አዲስ አበባ፦ በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ በተካሄደው ለውጥ ተቋማቱ ኢትዮጵያዊ ቅርፅ እንዲኖራቸው መደረጉ ተገለፀ። በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ የሚካሄዱ ለውጦችን በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው በመከላከያ ሚኒስቴር፣ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በኢንፎርሜሽንና የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በተካሄደው ሪፎርም የተመዘገቡ ውጤቶችን ዘርዝረው አስቀምጠዋል።
በዚህም ተቋማቱ ከየዕለት ተግባራቶቻቸው ባሻገር በህዝቡ ዘንድ የነበራቸውን ስም ለመቀየር ከፍተኛ ሥራ እንደተሠራ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በተካሄደው ሪፎርም እነዚህ ተቋማት የአመራር ችግር ሲነሳባቸው የነበረ በመሆኑ ለውጡን ሊሸከሙ የሚችሉ አመራሮች ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ ተሠርቷል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በአመራር ደረጃ በተቋማቱ የነበረውን የብሄር ስብጥር በማስተካከል ኢትዮጵያዊ ቅርፅ እንዲኖራቸው መደረጉንም፤ እንዲሁም ከለውጡ በፊት በአመራርነት የነበሩ እና የአቅም ክፍተት የነበረባቸው በደረጃቸው እንዲሠሩ መደረጉን በመግልፅ በህግ መጠየቅ ያለባቸውም በህግ እንዲጠየቁ መደረጉ፤ በሁለተኛ ደረጃ በተቋማቱ ለውጡን ተከትሎ እንዲመጣ የተደረገው የአመለካከት ለውጥ መሆኑተነግሯል።
በዚህም የፖለቲካ ወገንተኝነት ሲታይባቸው የነበሩ ተቋማት ገለልተኛና ነፃ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነታቸው እንዲሻሻል ሰፊ ሥራ እንደተሠራም ነው የጠቆሙት። እነዚህን ተቋማት ህብረተሰቡ በጥርጣሬ ሲመለከታቸው እንደነበረ የገለፁት አማካሪ ሚኒስትሩ፤ ይህም እንዲስተካከልና ተቀባይነት እንዲኖራቸው የህዝብ ግንኙነት ሥራ ተሠርቷል ብሏል። በዚህ ለውጥ ሌላኛው የተሠራው ሥራ የአሰራር ሥራ ለውጥ መሆኑን በመግለፅ ለዚህም የእስራኤል፣ አሜሪካ እና ሩሲያ ልምዶች ተወስደዋል።
ይህንንም ተከትሎ በግልፀኝነትና ተጠያቂነት፣ ከግዳጅ፣ አዋጅ የማሻሻል እና በኦፕሬሽናል ሥራዎችና አፈፃፀሞች ለውጥ ማምጣት እንደተቻለም አብራርተዋል። በእነዚህ በፀጥታና ደህንነት ተቋማት የመጣው ሌላኛው ለውጥ የአደረጃጀት ሲሆን፤ በአደረጃጀት ለውጡም ከነበሩት አደረጃጀቶች በተጨማሪ የባህር፣ የስፔስ እና የሳይበር አደረጃጀቶች በአዲስ መልኩ እንዲቋቋሙ መደረጉን አስታውቀዋል።
በተጨማሪ የሠራዊቱ አሰፋፈር ላይ በተካሄደው ለውጥ በአራት አቅጣጫዎች ተመጣጣኝ የሠራዊት አሰፋፈር እንዲኖር ተደርጓል። የብሄራዊ ደህንነትና መረጃ ኤጄንሲ ለውጡን ተከትሎ በአራት ክላስተሮች እንዲቋቋም ተደርጓል። ከዚህ ባለፈ በኤጀንሲው የኢኮኖሚ ደህንነት ዋና መምሪያ፣ የህግ ዳይሬክቶሬት እና የህገ ወጥ የጦር መሳሪያን ለመከላከል ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት የተቋቋመ ሲሆን፤ በእነዚህ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት መካከል የነበረውን በቅንጅት የመሥራት ችግር ለመቅረፍ በጋራና በቅንጅት እንዲሠሩ የሚያስችል ባህል እንዲዳብር መደረጉምን ተናግረዋል።
የክልል የፀጥታ ተቋማትን በተመለከተ በጋራ እየተሠራ መሆኑን ያብራሩ ሲሆን፤ የፌዴራል የፀጥታ አካላት ከክልሎች ፈቃድ ውጪ እንዳይገቡ እየተደረገ ነው። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝና ከክልሎች ጥያቄ ሲቀርብ ብቻ የፌዴራል የፀጥታ አካላት እንደሚገቡ እና ድጋፍ እንደሚደረግ በመግለጫው ተመልክቷል።
በሌላ በኩል በሀገሪቱ በዋነኝነት ያለው ስጋት ምንድን ነው? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የብሄር ፖለቲካው መሆኑን ያብራሩት አማካሪ ሚኒስትሩ ለዚህም በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በማሳያነትም በአሁን ወቅት የግል ግጭቶችም ወደ ብሄር እየተወሰዱ የተለያዩ የፀጥታ ስጋቶች እየተፈጠሩ መሆኑን በመጥቀስ፤ ለዚህም ልዩነቶች ማጥበብ እና መግባባትን መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
(ዘገባው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ነው)