አፍሪካ በእግር ኳስ ትልቅ አቅም ያላት አህጉር ብትሆንም እንደ ሌሎቹ አህጉራት ትልቅ ደረጃ መድረስ አልቻለችም። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ይቀመጣሉ። ለአፍሪካ እግር ኳስ እንቅፋት ብለው ባለሙያዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሚጠቅሱት ምክንያት አንዱ በትክክለኛው እድሜ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊና ወጣት ተጫዋቾች በበቂ ሁኔታ አለማፍራት ነው። በተለይም የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ በአፍሪካ የተለያዩ ውድድሮች የተለመደና መፍትሔ ያልተገኘለት መሆኑ የአህጉሪቱን እግር ኳስ እድገት እየጎተተው እንደሚገኝ የብዙዎች እምነት ነው። በተግባርም ይታያል። ካፍ በታዳጊና ወጣቶች በሚያካሂዳቸው ውድድሮች ይህን የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ ለመቆጣጠር የተለያዩ የእድሜ መመርመሪያ ቴክኖሎጂዎችን ሲጠቀም ቢስተዋልም ችግሩን ማስቀረት ግን አልቻለም። በዚህም አስደናቂ ተሰጥኦ ይዘው ወደፊት ትልቅ ደረጃ የመድረስ ተስፋ ያላቸው ታዳጊዎች በእድሜ የበላዮቻቸው ተውጠው ሕልማቸው እየጨለመ ይገኛል። ይህ ችግር እግር ኳሳቸው ዳዴ እያለ በሚገኝ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ብቻም ሳይሆን የተሻለ ደረጃ ላይ በሚገኙ የአፍሪካ አገራት ጭምር በስፋት መስተዋሉ የአህጉሪቱ እግር ኳስ ላይ ተስፋ እንዳይጣል ያደርጋል።
የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳኒ ጆርዳን፣ በአንድ ወቅት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ የአፍሪካን እግር ኳስ ወደኋላ እየጎተተው እንደሚገኝ ተናግረዋል። የአህጉሪቱን እግር ኳስ ከሌሎች አህጉራት ጋር ተፎካካሪ ሆኖ እንዲወጣ ከተፈለገም አሰልጣኞች የእድሜ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንዳለባቸው ሲጠቁሙ ነበር።
አፍሪካ ፊፋ በታዳጊና ወጣቶች መካከል የሚያካሂዳቸውን ሁሉንም ውድድሮች ማለት ይቻላል አሸንፋለች። አፍሪካ ኦሊምፒክን ጨምሮ፣ ከ17ና20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ውድድሮችን አሸንፋ አሳይታለች። ይሁን እንጂ በዋናውና በአዋቂዎቹ የዓለም ዋንጫ ከግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚነት የዘለለ ታሪክ የላትም። ይህም የሆነው አፍሪካ በታዳጊና ወጣቶች ውድድር ላይ ከእድሜ በላይ ተጫዋቾችን በማሰለፏ ነው ብለው የሚያምኑ ባለሙያዎች አሉ። በታዳጊ ውድድሮች አዋቂዎች ይጫወቱና ስኬታማ ይሆናሉ። ከዚያ ወደ አዋቂዎች ውድድር ሲሸጋገሩ አቅምና ጉልበታቸውን ጨርሰው በትክክለኛ እድሜ የብቃታቸው ጥግ ላይ ከሚገኙ የሌሎች አህጉራት ተጫዋቾች ጋር መፎካከር ይሳናቸዋል።
