አዲስ አበባ፡- የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የ2011 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የእቅድ አፈጻፀም ሪፖርት ጥንቅር ከፍተኛ ትችት ገጠመው። ሚኒስቴሩ በበኩሉ ችግሮቼን አስተካክላለሁ ብሏል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 4ኛ መደበኛ የሥራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባ የሚኒስቴሩን የስምንት ወራት አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት፤ ሚኒስቴሩ ያቀረበውን ሪፖርት ተችቷል።
የምክር ቤቱ አባላት እንዳሉት፤ የቀረበው የስምንት ወራት ሪፖርት ከተለያዩ ቦታዎች የተቃረሙና የራሱን ሥራ የማያጎሉ ናቸው። የሚኒስቴሩን አበይት ጉዳዮችን የዘነጋ፣ ወጣቶች በሚል ጥቅል አገላለፅ የሴቶችን ተጠቃሚነት በሚገባ ያላሳየ ነው። ሚኒስቴሩ ሥራውን በአግባቡ ስለመገምገሙ ለመናገር አስቸጋሪ ነው። ቀድሞ በነበረው የዘመቻ አሰራር ላይ መጠመዱን አመላካች ነው።
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሯ ዊም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለችግር የተጋለጡና ሴቶችና ህፃናት ያሉበትን ደረጃ በሚገባ የሚያሳይ ሪፖርት አለመካተቱም ድክ መት መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል። አስተያየታቸውን ከሰጡ የምክር ቤት አባላት አንዱ፤ ‹‹በሪፖርቱ ለተመላከቱ ሥራዎችም ዋጋ መስጠት ያስቸግራል›› ሲሉ ተደምጠዋል።
የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ፀጋይ በበኩላቸው፤ የምክር ቤት አባላት ያነሷቸው በርካታ ሐሳቦች ተቀባይነት ያላቸውና በቀጣይ መስተካከል እንደሚገባቸው አምነዋል። ይሁንና የሪፖርቱም ሆነ በአሠራር ችግሮች ቢኖሩም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ተጠቃሚ የሆኑባ ቸው አያሌ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ ባለፉት ስምንት ወራት ሴቶችን የቁጠባ ባህል ለማዳበርና የብድር አጠቃቀማቸውን ለማጎልበት ታስቦ ለ6ሚሊዮን 768ሺ 136 ሴቶች አራት ቢሊዮን 251 ሚሊዮን 635ሺ ብር እንዲቆጥቡ ተደርጓል። 556ሺ746 ሴቶች ደግሞ በአጭርና ረጅም ጊዜ የሚከፈል ከሦስት ቢሊዮን የሚልቅ ብር በቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።
13 ሚሊዮን ወጣቶችን በክረምትና በበጋ እንዲሁም በወሰን ተሻጋሪ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ መሳተፋቸውንና በዚህም 4ነጥብ6 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን በበጎ መልኩ የሚወሳ እንደሆነ አመልክተዋል። ሚኒስቴሩ እነዚህንና ሌሎች ጉልህ ተግባራትን በሰፊው እያከናወነ ቢሆንም ችግሮች እንዳሉበትም ጠቁመዋል።
እንደ ወይዘሮ ያለም ገለፃ፤ ከክልሎች የሚላኩ ሪፖርቶች ጥራታቸውንና ወቅታቸውን ያልጠበቁ መሆናቸው፣ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሴክተር ዘለል በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በእቅዶቻቸው ውስጥ አካተው በአግባቡ ኃላፊነታቸውን ያለመወጣታቸው፣ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲሁም የህፃናትን መብትና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ በሕበረተሰቡ ዘንድ የተሟላ አመለካከትና ለውጥ ላለመምጣቱ አሁንም ፈታኝ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር