የታሪክ ሰነዶችን አገላብጠን፤ ከወቅት ጋር አሰናኝተን በትውስታ ያለፈን ማሳየታችንን ቀጠልን። ዛሬም በሳምንቱ ውስጥ ኢትዮጵያ ላይ ሆነው ካለፉ ዓበይት ታሪካዊ ሁነቶች ውስጥ አንዱን መርጠን ወደናንተ ለማድረስ ብዕራችን አነሳን። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቀዳሚ ሴት መሪ በመሆን ይታወቃሉ። 14 ዓመታት ኢትዮጵያን ንግሥት ሆነው መርተዋል።
ሴቶች በአመራርነት ላይ ቢሳተፉ ብቁ መሆናቸውን በነገሡበት ዘመን በሠሩት ሥራ አሳይተዋል። በአገሪቱ አዳዲስ ሕጎችን በማውጣትና በመተግበር ሕግና ሥርዓት ተግባራዊ እንዲሆን ጥረዋል። ሀገራቸውን በዓለማቀፍ ደረጃ እውቅና እንድታተርፍና ተሳትፎዋ ከፍ እንዲልም ሠርተዋል። እኚህ ንግሥት ወደ ንግሥናው የመጡት መስከረም 21 ቀን 1909 ዓ.ም ነበር። ቆራጥና ብርቱዋ ንግሥት ዘውዲቱን በዛሬ ገፃችን ልንዘክር ወደናል። የተለያ ድረ ገፆችን፣ የኢትዮጵያ ታሪክ እና የ20ኛ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ፤ በጥላሁን ብርሀነ ሥላሴ መጽሐፍትን በዋቢነት ተጠቅመናል።
እነዋሪ ከተማ ሰገነት የተባለች መንደር ተወልደው እትብታቸው የተቀበረበት ነው። ቅዳሜ ሚያዚያ 22 ቀን 1868 ዓ.ም ደግሞ ወደዚህች ምድር የተቀላቀሉበት። አባታቸው ዳግማዊ ምኒሊክ በወቅቱ የሸዋ ንጉሥ ነበሩ። በኋላም ኢትዮጵያን በንጉሠ ነገሥትነት መርተዋል። እናታቸው ወይዘሮ አብችው ጠንካራና ቆራጥ ሴት እንደነበሩ ይነገራል። ንግሥት ዘውዲቱ ለአባታቸው ዳግማዊ ምኒሊክ ሦስተኛ ልጅ ሲሆኑ ከልጅ ኢያሱ ቀጥለው መኳንንትና ሕዝቡ መክሮና ዘክሮ በምርጫ በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ የተቀመጡ ብቸኛ ንግሥትም ናቸው።
የንጉሥ ልጅ እንደመሆናቸው እድገታቸው በድሎት ነበር። በእርግጥ ገና ጉልበታቸው ሳይጠና ነበር ያገቡት። በወቅቱ ሸዋን ያስተዳድሩ የነበሩት አባቷ ዳግማዊ ምኒሊክ ከትግራይ ገዢው አፄ ዮሐንስ 4ኛ ጋር ባለመግባባት ግጭት ውስጥ በተደጋጋሚ ይገቡ ነበር። ኋላ ላይ ሁለቱ ነገሥታት ባደረጉት ስምምነት መሠረት መግባባት ላይ ደረሱ። ግንኙነታቸውንም ለማጠንከር እንዲረዳቸው አፄ ዮሐንስ አፄ ምኒሊክን ይበልጥ ግንኙነታችን ይጠነክር ዘንድ ሴት ልጅዎትን ለወንዱ ልጄ አርዓያ ሣሕለ ሥላሴ ስጡኝ ብለው ጠየቁ።
ለዚህም አፄ ዮሐንስ ራስ ገብረኪዳን፣ ራስ አሉላ እና ቢትወደድ ገብረ መስቀልን በሽምግልና ወደ አፄ ምኒሊክ ላኩ። ዳግማዊ ምኒሊክም ልጃቸው ዘውዲቱን ከአፄ ዮሐንስ ልጅ ጋር ማጋባት ፈቀዱ። በዚህም ንግሥት ዘውዲቱ የስድስት ዓመት ሕጻን ሳሉ ለ12 ዓመቱ የአፄ ዮሐንስ ልጅ አርአያ ሥላሴ ዳሩዋቸው። ከሽምግልናው በኋላ ወዲያው ድግስ ማሰናዳትና ለሠርጉ የሚሆን መሰናዶ ማድረግ ተጀመረ።
