በዓለማችን ከድህነት ወለል በታች እንደሆነ ከሚነገርለት ህዝብ ዘጠና በመቶ የሚገኘው በአፍሪካ ነው። የንጹህ መጠጥ ውሃ የማያገኘው የአፍሪካ ህዝብ ቁጥሩ ቀላል አይደለም። በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚኖረው አፍሪካዊም የትየለሌ ነው። በየዓመቱ የሚላስ የሚቀመስ እያጣ እንደ ቅጠል የሚረግፈውን አፍሪካዊ ቤት ይቁጠረው።
አፍሪካ በእዚህ ገጽታዋ በስፋት ትታወቅ እንጂ በጉያዋ ሸሽጋ የያዘችው ሌላም መልክ አላት።ይህን እንድል ያስገደደኝ ሰሞኑን አንድ የናይጄሪያ ባለስልጣን የተናገሩት ነገር ነው። ገንዘብ የሚያደርጉትን ያሳጣቸው ልጥጥ ናይጄሪያውያን ፒዛ ከለንድን እንደሚያዙ የተናገሩት ባለስልጣኑ በአገሪቱ ድህነት ውስጥ የሚገኙ አያሌ ዜጎች መኖራቸውን በማስታወስ፣ ሁሉም ነገር ልክ አለው አደብ ብትገዙ ይሻላችኋል ዓይነት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ከአፍሪካ ባለስልጣናት አንደበት እንዲህ ዓይነት ሃሳብ መደመጡ በራሱ አንድ ድል ነው። ለወትሮ የአገሪቱን አንጡራ ሀብት በመዝረፍ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን በውጭ ሀገር ባንኮች በማስቀመጥ ህዝቧን የሚያራቁቱትና የሚያስርቡት መሪዎቿ ነበሩ። በርግጥ ይህ የአፍሪካውያን መሪዎች መለያ ባህሪ አሁንም እንዳለ ነው።
አንድ ድርጊት «ቅንጦት» ለመባል የግድ መጋነን የለበትም። ቅንጦት ጥጉ ብዙ ነው። ዘወትር ዳቦ በሻይ ለሚበላ ሰው እንጀራ በሽሮ ወጥ መብላት ሰለቸኝ የሚል ሰው ቅንጡ ነው። በእግሩ ለሚኳትን ሰው በአንበሳ አውቶብስ መሄድ ቅንጦት ነው። ጎዳና ላይ ተኝቶ መኖርን ህይወቱ አድርጎ ለተቀበለ ሰው ሦስት ብር ከፍሎ ኬሻ በጠረባ ቤት ማደር ቅንጦት ነው። ቅያሬ ልብስ ለሌለው ሰው የሌሊት ልብስ ቅንጦት ነው። ስለዚህ ለኛ ቅንጡ ሆነው የሚታዩንሰዎች እንዳሉ ሁሉ እኛን ቅንጡ አድርገው የሚያዩን ሰዎችም አሉ፡፡
እስቲ ላፍታ ቆም ብለን አኗኗራችንን እናጢን … እኛስ አፍሪካዊም አይደልን ? እኛ በረባ ባልረባው የምንዘራው ገንዘብ ለሌሎች ወገኖቻችን መኖርና አለመኖርን ወሳኝ ሊሆን እንደሚችል አስበን እናውቅ ይሆን ? እኔ የምለው … ማካፈልና መስጠት ያለበት የሞላለትና የተረፈው ብቻ ነው እንዴ ?
ብዙዎቻችን ማንጋጠጥ እንጂ ማጎንበስ አናውቅም። የጎደለንን በማሰብ የሚበልጡንን አንጋጠን ስናይ ስለምንውል፣ ያለን አንሶናል ብልን እያማረርን ስለመጨመር ብቻ ነው የምናስበው። ጎንበስ ብለን ከእግራችን ስር ያሉትን ለማየት ያልታደልን ሆነናል። ስለዚህ ያለን ብዙ እንደሆነ ተረድተን ማመስገንና ካለን ላይ በማካፈል መደሰት አልቻልንም፡፡ አንዳንዶቻችንን ስግብግብነታችን ልክ አጥቶ አስክሮናል። ይህ እንደውም ባለውና በሞላለት ይብሳል የሚሉ አሉ። አባባሌን ግልጽ የምታደርግ አንድ ታሪክ እንካችሁ።
አንድ የተትረፈረፈ ሀብት ያለው ሰው ብልጭ ይልበትና ብድግ ብሎ ወደ አንድ ቤተ እምነት ያመራል። እንደደረሰም እግሩን መሬት እንዳይነካው ተጠይፎ ከቅንጡ መኪናው ሳይወርድ የበሩን መስታወት ዝቅ አድርጎ ከቤተ እምነቱ የሚተላለፈውን ትምህርት ማዳመጥ ይጀምራል። ትምህርቱ «ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም ለእነርሱ አድርጉላቸው» የሚል ነው። ባለሀብቱ በሰማው ነገር ፈገግ አለ። ይህን ህግ ከመፈጸም አንዳች ነገር እንደማይከለክለው እርግጠኛ ሆነ። ከዚያም ለራሱ «እኔ ሌሎች ምንም እንዲያደርጉልኝ ስለማልፈልግ ለሌሎች ምንም አላደርግም» አለ። የቅንጦት ነገር …
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2011
የትናየት ፈሩ