በምርትና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ንረት ሲከሰት እና የኢኮኖሚ ጫና ሲፈጠር ሁለገብ የገበሬዎች የህብረት ሥራ ማህበራት (ዩኒየኖች) እና የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት በቅብብሎሽ የሚያከናውኗቸው ገበያን የማረጋጋት ሥራዎች፤ ለሸማቹ ማህበረሰብ ትልቅ የሆነ እፎይታን በመስጠት ይታወቃሉ። ማህበራቱ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ጫና ሲፈጠር የእሳት ማጥፋት ሥራ በመሥራት ብቻ ሳይወሰኑ፣ በአገር ደረጃ ድህነትን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ቁልፍ ከሆኑ የልማት ኃይሎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። በተለይም የገበሬዎች የህብረት ሥራ ማህበራት (ዩኒየኖች) ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ምርታማነት የሚውሉ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብአቶችን ተደራሽ በማድረግ በጊዜ፣ በጉልበትና በዋጋ አርሶአደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ። ዩኒየኖቹ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ እህል እራስን በመቻል ከድህነት ለመውጣትና ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ ክረምት ከበጋ በማምረት እንደአገር የተያዘውን አቅጣጫ ከግብ ለማድረስ ሚናቸው የጎላ ነው። እንዲህ ጉልህ የሆነውን ድርሻቸውን ለመወጣት የተሻለ የገንዘብ አቅም በመያዝ፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል በመመራት እንዲሁም በጠንካራ አደረጃጀት አቅማቸው አድጎ ከፍ ያለ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
የተቋቋሙበትን ዓላማ ለማሳካት፣ የአባላቶቻቸውን ጥቅም በማስጠበቅ፣ በኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ለመወጣት ጥረት የሚያደርጉ ጠንካራ ዩኒየኖች የመኖራቸውን ያህል፣በእርሻ ሥራ ወቅት ግብአትን በወቅቱና በተመጣጣኝ ዋጋ ባለማቅረብ፣ አርሶአደሩን ተጠቃሚ የማያደርግ የምርት ግዥ መፈጸም፣ ከተልእኮአቸው ውጭ ባልተገባ የንግድ ጥቅም ውስጥ ገብተዋል የሚባሉና ተያያዥ ጉዳዮች ቅሬታና ነቀፌታ የሚቀርብባቸው ዩኒየኖች መኖራቸው አይዘነጋም። እኩል ተልእኮን የሚያሳኩ ዩኒየኖችን መፍጠር ካልተቻለ ደግሞ የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ተልእኮ ለመወጣትም ሆነ ውጤት ማስመዝገብ አይቻልም።በጥንካሬ የሚነሱትን እንዲሁም በድክመት የሚሰጡ አስተያየቶችን መሠረት በማድረግ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር (ዩኒየን) ውስጥ ቀደም ሲል የዘር ብዜት ባለሙያ፣ አሁን ደግሞ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ሆነው በማገልገል ላይ ከሚገኙት አቶ ታደሰ ፈቃደ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፤ በቅድሚያ ወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር (ዩኒየን) እያከና ወናቸው ሥላለው ተግባር ቢነግሩን
