-ለመቐለ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት 229 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፀድቋል፤
-የምርጫ አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን አዋጅ ከብዙ ክርከር በኋላ አፀድቋል፤
አዲስ አበባ፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 4ኛ መደበኛ የሥራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባ 33 ቢሊዮን 986 ሚሊዮን ተጨማሪ በጀት አፀደቀ፡፡
የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለምክር ቤቱ እንደገለፁት፤ በ2011 በጀት ዓመት ካፀደቀው ጠቅላላ የወጪ በጀት 346ነጥብ9 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለመጠባበቂያ ተይዞ የነበረው 7ነጥብ2 ቢሊዮን ብር ባለፉት ሰባት ወራት ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲሁም 2ነጥብ2 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለድርቅና የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም ውሏል፡፡
የተለያዩ መስሪያ ቤቶች አስቸኳይ ስራዎችን ለማከናወን የተያዘው 3ነጥብ2 ቢሊዮን ብር በጀት ዝውውር በመደረጉ በአሁኑ ወቅት ለመጠባበቂያ በጀት በአገሪቱ ከደረሰው ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ለመከላከል አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የማያስችል ነው። ወደ አገር ውስጥ የገባው ስንዴ ለመክፈልም ሆነ በቀጣይ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍና ለማቋቋምና ሌሎች ድንገተኛ ወጪዎችን ለመሸፈንና ተጨማሪ በጀት መጠባበቂያ መያዝ አስፈላጊ ሆኗል፡፡
በተጨማሪም በካፒታል በጀት ሥራዎች ተሠርተው ክፍያቸው ያልተፈጸሙ 6ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክቶች ክፍያ ለመፈፀምና የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት የመንግሥት ድርሻ የሆነውን 240 ሚሊዮን ብር ለመክፈል የበጀቱ አስፈላጊነት ተገልጿል፡፡ ምክር ቤቱ በሌላኛው አጀንዳው የመቐለ ከተማን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለማቃለል ከቻይና ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ የተገኘውን 229 ሚሊዮን 784ሺ582 የአሜሪካን ዶላር ብድር አፅድቋል፡፡
ምክር ቤቱ የምርጫ ቦርድን እንደገና ለማቋቋም በረቀቀው አዋጅ ላይም፤ በረቂቅ አዋጁ አንቀፅ 6 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ የቦርድ አባላት ስብስብ ብቃትና ሥነ ምግባር እንደተጠበቀ ሆኖ ‹‹በተቻለ መጠን›› ብሄርና ፆታን ያማከለ አድርጎ መልምሎ ማቅረብ ተገቢ ስለሆነ በሚለው ንዑስ ቁጥር ላይ ‹‹በተቻለ መጠን›› የሚለው ሐረግ ይካተት ወይስ አይካተት በሚለው ላይ የምክር ቤቱን አባላት ለሁለት ተከፍለው ተከራክረዋል፡፡
‹በተቻለ መጠን›› የሚለው ሐረግ መካተቱ የብሄር ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን መብት የሚጋፋና ህገ መንግሥቱን የሚጣረስ በመሆኑ ‹‹ብሄርና ጾታን›› ያማከለ መሆን አለበት በሚል ይቀመጥ ብለው በአንድ ወገን ተከራክረዋል፡፡ በሌላ ወገን በተቻለ መጠን የሚለው ቃል መኖሩ የብሄር ብሄረሰቦችን መብትእንደማይጋፋ፤ አምስት አባላት ባሉት የሥራ አመራር ቦርድ ውስጥ ዕጩዎች ከተመሳሳይ ብሄር ቢመጡም እንኳ ምክር ቤቱ ካላመነበት ያለማፅደቅ መብት አለው፤ ቀደም ሲል የፀደቁ አዋጆችም ከዚህ የተለዩ አልነበሩም። የሚሉና ሌሎች መከራከሪያ ሃሳቦችን አንስተዋል፡፡ በዚህም የድምፅ ቆጠራ ለማካሄድ የተገደደ ሲሆን፤ ‹‹በተቻለ መጠን›› የሚለው ሐረግ ሳይቀየር ጥቅም ላይ ይዋል የሚለው ሃሳብ 136 ድጋፍ፣ በ83 ተቃውሞና በሦስት ተዐቅቦ ፀድቋል፡፡
በተመሳሳይ «የምርጫ ቦርድ በሥራ አመራርነት ያገለገሉ አባላት ኃላፊዎች የሥልጣን ዘመናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ በማናቸውም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ መሾም የለባቸውም» በሚለው ሐሳብ ላይ ከፍተኛ ክርክር የተደረገ ሲሆን፤ በመጨረሻ ሃሳቡ አግባብ መሆኑ ታምኖበት በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል፡፡ የዜግነት ጉዳይም ሰፊ ክርክር የተደረገበት ሲሆን፤ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሚገባ እንዲመረምረው ታሳቢ በማድረግ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ 1133/2011 ሆኖ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር