ደብረ ብርሃን፡- የደብረብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል በተመረጡ አካባቢዎች የአፕል፣ የሙዝ እና የበጎች መንደር ምስረታ ላይ ማተኮሩን አስታወቀ።
የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ አብይ ለገሰ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደተናገሩት፤ በሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ውጤት የሚሰጡ የአዝዕርት፣ የአገዳ፣ የፍራፍሬና የእንስሳት መንደር ምስረታ እየተከናወነ ነው። ለአብነትም ሸዋሮቢት፣ አጣዬና አንፆኪያ ገምዛ በተሰኙ አካባቢዎች የሙዝ መንደር ምስረታ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል። በሂደትም ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ገበያ ማቅረብ ውጥን መኖሩን ገልፀዋል። በምርምር በሄክታር 481 ኩንታል ሙዝ እየተገኘ ሲሆን፤ ቀደም ሲል ከዚህ በእጅጉ ያነሰ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከደብረ ብርሃን ከተማ ጀምሮ እስከ ቆላማው የሸዋሮቢትና አጣየ አካባቢዎች ድረስ ጠንካራ የበግ መንደር መመስረቱንም ጠቁመዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ በጎች የአማራ ክልል 35 ከመቶ የሚሸፍን ሲሆን፤ የሰሜን ሸዋ ዞን ደግሞ ከክልሉ አጠቃላይ ሃብት 19 ከመቶ በመሸፈኑ ለምርምሩ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። በባሶና ወራና ወረዳ አካባቢ ደግሞ የአፕል መንደር ምስረታው ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ፤ የምርምር ማዕከሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የበግና ምስር ዋና ማስተባበሪያ ማዕከል መሆኑን ጠቁመው፤ በዝርያ ማሻሻል ላይ በስፋትእየተሰራ ነው። በዞኑ ዋንኛ ምርቶች ከሚባሉት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስና ማሽላም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። ማዕከሉ በገብስ ላይ ባካሄደው ምርምር ቀደም ሲል በሄክታር 20 ኩንታል ገብስ እንደሚመረት አስታወሰው፤ በአሁኑ ወቅት 60 ኩንታል ማምረት ተችሏል።
የጥራጥሬ ምርቶችም የምርምሩ አካል ሆነዋል። ለሚ፣ መርሃቤቴ፣ ቀወት፣ ዓለም ከተማ፣ ሸዋሮቢት፣ አጣዬ እና ሌሎች ቆላማ አካባቢዎች ደግሞ በውጭ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ የሚፈለገውናበ90 ቀናት የሚደርሰው በባቄላና ምስር ምርት ላይም በሚደረገው ምርምር ጥሩ ውጤት እየተገኘ ነው። ይሁንና ሲያደብር፣ ሞረትና ጅሩ በሚባሉ አካባቢዎች አርሶአደሩ በጥንቃቄ ስለሚሰሩ በምርምር ከተገኘው የበለጠ ምርት እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ አብይ እንዳሉት፤ የምርምር ማዕከሉ አያሌ ተግባራትን እያከናወነ ቢሆንም ዞኑ በቅርበት ባለመስራቱ ከምርምር ማዕከሉ የሚወጡ በተለይም የሰብል ምርጥ ዘር ውጤቶች ተጠቃሚ እየሆነ አይደለም። የምርምር ማዕከሉም ለምርምርና ዘር ብዜት የመሬት እጥረት ስለገጠመው ከአርሶአደሮች መሬት እየተኮናተረ እንደሚሠራ ገልፀል። ለአብነትም በ2011 ዓ.ም ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ብር መክፈሉን ጠቁመዋል።
ምንም እንኳን የምርምር ማዕከሉ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ቢሆንም ችግሮች እንዳሉበትም ኃላፊው ተናግረዋል። ለአብነትም በምርምር የተደገፉና በአዕምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት እውቅና የተሰጣቸው የመንዝ በግ፣ የጅሩ በሬና የደብረሲና ቆሎ በቂ ገበያ እያገኙ እንዳልሆነም አስገንዝበዋል። ለዘር ማዳቀል ሥራ ለማከናወን የሚጠቅሙ ግብዓቶች የሚገኙት ከዓለም አቀፍ ምርምር ማዕከላት እና ከፌደራል የግብርና ምርምር ማዕከላት በመሆኑ እንደተፈለገው ምርት ማሳደግ ያለመቻሉንም ጠቁመዋል። የደብረብረሃን ግብርና ምርምር ማዕከል 1997 ዓ.ም ሥራ መጀመሩ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር