በየአመቱ በተለያዩ የአለማችን ከተሞች ከሚካሄዱ ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች ግንባር ቀደም በሆነው የለንደን ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ወጣት አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ጣፋጭ ድል ተቀዳጅታለች። በደመናማና ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ታጅቦ ትናንት ውድድሩ ሲካሄድ ያለምዘርፍ በአስደናቂ ብቃት ተፎካካሪዎቿን በፍጹም የበላይነት መርታት ችላለች።
በውድድሩ ሰላሳ ሁለተኛ ኪሎ ሜትር አካባቢ ከተፎካካሪዎቿ ጋር ባደረገችው ትግል ወድቃ የተነሳችው ያለምዘርፍ ተስፋ ባለመቁረጥ ወደ አሸናፊነት የመጣችበት ሁኔታ አስደናቂ ነበር። የሃያ ሶስት አመቷ ድንቅ ኢትዮጵያዊት አትሌት በመጨረሻው አምስት ኪሎ ሜትር ፍጥነቷን ጨምራ በመሮጥ በተፎካካሪዎቿ ላይ የወሰደችው የበላይነት በ2:17:26 ሰአት የድሉ ባለቤት ለመሆን አስችሏታል። በዚህም የለንደንን ማራቶን በትንሽ እድሜ ያሸነፈች የመጀመሪያ አትሌት ለመሆን በቅታለች።
ያለምዘርፍ በተለይም ያለፈው ውድድር አሸናፊና ትልቅ ግምት የተሰጣትን ኬንያዊቷን አትሌት ጆይስሊን ጂፕኮስጌን በመጨረሻው አምስት ኪሎ ሜትር ፋታ በማይሰጥ ፍጥነትና ጥንካሬ ማንበርከኳ አድናቆትን አትርፎላታል። ያስመዘገበችው ሰአትም ቀደም ሲል በርቀቱ ካስመዘገበችው የኢትዮጵያ ክብረወሰን በሶስት ሰከንድ ብቻ የዘገየ ሆኗል። ባለፈው ሳምንት የበርሊን ማራቶን አትሌት ትእግስት አሰፋ አሸናፊ ስትሆን፤ የኢትዮጵያን የማራቶን ክብረወሰን መስበሯ የሚታወስ ሲሆን ከዚያ ቀደም ክብረወሰኑ በያለምዘርፍ እጅ ነበር የሚገኘው።
ያለምዘርፍ ለዚህ ታላቅ ድል የበቃችው ገና በሁለተኛ የማራቶን ውድድሯ ነው። በሁለቱም ውድድሯ ግን አርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩን ያጠናቀቀችው 2:17 ቤት ነው። ይህች ድንቅ አትሌት በግማሽ ማራቶን ውድድርም በታሪክ ሁለተኛዋ ፈጣን አትሌት ስትሆን የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ክብረወሰንም በእጇ ይገኛል። ባለፈው ሚያዝያ በሃምቡርግ የኢትዮጵያን የማራቶን ክብረወሰን ስትሰብር ያስመዘገበችው 2:17:23 በርቀቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሮጠች አትሌት የተመዘገበ ፈጣኑ ሰአት እንደነበር ይታወሳል። ይህም የአለማችን ሰባተኛው የማራቶን ፈጣን ሰአት ባለቤት ያደርጋታል።
ያለምዘርፍ ካስደናቂው የለንደን ማራቶን ድሏ በኋላ “በለንደን ማራቶን በማሸነፌ ተደስቻለሁ፣ ለዚህ ውድድር ጠንክሬ ስሰራና በጥሩ ሁኔታ ስዘጋጅ ቆይቻለሁ፣ ድሉም አስደናቂ ነው” በማለት ለመገናኛ ብዙኃን አስተያየቷን ሰጥታለች።
ከውድድሩ ቀደም ብሎ ብዙ የተነገረላት ያለፈው ለንደን ማራቶን አሸናፊዋ ጂፕኮስጌ ከባለድሏ አትሌት ከአንድ ደቂቃ ባላነሰ ዘግይታ በ2:18:07 ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ልላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መገርቱ አለሙ በ2:18:32 ሶስተኛ ሆና ጨርሳለች።
በተመሳሳይ በወንዶች መካከል በተካሄደው ውድድር ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ትልቅ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም በ2:05:53 ሰአት አምስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
የመምና አገር አቋራጭ ውድድሮች ንጉስ የሆነው ቀነኒሳ ፊቱን ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች ካዞረ በኋላ በ2016 የለንደን ማራቶን ሶስተኛ፣ በ2017 ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ ከሚገጥመው ጉዳት ጋር እየታገለ በመምና በአገር አቋራጭ ውድድሮች የሰራውን ታሪክ በማራቶን ለመድገም ጥረት አድርጓል። በዚህም በ2019 የበርሊን ማራቶን በወቅቱ የአለም ክብረወሰን ከነበረው የኬንያዊው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ በሁለት ሰከንድ የዘገየ 2:01:41 ሰአት በማስመዝገብ ማሸነፉ ይታወሳል። ቀነኒሳ ይህን አስደናቂ ብቃት ካሳየ በኋላ በርካቶች የርቀቱን የአለም ክብረወሰን እንደሚሰብር ተስፋ ቢያደርጉም አልተሳካለትም። ይህ የ40 አመት የምንጊዜም ድንቅ አትሌት በተለይም በ2020 የለንደን ማራቶን ክብረወሰን ያስመዘግባል ተብሎ ሲጠበቅ በመጨረሻ ሰአት በጉዳት ምክንያት ሳይወዳደር ቀርቷል። ከዚያ በኋላም በ2021 የኒውዮርክ ማራቶን ስድስተኛ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው። ቀነኒሳ ከሶስት ሳምንታት በፊት ወደ ውድድር ተመልሶ በእንግሊዝ ግሬት ኖርዝ ረን ባደረገው የ21 ኪሎ ሜትር ውድድርም ዩጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞንና የቶኪዮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ቻምፒዮኑን ሰለሞን ባረጋን ተከትሎ ሶስተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል።
ኬንያዊው አትሌት አሞስ ኪፕሩቶ በ2:04:39 አሸናፊ በሆነበት በትናንቱ የለንደን ማራቶን ኢትዮጵያዊው አትሌት ልኡል ገብረስላሴ በ2:05:12 ሰአት ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ቤልጂየማዊው አትሌት በሺር አብዲ በሶስት ማይክሮ ሰከንዶች ተቀድሞ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ፈጽሟል። ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ክንዴ አጥናው 2:05:27 አራተኛ፣ ብርሃኑ ለገሰ 2:06:11 ስድስተኛና ሲሳይ ለማ በ2:07:26 ሰባተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2015