ጋብቻቸውም እጅግ በደመቀ ሁኔታ በተክሊልና በቁርባን ተፈጸመ። በዚያን ወቅት የሁለቱ ነገሥታት ልጅ እንደመሆናቸው የሠርጉም ማማርና የሽልማቱ ብዛት የተለየ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይጠቅሳሉ።
ነገር ግን የንግሥት ዘውዲቱና የአፄ ዮሐንስ ልጅ አርአያሥላሴ ጋብቻ የዘለቀው አርዓያሥላሴ እስከ አረፉበት 1880 ዓ.ም ብቻ ነበር። መቀሌ ላይ ሕይወታቸው ያረፈው የንግስት ዘውዲቱ ባል አርዓያሥላሴ የንጉሥ አፄ ዮሐንስ ቤተ መንግሥት ኅዘን አለበሰው። ከጊዜ በኋላም ደርቡሾች በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የሰሙት አፄ ዮሐንስ ለመዋጋት ወደ በጌ ምድር ጦራቸውን ይዘው ዘመቱ። ንግሥት ዘውዲቱም አብረው ዘመቱ።
ከዚያ ጦርነት በኋላ አፄ ዮሐንስና ንጉስ ምኒሊክ በተደጋጋሚ በመካከላቸው ቅሬታ እየተፈጠረ ይወቃቀሱ ነበር። በዚህም አፄ ዮሐንስ የአፄ ምኒሊክ ልጅ የሆነችውን ንግስት ዘውዲቱን በጎሐ ጽዮን በኩል ወደ አባታቸው ላኳቸው።
ከዚያ በኋላ ንግሥት ዘውዲቱ ከደጃዝማች ጓንጉል ዘገየ ጋር ተጋብተው አንድ ልጅ ወልደዋል። ልጅቷ ብዙም ሳትይቆይ በ2 ዓመቷ አርፋለች። ከደጃዝማች ጓንጉል ጋር ያደረጉት ጋብቻም ሳይፀና ቀርቶ ተፋተዋል። ቀጥሎም ከደጃዝማች ውቤ አጥናፍሰገድ ጋር ተጋቡ፤ ነገር ግን ከ4 ዓመት በላይ ሳይቆዩ ተፋቱ። መልሰው ከደጃዝማች ጉግሳ ወሌ ጋር ተጋቡ። ደጃዝማች ጉግሳ ወሌ በወቅቱ በጌምድርን ያስተዳድሩ ነበር።
ነገር ግን ንግሥት ዘውዲቱ ወደ አዲስ አበባ የሚመልሳቸው አንድ ጉዳይ ተፈጠረ። አባታቸው አፄ ምኒሊክ በፀና መታመማቸውን ሰሙ። ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ በ1901 ዓ.ም በታመሙ ጊዜ ንግሥት ዘውዲቱ ከደብረታቦር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አባታቸውን ከእቴጌ ጣይቱ ጋር በመሆን ማስታመም ጀመሩ። ለተከታታይ 6 ዓመታት ያስታመሟቸው አባታቸው በ1906 ዓ.ም መሞታቸውን ተከትሎ እጅጉን ኅዘን ዋጣቸው።
በኋላም ልጅ ኢያሱ እቴጌ ጣይቱና ንግሥት ዘውዲቱ ከቤተ መንግሥት እንዲወጡ ባልታወቀ ምክንያት ባዘዙ ጊዜ ከቤተ መንግሥት ለመውጣት ተገደዱ። ፋሌ ወደሚገኘው እርስታቸው ሄደው ተቀመጡ። ልጅ ኢያሱም ንግስት ዘውዲቱን ከሌላ ሰው ጋር ሊያጋቧቸው ብዙ ቢጥሩም በቁርባን ያገባሁት ጉግሳ ወሌ እያለ ሌላ አላገባም በማለታቸው፤ ባላቸው ከበጌ ምድር እንዲመጡና አብረው እንዲኖሩ አደ ረጉ።
በዚህ ሁኔታ ፋሌ ላይ የቆዩት ንግሥት ዘውዲቱ ወደ ስልጣን የሚመጡበት ጉዳይ ተከሰተ። እርሱም ልጅ ኢያሱ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ከስልጣን እንዲወርዱ ተፈረደባቸው። ልጅ ኢያሱ ከንግሥና ስልጣን ሲወርዱ፤ መኳንንቱና ሕዝቡ ስልጣን ለማን ይገባል በማለት መክሮና ዘክሮ አንድ ውሳኔ አሳለፈ። ዘውዲቱን ግርማዊት ንግሥተ ነገሥት፣ ራስ ተፈሪ መኮንንን አልጋ ወራሽ እና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ እንዲሆኑ ወስነው፤ መስከረም 21 ቀን 1909 ዓ.ም ዘውዲቱ “ንግሥተ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው ነገሡ።
በመኳንንቱ ምክር መሠረት ጳጳሱና እጨጌ ወልደጊዮርጊስ “ኢያሱን የተከተልክ፣ ያነገሥናትን ዘውዲቱንና ራስ ተፈሪን የከዳህ፣ ውግዝ ከመአርዮስ” እያሉ በአዋጅ አወገዙ። ከዚህ በኋላ የጥቅምቱ የሰገሌ ጦርነት ተደረገ፤ ከጦርነቱ በኋላ የዘውድ በዓሉ የካቲት 4 ቀን 1909 ዓ.ም እንዲሆን ታዝዞ፣ ለዘውዱ በዓል በኢትዮጵያ አዋሳኝ ያሉት የእንግሊዝ ሱዳንና የእንግሊዝ ሱማሌ ገዥዎች፤ የፈረንሳይ ሱማሌ ገዥ እና በኢትዮጵያም ታላላቅ ራሶች እንዲሁም የየአውራጃው ገዥዎች በተገኙበት በዕለተ እሑድ አባታቸው ባሠሩት በትልቁ ደብር በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ቅብዐ መንግስት ተቀብተው የንጉሠ ነገሥቱን ዘውድ ጫኑ።
ከዚህም በኋላ እንደ ሥርዓተ ንግሡ ሕግ፤ ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ በአባታቸው ዙፋን ተቀምጠው መንገሣቸውን፤ ደጃዝማች ተፈሪም ራስ ተብለው አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ መሆናቸውን በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት አዋጅ ተነገረ።
ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ በስልጣን ዘመናቸው የፈጸሙት ዓበይት ተግባራት
የኢትዮጵያን የዓለም መንግሥታት ማኅበር(ሊግ ኦፍ ኔሽን) አባልነት ማድረጋቸው ተጠቃሹ ነው። ንግሥቲቱ በስልጣን ላይ ሳሉ፤ የዓለም መንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ጠቅላላው ጉባዔ በፈረንጅ አቆጣጠር መስከረም 28 ቀን 1923 ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም 17 ቀን 1916 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያ አባል እንድትሆን ፈቃዱ መሆኑን ያሳወቁበት ጊዜ ነበር።
በዚያን ወቅት የኢትዮጵያው መልዕክተኛ ደጃዝማች ናደው አባልነቱ ለኢትዮጵያ መፈቀዱን በማስመልከት ከፍ ባለ ደስታ ስሜት የሚከተለውን ታሪካዊ ንግግር አድርገውም ነበር።
“ ክቡራን ሆይ!
ጠቅላላው ጉባኤ በበጎ ፈቃደኝነትና በትክክለኛ ፈራጅነት፣ በጥልቅ አስተሳሰብ መርምሮ ወደ ማኅበሩ ስለመግባት ያቀረብነውን ጥያቄ ስለ ተቀበለው፣ የኢትዮጵያ መልዕክተኞች በግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና በልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና ባለ ሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ስም፣ እንዲሁም በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋና ያቀርባሉ።
የሰውን ልጅ ወንድማማችነት የመመሥረት ዓላማ ባለው ውሳኔያችሁ የተሰማንንም ልባዊ ደስታ እንድገልጽላችሁ ይፈቀድልኝ ዘንድ እለምናለሁ። ኢትዮጵያ ባለፈው የጀግንነት ታሪክና በከፍተኛ ሥልጣኔዋ የምትኮራ ሀገር መሆንዋ፣ የዘመናዊ ድርጅቶች ከሚያስገኙላትም ፍሬ ተካፋይ ለመሆን ብርቱ ጥረትና ሙሉ ፈቃደኛነት እንዳላት የታወቀ ነው።
መንግሥታችንም ይህን ጥረት ወደ መልካም ግብ ለማድረስ የዓለም መንግሥታትን አንድነትና ኅብረት የሚያስፈልግ መሆኑን በጥብቅ ያምንበታል።” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈው ነበር። በዚህም ንግስት ዘውዲቱ ለኢትዮጵያ ዓለማቀፍ ግንኙነት ጠንካራ መሠረት የጣሉ የአገር ባለውለታ መሆናቸውን ብዙዎች ያነሳሉ።
የባሮች ነፃነት ደንብ ማውጣት
ይህ ደንብ ምንም እንኳን በወቅቱ በመኳንንቱ ባይወደድም ባሮችን ነፃ የሚያወጣና በአንፃራዊነትም ፍትሕ የሚያሰፍን ስለነበር በብዙዎች የተወደሰ ነበር። በልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን መጋቢት 16 ቀን 1916 ዓ.ም በግርማዊት ንግሥት ዘውዲቱ ፈቃድ ስለ ባሮች ነፃነት የወጣው ደንብ «ስለ ባሮች አስተዳደርና ነፃነት የቆመ ደንብ» የሚል ርዕስ ነበረው።
ይህ አብዛኛውን ኅብረተሰብ አስደስቶ የነበረ ደንብ እንደ መጽሐፍ ሆኖ በልዑል አልጋ ወራሽ ማተሚያ ቤት ታትሞ ወጥቶ ነበር። መጽሐፉ ባለ 10 ገጽ ሲሆን የደንቡ ቃል በ45 ቁጥሮች ተመድቦ የተለያዩ ውሳኔዎችንና ደንቦችን ይዞ ነበር።
በወቅቱ በወጣው ደንብ ምክንያት አንዳንድ መኳንንትና ባለብዙ ባሮች የሆኑት አንዳንድ ሰዎች በልባቸው ቅሬታ ገብቶ አዘኑ። ከዚያም ውስጥ የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ አንዱ ነበሩ።
የአፄ ቴዎድሮስ ዘውድ ማስመለስ
በቀደሙት ዓመታት ወደ እንግሊዝ ተዘርፎ የነበረውን የአፄ ቴዎድሮስ ዘውድ የማስመለሱን ሥራ የሠሩትና ያስተባበሩት ንግስት ዘውዲቱ ነበሩ። በብዙ ጥረት ከእንግሊዝ አገር የመጣው የአፄ ቴዎድሮስ ዘውድ ሐምሌ 4 ቀን 1917 ዓ.ም ቅዳሜ ለግርማዊት ንግሥት ዘውዲቱ ተመልሷል።
ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በነገሡ በ13 ዓመት ተኩል ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም በ10 ሰዓት አረፉ። የሞታቸው ዜና እንደተሰማም በከተማው የኅዘን ጥላ አጠላበት። አባታቸው ዐፄ ምኒልክ በተቀበሩበት በታዕካ ነገሥት በዓታ ቤተ ክርስቲያን ተቀበሩ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2015