ከአለማችን ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነው የለንደን ማራቶን ነገ ይካሄዳል። በዚህ ውድድር በርካታ የአለማችን የርቀቱ ከዋክብት አትሌቶች በሁለቱም ጾታ የሚያደርጉት ጠንካራ ፉክክር ይጠበቃል። በወንዶች መካከል በሚካሄደው ውድድር ጀግናው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በርቀቱ ትልቅ ስም ካላቸው ከዋክብት ቀዳሚው ሆኖ ከፊት እንደሚሰለፍ ታውቋል። ቀነኒሳ ባለፈው አመት የውድድሩ አሸናፊ ከሆነው የአገሩ ልጅ ሲሳይ ለማ ጋር የሚያደርገው ፉክክር በጉጉት ይጠበቃል።
የመምና አገር አቋራጭ ውድድሮች ንጉስ የሆነው ቀነኒሳ ፊቱን ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች ካዞረ በኋላ በ5 እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ መድረኮች መንገስ የቻለው ትውልደ ሶማሊያዊው የእንግሊዝ አትሌት ሞ ፋራህ በነገው የለንደን ማራቶን ይሳተፋል ተብሎ ነበር። ይሁን እንጂ ፋራህ ከቀናት በፊት በጉዳት ምክኒያት ከውድድር ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል። በ2016 የለንደን ማራቶን ሶስተኛ፣ በ2017 ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ቀነኒሳ በተደጋጋሚ ከሚገጥመው ጉዳት ጋር እየታገለ በመምና በአገር አቋራጭ ውድድሮች የሰራውን ታሪክ በማራቶን ለመድገም ጥረት አድርጓል። በዚህም በ2019 የበርሊን ማራቶን በወቅቱ የአለም ክብረወሰን ከነበረው የኬንያዊው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ በሁለት ሰከንድ የዘገየ 2:01:41 ሰአት በማስመዝገብ ማሸነፉ ይታወሳል። ቀነኒሳ ይህን አስደናቂ ብቃት ካሳየ በኋላ በርካቶች የርቀቱን የአለም ክብረወሰን እንደሚሰብር ተስፋ ቢያደርጉም አልተሳካለትም።
ይህ የ40 አመት የምንጊዜም ድንቅ አትሌት በተለይም በ2020 የለንደን ማራቶን ክብረወሰን ያስመዘግባል ተብሎ ሲጠበቅ በመጨረሻ ሰአት በጉዳት ምክኒያት ሳይወዳደር ቀርቷል። ከዚያ በኋላም በ2021 የኒውዮርክ ማራቶን ስድስተኛ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው። ቀነኒሳ ከሶስት ሳምንታት በፊት ወደ ውድድር ተመልሶ በእንግሊዝ ግሬት ኖርዝ ረን ባደረገው የ21 ኪሎ ሜትር ውድድርም ዩጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞንና የቶኪዮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ቻምፒዮኑን ሰለሞን ባረጋን ተከትሎ ሶስተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል።
ቀነኒሳ ከሳምንት በፊት በ2019 በርሊን ማራቶን ላይ ባስመዘገበው ሰአት ሁለተኛው የርቀቱ ፈጣን አትሌት ነበር። ባለፈው ሳምንት ኪፕቾጌ ሌላ የአለም ክብረወሰን በማስመዝገቡ ግን ቀነኒሳ የሶስተኛው ፈጣን ሰአት ባለቤት ሆኖ ነው ወደ ነገው ውድድር የሚገባው።
በነገው ውድድር በዋናነት የቀነኒሳ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ባለፈው ለንደን ማራቶን አምስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው አትሌት ብርሃኑ ለገሰ ነው። ከእሱ በተጨማሪ የለንደን ማራቶንን ጨምሮ ባለፉት ሁለት የፍራንክፈርት ማራቶን ማሸነፍ የቻለው ሲሳይ ለማ ትልቅ የአሸናፊነት ግምት የቸሰጠው አትሌት ሆኗል።
በሴቶች መካከል በሚካሄደው ውድድር ያለፈው አመት አሸናፊዋ ኬንያዊት ጆይስሊን ጂፕኮስጌ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣት አትሌት ነች። ይህች አትሌት ባለፈው አመት ውድድሩን ያሸነፈችበት 2:17:43 ሰአት በርቀቱ ታሪክ ሰባተኛዋ ፈጣን አትሌት ያደረጋት ሲሆን በ2019 የኒውዮርክ ማራቶን ማሸነፏ ይታወቃል።
ኬንያዊቷ አትሌት የአሸናፊነት ግምት ቢሰጣትም ከጠንካራ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ብርቱ ፉክክር እንደሚገጥማት ይጠበቃል። ባለፈው አመት ውድድር ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ደጊቱ አዝመራውና እሸቴ በክሪ ዘንድሮ ቀላል ተፎካካሪ እንደማይሆኑ ተገምቷል።
በነገው ውድድር ሁለተኛውን ፈጣን ሰአት(2:17:23) የያዘችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ያለምዘርፍ የኋላውም ለአሸናፊነት ከታጩ አትሌቶች አንዷ ነች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2015 ዓ.ም