አዲስ አበባ፡- ሰሞኑን ከጎረቤት አገሮች በመጡ ታጣቂ ኃይሎች በአፋር አርብቶ አደሮች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ በክልሉ የዜጎች ደህንነት ስጋት ውስጥ እንዳለ፤ በፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ተደርጎ የተሰራጨው መረጃ መሰረተ ቢስ መሆኑንና በአሁኑ ወቅት ሰላም የማስጠበቁም ሥራ ከክልሉ አቅም በላይ እንዳልሆነ የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አስታወቁ።
የአፋር ክልላዊ መንግሥት ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሱልጣን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ከጅቡቲና ከሱማሌ ላንድ የመጡ ታጣቂዎች መጋቢት 16 እና 17 በዱፍቲ ወረዳ ጋውሊ በተባለ አካባቢ እንዲሁም መጋቢት 19 እና 20 ቀን ሀዳአር በተባለው አካባቢ በሚኖሩ አርብቶ አደሮች ላይ ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ አጠቃላይ የክልሉ ህዝብ ደህንነት ስጋት ላይ እንደወደቀ ተደርጎ የተሰራጨው መረጃ ሚዛኑን የጠበቀ አይደለም። የክልሉና የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ጥቃቱ ሲፈፀም ዘግይተው ቢደርሱም በአሁኑ ወቅት ነዋሪውን በማረጋጋትና ድጋፍ በመስጠት የአካባቢውን ፀጥታ በአስተማማኝ ሁኔታ ማስጠበቅ ችለዋል።
እንደኃላፊው ማብራሪያ፤ ታጣቂዎቹ በዱፍቲ ወረዳ ባደረሱት ጥቃት አንድ ሰው ሲሞት በአንድ ሰው ላይ የመቁሰል አደጋ አጋጥሟል።በተመሳሳይም በሀዳአር አካባቢ በፈፀሙት ጥቃት ትምህርት ቤትና የጤና ተቋምን ጨምሮ 19 ቤቶች በቃጠሎ የወደሙ ሲሆን፣ በዚህም አንድ ሰውሲሞት አንድ ሰው ቆስሏል። ታጣቂዎቹ ይዘውት የመጡት የጭነት ተሽከርካሪም ተቃጥሏል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ባደረሰው የድረሱልን ጥቆማ መሰረት የክልሉና የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት ማጣራት ተሽከርካሪው ከፊት የኢትዮጵያ ታርጋ ከኋላ ደግሞ የሱማሌ ላንድ ታርጋ ያለው መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን፤ በውስጡ የአልሻባብና የሱማሌ ክልል ባንዲራዎች፣ ጭምብል፤ አንድ የጅቡቲ መታወቂያ ተገኝቷል። እንዲሁም ከብት ለመዝረፍ የሚረዱ፣ ማብሰያዎች፣ ሲሚንቶና ቆርቆሮና የመሳሰሉ ቁሶች መያዛቸውን ተናግረዋል።
ታጠቂዎቹ ከተለያዩ አቅጣጫ ተደራጅተው የመጡና ዓላማቸውም የአፋርን ማህበረሰብ በማጥቃት ግዛት ማስፋፋት ነው ያሉት አቶ አህመድ፤ ታጣቂዎቹ የመጀመሪያው ጥቃት አልሳካ ሲላቸው ሌላኛው የክልሉ አቅጣጫ በመሄድ ግጭቱ ከኢሳ ማህበረሰብ ጋር የተደረገ ለማስመሰል ጥረት ማድረጋቸውን አስገንዝበዋል። ይሁና የክልሉና የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት ማጣራት በከፍተኛ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ያደረሱ በመሆኑ ከወትሮው የአፋርና ኢሳ ግጭት የተለየ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉን አመልክተዋል።
ታጣቂዎቹ የመጡት ከዚህ ቀደም ኮንትሮባንዲስቶች ይጠቀሙበት በነበረው ከጅቡቲ ወደ ገዳማዪቱ በሚወስደው መንገድ መሆኑን አመልክተው፤ መንገዱ በአግባቡ ያልተሰራ በመሆኑ የፀጥታ ኃይሎች በአፋጣኝ በመድረስ አርብቶአደሮችን መታደግ እንዳልቻሉ አስረ ድተዋል።
«በወቅቱ ኔትወርክ ባለመኖሩም አርብቶ አደሮቹ የድረሱልኝ ጥሪ ማስተላለፍ ተቸግረው ነበር» ያሉት አቶ አህመድ፣ ጥቃቱ ከደረሰ ከአንድ ቀን በኋላ ግን የፀጥታ ኃይሎችና የክልሉ አደጋ ስጋት ዝግጁነት ቢሮ ለአርብቶ አደሮቹ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። በአሁኑወቅት ቤታቸው የተቃጠለባቸው አርብቶ አደሮች ወደ ሌላ መንደር ሄደው እንዲጠለሉ መደረጉንም አስረድተዋል።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ምንም እንኳ የክልሉ ልዩ ኃይል ሪፎርም ላይ ቢሆንም በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ተመድበው ሰላም የማስጠበቅ ሥራቸውን በብቃት እየከወኑ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅትም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በአስተማማኝ ሁኔታ ሰላም የሰፈነ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥትን ድጋፍ የሚያስፈልግበት ምክንያት የለም። ይሁንና ጥቃት አድራሾቹ ግዛት ከማስፋፋት ባለፈ ፀረ ኮንትሮባንድ ትግሉን ለማስተጓጓልና ህገወጥ የጦር መሳሪያ ለማስገባት ያለመ በመሆኑ ከገደማዪቱ ወደ ጅቡቲ የሚወስደውን መንገድ በአግባቡ መገንባት እንደሚገባ ጠቁመዋል። በቀጣይም የአገር ሰላምን የማስጠበቁን ሥራ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
የአፋር የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ጋአስ አህመድ ባለፈው ሳምንት ለአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን በአፋር ክልል የተከፈተው ጦርነት 3 ወራትን ያስቆጠረ መሆኑንና እስካሁን በተፈጸመው ጥቃትም ከ100 በላይ ወጣቶችና አርብቶ አደሮች ህይወታቸውን ማጣታቸውን፤ በቁጥር መገመት የማይቻል ንብረት መውደሙን ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው። የክልሉ መንግሥት ከጎረቤት አገራት በመጡ ታጣቂዎች የተከፈተበትን ጦርነት ለመከላከል የሚያስችል አቅም የሌለው መሆኑንና የፌዴራል መንግሥትም የሚፈለገውን ድጋፍ እያደረገ አለመሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
ማህሌት አብዱል