እየተገባደደ በሚገኘው የመስከረም ወር በተለያዩ የዓለማችን ታላላቅ ከተሞች በርካታ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች መካሄዳቸው የተለመደ ነው:: ባለፈው ሳምንት መጨረሻም በተመሳሳይ ከ5ኪሎ ሜትር አንስቶች እስከ ማራቶን በቁጥር በዛ ያሉ ውድድሮች ተካሂደዋል:: በእነዚህ ውድድሮች ላይም ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ውጤታማ ለመሆን ችለዋል::
ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ድል ካደረጉባቸው ውድድሮች መካከል አንዱ በጣሊያን የተካሄደው የትሬንቶ ግማሽ ማራቶን ውድድር ነው:: የግራዳ ሃይቅን ተንትርሳ በተቆረቆረችው ትሬንቶ ከተማ ለጎብኚዎች ተመራጭና ከየዓለምቱ የሚመጡ ቱሪስቶች መዳረሻ መሆኗ ይነገርላታል:: በዚህች ታሪካዊ ከተማም የሃይቁን ዳርቻ ተከትሎ የሚካሄድ ዓመታዊ የጎዳና ላይ የሩጫ ፌስቲቫል ይታወቃል:: እአአ 1907 ጀምሮ የሚካሄደው ይህ ፌስቲቫል ታዋቂ አትሌቶችን ጭምር በማሳተፍ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ቀነኒሳ በቀለን፣ ፓውል ቴርጋትንና ስቴፋኖ ባልዲኒን የመሳሰሉ ከዋክብት ሮጠውባታል::
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው የዘንድሮው የሩጫ ፌስቲቫል ላይም ኢትዮጵያዊያንና ኬንያዊያን አትሌቶችን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ አትሌቶች ተካፍለውበታል:: በወንዶች በኩል በተካሄደው ውድድርም የማራቶን የዓለም ቻምፒዮኑ አትሌት ታምራት ቶላ ስኬታማ መሆን ችሏል:: እአአ በ2017ቱ የለንደን ዓለም ቻምፒዮና የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረው ታምራት ከወራት በፊት በአሜሪካዋ ኦሪጎን በተካሄደው የዓለም ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያውን በማጥለቅ አገሩን ማስጠራቱ የሚታወስ ነው:: አትሌቱ በተካፈለበት በዚህ የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይም የተለመደ ብቃቱን በማስመስከር አሸናፊ ሆኖ ለመፈጸም በቅቷል:: ታምራት ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ሰዓትም 59:49 ሲሆን፤ ይህም የቦታው ፈጣኑ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦለታል::
በዚሁ የሩጫ ፌስቲቫል ላይ ከሚካሄዱ ውድድሮች መካከል አንዱ የ10ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ በዚህም ኢትዮጵያዊው አትሌት ሙክታር ኢድሪስ ቀዳሚ መሆን ችሏል:: የሁለት ጊዜ የመም ረጅም ርቀቶች የዓለም ቻምፒዮና መሆን የቻለው አትሌቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጎዳና ላይ ሩጫዎች ላይም እየታየ ይገኛል:: በጣሊያን በተካሄደው በዚህ ሩጫ ላይም ርቀቱን 28:47 በሆነ ሰዓት በመሮጥ፤ ከተፎካካሪዎቹ ጋር ሰፊ ልዩነት በማሳየት ባለድል ለመሆን ችሏል::
ኬንያዊው አትሌት ዌስሌይ ኪሙታይ ታምራትን ተከትሎ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል:: ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው ይህ አትሌት እጅግ ተቀራራቢ በሆነ ሰዓት 1:00:45 በማስመዝገብ ነው ውድድሩን ያጠናቀቀው:: ዩጋንዳዊው አትሌት ኬቨን ኪቤት ሶስተኛ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊው ሌሊሳ አራርሳ ደግሞ አራተኛ ደረጃን ይዟል::
በሴቶችም በተመሳሳይ የውድድሩ አሸናፊ የሆነችው አትሌት ኢትዮጵያዊት ናት:: በተለይ በማራቶን ውድድሮች የምትታወቀው አትሌት ብሩክታይት ደገፋ የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች:: አትሌቷ ርቀቱን የሮጠችውም 1:09:41 በሆነ ሰዓት ነው:: በጥቂት ሰከንዶች ልዩነት ሁለተኛ የሆነችው ኬንያዊቷ አትሌት ኢማኳሌት ቼፕኪሩይ 1:09:47የሆነ ሰዓት አስመዝግባለች:: ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ደሴ አንቺንአሉ ደግሞ 1:09:58 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ሆና ገብታለች::
በዓለም ዙሪያ ከሚካሄዱ ዓመታዊ የግማሽ ማራቶን ሩጫዎች መካከል ታዋቂ ከሆኑት መካከል በሚመደበው የካርዲፍ ግማሽ ማራቶንም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተካፋይ ነበሩ:: በዌልስ ዋና ከተማ ካርዲፍ የሚካሄደው ይህ ውድድር እአአ በ2003 የተጀመረ ሲሆን፤ ኬንያዊያን አትሌቶች የተሻለ የስኬት ታሪክ አላቸው:: በዘንድሮው ውድድር ላይም በተመሳሳይ ኬንያዊው ጄኦፍሪ ኮች 1:00:01 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ አሸናፊ ለመሆን ችሏል::
ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ለኬንያዊው ብርቱ ፈተና ቢሆኑበትም በሰከንዶች ዘግይተው አሸናፊነቱ ቦታ ሊወሰድባቸው ችሏል:: በዚህም ጊዜአለው አበጀ 1:00:17 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፤ ጪምዴሳ ደበሌ ደግሞ በአገሩ ልጅ በአንድ ሰከንድ ብቻ ተበልጦ ሶስተኛው አትሌት ሆኗል:: በሴቶች በኩል አንደኛ እና ሁለተኛ የሆኑት ኬንያዊያን አትሌቶች ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ዘውዲቱ አደራው እና ብርሃን ምህረቱ ሶስተኛ እና አምስተኛ ደረጃን ይዘው ሊያጠናቅቁ ችለዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2015