አዲስ አበባ፦ ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች ተነስተው በየካቲት 66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በጊዜያዊ መጠለያነት የገቡ ልጆች በመማር ማስተማር ሥራው ላይ ስጋት መፍጠራቸውን የትምህርት ቤቱ መምህራን አስታወቁ።
የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ የጎዳና ተዳዳሪዎቹን ለማቆየት የሚያስችል ሌላ ቦታ ባለመገኘቱ የተፈጠረ ችግር መሆኑን ገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ ተለምዶ “እሪበከንቱ” በሚባለው አካባቢ የሚገኘው የየካቲት 66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ብርሃኑ ታከለ ሰሞኑን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማቋቋም የጀመረው ፕሮጀክት የሚደገፍ ተግባር ነው። ይሁንና ትምህርት ቤቱ ውስጥ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንዲገቡ በመደረጉ በመምህራንና ተማሪዎች የእለት ተእለት ስራ ላይ ስጋት ፈጥሯል።
እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ፤ የጎዳና ተዳዳሪዎቹን ተቀበሉ የሚል ትዕዛዝ ከመንግስት በመምጣቱ ከሁለት ወራት በፊት ገብተዋል። የተወሰነውን የግቢውን ክፍል ተለቆ አጥር ተዘጋጅቷል። ነገር ግን መውጫም ሆነ መግቢያቸው በትምህርት ቤቱ ዋና በር በመሆኑ ጠጥተው የሚመጡ ወጣቶች የተማሪዎችን ስነልቦና ሲረብሹ ተስተውሏል። ወደ ክሊኒክ እንሄዳለን በሚል በየጊዜው የሚወጡት የጎዳና ተዳዳሪዎች በመማር ማስተማር ሒደቱ ላይ ችግር እየፈጠሩ ነው። በተጨማሪም አስነዋሪቃላትን የሚሰነዝሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች በመኖራቸው የመምህራንም ሆነ የተማሪዎች ስጋት ከፍተኛ ሆኗል።
ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ወቅት መጻሕፍት ቤቱን እና ቤተ ሙከራውን እንዲሁም መጸዳጃ ቤቱን ለጎዳና ተዳዳሪዎቹ በሚል መልቀቁን የሚናገሩት ምክትል ርዕሰ መምህሩ፤ በዚህ ምክንያት ተማሪዎች የሚያነቡበትም ሆነ የቤተ ሙከራ ስራ የሚያከናውኑበት ቦታ የላቸውም።የጎዳና ተዳዳሪዎቹ በጊዜያዊነት እንደሚቆዩና ትምህርት ቤቱን እንደሚለቁ ታስቦ ቢገቡም ለሁለት ወራት መቆየታቸው የተማሪው እና መምህራን ሥራ ላይ መጥፎ ጥላ እያጠላ ይገኛል።
በትምህርት ቤቱ የቋንቋ መምህር የሆኑት አቶ ሰለሞን ጌታቸው በበኩላቸው፤ የጎዳና ተዳዳሪዎቹ የተለየ አጥር ቢዘጋጅላቸውም በተለያዩ ምክንያቶች ከተማሪው ጋር መገናኘታቸው ከትምህርት ሒደቱ ጋር የማይጣጣም ተግባር ተፈጽሟል። በትምህርት ቤቱ አጥር ጀርባ ወንዝ በመኖሩና በወንዙ አዋሳኝ ግቢው አጥር ስለሌለው የጎዳና ተዳዳሪዎቹ በዚህ በኩል ከግቢያቸው ወጥተው ሲጋራ እና መጠጥ ጠጥተው ይመለሳሉ። በዚህም ምክንያት በግቢው ውስጥ ረብሻ እየተፈጠረ የትምህርት ሒደቱ እየተስተጓጎለ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ለጎዳና ተዳዳሪዎቹ ተብሎ በተዘረጋው የኤሌክትሪክ መስመር ምክንያት የፕላዝማ ትምህርት ስርጭቱ ከተቋረጠ ቆይቷል። ይህም በተለይ የብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ የሆኑ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያመጣ መምህሩ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ለወጣቶቹ ተብሎ በቆርቆሮየተሰራው የማዕድ ቤት ከትምህርት ቤቱ ህንጻ ስር በመሆኑ የእሳት አደጋ ሊያስከትል የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። የቤተመጽሐፍት አገልግሎቱ ተቋርጧል። በመሆኑም የጎዳና ተዳዳሪዎቹን ትምህርት ወደሚሰጥበት ግቢ ማስገባቱ ስህተት ነበር። አሁንም ወጣቶቹን ወደሌላ ቦታ ማዘዋወር አንደሚገባቸው መምህር ሰለሞን ጠይቀዋል።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ችግር ተጎጂዎች መልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው አበራ በበኩላቸው፤ 3 ሺ 147 የጎዳና ተዳዳሪዎቹ በአዲስ አበባ በሚገኙ ስምንት ማዕከላት መግባታቸውን አስታውሰው፤ ከዚህ ውስጥ የካቲት 66 ትምህርት ቤት አንዱ መሆንና ትምህርት ቤቱ ጊዜያዊ ማቆያነት የተመረጠው ሌላ በከተማዋ አማራጭ ቦታ በመታጣቱ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንደ አቶ እንዳሻው ማብራሪያ፤ የጎዳና ተዳዳሪዎቹን ወደ ተለያየ ቦታ እየተላኩ በመሆኑ በቅርቡ ከግቢው ይወጣሉ። እስከዚያው ድረስ ግን በትምህርት ቤቱ መቆየታቸው አይቀሬ ነው። ይሁንና የጎዳና ተዳዳሪዎች ማቆያ ማዕከላት እጥረት በመኖሩ እንጂ ከተማ ውስጥ ማቆየቱ አይመከርም። ምክንያቱም ወጣቶቹ ተመልሰው ወደ ሱስ እንዳይገቡ ከከተማ ወጣ ባለ ቦታ መቀመጥ ነበረባቸው።
በየካቲት 66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መረጃ መሰረት፤ በግቢው 251 የ9ኛ እና የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ይገኛሉ። በተጨማሪም 67 መምህራን እና ሰራተኞች አሉ። በአሁኑ ወቅት ከ50 በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች በትምህርት ቤቱ በቤተመጻፍህት ውስጥ ማደሪያቸውን አድርገዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
ጌትነት ተስፋማርያም