009 ዓ.ም ዋጋ ተመን መሠረት ሊሆን ይገባል የሚል ሃሳብ ያቀረቡ መሆኑን ይገልፃሉ::
ካቢኔውም መምህራን አገርን እያገለገሉ በመሆናቸው በ2009 ዓ.ም ዋጋ መሠረት እንዲተላለፍ ወሰነ:: ዘመናቸውን በሙሉ በዝቅተኛ ደመወዝ አገራቸውን ሲያገለግሉ የኖሩ ለጡረታ የቀረቡ መምህራን ይህም ቢሆን ሊፈትናቸው ይችላል:: ስለዚህ ለአገልግሎታቸው ሲባል ብዙም ባይመጥናቸውም እነርሱን ለመደገፍ በማሰብ ካቢኔው ውሳኔውን ካስተላለፈበት ቀን ጀምሮ ቤቱን እስከሚረከቡበት መጨረሻ ቀን ድረስ ጡረታ የሚወጡ መምህራን የቤት ኪራይ ተመላሽ ይሆንላቸዋል የሚል ውሳኔም የተላለፈ መሆኑን ያስረዳሉ:: ለሌሎች ግን 2009 ዓ.ም ላይ በነበረው ዋጋ ይተላለፍላቸው ተብሏል የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በዛው መሠረት ከሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት 2014 ዓ.ም ድረስ ጡረታ የሚወጡ መምህራኖች የቤት ኪራዩ ታስቦ ከሽያጩ ላይ እንዲቀነስላቸው የተደረገ መሆኑን ይናገራሉ::
ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ለማኅበሩ ፕሬዚዳንት ለመምህራን 5 ሺዎቹ ቤቶች ይተላለፉ የሚል ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ቤቱ የተሸጠላቸው መምህራኖች ነበሩ:: ይህንን አታውቁም? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ከዛ በፊት ቤቱ የተላለፈላቸው መምህራኖች በማን እውቅና ቤቱ እንደተላለፈላቸው አናውቅም:: ውሳኔው የተላለፈው ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ነው:: ከዛ በፊት ያዘዋወሩትን ማኅበሩ አያውቅም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል::
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ከዛ በፊት ሊያዘዋውሩበት የሚችሉበት መመሪያ አልነበረም ብለዋል:: ነገር ግን ከላይ እንደገለፅነው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ለመምህራን በኪራይ ስለሚቀርብ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለማስተላለፍና ማስተዳደርን በተመለከተ በተዘጋጀ መመሪያ ላይ የቤት ተከራይ መምህራን ዕጣ ከደረሳቸው ቤቱን በሽያጭ የሚያገኙበትን ሁኔታ በአንቀፅ 20 ላይ አስቀምጧል::
የመምህራኑን አቤቱታ በዝርዝር ያቀረብንላቸው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፤ በሌላ በኩል የ2011 ዓ.ም የቤት ዕጣ የወጣላቸው መምህራን በ2011 ዓ.ም ታሪፍ ስለከፈሉ ሌሎቹም ሁሉም በ2011 ዓ.ም ታሪፍ መሠረት ይክፈሉ የሚል አቋም የለንም ይላሉ:: በወቅቱ ዕጣው የወጣላቸው መምህራኖች የሚያዋጣቸውን የመረጡ መሆኑን በመግለፅ፤ የአሁኖቹ በ2013 ዓ.ም ቤቱን የገዙ መምህራኖች በ2009 ዓ.ም ታሪፍ ቤቱን በማግኘታቸው እንጂ፤ እነኚህኞቹ በ2013 ዓ.ም ታሪፍ ቤቱን ቢገዙ ኖሮ ጥያቄ ከማንሳት ይልቅ ተጠቃሚ ነን ሲሉ ጉዳዩን ያልፉት ነበር የሚል ምላሽ ሰጥተዋል::
