የዋጋ ንረት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዋነኛ ፈተናዎች ሆነው ከዘለቁት ችግሮች መካከል አንዱ ነው።የዋጋ ንረት በየጊዜው ማሻቀብ እንጂ ዝቅ ማለት አልሆነለትም።ይህም የሕብረተሰቡን፣ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል፣ ኑሮ እጅግ የከበደ እንዲሆን አድርጎታል።
እጅግ የሚያስገርመው ደግሞ አገሪቱ ከበቂ በላይ የምታመርታቸው ምርቶች ሳይቀሩ ዋጋቸው ሰማይ መድረሱ የዋጋ ንረቱን አስገራሚና ግራ የሚያጋባ አድርጎታል።ለአብነት ያህል ከበቂ በላይ ተመርተው ከማሳ የሚያነሳቸው አጥተው ለብክነት እንደሚዳረጉ የምርቶቹ ባለቤቶች የሚናገሩላቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በከተሞች ያለው ዋጋቸው ‹‹ጆሮ አይስማ›› የሚያሰኝ ነው።
ከዓመት ዓመት መጨመር እንጂ መቀነስ ለማያሳየው ከፍተኛ የዋጋ ንረት መንስዔዎቹ የግብይት ሥርዓትን ጨምሮ መሠረታዊ የሆኑ የምጣኔ ሀብት መዋቅሮች አለመስተካከል፣ የምርት አቅርቦት እየቀነሰ መምጣት እንዲሁም የሰላምና የፀጥታ መደፍረስ እንደሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ተደራርበው የኑሮ ውድነቱን ማክበዳቸውንም ይገልጻሉ።
የተጠቀሱት ችግሮች አካል የሆነው የግብይት ሰንሰለት ብልሽትም ለዋጋ ንረቱ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም በተደጋጋሚ ይገለፃል።በምርቶች ላይ ምንም ዓይነት እሴት የማይጨምሩ ነገር ግን ከአምራቹ እስከ ሸማቹ ድረስ ባለው የግብይት ሰንሰለት ውስጥ በብዛት ተሰግስገው የሚገኙት በርካታ አካላት (ደላላዎች) የምርቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ማድረጋቸው በገሃድ የሚታይ ነው።ይህ የግብይት ሰንሰለት መርዘም ደግሞ ለዋጋ ንረትና ለኑሮ ውድነት አንዱ ምክንያት ሆኗል።
በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግርማ፤ የግብይት ሰንሰለት በዋጋ ንረት ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ያስረዳሉ።እርሳቸው እንደሚሉት፤ የግብይት ሰንሰለት መርዘም የግብይት ሥርዓት ብልሽት አካል ነው።የግብይት ሰንሰለቱ ረጅም ሲሆን የትርፍ ህዳግን ያለአግባብ መጨመር፣ የእቃዎች እጥረት መከሰት ያጋጥማል።ከአምራች እስከ ገዢ ድረስ ያሉ አላስፈላጊ የግብይት ተዋንያን መብዛት ለዋጋ ንረት ከፍተኛ ሚና አላቸው።ጤነኛ በሆነ የግብይት ሰንሰለት ውስጥ የምርቶች ፍሰት ከአምራች ወደ ጅምላ አከፋፋይ፣ ከጅምላ አከፋፋይ ወደ ችርቻሮ አከፋፋይ ከዚያም ወደ ገዢው/ተጠቃሚው የሚጓዝ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ አለአግባብ የተፈጠሩ ብዙ ተዋንያን እንዳሉና ይህ ዓይነቱ ጤናማ ያልሆነ የግብይት ሰንሰለት፣ ሕጋዊ ተደርጎ ሲቆጠር እንደሚስተዋል አቶ ሀብታሙ ይገልፃሉ።‹‹በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዋጋ ንረት ምክንያት ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ በግብይት ሰንሰለት ምክንያት የተፈጠረው የግብይት መበላሸትና መዛባት ነው።የግብይት መዛባት የዋጋ ንረት እንዲከሰት መንስዔ ከሆኑ ቀዳሚ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል።›› ሲሉ ያብራራሉ።
የግብይት ሥርዓቱ እንዲበላሽ ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል አንዱ የግብይት ሰንሰለት መርዘም ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፣ የግብይት ሰንሰለት መርዘምና በሰንሰለቱ ላይ ቁጥጥር አለማድረግ የዋጋ ንረት እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል።በአንዳንድ ስፍራዎች በምርቱ መነሻ እና በመጨረሻው መዳረሻ (ሸማቹ) መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት ከእጥፍም በላይ ሆኖ እንደሚታይም ያመለክታሉ።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ ‹‹ፍሮንቲየርአይ›› (Frontieri) ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁም ረዥም የሆነና አላስፈላጊ አካላት የበዙበት የግብይት ሰንሰለት ውጤታማ የሆነ ገበያ እንዳይኖር በማድረግ የዋጋ ንረት እንዲሁም የምጣኔ ሀብት መናጋት እንደሚፈጥር ይገልፃሉ።
ዶክተር ሞላ የአንድ ሀገር ገበያ ውጤታማነት ከሚለካባቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ የግብይት ሰንሰለት ቀልጣፋነት መሆኑንም ያመለክታሉ።ገበያው አላስፈላጊ የግብይት ሰንሰለቶችን ያስወገደ ከሆነ ውጤታማ ገበያ ተደርጎ እንደሚታሰብም ይጠቅሳሉ።የግብይት ሰንሰለቱ እየረዘመ ሲሄድ በእያንዳንዱ ደረጃ ላይ ያለው ዋጋ ይጨምራል የሚሉት ዶክተር ሞላ፣ እቃዎች መጨረሻ ላይ ለሸማቹ ሲደርሱ ዋጋቸው በጣም ከፍተኛ ይሆናል ሲሉ ይገልጻሉ።የግብይ ሰንሰለት መራዘም፣ የጥራት መቀነስ እንዲሁም የጊዜና የወጪ መጨመርን ያስከትላል።የምርቱ ፈላጊ እቃውን በፈለገበት ጊዜ እንዳያገኘውም ያደርጋል።የግብይት ሰንሰለቱ ባጠረ ቁጥር ደግሞ የእቃዎች ዝውውር ቀልጣፋ ይሆናል፤ ወጪም ይቀንሳል ሲሉ ያብራራሉ።
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አረጋ ሹመቴም የግብይት ሰንሰለት ለዋጋ ንረት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይስማማሉ።እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፣ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን፣ የሸቀጦች የግብዓት ዋጋ መጨመር እና በግብይት ሰንሰለት ላይ ያሉ ሰው ሰራሽ ጣልቃ ገብነቶች ከዋነኞቹ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግሮች መካከል አንዱ ለሆነው ለዋጋ ንረቱ ዋነኛ መንስዔዎች መሆናቸውን በማብራራትም፣ በግብይት ሰንሰለት ላይ የሚፈጠሩ ሰው ሰራሽ ጣልቃ ገብነቶች የአቅርቦት እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ የዋጋ ንረት እንዲከሰት እንደሚያደርጉ ይጠቁማሉ።
እንደ ዶክተር አረጋ ገለጻ፤ ከአምራቹ እስከ ሸማቹ ድረስ የተራዘመ የግብይት ሰንሰለት ሲኖር የዋጋ ንረቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይሄዳል።ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ የፍጆታ ሸቀጦች የተራዘመ ግብይት ያላቸው ናቸው።በግብይቱ ላይ የሚሳተፉት አካላት ያለምንም እሴት ጭማሬ የየድርሻቸውን እንደ ትርፍ ስለሚወስዱ ምርቶቹ ሸማቹ ዘንድ የሚደርሱት በከፍተኛ ዋጋ ነው።ስለሆነም የግብይት ሰንሰለት በተራዘመ ቁጥር ቀጥተኛ የሆነ የዋጋ ንረት ይከሰታል።በተጨማሪም የግብይት ሰንሰለት መርዘም አቅርቦትን ያስተጓጉላል።
የግብይት ሰንሰለቱ እንዲረዝም ምክንያት ስለሆኑት ጉዳዮች ሲያስረዱም ‹‹የመረጃ ክፍተትም የግብይት ሰንሰለት እንዲረዝም ያደርጋል።የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም በተለይም የአቅርቦት ማነስ የግብይት ሰንሰለቱን የሚያረዝሙት ጣልቃ ገቦች እንደፈለጉ እንዲሆኑ አግዟቸዋል።ይህን ችግር ይቆጣጠራሉ የሚባሉ ተቋማት የግብይት ሰንሰለቱና የጥቅም ተጋሪ ሆነው በመገኘታቸው እንዲሁም መዋቅሩም የተዳከመና ብልሹ አሰራር የበዛበት በመሆኑ የግብይት ሰንሰለቱን የሚያራዝሙት አካላት እንደልባቸው እንዲሆኑ እድል አግኝተዋል።የመንግሥት መዋቅር ደካማ (ጠንክሮ መቆጣጠር የማይችል) በመሆኑና ግለሰቦችና ውሳኔ ሰጪ የመንግሥት አካላትም የችግሩ አካል ስለሆኑ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ አልተቻለም፤ የሚደረጉ አንዳንድ ቁጥጥሮችም ውጤታማ መሆን አልቻሉም›› በማለት ያብራራሉ።
ሀገራት የግብይት ሰንሰለትን በማቃለል የግብይት ውጤታማነታቸውን ለማሳደግና የአጠቃላይ ምጣኔ ሀብታቸውን እንቅስቃሴ ጤናማ ለማድረግ የተለያዩ እርምጃዎችን ይወስዳሉ።በኢትዮጵያ የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳጠርና ቀልጣፋ በማድረግ የገበያውን ውጤታማነት ለማሻሻል የተከናነወኑ አንዳንድ ተግባራት እንዳሉ የሚናገሩት ዶክተር ሞላ፤ የኢትዮጵያ ምርት ገበያን (Ethiopian Commodity Exchange – ECX) የዚህ ማሳያ አድርገው ይጠቅሳሉ።‹‹የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መቋቋም የግብይት አፈፃፀምን ለማቀላጠፍ ታስቦ የተቀረፀ ፕሮጀክት ነው።ችግሩ ግን ከምርት ገበያው የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ወደ ሌሎች ዘርፎችም ማስፋት አለመቻሉ ነው›› ይላሉ።
ዶክተር ሞላ ‹‹በግብይት ውስጥ የሚሳተፉ አካላት፣ በተለይ አምራቾችና ተጠቃሚዎች (ሸማቾች)፣ መረጃ እንዲደርሳቸው በማድረግ እንዲሁም ምርት አቅራቢዎችና ፈላጊዎች በቀጥታ የሚገናኙባቸውን መንገዶች (በመረጃ፣ በቴክኖሎጂ …) በማመቻቸት የግብይት ሰንሰለቱን ማሳጠር ይቻላል።በሌሎች ሀገራት የሚሰራባቸው የኤሌክትሮኒክ ግብይቶች የግብይት ሰንሰለትን ለማሳጠር የተተገበሩ የግብይት ዘዴዎች ናቸው።
በምርቶች ላይ ምንም ዓይነት እሴት የማይጨምሩ አካላት በገዢና ሻጭ መካከል መግባት እንደሌለባቸውም ነው ያመለከቱት።ብዙ ሰው በገዢና ሻጭ መካከል የሚገኙ አካላት (ደላላዎች) ለሚፈጥሩት የዋጋ ጭማሬ ሰለባ የሚሆነው በመረጃ እጥረት ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰው፣ ‹‹እነዚህን እሴት የማይጨምሩና አላስፈላጊ የሆኑ አካላትን ከግብይት ሰንሰለቱ ማስወጣት ይገባል›› በማለት የግብይት ሰንሰለትን እንዴት ማሳጠርና ግብይትን ቀልጣፋ ማድረግ እንደሚቻልም ያስረዳሉ።
‹‹አመለካከትና ግንዛቤ በግብይት ሰንሰለት ላይ ትልቅ ትርጉምና ውጤት አለው›› የሚሉት አቶ ሀብታሙ፤ ‹‹የሸማቾች ጥበቃ ፕሮቶኮል በሚገባ እየተተገበረ ነው? ጤነኛ የሚባለው የግብይት ሰንሰለት ስንት ደረጃዎች አሉት? የጅምላ አከፋፋዮችና የችርቻሮ አከፋፋዮች የትርፍ ህዳግ (Profit Margin) ስንት ነው?›› ብሎ መጠየቅ እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።
‹‹ችግሩ በቁጥጥር ብቻ የሚፈታ አይደለም።በዋናነት ሥነ ምግባር ያስፈልጋል።የትርፍ ህዳግን መወሰን፣ ሸማቹ ለመብቱ መከበር ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ እንዲሁም ሸማቹ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የዋጋ ሁኔታን እንዲያውቅ ማድረግ ያስፈልጋል።ነጋዴው በዘፈቀደ ዋጋ የሚተምንበትን ሥርዓት ማስተካከልም ይገባል።የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት በቁርጠኛነት መስራት አለባቸው።›› ሲሉ ያስገነዝባሉ። የግብይት ሰንሰለት ከዚህ ቀደም ተደጋግሞ ተነስቶ አሁንም ችግር ሆኖ የዘለቀው ጠበቅ ያሉ ተግባራዊ እርምጃዎች ስላልተወሰዱ መሆኑንም በማመልከት፣ ችግሩ ከምጣኔ ሀብታዊ እሳቤዎችና እርምጃዎች በተጨማሪ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትም እንደሚፈልግ ነው ያስገነዘቡት።
ዶክተር አረጋ የግብይት ሰንሰለትን ለማሳጠርና የገበያ ሥርዓቱን ጤናማ ለማድረግ ከሚጠቅሷቸው መፍትሄዎች መካከል አንዱ የመንግሥት መዋቅር ጠንካራና ከብልሹ አሰራር የፀዳ እንዲሆን ነው።
‹‹የግብይት ሰንሰለት በተራዘመ ቁጥር፣ አቅርቦትና ፍላጎት ተጣጥመው ገበያው ዋጋን መወሰን ሳይችል ሲቀር መንግሥት ጣልቃ ገብቶ እንዲያስተካክለው (ዋጋውን በመቆጣጠርና በመወሰን፣ ሌሎች አቅራቢዎችን በመጋበዝ …) ይመከራል›› የሚሉት ዶክተር አረጋ፤ አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ይህን መቆጣጠር የሚችል መዋቅር ስለሌለ ችግሩ ዘላቂ ሆኖ እንደቀጠለ ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ግብይቱ በገበያ መር የኢኮኖሚ መርህ መሰረት የማይካሄድ ከሆነ ጠንካራ የሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል።የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም፣ በተለይም የአቅርቦት ማነስ ካለ አቅርቦቱን መጨመር ይገባል።የአጭር ጊዜ መፍትሄዎች እየተወሰዱ ጎን ለጎን የረጅም ጊዜ መፍትሄዎች መወሰድ አለባቸው።ዋጋን የመቆጣጠርና አቅርቦትን የመጨመር እርምጃዎች የአጭር ጊዜ መፍትሄዎች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።የግብይት ሥርዓቱን ጠንካራ በሆነና ተጠያቂነት ባለው መዋቅርና አሰራር በመደገፍ የግብይት ሰንሰለቱን የሚያረዝሙ አካላትን መቆጣጠርና ከግብይቱ ማስወጣት ይገባል።
ከዚህ በተጨማሪም መሰረታዊ የሕብረት ስራ ማሕበራትን ምግብ ነክ በሆኑ መሰረታዊ ፍጆታዎች ግብይት ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል።ማኅበራቱ ምርቶችን ከአምራቾቹ በቀጥታ ለተጠቃሚዎች እንዲያደርሱ የሚችሉበትን እድል ማመቻቸት እና ለማሕበራቱ ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ ማሕበራቱን ማጠናከርም ይገባል።የመሬት፣ የፋይናንስ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችን በማሻሻል እንዲሁም ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ምርቶችን በተሻለ ዋጋ ከእርሻ በቀጥታ ወደ ተጠቃሚው የሚያቀርቡ ቢዝነሶችን ማበረታታት ያስፈልጋል።
‹‹መንግሥት ሁልጊዜም የሚወስዳቸው የአጭር ጊዜ መፍትሄዎች ናቸው:: የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን ወስዶ ዝም ከማለት ይልቅ ጎን ለጎን የረጅም ጊዜ መፍትሄዎችም ሊታሰቡ ይገባል›› ሲሉ ገልጸው፣ የማስታገሻ ስራዎች እየተሰሩ የረጅም ጊዜ መፍትሄዎች አለመሰራታቸው የዋጋ ንረቱ ለ10 ዓመታትና ከዚያ በላይ እንዲቀጥል ሆኗል ይላሉ። ስለሆነም ለችግሩ የተሻለ መፍትሄ ለማበጀት መንግሥት መዋቅሩን ጠንካራና ተጠያቂ ማድረግ አለበት›› በማለት ይመክራሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2015