አቶ ታደሰ፤ ዩኒየኑ ወደ 140 የሚሆኑ መሠረታዊ ማህበሮችን በአንድ ያሰባሰበ ሲሆን፣ ወደ 200ሺ የሚሆኑ አርሶ አደር አባላት ይዞ በተለያየ አገልግሎት ተደራሽ ለመሆን እየሰራ ይገኛል። ማህበሩ የእርሻ ግብአቶችን በማሰራጨት ተደራሽ ከሚያደርጋቸው ግብአቶች መካከል በግዥ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የአፈር ማዳበሪያ በሰሜንሸዋ ዞን ውስጥ ለሚገኙ 12 ወረዳዎች ያሰራጫል። ፀረ አረም፣ ፀረ ፈንገስ፣ ፀረ ተባይ ኬሚካሎችንም በአንድ ማእከል የአገልግሎት መስጫ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል። የምርምር ውጤቶች የሆኑ ከኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽንና ከሌሎችም የምርምር ተቋማት የተገኙ የስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስና ሌሎች ሰብሎች ምርጥ ዘሮችን በማዳረስ ተልእኮውን ይወጣል። ከ ማሳ መረጣ ጀምሮ የአርሶአደሩን የግብርና ግብአቶች አጠቃቀም በተመለከተም ዩኒየኑ ባሉት ባለሙያዎች የድጋፍና ክትትል ሥራ ይሰራል።
አርሶአደሩ ጊዜን በሚወስድና አድካሚ በሆነ ሁኔታ በበሬ አርሶ በግል ኑሮውም ሆነ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የኢኮኖሚ ለውጥ የሚያመጣ ውጤት እያስገኘ ባለመሆኑ፣ ጊዜውንና ጉልበቱን በሚቆጥብ ምርታማነቱን ለመጨመር የሚረዳውን ዘመናዊ የግብርና ዘዴ እንዲከተል ዩኒየኑ በሚያደርገው እገዛ የበሬ ጉልበትን የሚተካ የእርሻ ትራክተር አገልግሎት በማቅረብ አባላቱን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል። ከማህበሩ አባላት ውጭ ላሉ የአካባቢው አርሶአደሮችም ለማቅረብም አቅሙ ስላለው ጥያቄ ለሚያቀርቡ አገልግሎቱን ይሰጣል።
የግብርናውን ሥራ ከሚያግዙ የአገልግሎት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ማህበሩ በ2014/2015 የምርት ዘመን ካጋጠሙት ችግሮች መካከል የአፈር ማዳበሪያ እጥረት አንዱ ነበር። እጥረቱ አገራዊ ቢሆንም፣ ዩኒየኑ በተቻለው መጠን ለማዳረስ ጥረት አድርጓል።
አዲስ ዘመን፤ እንዲህ እንደናንተ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተቋቁመው አባላቶቻቸውንና ከማህበራቸው ውጭ ያሉትንም በማገዝ ሥራ እየሰሩ እንደሆነና ውጤታማነታቸውንም ይገል ጻሉ። ነገር ግን አንዳንድ አባላቶች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቅሬታ ያሰማሉ።ተጠቃሚነታቸው ከሚጠብቁት በታች እንደሆነና ዩኒየኖቹ በአርሶ አደሩ ስም ይነግዳሉ ወይም ይጠቀማሉ የሚሉ ሀሳቦች በአንዳንዶች ይነሳል። በቅሬታና አስተያየቶቹ ላይ ሀሳብዎን ቢያካፍሉን።
አቶ ታደሰ፤ ቅሬታና አስተያየቱ የለም ብዬ አልከራከርም። ከመሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት እስከታችኛው ተጠቃሚው አርሶአደር ድረስ የውይይት መድረኮች ተመቻችተው ሀሳቦች ይሰጣሉ። ዩኒየኑም ሀሳቡን በግብአትነት ይጠቀማል። ‹‹ዩኒየኑ አትራፊ ሆኗል።እኛንም በዋጋ እየጎዳን ነው። በአግባቡ ተደራሽ እየሆነ አይደለም›› የሚሉ ቅሬታዎች አሉ። አንዳንዶቹ ቅሬታዎች እውነታነት ያላቸው ቢሆኑም ከእውነታ ውጭም የሆኑም አሉ። እውነታነት የሌለው ቅሬታ ብለን ከምንጠቅሳቸው መካከል ለአብነት በ2014/2015 የምርት ዘመን እንደአገር የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት በማጋጠሙ አርሶአደሩ በሚፈልገው ልክ አልደረሰውም። ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ጠይቆ ከመረዳት ይልቅ ግብአቱ ለነጋዴ እንደተሸጠ አድርጎ የመውሰድ ነገር ተፈጥሯል። ያልተጣራ ነገር ይዞ መናገር አሉባልታ ነው የሚሆነው። ማዳበሪያ አቅርቦት ላይም ቢሆን፣ የዞን ግብርና መምሪያን ጨምሮ ከተለያየ አካላት በተውጣጣ የተዋቀረ ኮሚቴ አማካኝነት ነው የስርጭት ሥራው የሚከናወነው። የዩኒየኑ ድርሻ ማዳበሪውን ማድረስ በመሆኑ ለነጋዴ ተላልፎ የሚሰጥበት እድል የለም። ሆኖም ግን በአንዳንድ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከአሰራር ጋር በተያያዘ ክፍተቶች እንደሚኖሩ እንገነዘባለን። ክፍተቶችን ማስቀረት የሚቻለው ጥብቅ የሆነ የአሰራር ሥርአት ዘርግቶ በክትትል መሥራት ሲቻል ነው። የኛም ዩኒየን ትክክል የሆኑትንም ያልሆኑትንም ሀሳቦች በግብአትነት ወስዶ በጥብቅ የአሰራር ሥርአት ቅሬታዎችን መፍታትና አሰራሮችን መፈተሽ እንደሚገባ ይሰማኛል።
አዲስ ዘመን፤ በመኸሩ የግብርና ሥራ በዩኒየኑ በኩል የተደረጉት ድጋፎችና የግብአት አቅርቦቶች ላይ የነበረውን ስኬትና ተግዳሮት ያስታውሱን
አቶ ታደሰ፤ በመኸሩ የግብ ርና ሥራ ከግብአት አቅርቦት ጋር ተያይዞ እንደተግዳሮት ከሚ ነሳው አንዱ የአፈርማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ነው። ለዚህም በመፍትሄነት አስቀምጠን የተንቀሳቀስነው የግብርና ዘር ፉን ከሚመሩት በየደረጃው ካሉ ተቋማትና ባለሙያዎች እንዲሁም ከአርሶአደሩ ጋር በመሆን ማን ምን አይነት መሬት ላይ ምን ይዘራል? ትኩረት የሚያስፈልገው የትኛው የሰብል አይነት ነው? በሚል የማቻቻል ሥራ ነው የተከናወነው። ቀደም ሲል በነበረው አሰራር አንድ አርሶአደር አስር ኩንታልና ከዚያም በላይ እንደፍላጎቱ የሚያገኝበት የነበረውን አሰራር በመፈተሽና ያለውን የመሬት መጠን በመለየት እያንዳንዱ አርሶአደርም የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታውን ወይንም ደብተሩን ይዞ እንዲቀርብ በማድረግ በተቻለ መጠን ፍትሐዊነትን ለማስፈን ጥረት ተደርጓል። በተለይ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በኦሮሚያ ክልል አዳማ ላይ ካለው መጋዘን 26ሺ ኩንታል ማዳበሪያ፣ ዩሪያና ዳፕ በዩኒየኑ የማከፋፈል ሥራ ተከናውኗል።