ማኅበሩ ከዛ በፊት የሆነውን ነገር ወደ ኋላ ሔዶ እንደዚህ አድርጉ ብሎ ጥያቄ ለማቅረብ ለእርሱ በጣም አስቸጋሪ ነው ሲሉ መግለፃቸውን ተከትሎ፤ የዝግጅት ክፍሉ መምህራን ወደ እናንተ መጥተው አቤቱታ አላቀረቡም ወይ? በሚል ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የትኛው እንደሆነ ባይገባቸውም በ13ኛ ዙር የወጣው የቤት ዕጣን በሚመለከት የቀረበ አቤቱታ እንደነበር ያስታውሳሉ:: ያንን በተመለከተ ከቤቶች ልማት ጋር ተነጋግረናል የሚሉት አቶ ድንቃለም፤ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ የገለፀው ‹‹ እነዚህ መምህራን ማመልከቻ ፅፈው አስገብተዋል:: በ13ኛው ዙር የቤት ዕጣ የወጣልን ቢሆንም በመምህርነታችን በኪራይ መልክ ላገኘነው ቤት የማፅጃ ወጪ ስላወጣን የመምህራኑን ቤት በስማችን አዘዋውሩልን የሚል ጥያቄ አቅርበዋል:: ሆኖም ኤጀንሲው የመምህራን ቤትን ማዘዋወር አንችልም፤ እኛ የተባልነው አከራዩ በመሆኑ አንችልም›› የሚል መልስ መስጠቱን እንደገለፀ ተናግረዋል::
መምህራኖቹ የቤቶች ልማት ኤጀንሲ የሰጠውን ምላሽ ተከትሎ ‹‹ዓላማችሁ እኛን መጉዳት ነው:: ›› በማለታቸው፤ ቤቶች ልማት ማመልከቻ እንዲጽፉ ጠይቆ በራሱ መመሪያ መሠረት ማመልከቻ አስጽፏቸው በስማቸው አስተላልፎላቸዋል› የሚል ምላሽ የተሰጣቸው መሆኑን ገልፀዋል::
አቶ ድንቃለም በሌላ በኩል በመመሪያው መሠረት መምህራን በዕጣ አቻ ቤት ከደረሳቸው የፈለጉትን መርጠው መውሰድ ይችላሉ የሚል መመሪያ በመኖሩ በዛ ምክንያት መርጠው ወስደዋል በማለት፤ ካቢኔው 5ሺውን ቤት ለመምህራን ከመወሰኑም በፊት ቤቱ ለመምህራን ሲተላለፍ እንደነበር ይናገራሉ:: እንደማኅበሩ ፕሬዚዳንት ገለፃ፤ ቤቶች ልማት በ2009 ዓ.ም ታሪፍ መሠረት አስተላልፉ የሚል መመሪያ በወቅቱ ስላልነበር ጥያቄውን አስተናግደናል የሚል ምላሽ የሰጣቸው መሆኑን ይናገራሉ::
እንደማብራሪያቸው ጉዳዩ ለቤቶች ልማት ኤጀንሲም ሆነ ለመምህራኑ ለሁለቱም አስቸጋሪ ነው:: መምህሩ አቻው መምህር የተሻለ ተጠቃሚ ሆኗል:: ይህ ፍትሐዊ አይደለም፤ ይላል:: በሌላ በኩል ደግሞ ኤጀንሲው ‹‹እኛ ቤቱን በስማችሁ አዙሩ ብለን አላስገደድናቸውም ራሳቸው ማመልከቻ ጽፈው ጠይቀው ቤቱ በስማቸው በመሆኑ ወደ ኋላ ብለን መሥራት አንችልም›› ብሏል:: ቤቶቹ በቦንድ ብድር የተሠሩ በመሆናቸው ወደ ባንክ ብድር ስለተከፈለ ወደ ኋላ ተመልሰን በ2009 ዓ.ም ታሪፍ ልናደርግ የምንችልበት ዕድል የለም ማለታቸውን አቶ ድንቃለም ገልፀዋል::
የዝግጅት ክፍሉ ቀድሞም ቢሆን መምህራኑ ቤቱን የተከራዩት በ2009 ዓ.ም መሆኑን በመጥቀስ፤ በዛ ጊዜ በመመሪያው በዕጣ ቤት ያገኘ በወቅቱ የነበረውን የዋጋ ተመን ከፍሎ አንዱን ቤት መውሰድ ይችላል ስለሚል በዚህ መልኩ አስተናግዱን የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አላገኙም:: እናንተ ከመመሪያው አንፃር በወቅቱ የሚለውን መመሪያው ውስጥ ያለውን ቃል መሠረት በማድረግ ለምን አልተከራከራችሁላቸውም? የሚል ጥያቄም ያቀረበላቸው ሲሆን፤ የመምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት፤ ቃሉን በመጥቀስ ከመምህራን ማኅበር ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል:: ነገር ግን በመመሪያው በወቅቱ የሚለው ቃል የተተረጎመው አሁን ካቢኔው ሲወስን ማኅበሩ መምህራንን ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ በወቅቱ የሚለው ቃል ቤቱ በተከራዩበት ዘመን የጠቀሰ እንዲሆን ተወሰነ:: በፊት ግን በወቅቱ የሚለው ቃል አወዛጋቢ ነበር ይላሉ::
እንደአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ገለፃ፤ ከዛ በፊት ግን በወቅቱ የሚለው ቃል የሚያመለክተው የጊዜውን ዋጋ ሲሆን፤ ጡረታ የወጡ መምህራኖች ሲስተናገዱ የነበረው በ2009 ዓ.ም ዋጋ ሳይሆን ጡረታ በወጡበት ዕለት በነበረው ዋጋ መሠረት ነው:: ከሐምሌ 2013 ዓ.ም በፊት ጡረታ የወጡ መምህራኖች በዚህ ወቅት የነበረውን ዋጋ እየከፈሉ ሲስተናገዱ ቆይተዋል:: ይህን አቤቱታ ያመጡ መምህራን ከሐምሌ 2013 ዓ.ም በፊት ጡረታ ሲወጡ የነበሩ መምህራን በወቅቱ የሚለው ቃል የ2009 ዓ.ም ትርጉም ተሰጥቶት በዛ መልክ ተስተናግደው ስለመሆኑ መረጃ ይዘው ከቀረቡ በእነርሱ በኩል ከቤቶች ልማት ጋር ለመነጋገር ያመቻል ሲሉ ገልፀውልናል::
የመምህራኑን አቤቱታ ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ጥያቄ አቅርበናል:: ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ በ2009 ዓ.ም ቤት በኪራይ መልክ 5000 መምህራን የተሰጣቸው መሆኑ ይታወሳል:: ቤት በኪራይ መልክ ካገኙ መምህራኖች መካከል የተወሰኑት በ2011 ዓ.ም በዕጣ ቤት ደርሷቸዋል:: እነኚህ ሁለት ቤት ማግኘት ስለሌለባቸው አንዱን ቤት ምረጡ ተብለው የመረጡትን ቤት በግዢ ወስደዋል:: ነገር ግን ቤቱን ሲወስዱ ሙሉ ክፍያም ሆነ ቅድመ ክፍያ የከፈሉት በ2011 ዓ.ም የዋጋ ተመን ነበር::
በጊዜው ማለትም በ2011 ዓ.ም ‹‹መምህራን የኪራይ ቤት ደርሷቸው በድጋሚ ዕጣ ቢደርሳቸው ቤቱን ማግኘት ያለባቸው በወቅቱ ዋጋ ነው›› የሚል መመሪያ ቢኖርም፤ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ግን በአምስት ቀን ውስጥ በ2011 ዓ.ም ታሪፍ እንድንዋዋል አስገድዶናል:: ከውሉም በኋላ ተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አጥተናል:: በ2013 ዓ.ም ደግሞ ለሌሎቹ መምህራኖች ግን ተመሳሳይ ቤት በ2009 ዓ.ም ታሪፍ ተሰጥቷቸዋል:: ይህ ፍትሐዊ አይደለም:: የሚመለከተውን አካል አነጋግሩልን ሲሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቤቱታ አቅርበዋል::
ጨምረውም ለግማሹ በ2011 ታሪፍ ለግማሹ በ2009 ዓ.ም ታሪፍ ቤቶቹ ለመምህራኖች መተላለፋቸው ምን ያህል ተገቢ ነው? እንደመምህራኖቹ ገለፃ፤ ‹‹በ2009 ዓ.ም ታሪፍ አለመዋዋላችን እኛን ጎድቶናል አሁንም እየከፈልን ያለነው ከሌሎች ሰዎች በላይ ነው:: ›› ሲሉ መምህራኖቹ አቤቱታ አቅርበዋል:: ስለዚህ ኤጀንሲው መምህራኖቹን ለምን በ2011 ዓ.ም በ2009 ዓ.ም ታሪፍ አላስተናገዳቸውም? እነርሱ በዛ መልክ ካልተስተናገዱ ሌሎቹ ማለትም በ2013 ዓ.ም ቤቱን የገዙ መምህራን ለምን በ 2009 ዓ.ም ታሪፍ ተስተናገዱ? በመመሪያው ላይ ‹‹በወቅቱ ታሪፍ›› የሚለው የ2009 ዓ.ምን ታሳቢ የማያደርግ ከሆነ ወይም በወቅቱ የሚለው የግዢ ውል ሲፈፀም የሚያመለክተው ጊዜን ከሆነ ለምን በተለያየ መልኩ ተስተናገዱ? ከዚህ በኋላ ማድረግ የሚቻለው ምንድን ነው? ስንል ጥያቄ አቅርበናል:: ነገር ግን ጥያቄውን ባቀረብንበት ጊዜ የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አዳማ መሆናቸውን ገልጸውልናል:: ከአዳማ ከመጡም በኋላ ጥያቄው እንዲላክላቸው እና ለሚመለከተው አካል የሚያቀርቡ መሆኑን በስልክ ስለገለፁልን ከላይ የጠቀስናቸውን ጥያቄ አካተን በቴሌግራማቸው ልከናል:: ሆኖም ግን ጥያቄውን ከላክን በኋላ በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም:: በመሆኑን የቤቶች ልማት ኤጀንሲን ምላሽ አላካተትንም። ሆኖም ግን ኤጀንሲው በቀጣይ ምላሽ ከሰጠን የምናስተናግድ ይሆናል::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም