አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በታየው ለውጥ ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስ እንዳልቀረበባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ማግስት ጀምሮ ታስረው የነበሩ በርካታ ጋዜጠኞችንና ፖለቲካኞችን ከመፍታቷ ባለፈ ባለፈው አንድ ዓመት አንድም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስ አልቀረበባትም። በዚህም በሰብዓዊ መብት ዙሪያ በተደረጉ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ከፍተኛ አድናቆት ተችሯታል።
ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የታሰረ ጋዜጠኛ ባለመኖሩ ለአገሪቱ እውቅና ለመስጠት በመጪው የሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ዓለም አቀፉን የፕሬስ ቀን ኢትዮጵያ የምታከብር መሆኑን ቃል አቀባዩ አመልክተዋል። ቀኑ ከአፍሪካ ሕብረትና ዩኔስኮ ጋር በመተባበርም በድምቀት የሚከበር መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመግለጫው እንደተጠቀሰው፤ ከ130 በላይ ኤምባሲዎች ያላት አዲስ አበባ፤ ከተማዋን ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር እየተሠራ ይገኛል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ትልም የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት አዲስ አበባ ከሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ጋር ምክክር ተደርጎበታል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪ ለውጭ አገር የዲፕሎማት ማህበረሰብ ስለፕሮጀክቱ ገለጻ በተደረገላቸው ወቅት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። ከመቶ ዓመታት በላይ የቆዩ ኤምባሲዎች ስላሉ ከውጭ የመጡ ዲፕሎማቶችና ማህበረሰቦች እንደራሳቸው ከተማ የሚይዋት በመሆኑ ለፕሮጀክቱ መሳካት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ተብሎ ይታመናል ብለዋል።
በቻይና በእስር ላይ የምትገኘውን የወይዘሪት ናዝራዊት አበራን ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተከታተለው እንደሆነም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። በቻይና ጁዋንግ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ወይዘሪት ናዝራዊትን ሦስት ጊዜ በአካል በመገኘት የጎበኛትመሆኑን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅትም በመልካም ጤንነት ላይ እንደ ምትገኝ አመልክተዋል። ለአራተኛ ጊዜም የፊታችን ማክሰኞ ጉብኝት የሚደረግላት መሆኑን ጠቁመዋል። ግለ ሰቧን በተመለከተ በማህበ ራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የሚ ሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆ ኑን የጠቀሱት ቃል አቀ ባዩ፤ እስካሁንም በአቃቤ ህግ ክስ እንዳልተመሰረተባት ተናግ ረዋል።
እንደ ቃል አቀባዩ ገለፃ፤ የረጅም ዘመን ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያና አርመኒያ በቀጣይም ታሪካዊ ግንኙነታቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ። የአርመኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዚህ ሳምንት የሁለት ቀናት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ በሁለቱአገራት መካከልም የፖለቲካ ምክክር ስምምነት ተፈርሟል። አርመኒያ በኢትዮጵያ ኤምባሲ እንድትከፍትም እቅድ ተይዟል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው አንድ ዓመት ስኬት ያስመዘገበው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ መምጣት ወዲህ በተደረገው የአደረጃጀት ለውጥ መሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
ዋለልኝ አየለ