መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ተመርቷል። ዶሴው የሚናገረው ታሪክ ግን ዛሬም ድረስ አለ። የተወሳሰቡ ወንጀሎች ከተራቀቁ የምርመራ ሂደቶች ጋር ዶሴው ውስጥ ናቸው። በዚህ ዓምድ ታሪካቸውን ልንሰማ የፈቀድናቸውን ዶሴዎች እንዲናገሩ ገልጠናቸዋል። የእውነተኛ ባለታሪኮችን ስም ማህበራዊ ሓላፊነት ወስደን ለደህንነታቸው ሲባል ቀይረናቸዋል።
ገጠር እያለ የከተማን ህይወት ሲናፍቀው ኖሯል። ከእርሱ ከፍ ያሉ የመንደሩ ልጆች ከቀዬው ርቀው በጉልበታቸው ማደራቸውን ያውቃል። ጥቂት ቆይተው አገራቸው ሲገቡ ልብሳቸው አምሮ፣ አካላቸው ተውቦና ንግግራቸው ተለውጦ አይቷል። ይህን እውነት ደግሞ የገጠሩ ጉብል ሲያይና ሲሰማው አድጓል። ብዙዎቹ ዓመታትን ቆይተው ከሰፈሩ ሲመለሱ ወግና ጨዋታቸው ሁሉ የከተማው ድምቀት ነው። የኖሩበት ህይወት አገሬው ካለበት ኑሮ ይለያል። ለእርሱ ደግሞ ከኪሳቸው የሚመዙት ገንዘብና ከአንደበታቸው የሚያፈልቁት ጨዋታ ይማርከዋል። የልብሳቸው ጠረንና የአካላቸው ወዘና ያስገርመዋል። ሁሌም ለወላጆቻቸው የጎጆ ቀዳዳ መድረሳቸውን ሲያይ ደግሞ በእጅጉ ይደነቃል። የሚቸራቸውን ምርቃትና ምስጋና እያሰበም ራሱን በቦታቸው ይተካል። እንዲህ መሆኑ የወደፊት እቅዱን እያለመ ወደማያውቀው አገር እንዲሻገር ሰበብ ሆነው። ልጅነቱን ተሻግሮ ወጣትነትን ሲላበስ ተመስገን ሞላ በራስ ውሳኔ መመራትን አወቀ። የአገሩ ልጆች አዲስ አበባ ተሻግረው ኑሯቸውን ቀይረዋል። አብሮ አደግ ባልንጀሮቹም በየጊዜው መለወጣቸውን አሳይተውታል። እሱም ቢሆን ከዚህ የተለየ ህልም የለውም። መሀል ሸገር ገብቶ በጉልበቱ ማደርን ይሻል።
በሌሎች ያየውን ገንዘብ በራሱ እጆች መቁጠር ያምረዋል። ዓመት ሞልቶት አገሩ ሲገባ ሲናፍቀው የቆየውን ምስጋና መቀበል ምኞቱ ነው። ጉልበት ስሞ የሚያገኘው ምርቃት ለቀሪው ህይወቱ ስኬት እንዲሆን ይሻል። የእናት አባቱ ጸሎት ለመንገዱ መቅናት፣ ለእርምጃውም ብርታት ነው። እናም ተመስገን ይህን አስቦ ጓዙን ሸከፈ። አባይ በርሀን ተሻግሮ የጎጃም ምድርን ራቀ። የሰማውን በልቡ ይዞ መንገዱን ሲያቀና መድረሻው አዲስ አበባ ሸገር ላይ ሆነ። ከሞቀው ከደመቀው ገበያ መሀል መርካቶ ጥግ። በዚህ ስፍራ በርካታ የአገሩ ልጆች ከትመዋል። እነርሱ የቱንም ስራ አይንቁም። ጉልበት በሚጠይቀው ሁሉ ሮጠው ይደርሳሉ። ያገኙትን እየሰሩ፣ የተከፈላቸውን እየቆጠቡ ነገን ተስፋ ያደርጋሉ።
ከነሱ መሀል መጽሀፍና ሎተሪ አዟሪዎች፣ አዲስ ልብስና ልባሽ ሻጮች፣ ግንበኛና አናጺዎች፣ በርካቶች ናቸው። ባገር ልጅነት የሚግባቡ፣ በዝምድና የሚፈላለጉ፣ በችግር ግዜ የሚረዳዱም ጥቂቶች አይደሉም። አብዛኞቹ የሰው አገር ሰውነታቸው አንድ ያደርጋቸዋል። ሲገናኙ ችግራቸውን ይረሱታል። ሲተባበሩ አንድነታቸው ይደምቃል። ተመስገን ከሀገሩ ከወጣ ጀምሮ ወዳጅ ዘመድ አላጣም። የአጎቱን ልጅ ጨምሮ የቀረቡትን ሁሉ በልዩ ትህትና ይግባባል። አዲስ አበባ መስራት ለሚፈልጉ ዕድሏን አትነፍግም። ዝቅ ብለው ስራን ለሚያከብሩ ሁሉ በረከቷ ሰፊ ነው። ተመስገንም ሸገር ከገባ ወዲህ በርካቶችን አስተውሏል። ሁሉም ሲሮጥ በሚውልበት ሙያ ለጉሮሮው አጥቶ አያውቅም። የእንግድነት ጊዜው እንዳበቃ ወደስራ ገብቶ እንደ አቻዎቹ መሆን ፈለገ።
ይህ ደግሞ ከቀዬው ያራቀው፣ ከሀገሩ ያወጣው ዕቅዱ ነው። መለስ ቀለስ ባለባቸው ስፍራዎች በርካታ ስራዎችን ቃኝቷል። አንዱን ከሌላው ሲያማርጥ ግን ልቡ የፈቀደው ለውዝ እያዞሩ መነገድን ሆነ። ይህ ስራ ለአጎቱ ልጅ መተዳዳሪያው ከሆነ ቆይቷል። በዚህ ውሎ በሚያገኘው ገንዘብ ቤት ተካራይቶ ራሱን ያስተዳድራል። ከዕለት ገቢው ቀንሶም የአቅሙን ያህል ይቆጥባል። ተመስገን ከአትራፊዎች ገዝቶ መልሶ ለማትረፍ ትኩሱን ለውዝ ይዞ መዞር ለመደ። ከሌሎች እንዳየውም በወረቀት እየጠቀለለና ጥቂት ቆንጥሮለደንበኞች እያቀመሰ ገበያ ለመሳብ ሞከረ። ለዚህ ቅልጥፍናው መርካቶና አካባቢው አላሳፈሩትም። የቅጣው ጠጅ ቤት ደንበኞች ሁሌም በሩቅ ሲያዩት ይጠሩታል። የዘወትር ጫት ቃሚዎችም ተመስገንን ሳይፈልጉት አይውሉም። የመርካቶ ሰፈር ለተመስገን ምቹ ሆነለት። ከአገሩ ሲነሳ የነበረው ምኞትና ተስፋው በእርሱ ሮጦ ማደር እውን መሰለ።
ያገሩ ልጆች እንደሱ ባተሌዎች ናቸው። አንዳንዴ ደግሞ ጊዜ ሲኖርና እረፍት ሲገኝ መዝናናትን ለምደዋል። አልፎ አልፎ ከመጠጥ ቤት ጎራ እያሉ የጠርሙስ አንገት ይጨብጣሉ። ይህ አጋጣሚ አብሮነታቸውን አዳብሯል። በዚህ ሰአት የቤተሰብና የዘመድ ወግ ይደምቃል። የአገርቤቱ ትዝታም ይወሳል። የመርካቶና አካባቢው ሰው መልከ ብዙ ነው። ሰርቶ እንደሚያድረው፣ ሰርቆ የሚሮጠው ይበዛል። ሁሌም ግርግር የማያጣው ግዙፍ ገበያ ገዢን ከሻጭ ሲያገናኝ ይውላል። ብርቱዎች በሚተጉበት፣ ዳተኞቹም ጥግ ይዘው በሚቆዝሙበት ስፍራ ተፈልጎ የሚጠፋ የለም። ሁሉም በአቅምና ፍላጎቱ ያሻውን ሸምቶ ያየውን ጠይቆ ይመለሳል። መሀመድ ሁሴን የመርካቶን ገበያ ሳይረግጠው ውሎ አያድርም።
