ፍሬ ነገሩ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 በሚገኙት ህጻን ዓለም አፀደ ህጻናት እና አምስት ኪሎ አፀደ ህጻናት በሚያስተምሩ በመምህራን እና የሸማች ህብረት ሥራ ማህበር መካከል የተፈጠረ አለመግባባትም የሚመለከት ነው። ይህን ጉዳይ ከሁለት ወር በፊት ‹‹ወደ መጠጥ ቤት የተቀየረው ትምህርት ቤት ውዝግብ›› በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ማቅረባችን ይታወሳል። ታዲያ ከዚህ ዘገባ በኋላ ምን አዲስ ነገር አለ? ስንል ወደ ክፍለ ከተማው እና ወረዳው በማቅናት የሚመለከታቸውን የስራ ኃላፊዎች በማናገር ተከታዩን መረጃ አጠናቅረናል።
ቅሬታ አቅራቢ መምህራን
በወቅቱ በደል ተፈጽሞብናል ሲሉ አቤቱታ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የሚገኙት ህፃን ዓለም አጸደ ህጻናት እና አምስት ኪሎ አፀደ ህጻናት መምህራን ነበሩ። «በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የሚገኘው የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር በ2004 ዓ.ም በአደራ ከተረከባቸው ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነውን ህጻን አለም አፀደ ህጻናት ማስተማሪያ ህንጻ ወደ መጠጥ ቤት በመቀየር ተማሪዎችን ከመበተኑ ባለፈ መምህራንንም ላልተጋባ እንግልት ዳርጓል።
በወቅቱ ሸማች ማህበር በአደራ የተረከበውን የአምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት የሚያስተምሩ መምህራንን ጥቅማ ጥቅም በመከልከል እና መምህራንን አሰላችቶ ትምህርት ቤቱን ለቀው እንዲሄዱ በማድረግ የትምህርት ቤቱን ህንጻ ለግል ጥቅም ለማዋል በማሰብ በደል እየፈጸመብን ነው» ሲሉ ነበር። ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ቅሬታቸውን ያስረዱት፡
ከአቤቱታ አቅራቢዎች መካከል መምህርት ዓለም ጌታቸው አንዷ ነበሩ። በህጻን ዓለም ትምህርት ቤት መምህርት ናቸው። በትምህርት ቤቱ ለ30 ዓመታት ያህል መሥራታቸውም ይታወቃል።
ከ2004 ዓ.ም በፊት ህጻን ዓለም ትምህርት ቤት የህዝብ ትምህርት ቤት እንደነበርና በ2004 ዓ.ም በወጣው መመሪያ መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ እና ህዝብ ያስተዳድራቸው የነበሩ ትምህርት ቤቶች በመንግስት አስተዳደር ሥር እንዲሆኑ ተወሰነ። ይህን ተከትሎ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ይገኙ የነበሩ በርካታ የህዝብ ትምህርት ቤቶች መንግስት እንዲያስተዳድራቸው ሆነ ይላሉ መምህርት- ዓለም ጌታቸው።
ይሁን እንጂ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ከሚገኙ የህዝብ ትምህርት ቤቶች መካከል ህጻን አለም አጸደ ህጻናት እና የአምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት ምክንያቱ ባልተወቀ አግባብ ለሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበር በአደራነት ተሰጡ። ትምህርት ቤቶች ለማስተዳደር በአደራ የተቀበሉት አካላት ስለሙያው ግንዛቤ የሌላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እያደር የትምህርት ቤቱ ህልውና ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ መጣ። መምህራኑ በትምህርት ቤቱ መምህራን እና ህጻናት የሚፈጸሙ ሁሉም አስተዳደራዊ በደሎች ከነገ ዛሬ ይሻሻላሉ በማለት በተስፋ በመስራት ላይ ሆነው የወረዳ 6 የሸማች ማህበር የህጻን አለምን አጸደ ህጻናትን ህንጻ ለማደስ በሚል ሰበብ መምህራን ሙሉ ተማሪዎቻቸውን ይዘው ወደ አምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት እንዲቀላቀሉ መደረጉንም ይናገራሉ።
ወደ አምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት ተደርበው እንዲሄዱ ሲደረግ የትምህርት ቤቱ ህንጻ የቤቱ እድሳት እስከሚያልቅ ተብለው እንደነበር የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዋ፤ ይሁን እንጂ የህንጻው እድሳት ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ነበሩበት ህጻን ዓለም አጸደ ህጻናት እንዲመለሱ ሸማቾችን ቢጠይቁም ለዓመታት ትውልድን ሲቀርፁበት የነበረው ትምህርት ቤት ‹‹ለመጠጥ ቤት አገልግሎት መዋሉን›› እንደተነገራቸው ያስረዳሉ።
እንደ አቤቱታ አቅራቢዋ ገለጻ ፤ እስካሁን ድረስ ደመወዝ የሚከፈላቸው በህጻን ዓለም ትምህርት ቤት ሥም ነው። ለመከላከያ እና መሰል ሀገራዊ ግዳጆች መዋጮ የሚያደርጉትም በህጻን አለም አጸደ ህጻናት ስም ነው። በህጻን ዓለም አጸደ ህጻናት ሆነ በአምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት ትምህርት ቤት ሲሰሩ የሚከፈላቸው ደመወዝ በመንግስት ትምህርት ቤት ከሚሰሩ መምህራን እጅጉን ያነሰ ነው፤ የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዋ፤ የመምህራን ጥቅማ ጥቅም የሚባል ነገር ፈጽሞ እንደማይታሰብ ያስረዳሉ።
እንደ መንግስት መምህራን የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው እና ጥቅማ ጥቅሞችም እንደከበሩላቸው በተደጋጋሚ መጠየቀቻውን የሚናገሩት መምህርቷ ፤ እናንተ አክሳሪ እንጂ አትራፊ ስላልሆናችሁ ደመወዝ አይጨምርላችሁም የሚል መልስ ከሸማቾች እንደሚሰጣቸው መናገራቸውንም የዝግጅት ክፍላችን ዘግቦት ነበር።
አቤቱታ አቅራቢዎቹ እንደሚናገሩት፤ በመንግስት ትምህርት ቤት የሚያስተምሩና በአቻ ደረጃ የሚገኙ መምህራን የቤት አበል እስከ 3ሺብር ፣ የትራንስፖርት ( ፐብሊክ ሰርቪስ እና አንበሳ አውቶቡስ) እንዲሁም ደመወዛቸው ደግሞ ከ10 ሺህ ብር በላይ ሲሆን የእርሳቸው ግን 30 ዓመታትን በማስተማር አሳልፈው በወር ያልተጣራ ሦስት ሺህ ብር ብቻ እንደሚከፈላቸው ይናገራሉ።
ይህም የኑሮ ውድነቱን ያላገናዘበ ከመሆኑም ባሻገር ሞራል የሚነካ ድርጊት መሆኑን ያስረዳሉ። «ስለሆነም በእኛ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ መንግስት እና የኢትዮጵያ ህዝብ ይመልከትልን» ሲሉ ተናግረው ነበር።
ለመምህራን ቅሬታ የተሰጠው ምላሽ
ታዲያ ይህ ቅሬታ ለዓመታት ሲንከባለል የነበረ ቢሆንም መፍትሄ ለመስጠት በቂ ጥረት አለመደረጉን የሚናገሩ አሉ። ሆኖም በቅርቡ የሥራ ኃላፊዎች በአሁኑ ወቅት ያለውን የኑሮ ውድነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ጭማሪ መደረጉን ይናገራሉ። በዚህም መሰረት ለመምህራኑ በአማካይ ከ200 ብር እስከ 1000 ብር ጭማሪ ተደርጓል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 06 ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ አጌና እንደሚሉት፤ መምህራን በተከታታይ ሲያቀርቧቸው በነበረው ቅሬታ ላይ መጠነኛ ምላሽ ያገኙ ቢሆንም አሁንም ጥያቄያቸው ሙሉ ለሙሉ አለመመለሱን ያብራራሉ።
