አደብ ያልገዛው የዶላር የጥቁር ገበያ ምንዛሪ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑ ግልጽ ነው። በጥቁር ገበያ የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ ከ100 ብር በላይ መውጣቱን እና በቀጣይም ልጓም ካልተደረገለት በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ጫና አስከፊ መሆኑን አንዳንድ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው። እስከ አሁን ሰዓት ድረስ ደግሞ በመደበኛው የምንዛሪ ገበያ አንድ ዶላር ከ 53 ብር በታች እየተመነዘረ ይገኛል ።
ትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ ከተሰኘ ድረ-ገጽ የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው ባለፉት 10 ዓመታት በባንኮች የዶላር ዋጋ በ28 ብር ገደማ ጨምሯል። 2003 ዓ.ም. ላይ በባንክ 1 የአሜሪካ ዶላር በ16 የኢትዮጵያ ብር ይመነዘር ነበር። እኤአ 2022 መደበኛው ምንዛሪ ወደ 47̂ ነጥብ 7 ብር እንደሚያመራ ብሎም በ 2023 ወደ 54 ነጥብ 1 ብር ከፍ እንደሚል ተንብዮ ነበር።
የኑሮ ውድነት፣ የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚው በዶላር መንቀሳቀስ (dollarization of domestic economy) እንዲሁም የድህነት መባባስ፣ የብር ዋጋ መውደቅ የአጭር ጊዜ ጫናዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይህ በጊዜ ካልተገታ ኢኮኖሚያዊ ጫናው እየሰፋ እንደሚሄድ የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በረጅም ጊዜ ኢኮኖሚው ሙሉ በሙሉ የመውደቅ ቀውስ (Full blown economic crisis) ሊጋረጥበት የሚችል ሲሆን ይህም ኢኮኖሚው ከተለያዩ አቅጣጫ ቀውሶች ሲገጥሙት የሚከሰት ይሆናል። የውጭ ንግድ፣ የገንዘብ ፖሊሲው፣ ምርት፣ የብድር አስተዳደር ብሎም በኢንቨስትመንት ላይ የሚያሳድረው ጫና የኢኮኖሚ ውድቀት (Full blown economic crisis) ሊያጋጥም የሚችልበት እድል የሚኖር መሆኑን መረጃዎቹ ያመለክታሉ።
በአሁኑ ጊዜ መደበኛ እና ጥቁር ገበያው መካከል ያለው ልዩነት ከእጥፍ በላይ ሆኗል። በመደበኛ ገበያውም ላይም ቢሆን ቀላል የማይባል ከፍተኛ ማሻቀብ ታይቶበታል። ታዲያ የዚህ ጥቁር ገበያ ምንዛሪ እንዲህ ልጓም እንዳጣ ፈረስ መናር ምክንያት ምንድነው? ይሄንን ለመቆጣጠር ምን ማድረግ አለበት? መፍትሔውስ ምንድነው? በማለት የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግረናል።
የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ እንደሚሉት፤ በሀገሪቱ ፍራንኮ ቫሉት መፍቀድ ሕገ ወጥ የጥቁር ገበያ ምንዛሪ እንዲባባስ አድርጎታል። የዶላር እጥረቱ ሀገርን ኢኮኖሚ ወጥሮ አላላውስ ባለበት በዚህ ወቅት ፍራንኮ ቫሉታ ዋጋ ያረጋጋል ብሎ ማሰብ የማይሆን መፍትሔ ነው።
ፍራንኮ ቫሉታ ከተፈቀደም መንግሥት የሚቆጣጠርበት መንገድ ማበጀት ነበረበት የሚሉት አንጋፋ የፋይናንስ ባለሙያ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው አይነት መርሕ ሀገሪቱን የባሰ ዝቅጠት ውስጥ ይከታል። ኢትዮጵያ ዘላቂና የማያቋርጥ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ያለው ነጋዴም ሆነ ዲያስፖራ የላትም። ያለውም ዲያስፖራም ቢሆን የውጭ ምንዛሪውን ተጠቅሞ ቤትና መኪና ለመግዛት ከመታተር ያለፈ አቅም የፈጠረ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ዜጋ፣ ዲያስፖራ ሆነ መንግሥት ዶላር የማቅረብ ፍላጎቱ እንጂ አቅማቸው ውስን እንደሆነ ይታወቃል።
