
አዲስ አበባ፡- የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎት መጀመር ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን የብልጽግና ጉዟችን ሞተር አድርገን የመንቀሳቀሳችን ማሳያ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢንተርኔት አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ፣ የኩባንያው አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎት መጀመር ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን የብልጽግና ጉዞአችን ሞተር አድርገን የመንቀሳቀሳችን ማሳያ ነው ብለዋል።
በ(+2517) ኮድ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ኩባንያው፤ ቀደም ሲል በድሬዳዋ፣ ባህርዳር፣ አወዳይ፣ ጎንደር ፣ሞጆ፣ ሐረር፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱና ደብረ ብርሃን ከተሞች የኔትወርክ ሙከራ አገልግሎቱን መጀመሩ ይታወሳል።
ኩባንያው በአዲስ አበባ እና በአዳማ በ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የዳታ ማዕከል የገነባ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት በሁለቱም ከተሞች ሁለት ተጨማሪ የዳታ ማዕከል እንደሚገነባ አስታውቋል። በቀጣይ አሥር ዓመታት 8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በማፍሰስም የዘርፉን ተጠቃሚነት የማሻሻል ዕቅድ እንዳለውም አመልክቷል።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው፤ የሳፋሪ ኮም በኢትዮጵያ አገልግሎት መጀመሩ ቀጠናዊ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ ለኩባንያው በሞባይል የገንዘብ ዝውውር እንዲያከናውን እንደተፈቀደ ይፋ የሆነ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሳፋሪኮም የሞባይል ገንዘብ ዝውውር እንዲያደርግ በመፍቀዱ የተሰማቸውን ደስታ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፥ “የኬንያ ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ይህን እንዳስፈጽም የቤት ስራ ሰጥቶኝ ነበር፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን አገልግሎት በመፍቀዱ አመሰግናለሁ” ብለዋል።
ሳፋሪኮም በኬንያ በኤም ፔሳ የገንዘብ አገልግሎት ያገኘውን ስኬት በኢትዮጵያ ለመድገም እንደሚሰራም አስታውቋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከዚህ ቀደም የቴሌ ብር አገልግሎት በማስጀመር ሚሊዮኖችን ተጠቃሚ ማድረጉ ይታወሳል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2015