አዲስ አበባ፣ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) 29ነኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ህዝቡን በልማት እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ለሚደረገው ቀጣይ ትግል ራሱን በማዘጋጀት መሆኑን የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበርና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ።
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ ትናንት በሚሊየም አዳራሽ በፓርቲው 29ነኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር ኦዴፓ ዛሬም ልክ እንደትናንቱ የህዝቡን ጥቅም በማስቀደም እንደሚታገል ጠቅሰዋል። የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎችም በቀጣይ በሚደረገው ትግል የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸውም መልእከት አስተላልፈዋል።
«ኦዴፓ ለዛሬ ድል የበቃው ከህዝቡ ጋር በመሆን ነው» ያሉት ምክትል ሊቀ መንበሩ አቶ ለማ መገርሳ፣ በቀጣይ ህዝቡ ከፓርቲው ጎን እንዲቆምና ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። ህዝቡን በልማት እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ለሚደረገው ቀጣይ ትግልም ሁሉም ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል።
« ዛሬ እዚህ የደረስነው በአንድነታችን ነው፤ ታግለን አዲስ ዘመን ስለፈጠርንም በደስታ ሆነን በዓሉን በማክበር ላይ ነን» ሲሉም ተናግረዋል።
ወደ ፊትም የኦሮሞ ህዝብ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ለመቅረፍ እና የሚያጋጥሙትን እንቅፋቶች ለማለፍ ያለው ብቸኛ አማራጭ አንድነትን ማጠናከር ነው ያሉት አቶ ለማ የኦሮሞ ፓርቲዎችም በአንድነት ለመሥራት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት አጥብበው በአንድነት እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ለወጣቶች ባስተላለፉት መልእ ክትም «እናንተ በከፈላችሁት መስዋእትነት ዛሬ ላይ ደርሰናል፤ ወደ ፊትም በመደማመጥና በመተጋገዝ አሁን እንደ ሀገር የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል» በማለት ተናግረዋል። ይህ ዕለት ወጣቶች ለወገናቸው ሲሉ የታሰሩ፣ አካላቸው የተጎዳና የሞቱ መሆናቸውንም የምናስብበት ነው ብለዋል።
ለኦሮሞ ህዝብ ባስተላለፉት መልእክትም« ሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት የሚኖርባትን አዲሲቷን ኢትዮ ጵያ የመገንባት ኃላፊነት በኦሮሞ ላይ የተጣለ ነው» ያሉት አቶ ለማ፤ የኦሮሞ ህዝብ ከዚህ በፊት የሀገሪቱን ዳር ድንበር በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለና ትልቅ ታሪክም ያለው ህዝብ መሆኑን አንስተው አሁንም ሀገሪቱን አንድ በማድረግ ታሪክ መሥራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
የሀገሪቱን ሰላም በማረጋገጥ በፖለቲካው የተገኘው ድል ቀጣይነት ኖሮት በኢኮኖሚውም መደገም እንዳለበት የተናገሩት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ለማ ፤ ሰላምን በማስፈን ዙሪያ የህብረ ተሰቡ ሚና ከፍተኛ ሊሆን እንደ ሚገባ ገልጸዋል።
ኦዴፓ በቀጣይም የክልሉን ሰላም በማስጠበቅ በፖለቲካ ዘርፍ የተገኘውን ድል በኢኮኖሚውም ለመድገም በቁርጠ ኝነት የሚሠራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) በቀጣይ ጊዜያትም ለሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ያሉት የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ለማ፣ የሀገሪቱ ብሔሮችና ብሔረሰቦችም በዚህ ላይ እምነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።
በበዓሉ ላይ የአራቱ ብሔራዊ እህት ፓርቲዎች ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፣ ፕሮግራሙ በአባ ገዳዎች ምርቃት እና በአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የመክፈቻ ንግግር ተከፍቷል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2011
ኢያሱ መሰለ