ፍራንኮ ቫሉታን መፍቀድ፣ ዘለቄታ ባለው መንገድ የአቅርቦት ችግርን መዋቅራዊ በሆነ አካሄድ ለመፍታት የተሻለ አማራጭ መሆኑን እንደሚያምኑ የሚናገሩት አቶ እየሱስ ወርቅ ፍራንኮ ቫሉታን በመፍቀድ የአጭበርባሪ ነጋዴዎችን አቅም ማሳደግ ካልሆነ በስተቀር ለኢኮኖሚው ፋይዳ ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ልክ ያልሆነ አካሄድ መሆኑን ይናገራሉ።
ሌላው ኢኮኖሚው ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች መንግሥት ከውጭ ሀገራት በሚያገኛቸውን የምንዛሪ ፈሰሶች ላይ ጫና ይኖራቸዋል ። ግጭቶች ሲኖሩ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና ይዞት የሚመጣው ጥሬ ምንዛሪም አብሮ ቀሪ መሆኑን ያስረዳሉ።
አንዳንድ ነጋዴዎች ኤክስፖርት የሚያደርጉትን እቃ ከሀገር ውስጥ በርካሽ በመግዛትና በወደቀ ዋጋ ውጭ በመሸጥ እዛ ያገኙትን እቃ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በከፍተኛ ብር በመሸጥ ያልተገባ ትርፍ ሲያጋብሱ መመልከት የተለመደ ነው። ይህ ተግባር ደግሞ የብርን በፍጥነት ዋጋ ማጣት ያባብሳል።
የብር በፍጥነት ዋጋ ማጣት ከውጭ የሚገኙ ብድሮችን የመክፈል አቅምን ያዳክማል። ይህ የመንግሥትም ሆነ የግል ተበዳሪዎችን ኪሳራ ውስጥ ሊከት ይችላል። ብድሩንም ሆነ ወለዱን በውጭ ምንዛሪ የመቀየር ኃላፊነት የሚወድቅበት መንግሥትም ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይወድቃል ሲሉ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ያስረዳሉ።
ፍራንኮ ቫሉታ ከተፈቀደ በኋላ በብዛት አዳዲስ ሞዴል ውድ ዋጋ ያላቸው መኪኖች መዲናይቱን ማጥለቅለቁን መመልከት ይቻላል። በዚህም እጅግ መሠረታዊ ለሆኑ ፍላጎቶች ተብሎ የተፈቀደው ፍራንኮ ቫሉታ ባልተገባ መንገድ እየተጠቀሙት መሆኑን መረዳት አይከብድም።
የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑትን ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ተስፋ በበኩላቸው፤ የጥቁር ገበያ ዋጋ ማሻቀብ ዋነኛው ምክንያት በሀገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው። በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሀገራት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲኖር የዶላር ምንዛሪ ዋጋ ከፍ ይላል። ለምሳሌ በኬኒያ የአንድ ዶላር ዋጋ አርባ ሽልንግ የነበረ ሲሆን አሁን በመቶ ሽልንግ የኬኒያ ባንክ እየመነዘረ ይገኛል። ይህም የውጭ ምንዛሪ ሲንሳፈፍ ገበያው ራሱ የሚያምንበት ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው።
በሀገራችን ግን ሁልጊዜ ዋጋ የሚተምነው ብሔራዊ ባንክ ነው። በዚህም ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ መሆኑ ሲቀር ሰዎች ሌላ አማራጭ ይፈልጋሉ። ወደ ውጭ ሀገራት ለሕክምና፤ ለስብሰባ፤ ለሀይማኖታዊ ጉዞዎችና ሌሎች የግል ጉዳዮች ለመጓዝ የሚፈልጉ ሰዎች ባንክ ሄደው ገንዘብ ሲጠይቁ ከመቶ ዶላር የበለጠ ስለማያገኙ ጥቁር ገበያን አማራጭ ያደርጋሉ።
አሁን በሀገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከዳቦና ቆሎ መሸጫ ባላነሰ የአዲስ መኪና መሸጫዎች እንደ አሽን ፈልተዋል። ለምሳሌ በደንበል ወደ አፍሪካ ኅብረት የሚወስድ መንገድ ላይ አስራ አንድ የመኪና መሸጫዎችን መቁጠራቸውን የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ይህ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ አይታወቅም ይላሉ። እነዚህ አዳዲስ መኪኖች ታዲያ ወደ ሀገር የገቡበት የውጭ ምንዛሪ ከየት ይመጣል የሚለው ጥያቄ መጠየቅ ይገባዋል ባይ ናቸው።
በአጠቃላይ ሀገሪቱ ከ1 ነጥብ 5 እስከ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሚሆን ገንዘብ ሕገወጥ በሆነ የገንዘብ ዝውውር እንደምታጣ የኢኮኖሚ ባለሙያው ይናገራሉ። ይህም የሆነበት ምክንያት ለአብነት ማሌዢያ ከኢትዮጵያ ከብት ታስገባለች ፤ ነገር ግን አንዱም በሕጋዊ መንገድ ሄዶ አያውቅም። በበርበራ በኩል በሕገወጥ መንገድ ወርቅ ይወጣል፤ ቡና ይወጣል፤ እጣን ይወጣል፤ የከበሩ ድንጋዮችና ሌሎችም ይወጣሉ። ይህንን ደግሞ መቆጣጠር የተቻለ አይመስለኝም ይላሉ። ስለዚህ ሀገር ውስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ በብሔራዊ ባንክ በኩል ማስተካከል ካልተቻለ ጉዳዩ ወደ አስከፊ ደረጃ ከፍ ሊል እንደሚችል ስጋታቸውን ይጠቅሳሉ።
ብሔራዊ ባንክ ይሄንን ችግር የሚያስተካክልበት ብዙ መንገዶች እንዳሉም የኢኮኖሚ ባለሙያው ይጠቁማሉ። የዶላር ምንዛሪው ገበያው ቢተምነው ዲያስፖራው የሚልከው ገንዘብ በቀጥታ በሀገሪቱ ባንኮች በኩል ስለሚገባ በኔ ግምት ሀገሪቱ እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ታገኛለች ብዬ አስባለሁ። ገንዘቡ የሚላክላቸው ሰዎችም በርከት ያለ ብር ቢያገኙ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊጎዳ አይችልም።
የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ መሠረታዊ ፍለጎቶች አሉ። ሀገሪቱ አሁን እያከናወነችው ያለችውን ትላልቅ ፕሮጀክቶች ማቆም የሚችሉትን ለተወሰነ ጊዜ ገታ በማድረግ የሚቻል ከሆነ በቆዩ ለእነሱ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ያግዛል ብለዋል። የልማት እቅዱና የገንዘብ በጀትን በማጣጣም መሥራት ተገቢ መሆኑን ይገልጻሉ።
ሌላው መፍትሔ ያሉት የፋይናንስ ሥርዓቱን ማስተካከል ነው። የፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ ሁሉንም ነገር መንግሥትና ትውልደ ኢትዮጵያዊው መያዝ አለበት የሚል አለ። ይሄ ሀገሪቱን ወደ አልተገባ ሁኔታ ይከታታል። ሌላው ችግር በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ አለመኖር ነው። ካፒታል ገበያ እንዲቋቋም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ሰጥቷል። የውጭ ባንኮችም እንዲገቡ ውሳኔ ተላልፏል። የውጭ ባንኮች ሲመጡ የሀገር ባንኮችን ይገላል፤ ዘርፈውን ይሄዳሉ የሚባል ያልሆነ ውዥንብር አለ። ያ ትክክል አይደለም። የውጭ ባንኮች ካፒታል ይዘው ይመጣሉ፤ ቴክኖሎጂ ይዘው ይመጣሉ፤ የማኔጅመንት ሥርዓት ይዘው ይመጣሉ። የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ የሚያስተዳድረው የማኔጅመንት ሥርዓት ነው። የውጭ ባንኮች ከሙስና የፀዳ አሠራር አላቸው። ኢንተርናሽናል ባንኮች በመሆናቸው የተነሳ ስህተት ቢገኝባቸው ሙሉ ድርጅታቸውን ስለሚያበላሽ በሥርዓት ይሠራሉ።
በተጨማሪም የካፒታል ሥርዓት መዘርጋቱ ማንም ሰው ካለበት ሀገር ሆኖ ያለውን ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ አክሲዮን መግዛቱ የውጭ ምንዛሪ ለማስጋባት የላቀ አስተዋፅኦ አለው። ሰው ገንዘቡን ባንክ ከሚያስቀምጥ ይልቅ ካፒታል ገበያ ውስጥ አክሲዮን ቢገዛ ከወለድ የሚበልጥ ገቢ ያገኛል ማለት ነው።
አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ መንግሥት ይህንን ችግር ለመፍታት ወይም ለማቃለል የብርን በፍጥነት መዳከምን ጨምሮ በርካታ የአስተዳደር እርምጃዎችን መውሰድ አለበት ብለው ያምናሉ። በተጨማሪም ጥብቅ የሆነ የሞኒተሪ ፖሊሲን መተግበር ከመፍትሔዎቹ መካከል የጠቀሷቸው ናቸው። ዋናው ጉዳይ ግን የቁጥጥር ሥርዓትን መዘርጋት መሆኑን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ጉዳዩን አስመልክተው እንዳሉት፤ ጥቁር ገበያውን በሥርዓት ለመምራት እርምጃ መወሰድ ተጀምሯል። በእርምጃውም 391 የሚደርሱ ሕገ ወጥ የሐዋላ አገልግሎት ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው እንዲዘጋ ተደርጓል። ይህ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ብሔራዊ ባንኩ የግለሠቦቹን ስም ዝርዝር ለፍትሕ ሚኒስቴር በመላክ ክስ የመመሥረት ሂደት ተጀምሮባቸዋል። ይህም የቁጥጥር ሥርዓቱን የሚያጠናክረው መሆኑን አንስተዋል።
በሌላ በኩል በባንክ ቤቶች ውስጥ ያሉ የባንክ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በዚህ ሕገወጥ ተግባር ላይ የተሠማሩ አካላትም መኖራቸውን ተደርሶበታል፤ በእነዚህ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የቁጥጥር ሥርዓት መጀመሩን ገልፀዋል። ይሕን ሕገወጥ ድርጊት ለሚጠቁሙ ዜጎች የወሮታ አከፋፈል ሥርዓት ተዘጋጅቷል።
ከተፈቀደው በላይ በቤት ውስጥ የብር ክምች የሚያደርጉ፣ የሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን የሚሠሩና የሚያሠራጩ አካላት እንዲሁም በሕገ ወጥ መልኩ የሐዋላ አገልግሎት የሚሠጡ ወይም በጥቁር ገበያ ላይ የተሠማሩ አካላትን ለሚጠቁሙ ዜጎች ደህንነታቸውና ሚስጥራዊነታቸውን በጠበቀ መልኩ የሚሸልምና ወረታውን የሚከፍል አሠራር መኖሩንም ነው የጠቀሱት።
መንግስት በሀገሪቱ የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር የዘረጋውን የፍራንኮ ቫሉታ ፍቃድ እንደ መልካም እድል የተጠቀሙ ነጋዴዎች በሕገወጥ መንገድ ዶላር በመጠቀም ሸቀጦችን የማስገባት ተግባር እየዋሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአስመጪነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የባንክ ማስረጃ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያቀርቡ የሚደረግ ሲሆን ይህ የፍራንኮ ቫሉታን እድል ለሕገወጥ ድርጊት ይጠቀሙ የነበሩ ነጋዴዎችን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሚያደርግ መላ መሆኑን ነው ያብራሩት። በአጠቃላይ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የሁሉም ማኅበረሰብ የጋራ ርብርብን ይጠይቃልና መንግሥታዊ አካላትም፤ የንግዱ ማኅበረሰብም፤ ኅብረተሰቡም በተባበረ ክንድ በመተጋገዝ ነገን የተሻለ ለማድረግ መሥራት እንደሚገባቸው ሁሉም የዘርፉ ሙያተኞች ይናገራሉ።የፍራንኮ ቫሉታ አሠራርን መፈተሽ፤ የክትትልና የቁጥጥር ሥራችን ማካሄድ፣ ኮንትሮባንድን መከላከል ጥሩ የመፍትሔ አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/ 2015 ዓ.ም