ትክክለኛ መረጃ የሚመነጨው ከእውነት ነው። እውነት ደግሞ ከሁሉም በላይ ታማኝነትን የሚጠይቅ ከፍ ያለ ሰብዓዊ እሴት ነው። ከዚህ ውጭ ስለመረጃ ሆነ ስለመረጃ ታማኝነት ማውራት የሚቻል አይሆንም። በማውራት ብዛትም ታማኝነትን ለመፍጠር የሚደረግ የትኛውም አይነት ሙከራ ለጊዜው ትርፍ ያስገኘ ቢመስልም ፍጻሜው ግን ተጠያቂነት ማስከተሉ የማይቀር ነው።
በተለይም ከበስተጀርባቸው የፖለቲካ ተልእኮና አጀንዳ ያላቸው “በበሬ ወለደ” ላይ የሚመሰረቱ መረጃዎች የቱንም ያህል በደጋፊና ተሸካሚ የፈጠራ /የውሸት/ ትርክቶች ታጀበው አደባባዮችን የመሙላት አቅም ቢያጎለብቱም “እውነትና ጉም እያደር ይጠራል” እንደሚባለው መጥራታቸው የማይቀር ነው።
መረጃዎች በጠሩ ማግስት የሚፈጥሩት ተጠያቂነት፤ ከፈጠሩት ችግርና ችግሩ ካስከፈለው ዋጋ አንጻር የሚተመን ፤ የታሪክ ተጠያቂነት እስከማስከተል የሚዘልቅ፤ ትውልዶችን እና አገራትን ጭምር አንገት የሚያስደፋ ሊሆን እንደሚችል የተለያዩ አገራትና ሕዝቦች ታሪክ የሚያረጋግጠው እውነታ ነው።
በእኛም አገር ለውጡን ተከትሎ በአገር ውስጥ የሚገኙ የጥፋት ኃይሎች፤ እነሱን መሳሪያ አድርገው የሚጠቀሙ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና የለውጡ መንገድ ያላስደሰታቸው ኃይሎች በቅንጅት መረጃዎችን በማፋለስ የለውጡን ኃይል አንገት በማስደፋት ለውጡን ለመቀልበስ የሄዱበት ረጅም ርቀት እንደ ህዝብ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል።
በተለይም አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት በግልጽ ከተቋቋሙበት ዓለም አቀፍ መርህ፤ ከዚያም ባለፈ ከመተዳደሪያ ቻርተራቸው ባፈነገጠ መንገድ ዓለም አቀፍ አሰራርን በሚጻረር ሁንታ የተዛቡ መረጃዎችን በማደራጀትና በማሰራጨት ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ለማሳሳት በስፋት ሰርተዋል፣ እየሰሩም ነው።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሕዝባዊ እንቢተኛነት ከስልጣን የተወገደውን /የአሸባሪውን ትህነግ/ የጥፋት ተግባራት አይቶ እንዳላየ ከመሆን ጀምሮ በቡድኑ የሚፈጠሩ ፈጠራ ትርክቶችን በማስተጋባት በመንግስት ላይ ከፍ ያሉ ጫናዎችን በመፍጠር ለራሳቸው የፖለቲካ ተልእኮ ለማንበርከክ ጥረዋል።
ለዚህም ትልቁን ዓለም አቀፍ ተቋም /የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን/ ጨምሮ የአውሮፓ ኅብረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን ተጠቅመዋል። በተለይም ሰብዓዊ መብቶችን ሽፋን በማድረግ የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ ተግባራትን ፈጽመዋል። ለዚህም መረጃዎችን ከማዛባት ጀምሮ ፍጹም መሬት ላይ የሌሉ እውነታዎችን ፈጥረው እስከማሰራጨት የደረሰ ድፍረት ውስጥ ገብተው ተስተውለዋል።
እነዚህኑ መረጃዎችን በአንዳንድ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን እንዲሰራጩ በማድረግም አገሪቱን እና ሕዝቦቿን ባልተገባ መንገድ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ለማድረግ ብዙ ርቀት ሄደዋል። ጫናዎችንና ማዕቀቦችን ለተልእኳቸው ስኬት አቅም መግዣ አድርገው በመጠቀምም የለውጡ መንገድ መንገጫገጭ እንዲበዛበት ሰርተዋል።
መንግስት በሰብዓዊ መብቶችም ሆነ በየትኛውም ጉዳይ ዙሪያ ከየትኛውም አካል ጋር ተባብሮ የመስራት ቁርጠኝነቱን በተደጋጋሚ በየአደባባዮች እያሳወቀ ባለበት እና በተጨባጭም ቁርጠኝነቱን እያሳየ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ ከመስራት ይልቅ መንግስትን ባልተገባ መልኩ በመፈረጅ ለዚሁ የተገዛ መረጃዎችን በመፈብረክና በማሰራጨት ላይ ተ ጠምደዋል፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ የሆነው እንዳለ እንኳን ሆኖ በቅርቡ ራሱን የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የባለሙያዎች ቡድን በማለት የሚጠራው አካል ይዞት የወጣው ሪፖርት ለዚሁ ተጨማሪ ማሳያ የሚሆን ነው። ገና ከውልደቱ ጀምሮ ሕጋዊነት የሌለው ይህ አካል የተዛባ ድምዳሜውን በተዛባ መረጃ ለማጠናከር የሄደበት ርቀት ቡድኑን ብቻ ሳይሆን ከቡድኑ በስተጀርባ ያለውን ተቋም ተአማኒነት ተጨማሪ ጥያቄ ላይ ጥሎታል።
በአንድ በኩል ለሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ነኝ የሚል ተቋም ከሚያነሳው ጉዳይ ትልቅነት አንጻር፤ ራሱን በሚያሳንሰው መረጃ የመፈብረክ ተግባር ውስጥ መገኘቱ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሚፈበርካቸው መረጃዎች ሰብዓዊ መብቶችን በአደባባይ ለሚጥስ ቡድን /አሸባሪው ትህነግ/ በጥፋት እንዲቀጥልበት የልብ ልብ የሚሰጥ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል።
ይህ በዓለም አቀፍ ተቋማት ስም የሚደረግ የተዛቡ መረጃዎችን የመፈብረክና እውቅና እንዲያገኙ የሚደረግ የሚዲያ ዘመቻና ጫና፤ የተቋማቱን የቀደመ ስም ከማጉደፍ ባለፈ በነዚህ ተቋማት ላይ እምነት የሚጥሉ አገራትና ሕዝቦችን እምነት በመሸርሸር ቀጣይ ተቋሟዊ ጉዞው ችግር ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል።
ከዚያም ባለፈ በተቋሙ ስም የሚፈበረኩ እና የሚሰራጩ የተዛቡና የሚፈበረኩ መረጃዎች አገራትና ሕዝቦችን ሊያስከፍሉ ከሚችሉት ያልተገባ ዋጋ አንጻር የታሪክ ተጠያቂነትን ማስከተላቸው አይቀርም። ከዚህ አንጻር ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በዓለም አቀፍ ተቋማት ስም በሚፈበረኩና በሚሰራጩ መረጃዎች ላይ በቂ ትኩረት ሊያደርግባቸው ይገባል!
አዲስ ዘመን መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም