ልጆች እንኳን አደረሳችሁ በሚል ልጀምር መሰለኝ። ምክንያቱም ትናንት መውሊድን ያከብሩ ብዙ ሙስሊም ልጆች ነበሩ። ልጆች ዛሬ ልነግራችሁ የምፈልገውም ጉዳይ ይህንኑ በሚመለከት ነው። ስለመውሊድ ከማውራታችን በፊት ግን ሳምንታችሁ እንዴት እንዳለፈ ልጠይቃችሁ? ምክንያቱም ባለፉት ሳምንታት ሁለት አበይት የአደባባይ በዓላትን አክብረናል። አንደኛው የመስቀል በዓል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የኢሬቻ በዓል ነው። እናም እሁድን ጨምሮ ደስ በሚል ሁኔታ እንዳሳለፋችሁ ይሰማኛል።
የአደባባይ በዓላቱ ሞቅ ደመቅ ብለው አልፈዋል። ለብዙዎቻችን መዝናናትን ብቻ ሳይሆን አብሮ መሆንን አሳይተውንም ተጠናቀዋል። በተለይም ከቤተሰብ ጋር በስፋት የተገናኘንባቸው ጊዜያት እንደነበሩም ግልጽ ነው። አሁን ደግሞ በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ የሚከበረው በዓል ታላንት በደስታ ተከብሯል። ይህም በዓል የመውሊድ በዓል ነው። እናም ስለበዓሉ ምንነት፣ አከባበርና ጠቀሜታው በዚህ አምዳችን ላይ እንዳስሳለን።
ልጆች መውሊድ ለምን እንደሚከበር ታውቃላችሁ? ሙስሊምም ባትሆኑ ብታውቁት መልካም ነው። ምክንያቱም በዓላት ለእያንዳንዳችን የሚሰጡን ነገር አላቸው። የመጀመሪያው የእርስ በእርስ መረዳዳትን ባህላችን እንድናደርገው ያለማምዱናል። ለሰዎች አጥብቀን እንድንደርስላቸው ያደርጉናል። ሰብሰብ ብለን የምንበላባቸውና የምንጠጣባቸው ጊዜያትም ስለሆኑ በመሰባሰባችን ውስጥ የማናውቃቸውን መልካም ባህሎች ያስተምሩናል። እናም ማወቁ ጠቃሚ ነው። ስለዚህም ስለምንነቱ ከሃይማኖት አንጻር ብቻ ሳይሆን ከዚያም ውጭ አይታችሁት መረዳትና ማወቅ አለባችሁ።
ወደ ጉዳዩ ስንገባ ‹‹ መውሊድ›› የሚለው ቃል ምንጩ አረብኛ ቋንቋ ነው። ትርጉሙ ደግሞ ‹‹ የመወለጃ ቦታ ወይም የመወለጃ እለት›› ማለት እንደሆነ ይነገራል። ወደ መንፈሳዊ ትርጓሜው ስንወስደው ደግሞ መውሊድ ማለት የነብዩ ሙሐመድ ልደት ነው። በሙስሊሞች ዘንድ በዓሉ የሚከበረውም ይህንን መሰረት አድርጎ ነው።
ልጆች ስለበዓሉ አከባበርና አጀማመር ሲነገር ሁለት አይነት ምልከታ አለው። የመጀመሪያው መውሊድ መከበር የጀመረው በራሳቸው በነብዩ ሙሐመድ አማካኝነት ነው የሚል ሲሆን፤ አከባበሩን በተመለከተ ደግሞ ነብዩ የተወለዱበት ቀን መከበር ያለበት በጾም ነው የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ እርሳቸው ካረፉ በኋላ መከበር ጀመረ የሚለው ሲሆን፤ ይህም መካ ወደሚገኘው የነብዩ ወደተወለዱበት ቤት ዚያራ (መንፈሳዊ ጉብኝት) በማድረግ ይከበራል ይባላል። ለመሆኑ እንደ ኢትዮጵያስ እንዴት ይከበራል ካላችሁ መልሱ ልዩ ልዩ ነው።
እንደምታውቁት ማንኛውም በዓል በልዩ ድምቀት ይከበራል። ስለዚህም መውሊድም በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ዘንድ ልዩ ክብር ተሰቶት በአደባባይ ተወጥቶ የሚከበር በዓል ነው። ይህ በዓል መከበር የጀመረው በ18ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአገራችንም በስፋት የማክበር ልምድ አለ። ቦታዎቹን ቀድመን ብናነሳ መነሻችን የሚሆነው የግለሰቡ ቤት ነው። ሁሉም መውሊድን ማክበር የሚጀምረው ከቤቱ ጀምሮ ነው። በመቀጠል መስጊድ በመሄድ ያከብሩታል።
ወደ ጊዜውን ስንገባ ደግሞ ነብዩ በተወለደበት ወር፤ በ12ኛው ቀን፤ ወይም በተወለዱበት ወር ውስጥ በተገኘው ሰኞ፣ ወይም በማንኛውም ወር ውስጥ በሚገኝ ሰኞ፤ ወይም በማንኛውም ወርና ቀን ይከበራል። ይህ በዓል ሁሉንም የሚያሳትፍ ሲሆን፤ አዛውንት ፣ ወጣት፣ ህጻናት፣ ሴት ወንድ፣ ከተሜ ባላገር አይባልበትም። ሁሉንም በእኩል ደረጃ የሚያሳትፍና ተደስቶ እንዲመለስ የሚደረግበት ነው። በዚህ በዓል ላይ በርካታ ክዋኔዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ትልቁን ቦታ የሚይዘው የሰደቃ ወይም የምጽዋት ጊዜ ሲሆን፤ ሕዝበ ሙስሊሙ የመስጠት ባህሉን የሚያዳብርበት ነው።
ሰዎች ባህላዊ ክዋኔያቸውን በአንድነት የሚከውኑበትም ነው። በዚህ ውስጥ ደግሞ አብሮ መብላት፣ አብሮ መጠጣትና መጫወት እንዲሁም ተሰብስቦ መደሰት ይፈጠራል። ስለዚህም ይህ በዓል ደስታን ለራስ መፍጠሪያም ነው። ሌላው ይህ በዓል በቁርአንና በመውሊድ ንባብ ለሰናዮች መልካሙ ነገር ይበሰርበታል። ለሕዝቡም መጥፎውንና የማይፈቀደውን ነገር ያስተምሩበታል።
ልጆች በዚህ ክብረ በዓል ወቅት ሌላው ሰፊውን ጊዜ የሚወስደው ክዋኔ የመንዙማ ጊዜ ሲሆን፤ መንዙማ የሕዝበ ሙስሊሙ መንፈሳዊና ምድራዊ ሕይወት የሚገለጽበት፣ ደግና ክፉው የሚነገርበት፣ ድጋፍና ተቃውሞ የሚንጸባረቅበት በአጠቃላይ ማህበራዊ፣ ኦኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ባህላዊ ሀሳቦች የሚንጸባረቁበት የቃል ግጥም ነውና በስፋት ይከወንበታል።
ልጆች የመውሊድ መከበር ለምን ያስፈልጋል? ካላችሁ ጥቂት ጥቅሞቹን ላውጋችሁ። የመጀመሪያው ሕዝበ ሙስሊሙ ተሰባስቦ መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ ባህሉን እንዲያዳብርና ስለእምነቱ ምንነት በሚገባ እንዲያውቅ ያደርገዋል። ሌላው ከማህበራዊ ግንኙነት ጋር ይያያዛል። ሕዝበ ሙስሊሙ እርስ በእርስ እንዲተሳሰብና ማህበራዊ ሁኔታው እንዲጠብቅ የሚያደርግበት በዓል ነው። በዓሉን ተመርኩዘው መሰባሰቦች ስለሚኖሩ የተጣሉ ይታረቁበታል፤ የተራራቁም ተቀራርበው ናፍቆታቸውን እንዲወጡ ይሆኑበታል።
ያለው የሌለውን የሚፈልግበት ወቅትም ነው። ምክንያቱም ባለሀብቱ ፈጣሪውን ፍለጋ በምጽዋዕት አማካኝነት ደሃው ጋር ይደርሳል። ሌላው የፈጠራ ችሎታ የሚለይበት በዓልም ነው። ለምሳሌ መንዙማ የሚያወጡት ሰዎች ችሎታቸውን ከቀን ወደቀን ያዳብሩበታል። የማይችሉም ቢሆኑ በሚሞክሩበት ወቅት አቅማቸውን እንዲያዩ ይሆኑበታል። የተዝናኖትና የፍስሃ አገልግሎት ማግኛ ቦታም ነው። ስለዚህ ልጆች ይህንን ሁሉ ጥቅም ያለው በዓል ልንጠብቀውና ልንከባከበው ይገባል። ልንጠቀምበትም እንዲሁ። በሉ ልጆች በሚቀጥለው ሳምንት በሌላ ጉዳይ እንገናኛለን። መልካም በዓል!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረመ 29/2015