መምህራን የደመወዝ ጭማሪ ቢደረግላቸውም አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ አይደለም በሚል ቅሬታ እንዳላቸው ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርት ቤቱን ወደ ቀድሞ ስራው በአግባቡ ለመመለስና አስተዳደራዊ ጉዳዮችንም በአግባቡ ለመምራት የሚችል አመራር የለም የሚለው የመምህራን ቅሬታ አሁንም አለ።
በተለይም በሸማቾች መተዳደሩ የመምህርነት ሙያን ከአገልግሎት አኳያ ሳይሆን በሌላ የንግድ ዕይታ እንዲዳኝ የተዛባ እይታን እየፈጠረ ነው የሚለው ቅሬታ አሁንም መኖሩን ያብራራሉ።
በአራዳ ክፍለ ከተማ የህብረት ሥራ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል እስማኤል በበኩላቸው፤ ትምህርት ቤቱን ሆነ መምህራን በተመለከተ አሁንም ቢሆን ያልተፈቱ ጉዳዮች ቢኖሩም የተወሰነ የመፍትሄ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ይገልፃሉ። የኑሮ ውድነቱን ከግምት ውስጥ በማስገባት የደመወዝ ጭማሪ የተደረገ ሲሆን፤ በሂደት የሚስተካከሉ ጉዳዮች እንደሚኖሩም ይናገራሉ።
በሌላ ጎኑ ግን በሸማቾች የሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው ላይ የሚቀርበው ቅሬታ አግባብ አለመሆኑንና ይህ የመንግስት ፖሊሲ አቅጣጫ እንጂ የግለሰቦች ፍላጎት አለመሆኑን ያብራራሉ። ይህም የሆነው በመንግስትና በግል ክፍለ ኢኮኖሚ የሚመሩ ትምህርት ቤቶች ውጭ በሸማቾች የሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው እንደ አማራጭ የመጡ እንጂ የቅሬታ ምንጭ መሆን የለባቸውም ባይ ናቸው።
ይህ በሌላውም ዓለም የተለመደ ከመሆኑም በተጨማሪ ከአራዳ ውጭ በሌላው ክፍለ ከተማም መኖሩን በመጠቆም የአራዳ ክፍለ ከተማ የተለየ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ይላሉ። በአጠቃላይ ግን ለመምህራን፣ ወላጆችና ነዋሪዎች ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት አማራጮችን ሁሉ እንደሚመለከቱና ለመፍትሄውም እንደሚተጉ ገልፀዋል።
አቶ ጀማል እስማኤል አያይዘውም ትምህርት ቤቱ ወደ መጠጥ ቤት ከተቀየረ አንድ ዓመቱ ነው። እኔ ደግሞ ወደ ቦታው የመጣሁት እነዚህ ሁኔታዎች ከተከሰቱ በኋላ ነው። ይሁንና ትምህርት ቤቱ ያለበት ሁኔታን በወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት በኩል ያልተወደደ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እስከመሆን ስለመድረሱ ይናገራሉ።
ይህን መረጃ እንደሰማሁ ይላሉ አቶ ጀማል፤ ጉዳዩን ለማጣርትና መማር ማስተማሩ ለምን እንደቆመ ለማጣራት በኮሚቴ ለማየት ሞከርን። መጀመሪያ ትምህርት ቤቱ ዕድሳት በሚል ሰበብ፤ ሥራ ማቆሙንና ይህንን ዕድሳት ለማከናወንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዚም ቢሮ ቤቱ ቅርስ ስለሆነ ማሳደስ እንደሚፈልግ አሳወቀ። በዚህም የተነሳ እድሳቱ ተደረገ። ይሁንና ከእድሳቱ በኋላ የቢሮ ኃላፊ ሥምና ፊርማ የወጣ ደብዳቤ የተፃፈ ሲሆን መማር ማስተማር ሂደቱን መቀጠል እንደሌለበት አስታወቀ። በቀጣይ ሌላ አገልግሎት የሚሰጥና ጥበቃ የሚያስፈልገው ስለመሆኑም አዘዘ።
ታዲያ ይህን ጉዳይ በመረዳት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግር የጀመሩት አቶ ጀማልና የክፍለ ከተማው የስራ ባልደረቦቻቸው በኋላ ግን ለመማር ማስተማር እክል የሚሆን ነገር አለመኖሩን ማረጋገጥ መቻሉን ይናገራሉ። የሚማሩበት ህፃናት ስለመሆናቸውና ለአደጋ አለመጋለጡን ከሚመለከታቸው አካላትበጋር በመሆን ማረጋገጥ መቻሉንና በረጅም ዓመታት የመጣበት መማር ማስተማር ሂደቱን ማስቀጠል እንደሚቻል በመተማመን በ2015 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንዳለበት ሥምምነት መደረጉንና ከሃምሌ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
ከሁለት ዓመት በላይ የተዘጋው ትምህርት ቤትም ወደ ሥራው ይግባ በሚለው ሃሳብ ላይ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አሁንም መንግስት የሚሰጠንን አቅጣጫ ይዘን ለመሥራት ችግር የለብንም የሚል ምላሽ እንደነበርም አቶ ጀማል ያስታውሳሉ።
ሌላው ፈተና
ቀድሞ ትምህርት ቤት የነበረው ወደ መጠጥ ቤት ከተቀየረ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ቁሙናው የድራፍትና አልኮል መሸጫ እንጂ ትምህርት ተቋም መሆኑ ተዘንግቷል። ከመሰረተ ልማቶቹ መጓደል በበለጠም አሁን ትምህርት ቤቱ የያዘው ቁመና ወይንም ከውስጥ ያሉት መሰረተ ልማቶች ያው ቀድሞ እንደነበሩት የመዝናኛ ስፍራ ናቸው። ይህን ለማስተካከል የተወሰደው እርምጃም እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አላመጣም። በተለይም ለህፃናት የሚስማማ ምህዳር በማድረግ ረገድ ብዙ ሥራ የሚቀረው ስለመሆኑና አሁንም ቢሆን 10 ተማሪዎችን ብቻ ይዞ ለመቀጠል አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉ። ሌላው ቀርቶ ውስጡን መከፋፈልና የህፃናት መማሪያ ስፍራ ማስመሰል አልተቻለም።
በሌላ ጎኑ ደግሞ በወረዳው 120 ህፃናት የሚማሩበት ስፍራ አጥተው ወላጆች በየቀኑ በየትምህርት ጽህፈት ቤቱ ደጅ እየጠኑ ነው። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ደግሞ እንደ ከተማ አስተዳደር ከመስከረም
9 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም ተማሪ በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት አለበት በሚል መማር መስተማር ሥራውን በይፋ ጀምሯል። በዚህም በርካታ ትምህርት ቤቶች ሥራቸውን በአግባቡ እያከወኑ ነው። ይሁንና ህጻን ዓለም የሚባለው ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ይቅርና ገና አሁንም ተመዝገቡ ብሎ ተማሪዎችን እየቀሰቀሰ ወላጆችንም እያግባባ እና እየወያየ ይገኛል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 6 ትምህርት ጽህፈት ኃላፊ አቶ አቶ አበራ አጌና፤ በወረዳው ያለው የአጸደ ህጻናት ፍላጎት እና ያለው ተደራሽነት አይመጣጠንም። ይህንንም ተከትሎ በፈረቃ ለማስተማር የተገደዱባቸው ጊዜያት እንደነበሩም ያስታውሳሉ።
አወዛጋቢ ደብዳቤዎች
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ለትምህርት መስተጓጎልም ሆነ ትምህርት ቤቱ ወደ መጠጥ ቤትነት ሲቀየር የራሱ ድርሻ ያለው ሲሆን፤ አወዛጋቢ የሆኑ ደብዳቤዎችን ሲፅፍ ነበር።
ለአብነትም መስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም ለአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ የፃፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል። ጉዳዩ ‹‹የህፃን ዓለም ታሪካዊ ቅርስ ቤትን ይመለከታል›› በሚለው ደብዳቤው፤ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ‹‹የህፃን ዓለም ታሪካዊ ቅርስ ቤትን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ጥገናና እድሳት እንዲያገኝ ማድረጉ ይታወሳል።
በመሆኑም ታሪካዊ ቅርስ ቤቱ በቅርስ አዋጅ መሰረት ቀድሞ ይሰጥ የነበረው የመማር ማስተማር አገልግሎት መስጠት ስለማይገባው እና የቅርሱም ደህንነት አደጋ ላይ ስለሚጥል ለቱሪስት መስህብነት አገልግሎት እንዲውል ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲቻል በእናንተ በኩል ታሪካዊ ቅርስ ቤቱን ከሚያስተዳድረው ወረዳ 06 ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ጋር በመነጋገር ታሪካዊ ቅርስ ቤቱ ነፃ የሚሆንበትን መንገድ እንድታመቻቹ ስንል እናሳውቃለን›› ሲል ለአራዳ ክፍለ ከተማ ባህል፤ ኪነጥበብና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት፣ ለባህል ዘርፍ ምትል ቢሮ ኃላፊ ብሎም ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት በግልባጭ አሳውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ለአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር እና ለወረዳ 06 አንድነት ቀበሌ11/12 ሸማች ሕብረት ስራ ማህበር በፃፈው ደብዳቤ፤ ‹‹ጉዳዩ የህፃን ዓለም አፀደ ህፃናት ታሪካዊ ቅርስ ቤት ጥገና እና እድሳት ሥራ መጠናቀቁን ስለመግለፅ›› በሚል የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የህፃን ዓለም አፀደ ህፃናት ታሪካዊ ቅርስ ቤትን በጀት በመመደብ ጥገና እና እድሳት እንዲያገኙ መድረጉ ይታወቃል። ታሪካዊ ቅርስ ቤቱ በቢሮ እና በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ እየተደረገለት የጥገና ሥራው በባለሙያዎች ተረጋግጦ በመጠናቀቁ የሳይት ርክክብም የጥገና ሥራውን ሲያከናውን ከነበረው ተወለ እና ብርሃን ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር ተፈጽሟል ይላል።
በመሆኑም ይህ የህፃን ዓለም አፀደ ህፃናት ታሪካዊ ቅርስ ቤት ቀድሞ ይሰጥ የነበረውን የመማር ማስተማር አገልግሎት ለቅርሱ ደህንነትና ጥበቃ ለመማሪያ ተግባር መዋል ስለማይገባው ቅርሶች ተጠግነውና እንክብካቤ ተደርጎላቸው የቅርስ አዋጁ በሚያስቀምጠው አገልግሎት ላይ ብቻ መዋል ስለሚገባቸው የከተማ አስተዳደሩ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ በማንና ለምን አገልግሎት ማዋል እንደሚገባው እስከሚገልጽ ድረስ እንድትጠብቁ ስንል እናሳስባለን›› ሲል በግልባጭ ለቅርስ ጥበቃና ባለስልጣን፣ ለአራዳ ክፍለ ከተማ ባህል፤ ኪነጥበብና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት፣ ለህፃን ዓለም አፀደ ህፃናት ትምህርት ቤት፣ ለባህል ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ብሎም ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት በደብዳቤዎቹ በግልባጭ ማሳሰቡ ይታወቃል።
ዳሩ ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እነዚህን ደብዳቤዎች ቢጽፍም እንደተባለው ሆኖ አልተገኘም። ታድሷል የተባለውና ቅርስ የተባለው ቤት እንደተባለው ለቱሪስት መስህብ አልዋለም። ይልቁንም ህፃናት እንዳይማሩበትና የመማር ማስተማር አገልግሎት መስጠት እንደማይችል
በማሳሰብ ትምህርት እንዳይሰጥበት አድርጓል በደብዳቤው መሰረት። በሌላ ጎኑ ግን በዚህ ታሪካዊ ነው ብሎ ባሳወቀውና 300 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ ዕድሳት በተደረገለት ቤት አዋቂዎችና ወጣቶች ድራፍት ሲጠጡበት እና እንደልባቸው ሲንፈላሰሱበት ማስቆም ሆነ ለመከላከል ያደረገው ጥረት የሚያሳይ መረጃ አላገኘንም። በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊነቱን በአግባቡ ስለመወጣቱ አጠራጣሪ ያደርገዋል።
አሁናዊ ፈተናዎች
አቶ አበራ አጌና በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 06 ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንደሚሉት፤ ትምህርት ቤቱ ከዚህ ቀደም የቆየው መጠጥ ቤት ሆኖ ነው። በዚህም የተነሳ ከውስጥ የነበሩት መማር ማስተማር መሰረተ ልማቶች ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ከጥቅም ውጭ የሆኑ ናቸው። በዚህም የተነሳ አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር አስቸጋሪ ያደርገዋል የሚል እምነት አላቸው።
በተለይም ህንፃው በትምህርት ቤት ‹‹ፎርማት›› የተዘጋጀ እና ህጻናትን ያስተናግድ የነበረ ቢሆንም፤ አሁናዊ ገጽታው ግን መጠጥና የመጠጥ ቤት ተክለ ቁመና የያዘ ነው። ከወንበሮቹ ጀምሮ ለህፃናት የሚመቹ አይደሉም። ይህን ሙሉ ለሙሉ አስተካክሎ ወደ ሥራ ማስገባቱ አስቸጋሪ እንደሚሆንም ይናገራሉ።
የተማሪዎች ምዝገባ ይከናወን ተብሎ ቅስቀሳዎች ቢደረጉም እስካሁን ድረስ ከ10 የማይበልጡ ተማሪዎች ብቻ መመዝገባቸውን ነው የሚናገሩት። ታዲያ ትምህርት ቤቱ ቀደሞ ከነበረው ጥሩ ሥም ዝና ባሻገር በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ 10 ተማሪዎች ብቻ መመዝገባቸው የችግሩን ጥልቀት ያሳያል ይላሉ። አሁንም ቢሆን ችግሩን የመፍታት ፍላጎት ያለ ቢመስልም ለወላጆች፣ ሰራተኞች፣ መምህራንና ተማሪዎች ሁነኛ መፍትሄ ባለመቀመጡ ትምህርት ቤቱን እንደ ቀድሞው ትምህርት ቤት ማሰኘት አስቸጋሪ መሆኑንና ለዚህም ጠንክራ ሥራ መስራት ይጠበቃል የሚል ሃሳብ አላቸው።
አቶ ጀማል እስማኤልም የአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 06 ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊን ሃሳብ ይጋራሉ። ትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሥራውን ካቆመ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ወደ መዝናኛ ሥፍራነት በመቀየሩ መሰረተ ልማቶቹ ተጓድለዋል። በአሁኑ ወቅትም ሙሉ ለሙሉ የተሟላ አይደለም። ይሁንና ከነችግሮቹም ቢሆን ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር አለበት የሚለው ሃሳብ ግን ቅቡል መሆን አለበት ብለው ያምናሉ።
ቀደም ሲል የነበረው የትምህርት ቤቱ ቁሳቁስ ወደ ሌላ ቦታ መጓጓዙንና ይህን የማስመለስ ስራ አልተከናወነም። የተጓደሉትንም ሙሉ ለሙሉ መግዛት አልተቻለም። ትምህርት ቤቱ ወደ ሥራው እንዲመለስ ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ የነበሩ ግለሰቦችና ወላጆችም ከንግግር ባለፈ በተግባር እዚህ ግባ የሚባል ነገር አላደረጉም። ታዲያ ምንም እንኳን ነገሮች የተወሳሰቡ ቢሆንም በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ሆኖም ቢሆን ግን በ2015 ዓ.ም ተማሪዎችን ተቀብሎ እንዲያስተምር፤ መምህራን በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲሰማሩ እንፈልጋለን ባይ ናቸው።
ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ምን ይሆን?