አንድም ይሁን በሌላ ሰበብ ይህ አካባቢ የመገናኛው ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። እሱ አዲስ አበባ ተወልዶ ቢያድግም የእኩዮቹን ዕድል አላገኘም። ዕድሜው ከፍ ሲል ጓደኞቹ ትምህርት ቤት ሲሄዱ አስተውሏል። ውለው ሲመለሱም ዓይኖቹ የእነሱን ዕድል እያሰቡ በምኞት ተንከራተዋል። ለወላጆቹ ግን ይህ ሁሉ ምናቸውም አልነበረም። የእነሱ ፍላጎት ሀይማኖቱን እንዲያጠብቅ እምነቱን እንዲያጠነክር ነው። በውሳኔያቸውም ቁርአን እንዲቀራና፣ ትምህርት ይሉትን እንዳይጠይቅ አስገደዱት። ምርጫ ያልነበረው ትንሹ መሀመድ ለትዕዛዛቸው «እሺ» ሲል ተገዛ። የትምህርት ምኞቱን ተሰናብቶም ቁርአን መቅራትን ብቻ አዘወተረ። በዕድሜው ከፍ ሲል ከእኩዮቹ ጋር የሚያውል ሰበብ አልነበረውም።
አብሮ አደጎቹ በትምህርት ልቀው፣ በዕውቀት ጎልብተው ነበር። የፊደልን ሀሁ… ያልቆጠረው መሀመድ በአቅሙ ሰርቶ ከማደር ሌላ ምርጫ አላገኘም። ጫማ እየጠረገ ራሱን መደጎም ሲጀምር በርከት ያሉ ደንበኞችን አፈራ። አሮጌውን መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ተመርቷል። ዶሴው የሚናገረው ታሪክ ግን ዛሬም ድረስ አለ። የተወሳሰቡ ወንጀሎች ከተራቀቁ የምርመራ ሂደቶች ጋር ዶሴው ውስጥ ናቸው። በዚህ ዓምድ ታሪካቸውን ልንሰማ የፈቀድናቸውን ዶሴዎች እንዲናገሩ ገልጠናቸዋል። የእውነተኛ ባለታሪኮችን ስም ማህበራዊ ሓላፊነት ወስደን ለደህንነታቸው ሲባል ቀይረናቸዋል። እየጠገነ የሊስትሮነት ወዙን መቆጠብ ሲለምድ እያደር አቅሙ በረታ። ይህኔ ስራ ለመቀየር አሰበ ። በአካባቢው የሚያያቸው አንዳንዶች ጥቅም ላይ የዋሉ ጫማዎችን ሲሸጡ ተመልክቷል። ይህ ስራ ከነችግሩም ቢሆን ለብዙዎች አትራፊና ተፈላጊ ነው። በተለይ መሸት ሲል መርጠው አማርጠው የሚወስዱ ገዢዎች ይበረክታሉ። መሀመድ ስራውን ሲገባበት እንዳሰበው ሆኖ አገኘው።