አገር ውስጥ የማይገኙ ከውጭ አገር በግዥ የሚገቡ አንዳንድ ኬሚካሎችም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የአቅርቦት ማነስ አጋጥሟል። በዚህ በኩል የነበረውንም ክፍተት ለመሙላት በተለያየ መንገድ መግዛት ያልተቻለውን ኬሚካል መተካት የሚችል ሌላ ግብአት በማካካስ እጥረቱን መፍታት ተችሏል። የአረም ማጥፊያ ኬሚካሎች የአቅርቦት እጥረትንም ለመፍታት የማረሙ ሥራ በሰው ጉልበት እንዲከናወን በማድረግ አማራጭ ተወስዷል። ዩኒየኑ በቂ የሆነ የግብርና ባለሙያ ባይኖረውም በተቻለው ሁሉ ከአርሶአደሩ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመሥራት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፤ አርሶአደሩ በተለያየ ድጋፍ ታግዞ ምርታማነቱ ከጨመረ በኋላ ደግሞ ያመረተውን ሸጦ ኑሮውን መለወጥ ይፈልጋል።ይሁን እንጂ ለዩኒየኖች የሚያስረክብብት ዋጋ በሚ ፈልገው ልክ ዋጋ እያገኘበት አለመሆኑንና ተጠቃሚዎቹ ዩኒየኖቹ እንደሆኑ አንዳንዶች ቅሬታ ያነሳሉ። ምርቱን ለዩኒየኖች ከመሸጥ ቀጥታ ከሸማቹ ጋር መገበያየትን ምርጫው የሚያደርጉም አሉ።እዚህ ላይስ ምን ይላሉ? ከእናንተ ዩኒየን በመነሳት ምላሽ ይስጡበት
አቶ ታደሰ፤ እንዲህ ያሉ አስተያየቶችም ለዩኒየናችን ደርሷል። ዩኒየኖች በርካሽ ገዝተው በውድ ዋጋ ይሸጣሉ ለሚባለው የሀገሪቱን ወቅታዊ የገበያ ሁኔታ ካለመገንዘብ የተሰጠ አስተያየት ነው ብዬ እወስዳለሁ።ገበያው የተረጋጋ አይደለም።በየጊዜው ይለዋወጣል። ከአርሶአደሩ በኪሎ በ36 ብር ስንዴ ገዝተን ቀናት ሳይቆጠር 40 ብርና ከዚያ በላይ ዋጋ ጨምሮ ይገኛል። ወቅታዊ ገበያን መሠረት አድርጎ ግብይቱ ይፈጸማል።አርሶአደሩ በሚሸጥበት ወቅት ያለው ዋጋና ከሸጠ በኋላ ባለው ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት ነው ቅሬታ የሚያስነሳው። ዩኒየኖች የተለያዩ ወጭዎች ስላሉባቸው ይህን ታሳቢ ያደረገ ሽያጭ ነው የሚከናወነው። ነገሮችን ባለመረዳትና ባለመገንዘብ ዩኒየኖችን ትቶ እንደማንኛውም ነጋዴ ለመገበያየት የሚደረግ ጥረት መኖሩን እናውቃለን።የዩኒየኖችንና አርሶአደሮችን ግንኙነት ለመለያየት በትንሽ የትርፍ ልዩነት ሚዛን ይዘው በመሄድ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችም አሉ። ችግሩን ለመቅረፍም ከከተማ ንግድና ኢኮኖሚ ቢሮ ጋር በመሆን ነጋዴው ከተመደበለት የመገበያያ ውጭ እንዳይንቀሳቀስና ህገወጥነት እንዲቀር ዩኒየኑ ተንቀሳቅሷል። ዩኒየኖች በኃላፊነት እንደሚሰሩም መገንዘብ ያስፈልጋል። ነጋዴው ዋጋ በጨመረ ቁጥር ዩኒየኖች እርሱን ተከትለው ዋጋ አይጨምሩም። የዩኒየኖች ዓላማ ገበያው እንዳይረበሽ ማድረግ ነው። ሌላው መዘንጋት የሌለበት ማህበራት ትርፋማ ሲሆኑ አባላቶችም ተጠቃሚ የሆናሉ።የሚገኘው ትርፍ ለአባላት ይከፋፈላል። ይህን የተረዱ የዩኒየናችን አባላት አሁንም ምርቶቻቸውን ለመሰረቱት ዩኒየን በመሸጥ ማህበሩ እንዲያድግና የትርፍ ተጠቃሚ ለመሆንም የበኩላቸውን እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፤ በ2014/2015 የምርት ዘመን ዩኒየኑ ከአርሶአደሩ በግዥ ምን ያህል ምርት ለመሰብሰብ አቅዷል? የምርት ዘመኑን ምርታማነትስ እንዴት ገመገማችሁት?