ኢትዮጵያ እያስተናገደች በምትገኘው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ(ሴካፋ) ከ17 አመት በታች ውድድር ላይ በተለያዩ አገራት ተጫዋቾች ላይ እየተስተዋለ የሚገኘው የእድሜ ማጭበርበር ችግርም ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው። ውድድሩ ከመጀመሩ አስቀድሞ የእድሜ ምርመራ ሲደረግ ሱዳንና ጅቡቲ የMRI ምርመራ ማለፍ አለመቻላቸውን ተከትሎ ከውድድሩ ተሰናብተው የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብሩ እንደ አዲስ ሊከናወን ተገዷል። ሁለቱ አገራት በርካታ ተጫዋቾቻቸው ከተቀመጠው እድሜ በላይ ሆነው በመገኘታቸው ከውድድሩ ተሰናብተዋል። በውድድሩ እየተካፈሉ የሚገኙትም ቢሆኑ ሙሉ በሙሉ ይሄ ችግር የለብንም ብለው በድፍረት መናገር አይችሉም።
ይህን የእድሜ ችግር በቅርቡ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ኪንሻሳ ላይ በተካሄደው የፓን አፍሪካ የትምህርት ቤቶች ውድድር ላይም በስፋት ተስተውሏል።
የአንድ ሃገር የወደፊት እግር ኳስ ስኬት ያለው በትምህርት ቤቶች በሚገኙ ታዳጊዎች ላይ መሆኑን ባለሙያዎች ሁሌም ይናገራሉ። ከእድሜ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ፊት ለፊት አውጥቶ በመነጋገር መፍትሔ ማበጀት እንደሚያስፈልግ ያምናሉ። ለዚህም አሰልጣኞች ችግሩን በቅርበት ተከታትለው እንዲቀርፉ የአሰለጣጠን መንገዶችን ማስተካከል አስፈላጊ መሆኑን ይታመናል። እግር ኳሳቸው ባደገ እንደ አውሮፓ ባሉ ሃገራት አንድ የታዳጊ አሰልጣኝ ለሃያ ተጫዋቾች ነው የሚመደበው፣ እንደ አፍሪካ ባሉ አገራት ግን ብዙ ጊዜ አንድ አሰልጣኝ ሁለት መቶ ታዳጊዎችን ሊያሰለጥን የሚችልበት ሁኔታ መኖሩ ችግሩን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው ዶክተር ዳኒ በሰጡት ቃለምልልስ ለመጠቆም ሞክረዋል።
እግር ኳስ ትልቅ የገቢ ምንጭ እየሆነ በመጣበት በዚህ ወቅት በአፍሪካ ከአሰልጣኞች በተጨማሪ የተጫዋች ወኪሎች በአቋራጭ ጥቅም ለማግኘት በታዳጊ ውድድሮች አዋቂዎችን ማበረታታቸው ችግሩን ውስብስብ እንዳደረገው ሁሉም የሚያውቀው ሃቅ ነው። ለዚህም ተጫዋቾች የተለያየ ሁለት እድሜ ይለጠፍባቸዋል። በርካቶቹ የአውሮፓ ክለቦችም ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎችን ለመመልመል በዚህ እንደሚቸገሩም ይታወቃል።
“እድሜ ማጭበርበር የአፍሪካን እግር ኳስ መግደል ነው” የሚሉት የግብጽ እግር ኳስ ማኅበር የሚዲያ ኦፊሰር ሜድሃት ሻላቢ እድሜ ማጭበርበርን በአፍሪካ እግር ኳስ እንደ ካንሰር አድርገው ይገልጹታል። ይህ መጥፎ ልማድ የአፍሪካን እግር ኳስ እያጠፋው ነው የሚሉት ባለሙያ እድሜ የሚጭበረበር ከሆነ በተለያዩ ደረጃዎች የሚካሄዱ የታዳጊና ወጣት ውድድሮች ፋይዳ ምኑ ላይ ነው? ብለው ይጠይቃሉ።
የእድሜ ማጭበርበር ችግሮችን ለመቅረፍ ፊፋ እኤአ በ2009 ከ17 አመት በታች የዓለም ዋንጫ ጀምሮ ማግኔቲክ ሪሶናንስ ኢሜጂንግ(ኤም አር አይ) የተባለውን ቴክኖሎጂ በተለያዩ የወጣት ውድድሮች ላይ ለመጠቀም መወሰኑ ይታወቃል። ይህ ቴክኖሎጂ እስከ 17 ዓመት ድረስ ያሉ ታዳጊዎችን ትክክለኛ እድሜ ለመለየት 99 በመቶ ስኬታማ ነው ቢባልም ከተጠቀሰው እድሜ በኋላ ለመለየት ሲቸገር ተስተውሏል። በኢትዮጵያም ቴክኖሎጂው ታላቅን ታናሽ፣ ታናሽን ታላቅ አድርጎ የለየበት አጋጣሚ እንደነበር አይዘነጋም። ይህም ቴክኖሎጂው ላይ ያለውን እምነት እየሸረሸረ እንደ ፊፋ ያሉ የእግር ኳስ ተቋማት ለችግሩ መፍትሄ ሌሎች አማራጮችን መፈለግ እንደሚገባቸው ምክረ ሃሳብ የሚሰጡ ሰዎች እንዲበረክቱ አድርጓል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2015