በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም እንዲሁም ሌሎች ደረጃዎች የተሰጣቸው ውድድሮች እንደተለመደው በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ተከናውነዋል። በእነዚህም ውድድሮች ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በውጤታቸው የራሳቸውንና የሃገራቸውን ስም ማስጠራት ችለዋል። የፕላቲኒየም ደረጃ ባለው የቺካጎ ማራቶን ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በሁለቱም ጾታ የተወዳደሩ ሲሆን፤ በወንዶች በኩል ሰይፉ ቱራ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።
በወንዶች መካከል በተደረገው ውድድር ኬንያዊው አትሌት ቤንነን ኪፕሩቶ አሸናፊ ሲሆን፤ የገባበት ሰዓትም 2:04:24 ሆኖ ተመዝግቦለታል። ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረውና አስቀድሞ የአሸናፊነት ግምት አግኝቶ የነበረው አትሌት ሰይፉ ደግሞ በጥቂት ሰከንዶች ልዩነት ተቀድሞ ሁለተኛ በመሆን አጠናቋል። አትሌቱ የገባበት ሰዓትም 2:04:49 ነው።
በሴቶች በኩል ኬንያዊቷ ሩት ቺፕጌቲች አሸናፊ ስትሆን፤ ፈጣን በነበረው ሩጫ ከፍተኛ ልዩነት በመፍጠርም ነው ድሏን ያጣጣመችው። አትሌቷ ርቀቱን የሸፈነችበት 2:14:18 የሆነ ሰዓት ደግሞ ሁለተኛው የማራቶን ፈጣን ሰዓት በሚል ሊያዝላት ችሏል። አሜሪካዊቷ ኤምሊ ሲዝን እና ኬንያዊቷ ቪቪያን ኪፕላጋት ደግሞ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነዋል። ብርቱ ተፎካካሪዎች የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ሩቲ አጋ እና ዋጋነሽ መካሻም አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ለመፈጸም ችለዋል።
በፖርቹጋል በሚካሄደውና በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የሊዝበን ማራቶንም በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የተደረገ ውድድር ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ውጤታማ ሊሆኑ ችለዋል። ዘንድሮ ለ36ኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ውድድር ላይ በወንዶች በኩል የአምናው አሸናፊና የቦታው የክብረወሰን ባለቤት አንዷለም በላይ በድጋሚ ሰዓቱን በማሻሻል አሸናፊ ሆኗል። አትሌቱ ባለፈው ዓመት ድሉ 2:05:52 የሆነ ሰዓት ያስመዘገበ ሲሆን፤ በዘንድሮው ውድድርም ከአምናው በደቂቃዎች የፈጠነ ሰዓት በመሮጥ የሃገሩን ልጆች አስከትሎ ገብቷል። ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን የፈፀመው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሃፍቱ ተክሉ 02:06:33 የሆነ ሰዓት ሲያስመዘግብ፤ ብርሃን ነበበው ደግሞ 02:07:04 በሆነ ሰዓት የሶስተኝነቱን ደረጃ ይዟል።
በዚህ ውድድር በሴቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሻለ የአሸናፊነት ታሪክ ያላቸው ሲሆን፤ ዘንድሮ ግን በኬንያዊቷ አትሌት ቦርነስ ጄፕኪሩይ የበላይነት ሊጠናቀቅ ችሏል። ይሁንና ከአንድ እስከ አስር ባለው ደረጃ ከጥቂት የውጪ አትሌቶች በቀር በኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች የተያዙ ናቸው። ከአንድ ደቂቃ መዘግየት በኋላ የርቀቱን የመጨረሻ መስመር በሁለተኝነት የረገጠችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሶሮሜ ነጋሽ ስትሆን፤ ብዙነሽ ጌታቸው፣ ኡርጌ ዲሮ፣ ፎዚያ ጀማል እና ዘርፌ ልመንህ እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ተቆጣጥረዋል። ጸዳል ገብረጻዲቅ እና ጌጤ ጉታ ደግሞ ስምንተኛ እና አስረኛ ሆነዋል።
የ31ዓመት እድሜ ባለውና ከማራቶን ጎን ለጎን በሚካሄደው የሊዝበን ግማሽ ማራቶንም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤታማነታቸውን አሳይተዋል። አስደናቂ የሆነ ፉክክር በታየበት የወንዶቹ ውድድር አንደኛ እና ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቁት አትሌቶች በመካከላቸው የነበረው የሁለት ሰከንዶች ልዩነት ብቻ መሆኑ የስፖርት ቤተሰቡን አስገርሟል። በጎዳና ላይ ሩጫዎች እምብዛም ባልተለመደውና ተያይዘው በገቡበት በዚህ ውድድር አሸናፊ የሆነው ኬንያዊው ቻርለስ ኪፕኩሩይ ሲሆን፤ በሁለት ሰከንዶች ብቻ የተቀደመው ኢትዮጵያዊው ድንቃለን አየለ ደግሞ ሁለተኛ ለመሆን ተገዷል። ዩጋንዳዊው አይዛክ ኪቤት ደግሞ ሶስተኛው አትሌት ሆኗል።
ኢትዮጵያውያን የተሻለ የአሸናፊነት ታሪክ ባላቸው የሴቶች ግማሽ ማራቶን ውድድር እንደተለመደው በበላይነት ተጠናቋል። አሸናፊዋ አትሌትም እመቤት ንጉሴ ስትሆን የገባችበት ሰዓትም 1:09:35 ሆኖ ተመዝግቧል። ኬንያውያኑ ሉድዊና ቼፕንጌቲች እና ፌይዝ ኪሙታይ ደግሞ ኢትዮጵያዊቷን ተከትለው የገቡ አትሌቶች ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/ 2015 ዓ.ም