በዚህ ክረምቱ ለበጋው ተራውን እየለቀቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ወደ ገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ወጣ ያለ መንፈሱ ሁሉ ይታደሳል። የደረሰው ሰብል በንፋስ ኃይል ሲዘናፈል፣ ከብቱ በየመስኩ ተሰማርቶ ለምለሙን ሳር ሲግጥ፣ በክረምቱ ደፍርሶ ሲያስፈራ የቆየው ወንዝ ሰከን ብሎ ውሃው ጥርትና ኮለል ብሎ ሲወርድ ይመለከታል። የአየሩ ነፋሻነት፣ የሜዳ ሸንተረሩ በአበባ በለምለም ሳር መድመቅ ሌላው የገጠሩ ክፍል የዚህ ወቅት ትዕይንት ነው። በተለይ ሰብሉን ሲያይ አይኑ ይጠግባል።
አዝመራ ከማሳ ተሰብስቦ ጎተራ እስከሚገባ አይነገርም በሚለው ብሂል እንጂ በቅርቡ ለሥራ ጉዳይ ወደ ገጠሩ ክፍል በሄድኩበት ወቅት በአለፍ ገደም እንደተመለከትኩትም፣ ከአንዳንድ አርሶ አደሮች እንደሰማሁትም በማሳ ላይ ያለው የመኸር ወቅት ሰብል አያያዝ አጠቃላይ ሁኔታ ሲታይ ይዞታው ጥሩ ነው። ገበሬው እንዲህ ያለ ተስፋ ከማሳው ሲመለከት ከወዲሁ ያጠግባል።
በአሁኑ ወቅት ያለው የኢትዮጵያ የግብርና ሥራ እንደ ቀደመው ጊዜ ወይንም ኋላቀር የግብርና ዘዴ እየተባለ ሲገለጽ እንደነበረው አይደለም። በክረምቱ ወይም በመኸሩ የተዘራውን ሰብል ለመሰብሰብ ከመዘጋጀት ጎን ለጎን የበጋ መስኖ ሥራ ይቀጥላል፤ ከዚያ ደግሞ በልግ ይመጣል፤ በመሆኑም በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቡና ተክል በሁሉም ልማቱን የማጠናከር ሥራ እንደ ሀገር ተጠናክሯል።
በቅርቡ ለሥራ ጉዳይ ሲዳማ ክልል በንሳ ወረዳ በተገኘሁበት ወቅት ከአካባቢው የተለያዩ ወገኖች እንደተረዳሁት፤ አካባቢው ሰብል አምራች ብቻ ሳይሆን፣ በቡና ልማትና በእንስሳት ሀብትም ይታወቃል።አርሶ አደሩ በነዚህ ሁሉ አማራጮች በመጠቀም ኑሮውን እንዲያሻሽል፤ በአካባቢውና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ከክልሉ አመራር ጀምሮ እስከታች ባለው መዋቅር የተናበበ ሥራ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው።
ለዚህም የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የወተት ላሞችን ምርታማነት ለመጨመር እየተደረገ ያለው ጥረት አንዱ ማሳያ መሆኑን ተመልክቻለሁ። በወረዳው ስለምርት ዘመኑ የግብርና ሥራ እና ስለሚጠበቀው ምርት፣ ለበጋ መስኖ ልማት እየተደረገ ስላለው ዝግጅት ከበንሳ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ ዘነበ ባናታ ጋር ቆይታ አድርጌያለሁ።
በእንስሳት ልማት
አቶ ዘነበ እንዳስረዱት፤ በቤተሰብ ደረጃ የአርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል (ብልጽግና ማምጣት) የሚቻለው በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቡና ልማትና በከብት እርባታ ሁለገብ የሆነ የግብርና ሥራ በማከናወን ነው። ክልሉም ሆነ ወረዳው በዚህ መንፈስ በልማቱ ላይ በትኩረት እየሠሩ ይገኛሉ።
በእንስሳት ልማቱ የሀገረሰብ ከብትን ከውጭ ዝርያ ጋር በማዳቀል ምርታማነትን ለማሳደግ በተለይም በወተት ምርታማነት ላይ እየተከናወነ ባለው ሥራ ወረዳው ውጤታማ ተግባር እያከናወነ ነው። ለውጤቱ ወረዳው አስፈላጊውን የድጋፍና ክትትል ሥራ ሲሠራ፣ አርሶ አደሩ ደግሞ ፍቃደኝነቱን አሳይቷል። በዚህ መልኩ የተናበበና የተቀናጀ ሥራ ማከናወን ተችሏል።
የወረዳው ሥራ በዚህ ረገድ አርሶ አደሩ ዝርያቸው ለተሻሻለ እንስሳቱ በቂ መኖ ለማቅረብ እንዲችል ለመኖ ማልሚያ ወደ አንድ ሺ ሄክታር መሬት ምቹ በማድረግ፣ የተመጣጠነ የመኖ አዘገጃጀት ዘዴን እንዲጠቀምም በወረዳው ባለሙያዎች በማገዝ፣ በ24ቱም የወረዳው ቀበሌዎች የእንስሳት ጤና አገልግሎት መስጫ ኬላዎችን በማመቻቸትና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች በማሟላት ይገለጻል።
በቡና ልማት
ወረዳው በቡና ልማትም ይታወቃል ያሉት አቶ ዘነበ፣ ከወረዳው 24 ቀበሌዎች ከአንዱ ቀበሌ በስተቀር ሁሉም ቡና አብቃይ መሆናቸውን ያመለክታሉ። አስራ ስድስት ሺ ሶስት መቶ አስራ አምስት (16ሺ315) ሄክታር መሬት በቡና ተሸፍኗል፤ ከዚህ ውስጥም አስራ አምስት ሺ ሶስት መቶ ሃምሳ ሶስት (15353) ሄክታር የሚሆነው ምርታማ ነው።
በወረዳው 53 የቡና ኢንዱስትሪዎችም ይገኛሉ። አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም የግብርና ዘዴ እንዲጠቀም ፣ የጥላ ዛፍ ችግኞችን በመትከል፣ ማዳበሪያ በማቅረብ፣ ወቅቱን ጠብቆ ጉንደላ በማካሄድና ሌሎች ምርታማነትን የሚጨምሩ ወደ 11 የሚሆኑ ግብዓቶችን (ፓኬጆች) በማቅረብና የባለሙያ እገዛ በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል።
ከቡና ጉንደላ ጋር ተያይዞ ይነሳ የነበረውን ችግር ለማስቀረትም ወረዳው እንቅስቃሴ ማድረጉንና ከጉንደላ ባለፈም ምርታማ ያልሆነውን ቡና ነቅሎ ጥሎ በሌላ በመተካት ጭምር በወረዳው ሰፊ ተግባራት ተከናውነዋል። በወረዳው ብቻ ወደ ሶስት ሺ የቡና እግር ተነቅሎ በአዲስ ተተክቷል። 358 ሄክታር የቡና ተክል ተጎንድሏል።
እስካሁን ባለው የቡና ልማት ሥራ በወረዳው በሄክታር 10 ኩንታል የቡና ምርት እየተገኘ ነው። ሞዴል የሚባል አርሶ አደር ግን እስከ 20 ኩንታል የሚያገኝበት ሁኔታም አለ። በሞዴል አርሶ አደርና በሌሎች መካከል የሚገኘው የምርት መጠን የሚለያይ በመሆኑ ይህን ማመጣጠንና ከፍተኛ ምርትም ለማምረት የበለጠ መሥራት ይጠበቃል። በዘንድሮ የምርት ዘመን በሄክታር 13 ኩንታል ለማግኘት እየተሠራ ነው። ቡና ከሚሰጠው የምርት መጠን አንጻር ብዙ እንዳልተሠራ አቶ ዘነበ ይናገራሉ።
በወረዳና በክልል ደረጃም በታዩ ጉድለቶች እና የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ በመነጋገር ምርታማነት ላይ ጠንክሮ ለመሥራት ከመግባባት መደረሱን አስታውቀዋል። አርሶ አደሩ በሚያገኘው ጥቂት ምርት ረክቶ እንዳይዘናጋ የግብርና ኤክስቴንሽንን በማጠናከር ረገድ የልማት ሠራተኛው ውሎና አዳሩን ከአርሶ አደሩ ጋር በማድረግ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል በማድረግና በማንቃት የበለጠ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።
ከቁጥጥር ውጭ የሆነው የአየር ንብረት መዛባት ለምርታማነት መቀነስም የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይህን መከላከል የሚቻለው ጥላ ዛፍ በሰፊው በመትከል ነው። አርሶ አደሩ ይህን እንዲያከናውን የኤክስቴንሽን ባለሙያው ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ ይገባል።
