አባቴ ባርኔጣ ሲያደርግ አልወድም። አንድም ቀን ግን የአባቴን ራስ ያለባርኔጣ አይቼው አላውቅም። ተወልጄ እቅፉ ውስጥ ቦርቄ፣ ዩኒቨርሲቲ እስከላከኝ ቀን ድረስ አባቴን የማውቀው በባርኔጣ ነው። ለብሶና ዘንጦ በዛ ሽቅርቅርነቱ ላይ ባርኔጣውን ሲደፋ ሞገሱ ይሰወርብኛል። አባቴን ያለባርኔጣ ለማየት ያላደረኩት ጥረት የለም። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ከነባርሜጣው ነው የግቢያችንን አበባዎች ውሀ እያጠጣ የማየው። ማታም ከነባርሜጣው ብቻውን ትቼው አጠገቡ ላይ እንቅልፍ ያዳፋኛል። አባቴን ያለባርኔጣ እንዳየው ብዬ ጠዋት ከእንቅልፌ ነቅቼ ወደመኝታው ሄጄ አውቃለሁ..ግን አይቀናኝም። ባርኔጣው ከጭንቅላቱ ጋር አብሮ የተሰፋ ይመስል ከነባርሜጣው አገኘዋለሁ። አንዳንዴ አብሬው ካልተኛሁ ብዬ አለቅስና አብሬው እተኛለሁ..የአባዬን ሁኔታ ለማየት ብዬ እንቅልፍ እያዳፋኝ ብዙ እቆያለው..ግን መጨረሻውን ሳላይ በእንቅልፍ ተሸንፌ ራሴን አጠገቡ ተኝቼ አገኘዋለሁ። ጠዋት አጠገቤ መጥቶ ከእንቅልፌ የሚቀሰቅሰኝ ከነባርሜጣው ነው።
አንድ ቀን..ነፍሳባታችን ቤት መጡ። ሁላችንም መስቀል መሳለም ስለነበረብን በተዋረድ ቆምን። መጀመሪያ አባዬ ከዛ እማዬ ..ከእማ ቀጥሎ አጎቴ መጨረሻ ላይ እኔ ቆምኩ። የኔ አይን አባቴ ባርኔጣውን አውልቆ ነው ሳያወልቅ የሚሳለመው የሚለውን ማየት ነበር። እውነት ለመናገር እንደዛ ቀን አዲስ ነገር ለማየት የናፈኩበት አጋጣሚ አልነበረም። አባቴን በልቤም በነፍሴም ጠበኩት። ያን ቀን ዛሬም ድረስ በሚገርመኝ ሁናቴ አባቴን ያለባርሜጣ አየሁት። ባርሜጣውን አውልቆ ተሳለመ። አይኔን ከታች ወደላይ ኣሽቀንጥሬ ብርቅ የሆነብኝ የአባቴ ራስ ላይ እስካደርሳቸው ድረስ አባቴ የአባን መስቀል ስሞ ባርኔጣውን ጭንቅላቱ ላይ ደፋ። አይኔ ሜዳ ላይ ቀረ። ያ ቀን አባቴን ለአንድ ጊዜ..የምን ለአንድ ጊዜ አፍታ ለማትሞላ ቅጽበት ያለባርሜጣ ያየሁበት ቀን ሆነ። ያቺ ቀን አባቴን ያለባርሜጣ በማየቴ ብቻ የሕይወቴ አዲስ ቀን ሆና አለፈች። ዛሬም ድረስ የሕይወትሽ አዲስ ነገር ምንድነው ላለኝ ያን ቀን አባቴን ያለባርሜጣ ማየቴ ስል እመልሳለሁ። አባዬን ያለባርሜጣ ለማየት ስል ቄሱ እኛ ቤት በየጊዜው በመጡ ስል ስመኝ ነበር። ግን በዓመት አንድ ጊዜ ነበር የሚመጡት..ወይም እኔ ተኝቼ ባንቀላፋሁበት ቤታችንን ጸበል ለመርጨት ይመጣሉ። ያኔ በእናቴና በአባቴ ታጅበው ቀዝቃዛውን ጸበል ፊቴ ላይ ሲቸልሱት..ከእንቅልፌ እመነጠቃለሁ። አባዬን ቄሱ ፊት በጸበል ርሶ ሳየው..ባርሜጣውን እውልቆ የተሳለመባትን ቅጽበት ባለማየቴ እቆጫለሁ።
አባቴን ያለባርሜጣ የማየት ፍላጎቴ አልቆመም። ቀን በቀን በረታ እንጂ። አንድ ቀን አባቴ የበዓል ጠላ ጠጥቶ የሰከረበትን ቀን ጠብቄ ወደ ክፍሉ ዘው አልኩ። እኩለ ቀን ነው..አይነቃም ብዬ ያሰብኩበት ቀን። ሲያንኮራፋ ይሰማኛል..በዛ ውድቅት ሌሊት አባቴን ከነባርሜጣው ካገኘሁት ለዘላለም ሲገርመኝ ይኖራል እያልኩ ነበር። እናባዬ ሲተኙ በር ስለማይዘጉ በተከፈተው በር አልፌ ወደ አባዬ አቀናሁ። እንደፈራሁት ከነባርሜጣው አልነበረም። ለዘላለም በሚመስል የጊዜ ርቀት ያላየሁትን የአባቴን ራስ ያለባርሜጣ አየሁት። እውነት አልመሰለኝም..እንደ ቶማስ ካልነካሁ አላምንም ብዬ ወደ አባቴ ሌጣ ራስ ተንደረደርኩ። በራ ራሱ ብርቅ ሆኖብኝ ለመሳም በቀረበ መልኩ ተጠግቼ አየሁት። አባቴን ያለባርሜጣ አየሁት..ለመጀመሪያ ጊዜ። በአባቴ መላጣ ራስ ላይ ግን አንድ ነገር አየሁ..‹መዐዛ› የሚል ንቅሳት። አባቴ አይነቃም ብዬ ባሰብኩበትና በተሳካልኝ በዛ ውድቅት ሌሊት ሌላ ሀሳብ ሰንቄ በተደናበረ ርምጃ ወደ መኝታ ክፍሌ ተፈተለኩ። ያን ሌሊት ሳልተኛ አሳለፍኩት..ውዬ ማደር አልቻልኩም። ሲነጋ በእንቅልፍ ጥማት የተጎለጎሉ አይኖቼን ይዤ አባቴ መላጣ ላይ ስላየሁት የሴት ስም እናቴን ልጠይቅ ድምጽዋን ወደሰማሁበት ሄድኩ። ከመቼው እንደነቃች እንጃ ማግስቱ ጾም የሆነውን በዓል በሽሮ ለማሳለፍ ጭኗ ላይ ትሪ አስቀምጣ ምስር እየለቀመች አገኘኋት። አባቴ ማታ የጠጣው የበዓል ጠላ ደብቶት ይሁን እንጂ አልተነሳም።
አይኖቼን በመዳፌ እያሻሸሁ ‹ሰናይት? አልኳት። በስሟ ነው የምጠራት።
ቀና ብላ አየችኝ..
አልተግደረደርኩም..አልተርበተበትኩም..ወዲያ ወዲህ አላልኩም ‹መዓዛ ማናት? አባዬ መላጣ ላይ..› ብዬ ሳልጨርስ እንቅልፍ ያባባው ጉንጬ ላይ አንድ ጊዜ በጥፊ ደረገመችልኝ። ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ..ብዙ አይነት ቀለማት አንጃበቡብኝ። እናቴ እኔን ልትመታ እጆቿን ስታሰላ ጭኗ ላይ ያለው ትሪ ተደፋና ምስሩ ፈሰሰ። እሷ ወደ ምድር ስታቀረቅር እኔ የተመታ ጉንጨን ይዤ ከአጠገቧ ሸሸሁ። ሌላ ሀሳብ..ሌላ ትካዜ ተፈጠረብኝ። በስንት ጥረትና በስንት ዘመኔ የአባቴን መላጣ ባይ የእናቴ ጥፊ ትርጉሙ አልገባህ አለኝ። ያን እለት በማላውቀው ምክንያት በጥፊ መመታቴ የአባቴ መላጣ የሆነ ሚስጢር እንዳለው እንዳስብ አደረገኝ። ብዙ ቆይቼ ግን አንድ እውነት ላይ ደረስኩ። መዓዛ የአባቴ የመጀመሪያ ፍቅረኛ ነበረች። ጭንቅላቱ ላይ ስለተነቀሳት እናቴ ስለምትቀና ከእናቴ ሽሽት ባርሜጣ እንደሚያደርግ ደረስኩበት። ሌላም እውነት ላይ ደረስኩ እኔ ተወልጄም ሆነ ሳልወለድ እኛ ቤት እማዬና አባዬ የሚጣሉት አባቴ ባርሜጣ ሳያደርግ ቀርቶ እናቴ መዓዛ የሚለውን ስም ስታይ ነበር።
………አባቴ በዛ ባርሜጣ ከሰፈር አባቶች ሁሉ ልዩ ነው። ባርሜጣ የሌለው ራሱ እንደናፈቀኝ ዩኒቨርስቲ ገባሁ። ዩኒቨርስቲም ገብቼ የአባቴ ባርሜጣ አለቀቀኝም። ከሚያስተምሩን አምስት መምህራኖች ውስጥ ሶስቱ ባርሜጣ የሚያደርጉ ነበሩ። በጣም የሚገርመው ደግሞ ከነዛ ሶስት ባለባርሜጣዎች ውስጥ ትቸር ጋሹ የሚባሉት መምህራችን ልጄን ትመስይኛለሽ ማለታቸው ነበር። ዘወትር ክፍል በገቡ ቁጥር ‹ልጄ የታለች? ማለት ከሚወዱት ትኩስ ቡና ቀጥሎ አፋቸው ላይ የሚጠማቸው ወሬ ሆነ። እኔም አውቄ ይሁን ሳላውቅ አባትነታቸውን አምኜ መቀበል ጀመርኩ። ብዙ ነገራቸው ቤት ትቼው ከመጣሁት እውነተኛ አባቴ ጋር ይመሳሰል ነበር። እየቆየሁ ስሄድ የእውነትም አባቴን ይመስሉኝ ጀመር። በእሳቸው አባትነት እውነተኛውን አባቴን እየረሳሁት መጣሁ። በቀን አስር ጊዜ ድምጹን ካልሰማሁ ሰላም የማይሰማኝን አባቴን በሳምንት አንድ ቀን ብቻ አገኘው ጀመር። አንዳንድ ጊዜ መምህርነታቸውን ረስቼ እንደ እውነተኛ አባቴ እባጥጥባቸው ነበር።
ክፍል ውስጥ፣ ግቢ ውስጥ ሁሉም ሰው አባትና ልጅ አድርጎ ተቀበለን። በዛ ሁሉ የአባትና ልጅ ግንኙነታችን ውስጥ የጎንደር ልጅ ከመሆኔ ባለፈ አንድም ቀን ስለቤተሰቦቼ ጠይቀውኝ አያውቁም። እንኳንም አልጠየቁኝ እላለሁ። ቢጠይቁኝ ምን እላቸው ነበር? አባቴ እንደ እርሶ በባርኔጣ ተኝቶ የሚነቃ ነው። ዘመኔን ሙሉ እጁ ላይ ስቦርቅ፣ ክንዱ ላይ ስዘል ሌጣ ራሱን አይቼው አላውቅም። ዛሬ ደግሞ ቁርጥ አባቴን የሚመስሉ ርሶ ላይ ወደኩ አልላቸው ነገር።
ከአምስት ዓመት የተማሪነት ሕይወት በኋላ ተመረኩ። አመራረቄ ለኔም ለታሪኬም እንግዳ ነበር። የምርቃቴ ቀን በሁለት ባርሜጣ ባደረጉ አባቶች ተከብቤ ተመረኩ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2015 ዓ.ም