አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ባሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ በቅርቡ በተከናወነ የዳሰሳ ጥናት 46 ተቋማት ላይ ግድፈት መታየቱ ተገለጸ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም በእነዚህ ተቋማት ያለው አሰራር ተጠቃሚነትን ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትን ማዕከል አድርጎ መከናወን እንዳለበት አሳስቧል። የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱአለም አድማሴ ትናንት ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በተካሄደ ውይይት ወቅት እንደተናገሩት፤ በ174 ተቋማት በተደረገው የዳሰሳ ጥናት 46 ተቋማት ግድፈት ታይቶባቸዋል።
በዚህም መሰረት 27 ያለፈቃድና እውቅና የሚ ሠሩ፣ 4 ባልተሰጣቸው መርሃ ግብር የሚያስተምሩ፣ 6 እውቅናቸውን ያላሳደሱ፣ 3 ሳያሳውቁ ህንጻ የቀየሩ፣ 3 ባልተሰጠ ስያሜ ሲጠቀሙ የተገኙ ሲሆን፤ 3 ተቋማት ደግሞ መረጃ ላለመስጠት ተቋም ዘግተው ተሰውረዋል። ከዚህ ባለፈ በተቋማቱ የተሻለ ተጠቃሚነትን በሚያስገኝ አግባብ ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት እያደገ የመጣ ሲሆን፤ ይሄንኑ መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎች እየበረከቱ እንደመሆናቸው ችግሩ ከመሰረቱ ተፈትሾ ሊፈታ ይገባል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ትምህርት በአንድ አገር ለሚኖር ሁለንተናዊ እድገት ተኪ የሌለው መሳሪያ ነው። ለዚህም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን፤ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በዚህ ውስጥ የበኩላቸውን እያበረከቱ ይገኛል። ይሁን እንጂ ጉዟቸው በችግር የተሞላና አገርና ህዝብን የሚጎዳ መስመር ውስጥ በመግባቱ ተቋማቱ አሰራራቸው ተጠቃሚነትን ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትንም መሰረት አድርጎ መሄድ ይገባዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ባሉ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት እንዳመለከተው፤ በተቋማቱ ፈቃድና እውቅና ሳኖራቸው ያስተምራሉ። ፈቃድ ያላቸውም ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ። ባልተሰጠ የሥልጠና መርሃ ግብር ያሠለጥናሉ፤ የመመዝገቢያ መስፈርት ያላሟሉ ተማሪዎችን አሠልጥነው ያስመርቃሉ። የተሰጠውን የትምህርት ዘመን ሳያሟሉም በአንድና ሁለት ወር (ለምሳሌ በማስተርስ) ተማሪዎችን ያስመርቃሉ። ለዘርፉ ባልተሰጠ የሥራ ፈቃድ (በአስመጪና ላኪ፣ በድለላና ሌሎች ፈቃዶች) እየሠሩ ይገኛሉ። ይህ አካሄድ ደግሞ የራስን ጥቅም ከመፈለግ ያለፈ በአገርና ህዝብ ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ የዘነጋ ነው። ምክንያቱም በዚህ መልኩ ተምረው የሚወጡ ተማሪዎች ወደሥራ ኢንዱስትሪው ሲገቡ አገርንም ህዝብንም ይጎዳሉ። ይሄም ከሚያሳድረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ባለፈ አገርን የማፍረስ አቅምም አለው። እናም እነዚህ ተቋማት ሥራቸውን ሲያከናወኑ ተጠቃሚነታቸውን ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነታቸውንም አስበው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
መንግሥትም ይህ ችግር እንዲቃለል የሚያስችሉ እርምጃዎችን የሚወስድ ሲሆን፤ የአሰራር ሥርዓቱን ከማዘመንና ተጠያቂነትን ከማስፈን ባለፈ፤ ከዚህ ችግር መውጣት ያልቻሉ ተቋማትን እስከመዝጋት እርምጃ ይወስዳል። መረጃዎችንም በየጊዜው ለህዝብ ያደርሳል። የመድረኩ ተሳታፊ ባለድርሻዎች በበኩላቸው እንዳሉት፤ ችግሩ ኤጀንሲውን ብቻ ሳይሆን ተቋማቱንም ሲታመሙበት የነበረ ጉዳይ እንደመሆኑ በዚህ መልኩ ታይቶ ለመፍትሄው አቅጣጫ መያዙ አስደሳች ነው። አሁንም ችግሮቹ በትክክል በመለየት በዛው ልክ መፍትሄ ማስቀመጥ ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል። ለተግባራዊነቱም አንድ አካል ብቻ ሳይሆን በሁለቱም አካል ኃላፊነታቸውን መውሰድ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
ወንድወሰን ሽመልስ