መጀመሪያ ትምህርት ቤቱ ወደ መጠጥ ቤት መቀየሩ በራሱ ትልቅ ስህተት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጀማል፤ ትውልድ ይቀረጽበት የነበረን ተቋም ወደ መጠጥ ቤት መቀየር ከሞራል አኳያም አግባብ አለመሆኑ በመጠቆም፤ ይህ ትምህርት ቤት ትምህርት የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲስተጓጎል ያደረጉ ኃላፊዎችም በሚገባው ልክ ምላሽ ሊሰጡና የሚመለከተው አካል ሁሉ በግልጽ አቋም መውሰድ እንዳለበት ይናገራሉ።
ታዲያ ከትምህርት ቤትነት ወደ መጠጥ ቤት ተቀይሮ የነበረው ትምህርት ቤት፤ በቀጣይ የሚኖረው ዕጣ ፋንታ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደ ቀድሞው ሁሉ ማስተማር ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን በትምህርት ሥርዓቱ መሰረት መምህራንና ሰራተኞችን መብት በመጠበቅ መቀጠል ነው። ይሁንና ተማሪዎችን ተቀብሎ ባያስተምር እንኳን ‹‹በምንም ተዓምር›› ወደ ቀድሞ የመጠጥ ቤትነት እንደማይመለስ ያብራራሉ። ይህ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ውሳኔ ከመሆኑም በተጨማሪ እንደ መንግስትም ተገቢነት የሌለው አቅጣጫ በመሆኑ የባለፈው ስህተት እንደማይደገም አረጋግጠዋል።
የወረዳ 06 ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ፤ ወትሮም ከትምህርት ቤትነት ወደ መጠጥ ቤት መቀየሩ በማንኛውም መመዘኛ ትክክል አለመሆኑን በመጠቆም የዚህ ተቋም ዕጣ ፋንታ ትምህርትና ትምህርት ብቻ መሆን አለበት የሚል ምላሽ አላቸው። ለመምህራንና ሠራተኞችም በአግባቡ ምላሽ የሚሰጥ አመራርም መኖር እንዳለበት ይጠቁማሉ። ይህ ካልሆነ ግን አሁንም መፍትሄ አልባ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል። ጉዳዩም ጥሩ ጎኑ ግን፤ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ከተማ አስተዳደሩ ድረስ የሚታወቅ በመሆኑም መፍትሄ ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ አበራ ይናገራሉ።
የከተማዋ ትምህርት ቢሮ….
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ በተደጋጋሚ የእጅ ስልካቸው ላይ የዝግጅት ክፍላችን ቢደውልም በወቅቱ የሥራ መደራረብ የተነሳ ማግኘት ባለመቻሉ የቢሮውን ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም። ይሁንና የዝግጅት ክፍላችን ጉዳዩን በመከታታል መረጃው እንደተገኘ ዘገባውን የሚያስተላልፍ ይሆናል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2015