የ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ባለፈው አርብ በባህርዳር ስቴድየም ተጀምሯል። ባለፉት ቀናትም የአንደኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተካሂደው ከትናንት በስቲያ ተጠናቀዋል። የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ይቀጥላሉ። ከዓምናው የውድድር ዓመት በተለየ በበርካታ ግቦች ተንበሽብሸው በጀመሩት የዚህ ዓመት የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች በአጠቃላይ ሃያ አንድ ግቦች ከመረብ አርፈዋል። ይህም ተመልካቹ ካለፈው የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ከእጥፍ በላይ ግቦችን እንዲመለከት አስችሎታል። በአንድ ጨዋታ ከግማሽ ደርዘን በላይ ግቦች ሲቆጠሩም የታየበት የፕሪሚየርሊግ ጅማሬ ሆኗል።
ባለፈው የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች አስር ግቦች ብቻ የተቆጠሩ ሲሆን ዘንድሮ ሃያ አንድ ግቦች ተስተናግደዋል። አምና ሶስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሁለቱ ምንም ግብ ያልተቆጠረባቸው ናቸው። አንዱ ጨዋታ ብቻ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ነበር ያለቀው። ዘንድሮ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁት ሁለት ጨዋታዎች ሲሆኑ አንዱ ካለምንም ግብ ሌላኛው ደግሞ ሁለት ለሁለት የተጠናቀቀበት ነው። የአቻ ውጤቶች የበዙበትና ከጅምሩ የግብ ድርቅ የመታው የዓምና ውድድር ዓመት ጅማሬ በአቻ ውጤት ካልተጠናቀቁ አምስት ጨዋታዎች ሶስቱ ከአንድ ለዜሮ የበለጠ ግብ አልተቆጠረባቸውም። ዘንድሮ በአንድ ለዜሮ ውጤት የተጠናቀቁት የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ ወልቂጤ ከተማ አርባምንጭ ከተማን የረታበትና በመጨረሻው ጨዋታ መቻል ሃዲያ ሆሳእናን በተመሳሳይ ውጤት የረታበት ጨዋታ ነው። ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ቡና ያደረጉት ጨዋታ ብቻም ካለምንም ግብ አቻ የተጠናቀቀ ነው። በተቀረ አምስት ጨዋታዎች ላይ ሶስትና ከዚያ በላይ ግቦች ከመረብ አርፈዋል።
ባህርዳር ከተማ ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀለውን ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2ለ 1፣ ፋሲል ከነማ አዳማ ከተማን 2ለ 1፣ ያሸነፉበት ተመሳሳይ ውጤት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ እየተሳተፈ የሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ ሐዋሳ ከተማን በመርታት ደግሞታል። ዓምና ከመውረድ ለጥቂት የተረፈው ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ሁለት ለሁለት የተለያዩበት ጨዋታ በርካታ ግብ የተስተናገደበት ነው። ከስምንት ዓመታት በኋላ ሊጉን የተቀላቀለው ኢትዮጵያ መድን በቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰባት ለአንድ የደሰረበት ሽንፈት ያልተጠበቀና በርካታ ግቦችን ያስተናገደ ጨዋታ ሆኗል። በዚህ ጨዋታ የተቆጠሩ ግቦች ብቻ አምና በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታዎች እንዳጠቃላይ ከተቆጠሩ ግቦች በሁለት ብቻ ያነሰ ነው።
ባለፈው ዓመት ውድድር በመጀመሪያ ሳምንት ብቻም ሳይሆን በአንደኛው ዙር ውድድር በርካታ ግቦች መቆጠር እንዳልቻሉ ይታወሳል። ለዚህም የመጀመሪያውን ዙር ውድድር ያስተናገደው የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መጫወቻ ሜዳ ምቹ አለመሆን እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ በአሰልጣኞች ጭምር ወቀሳ ሲሰነዘርበት እንደነበር አይዘነጋም። ዘንድሮ የመጀመሪያውን ዙር የሚያስተናግደው የባህርዳር ስቴድየም መጫወቻ ሜዳ ላይ የተሻለ ለውጥ በመኖሩና ተጫዋቾች ኳስ እንደፈለጉ ማንሸራሸር በመቻላቸው በርካታ ግቦች ለመቆጠራቸው አንድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አስተያየት የሚሰጡ አሉ። ይህን እርግጠኛ ሆኖ ለማስቀመጥ ከዛሬ ጀምሮ የሚካሄዱ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎችና ቀጣይ መርሃግብሮች ላይ የሚቆጠሩ ግቦችን የምናይ ይሆናል።
ያም ሆኖ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በሚደረጉ ሁለት መርሃግብሮች ሲቀጥሉ የመጀመሪያውን ሳምንት በድል የጀመሩት ባህርዳር ከተማና ወልቂጤ ከተማ ቀን ሰባት ሰአት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። አስር ሰአት ላይ ደግሞ በተቃራኒው የመጀመሪያውን ጨዋታ በሽንፈት የጀመሩት አርባምንጭ ከተማና ኢትዮጵያ መድን ይገናኛሉ።
የሁለተኛው ሳምንት መርሃግብሮች ነገ ሲቀጥሉም የመጀመሪያ ድሉን ከግማሽ ደርዘን በላይ ግብ በማስቆጠር የጀመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ይገጥማል። ለሊጉ እንግዳ የሆነው ለገጣፎ ለገዳዲም ከመጀመሪያ ድሉ ማግስት ነጥብ ጥሎ የመጣው ድሬዳዋ ከተማን ይገጥማል። ሃዲያ ሆሳእና ከሲዳማ ቡና፣ አዳማ ከተማ ከመቻል ከነገ በስቲያ የሚጠበቁ ጨዋታዎች ሲሆኑ ኢትዮጵያ ቡና ከሐዋሳ፣ ወላይታ ድቻ ከፋሲል ከነማ በመጪው ሰኞና ማክሰኞ የሚካሄዱ የሁለተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች እንደሚሆኑ የወጣው መርሃግብር ያሳያል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2015