ሲያሳምር፣ ሲጠርገው የቆየውን ጫማ ዋጋ አውጥቶለት ተደራድሮ ሲሸጠው ሚዛኑ ወደ ትርፍ አደላ። በአሮጌ ጫማዎች ንግድ መዝለቅ ሲጀምር ብቸኝነቱን የምትጋራ አቻውን ፈለገ። ትዳር ይዞ ጎጆን ሲቀልስ ጎዶሎው የሞላ ህይወቱ የታደሰ መሰለው። ውሎ ሲያድር ግን «አጋሬ» ከሚላት ሚስቱ ጋር ፍቅር ነሳው። ሰላም ያጣው ጎጆም ዘወትር ክፉ ንግግርን ከጭቅጭቅ ያስተናግድ ያዘ። መሀመድ በንዝንዝና ንትርክ ብቻ አልተመለሰም። ለጠብ የሚጋብዘው ክፉ አመሉ እንዳሻው ዱላ ማንሳትን አስለመደው።
አንድ ቀን ሚስቱ ከልቧ አዝና አመረረች። በዚህ ብቻ ግን አልቆመችም። ስለደረሰባት ችግር ከፖሊስ ጣቢያ ደርሳ በማስረጃ አስመሰከረች። መሀመድ በሚስቱ ላይ ባደረሰው በደል በጥፋተኝነት ተያዘ። ጉዳዩ ተጣርቶ መፍትሄ እስኪያገኝም በህግ ጥላ ስር ሆኖ ለቀናት ታሰረ። ይህ አጋጣሚ የእስር ቤቱን ውሎ አዳር አስተዋወቀው። ከእስር ከተፈታ በኋላ መሀመድ ወደ ጫማው ንግድ ተመለሰ። የፈዘዘውን ቆዳ እየቀባ፣ ያረጀውን ጎን እየጠገነ ገበያውን ለማሸነፍ ተጣጣረ። ከደንቦች ጋር እየሮጠ፣ ጊዜና ቦታ እየመረጠ ቀናትን በስራ አሸነፈ። የጎዳናው ላይ ንግድ ለመሀመድ ስራ ብቻ አልሆነም። ዓይኖቹ አርቀው መማተርን አስተማሩት። በስፍራው የሚውሉ ሰዎችን ማንነት አሳወቁት ። ውሎው ነጥቀው ከሚሮጡት፣ ዳብሰው ከሚዘርፉት ጋር አዛመደው።
መኪና ከሚያጥቡት አውልቀው እስከሚሰወሩት አወዳጀው። አንድ አካል በማጉደል ወንጀል ተከሶ ማረሚያ ቤት ታስሮ ተፈታ ቀን ግን ፖሊስ እሱንም በመኪና ዕቃዎች ስርቆት ጠረጠረው። ጥርጣሬው በምህረት ብቻ አልታለፈም። «ይገባሀል» ያለውን አስወስኖ በእስር አውሎ አከረመው። መሀመድ በሌላ ጊዜም በፍርድ ቤቶች ደጃፍ ተመላለሰ። የሌባ ተቀባይ በመሆንናጥር 11 ቀን 2003 ዓ.ም ዕለተ- ጥምቀት በደማቅ ድባብ ተጀምሯል። በዚህ ቀን ታቦታቱን ሸኝተው በጥምቀተ ባህሩ ያደሩ በርክተዋል። አዋቂ ከወጣት በሚታደምበት አውደ ዓመት በሀገር ልብስ ደምቀው፤ በዝነጣ የተዋቡ ሁሉ ለእይታ ይማርካሉ። ውሏቸውን በጭፈራና ሆታ አሳልፈው ምሽቱን ለመዝናናት የቀጠሩም በየመጠጥ ቤቱ ታድመዋል።
ቀኑን ምክንያት ያደረገ ባህላዊ ሙዚቃ በየስፍራው ደምቆ ይሰማል። ተመስገንና ጓደኞቹ ጥምቀትን በመዝናናት ሊያሳልፉ ተገናኝተዋል። ምሽቱ ቢገፋም ለጨዋታ የመረጡት ይህንን ጊዜ ነው። ጥምቀት ለእነሱ ልዩ ትዝታ አለው። የአገር ቤቱን ባህልና ወግ ያስታውሱበታል። የልጅነታቸውን ትዝታ ይመዙበታል። በዕለቱም የሆነው ይኸው ነበር። የጥምቀትን በአል በቢራ ጨዋታ ማጣጣም። ቀኑን በተለየ ድምቀት ማዋዛት። ሰአቱ እየገፋ፣ምሽቱ እየነጎደ ነው። አሁንም ግን ያላበው ቢራ ይወርዳል፤ ቀዝቃዛው ድራፍት ይቀዳል። ጣራ የነካው ሙዚቃም ያለማቋረጥ ይጮሀል። በሞቅታ የሚደንሱና ወገባቸውን ይዘው የሚውረገረጉ በዝተዋል። እኩለ ለሊቱ እንደተጋመሰ ተመስገን መፍዘዝና መዳከም ታየበት። ይህን ያስተዋሉ ባልንጀሮቹ ምነው? ሲሉ ጠየቁት። ድካም እንደተሰማውና ቤቱ ሄዶ ማረፍ እንደሚፈልግ ነገራቸው። አብሮት ያመሸው ያጎቱ ልጅ እየለመነ ሊያግባባው ሞከረ።
ተመስገን ግን መሄድ እንደሚፈልግ ተናግሮ ህመም ቢጤ እንደተሰማው አስረዳ። ባልንጀሮቹ በእሱ መሄድ ባይስማሙም «ቤቴ የምሰራው አለ» ማለቱ ይበልጥ አሳመናቸው። ሁሉንም ተሰናብቶ እንደወጣ የአጎቱ ልጅ ከኋላው ሮጦ ደረሰበት። ወደ ቤት ለመድረስ የሰፈራቸውን አቅጣጫ ይዘው ተራመዱ። ጥቂት ቆይቶ ሌሎቹም ከመጠጥ ቤቱ ለቀው ወጡ። ይህኔ ከምሽቱ ሰባት ሰአት ሆኖ ነበር። አሁንም የመርካቶና አካባቢው ጎዳና በግርግር ደምቋል። በአሉን ሰበብ አድርገው ደጅ ያመሹ አንዳንዶች በስካር መንፈስ እየተንገዳገዱ ነው። አልፎ አልፎ ከየመዝናኛው የሚሰማው ሙዚቃ ምሽቱን ቀን አስመስሎታል። የጥምቀት በአል ድባብ በድምቀቱ ቀጥሏል። በሌላ አቅጣጫ መሀመድና ጓደኞቹ በአንድ ግሮሰሪ ታድመዋል።
እነሱም መጠጡን የጀመሩት ገና በጊዜ ነው። ምሽቱ ገፍቶ ሌቱ ቢጋመስም የተጨነቁ አይመስሉም። እየተገባበዙ፣ ሂሳብ እየከፈሉ፣ መልሰው እያዘዙ ግለዋል። ሰአቱ እየገፋ ሲሄድ ከነበሩት ጥቂቶቹ ወደ ቤት መሄዱ ከበዳቸው። እናም ለመፍትሄው ባመጡት መላ ተስማምተው ከመጠጥ ቤቱ ለቀው ወጡ። ጉዞ እንደጀመሩ መሀመድ ለማደሪያ ያሰበውን አንድ ስፍራ ጠቆመ። በአካባቢው ባለ ግሮሰሪ ጓደኛው ይገኛል። እሱን ጨምሮ ባልንጀሮቹን ይዞ ቢሄድ በእንግድነቱ እንደማያሳፍረው አውቋል። እንደተባለው ሆኖ ሁሉም ወደሰውዬው መኖሪያ አቀኑ። ከስፍራው ደርሰውም በሩን በዝግታ አንኳኩ። በዕንቅልፍ የተሸነፈው ሰው በድንጋጤ በሩን ከፍቶ ወጣ። አመጣጣቸው ገብቶታል። ድርጊታቸው አልተመቸውም።
ባለግሮሰሪው በስካር ውስጥ ያሉትን ገላምጦ በደጅ አሰናብቶ ሸኛቸው። መሀመድን ግን ወደቤቱ እንዲገባ ጋበዘው። በሩ የተዘጋባቸው የምሽት እንግዶች ባደረገው ቢናደዱበት ለጠብ ተጋበዙ። ነገሩ በግልግል አብቅቶ ወደመንገዱ ሲመለሱ ከለሊቱ ስምንት ሰአት ሆኖ ነበር። ጥቂት ቆይቶ መሀመድ ሲጋራ በመግዛት ሰበብ ወደ ውጭ መውጣት ፈለገ ። መርካቶ ቅጣው ጠጅ ቤት አካባቢ ግርግሩ ደምቋል። መሀመድ ከቆመበት ስፍራ ሆኖ በአይኖቹ አማተረ። የግርግሩ ምክንያት አለመግባባት የፈጠረው ድብድብ መሆኑ ገባው። እሱ በርቀትም ቢሆን ጓደኞቹን ለይቷል። ከደቂቃዎች በፊት አብረውት የነበሩ ባልንጀሮቹ ከጠቡ ታድመው የድብድቡ ተዋናይ ሆነዋል። ይህን ሲያውቅ የሚገዛውን ሲጋራ ትቶ እየሮጠ ተቀላቀላቸው።አስቀድሞ ወደ ቤቱ የገባው ተመስገን ጓደኞቹ ከሌሎች ጋር መጣላታቸውን ቢሰማ ተደናግጦ ወጣ። ከድብድቡ መሀል የአጎቱ ልጅ መኖሩን አውቋል። ወዲያው ጠቡ ተባብሶ ሳይጋጋል ለማስቆም ሞከረ። እየለመነና እየተቆጣ ጭምር ከመሀል ገብቶ ግልግሉን ያዘ። ጠበኞቹ የመሀመድና የተመስገን ጓደኞች ናቸው። መሀመድ ሞቅታው አለቀቀውም። ንዴት ይዞታል። ጓደኞቹ በሌሎች እየተደበደቡ መሆኑን አምኗል። በስፍራው እንደደረሰ ከተመስገን ጋር ተፋጠጡ። ገና እንዳየው የእሱና የጓደኞቹ ወገን አለመሆኑን አወቀ። ተመስገን ገላጋይ እንጂ የጠቡ አካል አይደለም። መሀመድ ይህ ሁሉ አልታየውም። በዚህ ስፍራ ስላገኘው ብቻ አብሽቆታል። ገላጋዩ አሁንም መሀል እንደገባ ነው። መሀመድ ከወዲያ ወዲህ የሚለው ወጣት ላይ እንዳፈጠጠ በንዴት ቀረበው። በዚህ መሀል ከተመስገን የአጎት ልጅ ጋር ተያዩ። መሀመድ ለሌላ ጠብ እንደጋለ ቡጢውን ጨብጦ ተጠጋው። ተመስገን የሚሆነውን ባስተዋለ ጊዜ ፊቱን መልሶ ለመገላገል ከመሀል ገባ። መሀመድ አጥብቆ የጨበጠውን ቡጢ አልመለሰውም።
ጠንከር አድርጎ በተመስገን አንገት ላይ አሳረፈው። ክፉኛ የተመታው ገላጋይ እየተንገዳገደ የኋሊት ተዘረጋ። አወዳደቁን አይተው የደነገጡ ጠቡን ጋብ አድርገው ወደእሱ ከበቡ። ተመስገን በጀርባው ከወደቀበት አልተነሳም። ዳግመኛም ትንፋሹ አልተሰማም። ይህን ያስተዋለው መሀመድ በድንጋጤ ተዋጠ። ከአካባቢውም በፍጥነት ሮጦ አመለጠ። ጠበኞቹ ሲለያዩ ሁኔታዎች ተቀየሩ። የተመስገንን መሞት ያረጋገጡ ፈጥነው ለፖሊስ አሳወቁ።
የፖሊስ ምርመራ
በዕለተ ጥምቀት ከእኩለለሊት በኋላ ፖሊስ የተፈጸመውን ሰምቶ በስፍራው ደረሰ። የሟቹን አስከሬን በአግባቡ መርምሮም ወደ ሆስፒታል አደረሰ። በምሽቱ ጠብ ተሳትፈዋል የተባሉ በቁጥጥር ስር ውለው በጥብቅ ተመረመሩ። በአካባቢው የነበሩ እማኞችም ያዩ የሰሙትን ቀርበው መሰከሩ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ዋነኛው