በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ(ሴካፋ) ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ዋንጫ ከነገ በስቲያ ይጀመራል። በውድድሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ወንዶች ብሔራዊ ቡድንም ከጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ሙሉ የትጥቅ አቅርቦት ተደርጎለታል።
ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር የማጣሪያ ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ላይም ስምንት ሀገራት በሁለት ምድብ ተከፍለው የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከነገ በስቲያ መስከረም 22/2015 ዓም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጀመራል። አንድ ቀን ቀደም ብሎ ለመጀመር መርሐ ግብር ተይዞለት የነበረው ይህ ውድድር ከተጫዋቾች የእድሜ ምርመራ ጋር ተያይዞ ያላጠናቀቁ ብሔራዊ ቡድኖች በመኖራቸው አንድ ቀን ማራዘም እንዳስፈለገም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከትናት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
ፌዴሬሽኑ በውድድሩ ላይ ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሙሉ የትጥቅ አቅርቦት ከጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ማግኘቱንም በመግለጫው ጠቁሟል። የትጥቅ አቅርቦት ስምምነቱ ሃገር በቀል የስፖርት ትጥቅ አምራች ከሆነው ጎፈሬ ጋር ሲደረግ እንደተገለፀው፣ ለብሔራዊ ቡድኑ የስፖርት ትጥቁ በነጻ መቅረቡ የተጠቆመ ሲሆን ለ25 ተጫዋቾች የሚሆን ሶስት ዓይነት የመጫወቻ ትጥቅ፣ ሁለት የመለማመጃ፣ 10 የቴክኒክ ቡድን አባላትን እንዲሁም ሌሎችንም ያካተተ ስምምነት እንደተፈረመ ተገልጿል። በዓይነት የተደረገው ይህ ድጋፍ ወደ ገንዘብ ሲለወጥም 1ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣም የጎፈሬ ስፖርት ትጥቅ አምራች ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል መኮንን ጠቁመዋል።
ከተቋሙ ጋር የስፖንሰር ሺፕ ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ስምምነቱ የሃገር ውስጥ የስፖርት ትጥቅ አምራቾችን ከማበረታታት ባለፈ ለሌሎችም መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም የልምምድ ትጥቆችን ለተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች እንዲሁም ክለቦች ሲያቀርብ የቆየው ጎፈሬ የተሟላና ጥራት ያለው ትጥቅ ማምረት በመጀመሩ በውድድሩ ላይ ለሚካፈለው ቡድን እንዲያቀርብ ተደርጋል። በዚህም ፌዴሬሽኑ በነጻ ትጥቅ ከማግኘቱም ባለፈ ገበያውን በአፍሪካ ሃገራትም በማስተዋወቅ ላይ ለሚገኘው ተቋም የገበያ እድል የሚፈጥር በመሆኑ በስምምነቱ ሁለቱም አካላት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
ስምምነቱን ተከትሎ የጎፈሬ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል መኮንን፤ ትጥቆቹ በጥራት የተዘጋጁ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ከዚህ ቀደም የማይታወቅበትን ምርቶችንም ጭምር በማምረት ለዚህ ውድድር ብቻ ብሔራዊ ቡድኑን እንደሚደግፍ ተናግረዋል። ከክለቦች ጋር በስፋት እየሠራ የሚገኘው ጎፈሬ ለብሔራዊ ቡድን ሙሉ ትጥቅ ሲያቀርብ ይህ የመጀመሪያው ነው። ፌዴሬሽኑ ለሰጠው ለዚህ እድልም ሥራ አስኪያጁ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የተቋሙ እቅድም ምርቱን በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ማስተዋወቅና ማቅረብ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አያይዘው ገልጸዋል።
ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች እና የስፖርት መርሐ ግብር መሪ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ወደ ገበያው የገባ ተቋም ሲሆን፤ ከበርካታ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ጋር ይሠራል። ከሃገር ውስጥ ለ15 ክለቦች ትጥቅ ያቀረበ ሲሆን፤ ከዚህ ባለፈም ምርቶቹን በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ዩጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዛምቢያ በመላክም ጭምር የውጪ ምንዛሪ እያስገኘ የሚገኝ ተቋም መሆኑም በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ተጠቁሟል።
ለ20 ቀናት የሚካሄደው የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድር 10 ሃገራት ይካፈላሉ ተብሎ ቢጠበቅም 8 ብቻ እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል። ሃገራቱ በሁለት ምድብ ተከፍለው የሚወዳደሩ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ምድብ አዘጋጇ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ተደልድለዋል። በሌላኛው ምድብ ደግሞ ዩጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ብሩንዲ የሚገናኙ መሆኑን መርሐ ግብሩ ያሳያል። በዚህ ውድድር ላይ ተካፋይ የሚሆኑት ሃገራትም አስቀድመው ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ይገኛሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2015 ዓ.ም