አቶ ታደሰ፤ አጠቃላይ በሰሜን ሸዋ ዞን ሊገኝ የሚችለውን የምርት መጠን ለማወቅ የሚያስችል ነገር የለንም። ያም ሆኖ ግን በግምትና ካለፉ ተሞክሮዎች በመውሰድ ነው እቅድ የሚሰራው። በ2013/2014 የምርት ዘመን 80ሺ ኩንታል የተለያየ ሰብል ለመግዛት ነበር እቅዳችን። ነገር ግን በተለያየ ምክንያት አላሳካንም። ይሁን እንጂ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን በማስተካከል እንዲሁም በቅሬታ የሸሸ የማህበር አባል ካለም ችግሩን በመፈተሽ ማስተካከያዎችን በማድረግ ምርቱን ለዩኒየኑ የሚሸጠውን ለመጨመር ጥረቶች እየተደረጉ በመሆናቸው ከመኸሩ የምርት ዘመን የምንገዛውን ከፍ በማድረግ ወደ 150ሺ ኩንታል በመግዛት ለሸማቹና ለተለያዩ ተቋማት ለማቅረብ ነው ያቀድነው።
አዲስ ዘመን፤ ዩኒየኑ አቅሙን በመገንባት አባላቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረቶቹ ምን ይመስላሉ?
አቶ ታደሰ፤ ዩኒየኑ ለአርሶአደሩ የሚቀርቡ ግብአቶችን የሚያከማችበት የራሱ የሆነ መጋዘን ስለሌለው ለመጋዘን ኪራይ እስከ 90ሺ ብር በማው ጣት ነበር የሚያከማቸው። ወጭዎችን ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜም እያንዳንዳቸው 50ሺ ኩንታል የሚይዙ ሁለት መጋዘኖችን በማስገንባት ላይ ይገኛል። ዩኒየኑ በአባል ማህበራት በኩል ለአርሶአደሩ የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችን በማቅረብም በጊዜና በዋጋ ተጠቃሚ እንዲሆንም በመሥራት እያገዘ ይገኛል። የእንስሳት መኖም በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል።የዱቄት ፋብሪካም አቋቁሟል።
አዲስ ዘመን፤ ዩኒየኖች አርሶአደሩን በተለያየ መንገድ በማገዝና ተጠቃሚ እንዲሆን፣ ከዚያ ባለፈም በአገር ላይ የዋጋ አለመረጋጋት ሲከሰት ዋጋ በማረጋጋት ትልቅ ሚና አላቸው። ከዚህ አንጻር እርስዎ የሚመሩት የወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር (ዩኒየን) የተሳካ ሥራ ሰርቷል?
አቶ ታደሰ፤ በአሰራር ሥርአት፣ መሪዎች ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት፣ የዩኒየኑ ሠራተኞች በሚፈጥሩት ክፍተት፣ አባላቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ባሰበው ልክ ተንቀሳቅሷል የሚል እምነት የለኝም። ውስኑነቶች አሉ። እኛ በተለያየ ምክንያት ግብአቶችን ማቅረብ ባለመቻላችን የዩኒየኑ አባላት በከፍተኛ ዋጋ ከነጋዴ ገዝተው ለመጠቀም ተገደዋል። ይህ ሲባል ግን የዩኒየኖች መኖር እጅግ ጠቃሚ ነው። ከነክፍተቱም ቢሆን ጉልህ ሚና ተወጥተዋል። የወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር (ዩኒየን) ርዕይው ሰፊ ነው። የምግብ ማቀነባበሪያ (የምግብ ኮምፕሌክስ) እንዲሁም የትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለማቋቋም እቅድ አለው።
አዲስ ዘመን፤ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ታደሰ፤ እኔም አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም