አንድ የተደጋገመ ቀልድ እኔም ልድገመው (የፈጠራ ችግር እንዳለ ልብ እያላችሁ) ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ቃለ መጠይቅ ተደርጎለት ነው። ‹‹ጋሽ ስብሃት ግንቦት ሃያን እንዴት ታየዋለህ?›› ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹እንደ ሰኔ 20›› ብሎ መለሰ። ጠያቂው የጠበቀው ያው እንደተለመደው ‹‹ግንቦት ሃያ የብሄር ብሄረሰቦች መብት የተከበረበት፣ ኢትዮጵያ ከጭቆናና ከኋላቀርነት ተላቃ የበለጸገችበት›› ወይም ደግሞ ‹‹ግንቦት ሃያ አገሪቱን በብሄር የከፋፈለ፣ ጭቆናና አፈና የበዛበት…›› የሚል ነበር።
ጠያቂው እንደጠበቀው አልሆነለትም እንጂ! በነገራችን ላይ ጋሽ ስብሃት ነፃ ሰው ስለሆነ የፖለቲካ ትርጉም ባይሰጠውም ሰዎች ግን እየተጠቀሙበት ያለው ለፖለቲካ ትርጉም ነው። እሱ ምንም ትርጉም አይሰጠኝም ማለቱ ይሆናል። ሰዎች ግን እየተጠቀሙት ያለው ግንቦት ሃያን በመጥላትና በማጣጣል ነው። እንዲህ ነን እንግዲህ! ራሳችን መግለጽ ያቃተንን ነገር አጣመንም ቢሆን ሰው በገለጸው እንጠቀማለን። ጎበዝ እንግዲህ ለውጥ ተቀበል! ፖለቲካችን ተለውጧል።
ለምሳሌ ሰሞኑን መጋቢት 24 እየተከበረ ነው። ላለፉት 27 ዓመታት ደግሞ ግንቦት 20ን አክብረናል (ይሄኛውን ስንት ዓመት እንደምናከብረው ባይታወቅም)። ቆይ ግን የአገራችን ታሪክ 20 ምናምን ላይ ነው እንዴ የሚያርፈው? በዓለም ምንታወቅበት የዓድዋ ታሪክ የካቲት 23፣ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ከስደት የተመለሱበት የድል ቀን ሚያዚያ 27፣ ኢህአዴግ ደርግን አስወግዶ መግዛት የጀመረው ግንቦት 20፣ ኢህአዴግ ህገ መንግስቱ የጸደቀበት ነው ብሎ የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን የሚያከብረው ህዳር 29፣ ኢትዮጵያ የምትታወቅበት የዓባይ ወንዝ ሊገደብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ቀን መጋቢት 24፤ እነሆ ይሄው ቀን ታሪክ ይደረብብህ ሲለው ኢህአዴግ ሆየ እነሆ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መረጥኩላችሁ ያለበት መጋቢት 24።
አሁን ታሪክ ተቀየረ! የምን ግንቦት 20 ነው ደግሞ! በቃ ከዚያ በፊት የነበሩ ነገሮች ሁሉ መልካቸውን ቀየሩ። ለምሳሌ የህዳሴው ግድብ ከዚህ በፊት ይሰጠው የነበረውን ያህል ሽፋን አላገኘም። አሁን ነው እንግዲህ ከጋሽ ስብሃት ሀሳብ መውሰድ። እኔ ግን ታዋቂ ብሆንና ‹‹መጋቢት 24ን እንዴት ታየዋለህ?›› ተብየ ብጠየቅ ‹‹እንደ ሚያዚያ 24›› ብየ አልቀልድም፤ በቁም ነገር እንደ ‹‹እንደ ግንቦት 20›› ብየ ነበር የምመልሰው። በቃ ለእኔ ግንቦት 20 እና መጋቢት 24 ይመሳሰላሉ። እኔ እኮ ግርም የሚለኝ ነገር! ዋናው ኢህአዴግ ተቀምጦ ሰዎች የሚነታረኩት በሌሎች ሰዎች ነው። ለምሳሌ መድረኩ ላይ በሚገኙ ሰዎች፣ ለጉዳዩ ሽፋን በሚሰጡ መገናኛ ብዙኃን፣ አከባበሩን በሚቃወሙና በሚደግፉ ሰዎች… ነው ጭቅጭቁ። በቀዳማዊ ኢህአዴግ ዘመን እንደ ግንቦት ሃያ፣ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ባሉ መንግስታዊ ዝግጅቶች ላይ የሚገኝ አርቲስትም ሆነ የትኛውም ታዋቂ ሰው ምን ይባል እንደነበር ታውቃላችሁ። ከለውጡ በኋላም እነሆ አምሳለ ግንቦት 20 የሆነው መጋቢት 24 ገና በመጀመሪያው ዓመት ስለሌሎች ሰዎች ማከራከር ጀመረ። ኧረ ሰው ግን ምን ይሻለዋል? አሁንስ ማህበራዊ ሚዲያን እንደ ምንጭ ጠቅሶ ማውራት እያፈርኩ ነው። ለነገሩ ንቆ የሚተውም እኮ አልሆነም። መንግስት ራሱ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሚራገብ ነገር ብዙ ሀሳብ ቀያይሯል።
ግራ ገባን እኮ ጎበዝ! በአሁኑ ጊዜ በተለይም በከተማ ውስጥ ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ነው። ካፌ ብንገባ፣ ስብሰባ ብንገባ፣ የትኛውም ሰው የተሰባሰበበት ቦታ ብንሄድ የሚወራው ያው የማህበራዊ ሚዲያ ውጤት ነው። ስለዚህ ማህበራዊ ሕይወታችን ሆኗል ማለት ነው። ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 24 «ከመጋቢት እስከ መጋቢት» በሚል በተዘጋጀው የለውጥ መዘከሪያ ፕሮግራም ላይ ጋሽ ደበበ እሸቱ የመድረክ መሪ ነበር። ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ እና ገጣሚ ታገል ሰይፉ ደግሞ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል። እነዚህ ሦስቱ ሰዎች የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆነው ነበር።
ጋሽ ደበበ እሸቱና ታገል ሰይፉ ‹‹አሽቃበጡ›› የሚል ታርጋ ተሰጥቷቸዋል። ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ደግሞ ተመስግነዋል (ጀመረን እንግዲህ መንግስትን የሚተች ማድነቅ)። በነገራችን ላይ በቀዳማዊ ኢህአዴግ የሚደነቀው መንግስትን የሚሳደብ ነበር፤ በዳግማዊ ኢህአዴግ ግን በተቃራኒው መንግስትን ያመሰገነን ማድነቅ ጀምረን ነበር። ለማንኛውም ዶክተር በድሉ ዋቅጅራን እኔም አመስግኛቸዋለሁ። በቃ ልክ ልኩን መናገር የጀግና ተናጋሪ ባህሪ ነው። እንዲያው ባስበው ባስበው አልገባኝ ያለ ግን የታገል ሰይፉ ነው። መጀመሪያ ነገሩን የሰማሁት ካፌ ውስጥ ነው። ተንደርድሬ ቢሮ ገብቼ «ዩ ትዩብ» ከፈትኩና አየሁት። ግጥሙ ከርዕሱ ጀምሮ ስለፌስቡክ ነው።
በዚያ ግጥም ውስጥ መንግስትን የሚደግፍም ሆነ የሚነቅፍ ነገር አልታየኝም። የፌስቡክ ፀሐፊ ሁላ እስከ አፍንጫው ተሰድቧል፤ ለዚያውም «ደደብ፣ ደንቆሮ፣ መሃይም›› በሚሉ ከባባድ ቃላት። ታገል ከተወቀሰ በዚህ ነው መወቀስ ያለበት እንጂ በዚያ ግጥም ውስጥ ለመንግስት የሚያሽቃብጥ ነገር አልታየኝም (እስኪ እንግዲህ ደጋግሜ እሰማዋለሁ) የጋሽ ደቤ ነገር እንኳን ትንሽ ታስኬዳለች። ዶክተር አብይን ከመደገፍ ውጭ ምንም አይነት አማራጭ እንደሌለ እኮ ነው የተናገሩት። ዶክተር አብይን ምንም ነገር እንዳይነካቸው እያንዳንዳችን መጸለይ እንዳለብን መምከራቸው ግን ተመችቶኛል! ግን ግን ጸሎቱ ለሁሉም ሰዎች ይሁን! ጋሽ ደቤ በባህሪው ቀልደኛ ነው።
በዚያ ላይ ደግሞ መድረክ መሪ ሲኮን እንደዚሁ ነው የሚባል። መድረክ መሪ ብዙ ጊዜ ልብ ብላችሁ ከሆነ ያካብዳሉ፤ ያጋንናሉ። ምናልባት የታዳሚውን ቀልብ የያዝን እየመሰላቸውም ይሆናል። በዚያ ላይ ደግሞ አንድ ነገር እንመን። እዚያ የተገኘ ሰው በዚያ ጉዳይ የተስማማና ያመነ ነው የሚሆን። ጋሽ ደቤ መድረክ መሪ ሲሆን ይሄንን ነገር አምኖበት ነው ማለት ነው።
እስኪ አስቡት! ለዶክተር አብይ ምስጋና የተዘጋጀ መድረክ ላይ ምን ሊል ነበር ታዲያ? ምን ቢል ይደነቅ ነበር ብየ አሰብኩት። «ክቡራትና ክቡራን! አገራችን ከፍተኛ ብጥብጥ ላይ ናት፤ ስደትና መፈናቀል ተባብሶ ቀጥሏል። በተወለደበት አገር አገርህን ፈልግ ተብሎ በድንጋይ ተቀጥቅጧል… ይሄ ሁሉ የሆነው ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ነው» ብሎ ቢናገር ከመድረኩ ጋር አብሮ አይሄድም፤ ምክንያቱም መድረኩ የተዘጋጀው ለውጡን ለመዘከር (በጎ በጎውን መሆኑ ነው) እና ዶክተር አብይን ለማመስገን ነው። ለማንኛውም በሚቀጥሉት ዓመታት ከግንቦት 20 ጋር የሚኖረውን አንድነትና ልዩነት ለማየት ያብቃን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
ዋለልኝ አየለ