ከ60 ዓመት በፊት የታተሙትን የአዲስ ዘመን ጋዜጦች ለዓምዳችን አቅርበናል:: በውጋዴን የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶችን ለማስወገድ በዘመኑ የነበሩ ባላባቶች ያደረጉትን ምክክር ቃኝተኛል፤ በዘመናችን በየቦታው የሚታየውን የጀሌዎቹና‹ የጆሌዎቹ ›እኩይ ጽንፈኛ ተግባር ፤ በየአካባቢው ያሉ አመራሮችና የፀጥታ ጥበቃ አባሎች በንቃት ተመካክረው አውዳሚ ተግባራቸውን ለመቆጣጠር ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ያሳየናል:: የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት የነበሩት የመቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ በ1956 ዓ.ም የሕግ መምሪያ ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ሳለ በዮጎዛላቪያ በተካሄደው የኢንተር-ፓርላማ ጉባኤ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውንና ባደረጉት ንግግር አፍሪካውያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው ለመወሰን የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል:: ከዘመናችን ጋር ስናስተያየው ሀገራችን ችግሮቻችን የሚፈቱት በአፍሪካ ኅብረት ነው ማለቷን እናደንቃለን፤ ሌሎችም ዜናዎች አካተናል::
ሽፍቶችን ለማስወገድ ፈቃድ ጠየቁ
ሐረር ፤ በውጋዴን ግዛት የሚገኙ ባላባቶች ሁሉ ከየጐሣቸው አንዳንድ ታላላቅ ባላባቶች ወደ ሐረር በመላክ ሽፍቶቹ በሀገራቸው ላይ ስለሚያደርጉት ጉዳት አሳባቸውን ለጠቅላይ ግዛቱ እንደራሴ ለክቡር ሌተና ኰሎኔል ታምራት ይገዙ እንዲገልጹላቸው አድርገዋል ፤ የተላኩት ባላባቶችም መስከረም ፫ ቀን ፶፮ ዓ.ም. ወደ ክቡር እንደራሴ ቀርበው የተሰጣቸውን እምነትና አደራ የረሱ ከሃዲዎች በሀገራችን ላይ በመሸፈት ሀገራችንን ከማጥፋት በላይ በንብረታችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስላደረሱብን ተባብረን ለማጥፋት ቆርጠን የተነሳን ስለሆነ ፤ መንግሥታችን ይህንኑ እንዲፈቅድልን እንለምናለን :: ሽፍቶቹም ተወላጆቻችን አይደሉም በማለት አሳባቸውን ገልጸውላቸዋል::
ክቡር እንደራሴውም አሳባቸውን ካዳመጡ በኋላ ፤ ሰው ሆኖ የማያጠፋ የለም ፤ ቢቻል በምክር ውንብድነታቸውን ቢተዉ ምከሩአቸው ፤ ካልሆነ እያንዳንዳቸው እጃቸውን እየያዛችሁ ለመንግሥታችሁ ብታስረክቡ መልካም ነው ፤ በማለት መልስ ስለሰጡዋቸው ምስጋናቸውን አቅርበው ተመልሰዋል :: ከባላባቶችም የቀብሪ ደሐር አውራጃ ግዛት ሕዝብ እንደራሴ ቐኛዝማች አሙመር ባራሌ ፤ የቀላፎ አውራጃ ገዥ ቀኛዝማች በሽር ሴክ አብዲ ፤ የሬርሬር ወረዳ ግዛት አቶ መሐመድ ባሂር ሌሎችም እነሱን የመሳሰሉ ተገኝተው ነበር ሲል በጠቅላይ ግዛቱ የሚገኘው ወኪላችን አስታውቋል ::
( መስከረም 5 ቀን 1956 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ )
ከጎርፍ ሙላት አዳኑት
ደብረ ማርቆስ ፤መስከረም ፯ ቀን ፶፮ ዓ.ም ከሁለት ሰዓት በፊት በጣለው ኃይለኛ ዝናብ ምክንያት ፤ ደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው ውስታ የተባለው ወንዝ ሞልቶ ዕድሜው ፲፪ ዓመት የሆነ ልጅ ከጓደኛው ጋር በወንዙ ዳርቻ እንደቆመ ፤ የውሀው ማዕበል ስለወሰደው ፤ ወታደር የሺጥላ አፍኔ የተባለ የፖሊስ ባልደረባ ፤ አደጋውን ተመልክቶ ባሳሰበው መሠረት ፤ የአካባቢው ሰው እንዲሰበሰብ አድርጎ የወንዙ ሙላት ልጁን ከ፴ ሜትር በላይ እያንገላታ ከወሰደው በኋላ ፤ የተሰበሰበው ሰው አጠናና ልዩ ልዩ ነገር በማቀበል ፤ልጁን ከውሀ ሙላት አደጋ ሊያድኑት ችለዋል::
( መስከረም 9 ቀን 1956 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ )
የ ፻ አለቃ ግርማ ወ. ጊየርጊስ በኢንተር- ፓርላማ ጉባኤ
የኢትዮጵያ የሕግ መምሪያ ፕሬዚዳንት የተከበሩ የ ፻ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ለ፶፪ ኛው የኢንተር- ፓርላማ ጉባኤ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል::
የተከበሩ የ ፻ አለቃ ግርማ ለጉባኤው ባደረጉት ንግግር ፤ዮጎዝላቪያ ስላደረገችላቸው መልካም አቀባበል ከአመስገኑ ና በእስኮፔጅ ስለደረሰውም አሰቃቂ ጥፋት የተሰማቸውን ቅሬታ ከገለፁ በኋላ ፤ ‹‹ ብዙ የአፍረቃ አገሮች የራሳቸውን ጉዳይ ራሳቸው ለመወሰን የሚያደርጉት አስደናቂ ጥረት ፤ለአፍሪቃውያን ራሳቸውን ለማስተዳደር አልበቁም የሚለውን መሠረተ ቢስ ሀሜት የሚያስተባብል ነው ›› ብለዋል :: እንደዚሁም የአዲስ አበባው ከፍተኛ ጉባኤ በአፍሪቃ ታሪክ ውስጥ አንድ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን አስገንዝበዋል::
የተከበሩ የመቶ አለቃ ግርማ ፤ስለ ኑክሊየር በመስኮብ የተደረገው ውለታ አንድ ጥሩ ውጤት መሆኑ ከገለጡ በኋላ ሌላው የሰላም አስጊ ጉዳይ ደግሞ የዘርና የቀለም ጉዳይ መሆኑን አሳስበዋል ::ፕሬዚዳንት ኬኔዲ የቀለምን ልዩነት ለመደምሰስ የሚያደርጉትን ጥረት የመቶ አለቃ ግርማ አመስግነዋል ::
የደቡብ አፍሪቃ ሁናቴ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መሄዱን በመግለጥ ፤ በደቡብ አፍሪካ መንግሥትና በፖርቱጋል አገዛዝ ሥር በሥቃይ የሚገኙት አፍሪቃውያንን ለማዳን የፓርላሜንት አባሎች ሁሉ የተቻላቸውን ያህል እንዲረዱ የመቶ አለቃ ጠይቀዋል ::
( መስከረም 12 ቀን 1956 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ )
ለኩዩ አቦቴ ሰዎች በተስቦና ፈንጣጣ የነፃ ክትባት ተሰጠ
ፍቼ ፤በሰላሌ አውራጃ ግዛት በፍቼ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ሥራ የሚተዳደሩ የኩዩ አቦቴ ወረዳ ግዛት የገብረ ጉራቻ ወረዳ ግዛት ክሊኒክ ከመስከረም ፩ ቀን ሺህ ፱፻፶፭ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጳጉሜ ፮ ቀን ሺህ ፱፻፶፭ ዓ.ም ድረስ በተመላላሽ ፬ ሺህ ፸፭ በተስቦ ክትባት ፤፩ ሺህ ፱፻፹፫ ፤ በፈንጣጣ ክትባት ፩ ሺህ ፪፻፲ ፤ በጠቅላላው ለ፯ ሺህ፪፻፷፰ ሰዎች የነፃ ሕክምና ማድረጉን የክሊኒኩ ኃላፊ አቶ ዘመድኩን በነበሩ አረጋግጠዋል ሲል ወኪለካችን ገልጿል ::
( መስከረም 15 ቀን 1956 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ )
የፖሊሶች እርሻ
በገለብና ሐመር ባኮ አውራጃ የሚገኙ ፖሊሶች ከፀጥታ ጥበቃቸው ጋር ሕዝቡን ስለ እርሻ ጥቅም ያስተምራሉ :: ከዚህ ቀደም ባሳዩት የእርሻ አዝመራ አስደሳች የጤፍ ምርት አግኝተዋል :: ባለፈው ዓመትም እርሻቸውን በጥራጥሬ ዘር ሞክረውታል :: መሬቱም ፍጹም ድንግል በመሆኑ ፤አስደሳች የሆነውን ምርት አግኝተዋል ::
ሕዝቡም የፖሊሶቹን አርአያ በመከተል የእርሻን ሥራ እንደሚያስፋፋና የራሱን ኑሮ እንደሚያሻሽል ፖሊሶች ተስፋ ያደርጋሉ ::
( መስከረም 6 ቀን 1956 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ )
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2015 ዓ.ም