ሌላው የቡና ምርታማነትን የሚቀንሰው በሽታና ተባይ ነው። በተለይም ፍሬውን የሚያራግፍ በሽታ እየተከሰተ ነው። በዚህ ላይም ተከታታይ በሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ለችግሩ መፍትሄ እንዲገኝ ማድረግ ያስፈልጋል።
በዚህ ረገድ የወረዳው አመራር የንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት በትኩረት እየሠራ ይገኛል። በቡና ልማቱ ላይ እነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ ከሌሎች የክልሉ ወረዳዎች ጋር በንጽጽር ሲታይ በንሳ ወረዳ በተሻለ ቡና አምራች እንደሆነ አመልክተዋል።
በቅርቡ አዲስ አበባ ከተማ ላይ በተካሄደው የሽልማት መርሐ ግብርም የሽልማት መስፈርቱን አሟልተው ከተሸለሙት መካከል የበንሳ ወረዳ አንዱ እንደሆነም ጠቅሰዋል። በቡና አያያዝ፣ ከምርታማነት፣ ከግብይት አንጻርም የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገብ ከሌሎች ተሽሎ መገኘቱ ለሽልማት ካበቁት ምክንያቶች መካከል የሚጠቀስ እንደሆነ ነው ያስረዱት። የተገኘው የሜዳሊያ ሽልማት የበለጠ ምርታማ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸውና ከተሠራ የበለጠ ሽልማት እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በሰብል ልማት
በወረዳው በሰብል ልማት በ2014-2015 የምርት ዘመን በተከናወነው የመኸር ግብርና ሥራ ሶስት ሺ አራት መቶ አስራ አንድ (3411) ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ለመሸፈን ከተያዘው እቅድ ወደ ሶስት ሺ አምስት መቶ ስልሳ ዘጠኝ (3569) ሄክታር መሬት በተለያየ ዘር በመሸፈን እቅዱን ለማሳካት ተችሏል።
በወረዳው ዋና ዋና ሰብሎች ይለማሉ፤ ከእነዚህ መካከልም ጤፍ፣ቦለቄ፣ስንዴና ገብስ ይጠቀሳሉ።ምርትማነቱም ከሰብል ሰብል ይለያያል። ለአብነትም ጤፍ በሄክታር 18 ኩንታል ይገኝ የነበረውን ወደ 20 ኩንታል፣ በሄክታር 38 ኩንታል ይገኝ የነበረውን የገብስ ምርትም ወደ 44 ኩንታል ከፍ ለማድረግ ታቅዷል።
በዚህ መንገድ በአጠቃላይ ሰባት መቶ ስድሳ ዘጠኝ ሺ ስምንት መቶ ሰላሳ ሶስት (769833)ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ነው እየተሠራ ያለው። የአየሩ ሁኔታም ለእርሻ ሥራው ጥሩ በመሆኑና የሰብል ይዞታውም መልካም በሚባል ደረጃ ላይ ስለሚገኝ እቅዱ ይሳካል የሚል እምነት ተይዟል።
ወረዳው ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች አሉት። አርሶ አደሩ ወቅታዊው የኑሮ ውድነት ብዙ ያስተማረው በመሆኑ ምርታማነትን በማሳደግ ለራሱም ሆነ ለሸማቹ በቂ አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ተግቶ እየሠራ ይገኛል። ከመኸሩ በፊት በነበረው የበልግ ወቅት ለግብርና ሥራው ተስማሚ የአየር ፀባይ ባለመኖሩ ዝቅተኛ ምርት ነው የተገኘው። በተለይም በቆሎ ገና አንዱንም ሳይዘው ጠፍቷል።
አካባቢው በሰብል ልማት የሚታወቀው በበቆሎ ልማት ነው ስለሚባለውም አቶ ዘነበ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በቆሎ በቆላማው አካባቢ ወደ ሰባት ያህል በሚሆኑ ቀበሌዎች በስፋት ይመረታል። የበቆሎ ምርት ሲነሳ ጤፍ ይዘራበታል። ወደ ደጋው ደግሞ ስንዴና ገብስ ይለማል።በአጠቃላይ በወረዳው ብርዕ እና ጥራጥሬ ሰብሎች ይለማሉ።
በመኸሩ የተከናወነው የግብርና ሥራ ወደ መጠናቀቁና ምርት ወደ መሰብሰቡ እየተቃረበ ነው።ቀጣዩ የበጋ መስኖ ልማት ነው። ከዚህ አንጻር ወረዳው እያከናወነ ስላለው ተግባር አቶ ዘነበ እንዳስረዱት፤ በክልል ደረጃ በተደረገው ዝግጅት አቅጣጫ ወርዶ በወረዳው በበጋ መስኖ አንድ ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ወደ ሥራ ተገብቷል።
የመስኖ ልማቱ በአጭር ጊዜ በሚደርሱ ምርቶች እንደ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባሉት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ቢሆንም፣ ሌሎች ሰብሎችም እንዲለሙ ይደረጋል። የትኛው መሬትና ውሃ ለጥቅም ይውላል፣በውሃ መሳቢያ መሣሪያ (ጀነሬተር) ነው ወይንስ ውሃ በመጥለፍ ነው ሥራው የሚሠራው፣ማንስ ምን ይጠቀማል የሚለው የልየታ ሥራ ቀድሞ ተከናውኗል።
በወረዳው ቆላማ ክፍል የበቆሎ ምርት በመነሳቱ ለበጋው ልማት የመሬት ዝግጅት ተጀምሯል።የመኸሩ ምርት ሲነሳ ከስር ከስር የበጋው ልማት ሥራ ይቀጥላል። ለመስኖ ልማት አስፈላጊ የሆነው የውሃ አቅርቦትም በወረዳው ላይ እንደ ችግር እንደማይነሳም አመልክተዋል። ውሃ ከከርሰ ምድር የማውጣት አማራጭ በመኖሩም፣ ይህንንም በመጠቀም አነስተኛ የእርሻ መሬትም ቢሆን ለልማት እንዲውል የማድረግ አቅጣጫ ተይዟል።
የእርሻ ሥራው በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን የሜካናይዜሽን አጠቃቀምን በተመለከተም ሲገልጹ በዚህ ረገድ ወረዳው ገና ይቀረዋል ነው ያሉት። የመሬት አቀማመጡና የተበጣጠሰ የእርሻ ማሳ መኖሩ ለሜካናይዜሽን ምቹ እንዳይሆን አንዱ ምክንያት መሆኑም ትኩረቱን አናሳ አድርጎታል ይላሉ። ግን ደግሞ ወደፊት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረግ ወደቴክኖሎጂው ይገባል ብለዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሠራው ሥራ የአርሶ አደሩን ኑሮ መቀየርና የኑሮ ውድነትን ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር ወረዳው ክረምት ከበጋ በማምረት ስላለው ቁርጠኝነትም አቶ ዘነበ ሲገልጹም የተያዘው አቅጣጫ በገጠሩ ብቻ ሳይሆን የከተማ ግብርናን በማከናወን እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል። አርሶ አደሩ ቀደም ሲል የማይጠቀምባቸውን ቦታዎች ሁሉ ለልማት በማዋል እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ የግብርና ሥራውን በትኩረት መሥራት ግዴታ መሆኑን ነው ያመለከቱት። የወረዳ አስተዳዳሪው እንዳሉት፤ የሀገር ኢኮኖሚ እድገት መሠረት የሆነውን የግብርና ሥራ ማጠናከር ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2015