በረጅም ርቀት ሩጫዎች ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ እንዲሁም ክብረወሰንን ለማሻሻል ከፍተኛ ብቃትና ጽናት ያስፈልጋል። በዚህም ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ አዲስ ክበረወሰን ለመስበር ረጅም ዓመታትን መጠበቅ የግድ ይሆናል። ጥቂቶች ግን በትልልቅ የውድድር መድረኮችና ብርቱ ተፎካካሪዎች ባሉባቸው ሩጫዎችም ጭምር አዲስ ሰዓት በማስመዝገብ በክብር ላይ ክብርን ይቀዳጃሉ።
የፕላቲንየም ደረጃ ከተሰጣቸው የጎዳና ላይ ማራቶኖች መካከል አንዱ የሆነው የበርሊን ማራቶን ደግሞ በተደጋጋሚ የዓለም ክብረወሰን ከሚመዘገብባቸው ውድድሮች መካከል ቀዳሚው ነው። በዓለም አቀፉ ቫይረስ ኮቪድ 19 ምክንያት አንድ ዓመት ከመቋረጡ በቀር ለ48 ዓመታት በተካሄደው በዚህ ማራቶን፤ በወንዶች ለ9 ጊዜያት፤ በሴቶች ደግሞ ለ3 ጊዜያት በርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ተሰብሯል።
ለረጅም ዓመታት ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች ብቻ የነገሱበት ይህ ውድድር ዘንድሮም አዲስ ፈጣን ሰዓቶች ተመዝግበውበታል። በሴቶች በኩል ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ባልተጠበቀ ሁኔታ የራሷንና የቦታውን ምርጥ ሰዓት ስታስመዘግብ፤ በወንዶች ደግሞ ከሶስት ዓመት በኋላ ኬንያዊው ብርቱ አትሌት የዓለም ክብረወሰንን በድጋሚ ከእጁ አስገብቷል።
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ የቦታውን ክብረወሰን ከሁለት ደቂቃ በላይ በሆነ ሰዓት ያሻሻለች ሲሆን፤ የርቀቱን የመጨረሻ መስመር የረገጠችው 2:15:37 በሆነ ሰዓት ነው። ይህ ሰዓት ደግሞ ከኬንያዊቷ የክብረወሰን ባለቤት ብሪጊድ ኮስኬ (2:14:04) እና ለረጅም ጊዜ የርቀቱን ፈጣን ሰዓት የግሏ አድርጋ ከቆየችው እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ (2:15:25) በመቀጠል ሶስተኛው የርቀቱ ፈጣን ሰዓት በሚል ተይዞላታል። ኢትዮጵያዊያን የርቀቱን አትሌቶችም በፈጣን ሰዓቷ በቀዳሚነት የምትመራ አትሌት አድርጓታል።
የ28 ዓመቷ ወጣት አትሌት ትዕግስት አሰፋ 800 እና 4በ400ሜትር ርቀቶችን በመሮጥ የምትታወቅ አትሌት ስትሆን፤ እአአ የ2013 የአፍሪካ ወጣቶች ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊም ነበረች። በ2016 ደግሞ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና እንዲሁም የሪዮ ኦሊምፒክ ላይም ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ተካታ ሀገሯን መወከል ችላለች። እአአ ከ2018 ጀምሮ ደግሞ አትሌቷ ከመም ወደ ጎዳና ላይ ሩጫዎች የተሸጋገረች ሲሆን፤ በዚህ ዓመት የ10 ኪሎ ሜትር፣ የግማሽ እና የሪያድ ማራቶን ተሳታፊም ነበረች። በተደራራቢ ውድድሮች ላይ የቆየችው ብርቱዋ አትሌት ሜጀር በሚባለውና በርካታ ታዋቂ አትሌት ባሉበት በዚህ ውድድር ተካፍላ ብቃቷን ማስመስከር ችላለች።
ፈጣን በነበረው በበርሊኑ የማራቶን ሩጫ ላይ ስድስት የሚሆኑት አትሌቶች 1:08:13 በሆነ ሰዓት ርቀቱን ማጋመስ ችለዋል። 30 ኪሎ ሜትር ላይ ሲደርሱ ሰዓቱ 1:36:41 ሲሆን፤ ለአሸናፊነት ፉክክር ሲያደርጉ የነበሩት ደግሞ ሶስት ብቻ ነበሩ። እነርሱም ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ትዕግስት አባያቸው እና መሰረት ጎላ ናቸው። ከ35 ኪሎ ሜትር ጀምሮ ደግሞ የርቀቱ አሸናፊ ትዕግስት አሰፋ ከሀገሯ ልጆች ጋር የነበራትን ልዩነት ወደ 20 ሰከንዶች በማስፋት ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ጭምር ውድድሩን መፈጸም ችላለች።
ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ተከታትለው በመግባት አሸናፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ በሩጫው ወቅት ቢገመትም፤ ኬንያዊቷ አትሌት ሮዝሜሪ ዋንጂሩ 2:18:00 በሆነ ሰዓት በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ልትይዝ ችላለች። በሩጫው ወቅት ከፍተኛ ግምት ያገኘችው ትዕግስት አብያቸው ደግሞ በሶስት ሰከንዶች ብቻ በመበለጧ ሶስተኛ ሆናለች። አትሌት ወርቅነሽ ኢዴሳ እና መሰረት ጎላም እስከ አምስት ያለውን ደረጃ መያዝ ችለዋል።
በወንዶች የማራቶን ንግስናን የግሉ ማድረግ የቻለው ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ ደግሞ በርቀቱ የራሱን ክብረወሰን በድጋሚ ማሻሻል ችሏል። የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ አሸናፊው ኪፕቾጌ ከ25 ኪሎ ሜትር አንስቶ ተፎካካሪዎቹን ጥሎ በመግባት አሸናፊ ለመሆን ችሏል። የገባበት የዓለም ፈጣኑ ሰዓትም 2:01:09 ሲሆን፤ የበርሊን ማራቶንን ለሶስት ጊዜያት በማሸነፍ የአራት ጊዜ ተከታታይ ባለድል ከነበረው ኢትዮጵያዊው ጀግና አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ጋር ታሪኩን ለመጋራት ችሏል። አትሌቱ የርቀቱን ክብረወሰን በዚሁ ውድድር ላይ እአአ 2018 ላይ 2:01:39 በሆነ ሰዓት በመግባት ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው።
ሌላኛው የሀገሩ ልጅ ማርክ ኮሪር አራት ደቂቃዎችን በመዘግየት በሁለተኛነት ሲገባ ያስመዘገበው ሰዓትም 2:05:58 ሆኗል። ታዱ አባቴ (2:06:28) እንዲሁም አንዱአምላክ በልሁ (2:06:40) ደግሞ ኬንያውያኑን ተከትለው በመግባት ሶስተኛና አራተኛ በመሆን ውድድሩን የፈጸሙ አትሌቶች ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2015 ዓ.ም