ተፈላጊ መሀመድ ሁሴን አልተያዘም። ምሽቱን ከመታየቱ በቀርም ስለእሱ ሰማን የሚል አልተገኘም። በፖሊስ የመዝገብ ቁጥር 457/2004 የተከፈተ ው ፋይል በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተፈላጊ ስለሆነው ግለሰብ መረጃዎችን ይመዘግባል። ተጠርጣሪው በምሽቱ ከአካባቢው አምልጦ ርቋል ከመባሉ በቀር የተገኘ ፍንጭ አልነበረም። ፖሊስ የሟችን አስከሬን ፎቶግራፍ ካስነሳ በኋላ የሆስፒታል የህክምና ማስረጃውን ተቀበለ። ሀያ ሶስት ዓመት ዕድሜ የነበረው ሟች ተመስገን ሞላ አንገቱ ላይ በደረሰበት ከባድ ምት ምክንያት ህይወቱን አጥቷል። በግንባሩና በአንገቱ ጡንቻ ላይም መጠነኛ የደም መፍሰስ ተስተውሏል።
መሀመድ የዛን ዕለት ምሽት የፈጸመውን ባወቀ ጊዜ በሩጫ ወደ ቤቱ ገሰገሰ። ለቀናትም ራሱን ደብቆ በመሸማቀቅ ቆየ። ውሎ ሲያድር ግን ያደረገው ሁሉ ሰላም ይነሰው ያዘ። በስካር ግፊት የፈፀመውን ድብደባና የተጎጂውን መጨረሻ ለማወቅ ሰዎችን እየላከ በዘዴ አሰለለ። ጥቂት ቆይቶም እውነታውን ሰማው። የሆነውን ባወቀ ጊዜ መሀመድ አያቶቹ ወደሚገኙበት ገጠር ለመሄድ ጓዙን ሸከፈ። ቆይታው ግን እምብዛም አልዘለቀም። ተመልሶ አዲስ አበባ እንደገባ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ። አሁን ፖሊስ ያደረጀውን መዝገብ በበቂ መረጃዎች አጠናክሯል። ተጠርጣሪውን በአቃቤህግ ክስ አስመስርቶ ለፍርድ ውሳኔ የሚያበቃውን ማስረጃም ሰንዷል። በዋና ሳጂን ያሬድ አለማየሁ የተያዘው ምርመራ ስራውን አጠናቋል።
የሰዎች ምስክርነት፣ የህክምና ማስረጃዎች፣ የተጠርጣሪው የኋላ ታሪክና ሌሎችም ክሱን ለመመስረት በቂ ሆነው ተገኝተዋል።
ውሳኔ
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት አንደኛ የወንጀል ችሎት ሆን ብሎ ሰው በመግደል ወንጀል የተከሰሰውን ተጠርጣሪ ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቶታል። ፍርድ ቤቱ ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎትም ለተከሳሹ ያስተምራል፣ ለሌሎችም ያስጠነቅቃል ያለውን የአስር ዓመት ጽኑ እስራትን አሳልፏል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
መልካምስራ አፈወርቅ