በሙያው ከ14 ዓመት በላይ ቆይታለች:: “ስራሽ ጥሩ ነው ሽልማት ይገባሻል” ተብላ በአገር ደረጃ እውቅናና ሽልማት አግኝታለች:: በጉማ ፊልም አዋርድ ላይ የዓመቱ ምርጥ ሜካፕ አርቲስት ተብላም ተሸልማለች:: ከ32 በላይ ፊልሞች ላይ በጥበበኛ እጆቿ አሻራዋን አሳርፋለች:: አብረዋት የሰሩ ሁሉ በትጋቷ ያውቋታል:: አዲስ ነገር በመፍጠርና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየች ላለችው ለውጥም አድናቆት አላቸው። ተዋንያንን ውበት ማልበስ፣ ለሚፈለገው ገፀ ባህሪ የሚፈለገውን አይነት መልክ ማላበስ ትችልበታለች:: ወጣቷና ስመ ጥሯ ሜካፕ አርቲስት መሰረት መኮንን:: በዛሬው የፋሽን ገጻችን ይህች ባለሙያ ባደረገችው አጭር ቃለ ምልልስ ስለ ስራዎቿና አጠቃላይ የሜካፕ ሙያን የተመለከቱ ጉዳዮችን አጫውታናለች። እኛም እንደሚከተለው ለንባብ አቅርበነዋል።
ጉዞ ወደ ሜካፕ ጥበብ
ወደ ሜካፕ ባለሙያነት ከመምጣቷ በፊት በፊልም ሽያጭ ንግድ ስትሰራ ቆይታለች:: ባለቤቷ የፊልም ባለሙያና ሜካፕ አርቲስት መሆኑ ስለ ሜካፕ ሙያ ደጋጋማ እንድታስብ አድርጓታል:: ቀስ በቀስም ሜካፕ አርቲስት የመሆን ፍላጎት አየለባትና እራሷን በሙያው ብቁ በሚያደርጋት ዝግጅትና ስለሙያው እውቀት የምትሸምትባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አደረገች:: በተለያየ መንገድም እራሷን ለሙያው ብቁ የማድረግ ስራ ላይ አተኮረች::
ለዚህ ሙያዊ ፍቅር እውን መሆን ጥሩ መንገድ አድርጋ የወሰደችው ደግሞ በፊልም ስራ የሜካፕ ሙያ ላይ ትኩረት ማድረግን ነው:: ለዚህም የፊልም ባለሙያና ሜካፕ አርቲስት የሆነው ባለቤቷ ትልቅ ድጋፍ አደረገላትና እራሷን ካበቃች በኋላ ወደ ስራው ገባች። በዚህ ብቻ ግን ተወስና አልቀረችም። አሁንም ከፊልም ስራ ጎን ለጎን በተለያዩ የሜካፕ ሙያዎች ላይ ትሰራለች:: ነገር ግን ዋነኛ ትኩረት ያደረገችው የፊልም ጥበብ ላይ የራሷን አሻራ ማሳረፍ ነው።
የአርቲስቷ ልዩ ትኩረት
ዘርፈ ብዙ ከሆነው የሜካፕ ሙያ አይነት ውስጥ በፊልም እና ሌሎች ጥበቦች ላይ በስፋት የሚሰራበት “ስፔሻል ኢፌክት” የሚባለው የሜካፕ ዘርፍ የአርቲስቷ ትኩረት ነው:: ስትሰራውም በደስታ ነውና ትልቁ ትኩረት የምትሰጠው የሜካፕ ሙያ አይነት “ስፔሻል ኢፌክት” የተባለው ነው::
ይህ በፊልም ሙያ ላይ የሚተገበር የሜካፕ አይነት ገፀ ባህሪያት ወይም ወካዮችን የተለያየ አደጋ ወይም ጉዳት የደረሰባቸው አስመስሎ መስራት ነው:: እዚህ ላይ በዋናነት ሙያው የሚጠይቀው ጥበብ በእውን የነበረን ገፅታ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል መቀየር ሲሆን፤ የሜካፕ ጥበብን በመጠቀም ወፍራምን ቀጭን፣ ወዛማ ፊትን ማገርጣት፣ ማክሳት ወይም ሌላ መልክ ማላበስን ይጨምራል:: የተቆራረጠና በአደጋ የተጎዳ የሰውነት ክፍልን አስመስሎ መስራትም የዚሁ ጥበብ አካል ነው። መሰረት ይህን የሜካፕ አይነት ለመስራት የምትመርጠው ፈጠራ የታከለበትና አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ነው።
ሜካፕ አርቲስት መሰረት ከፊልም ስራው ውጪ ተዋንያንን ከጸጉር እስከ እግር ጥፍር በማስዋብ እንዲሁም እንደ ገፀ ባህሪያቱ ሁኔታ በተለያየ መልክ ገፅታን ማላበስ የተካነችበትና ሁሌም የምትተገብረው ሙያዋ ነው::
የተሳተፈችባቸው ስራዎች
በአብዛኛው ትኩረቷ ፊልም እንደመሆኑ በተለያዩ የፊልም ስራዎች ውስጥ የራስዋን ሙያዊ አሻራ አሳርፋለች:: ከ32 በላይ የአገራችን ፊልሞች ላይ ተሳትፋለች:: ከእነዚህም መካከል ያልታሰበው፣ የወደዱ ሰሞን፣ ሊነጋ ሲል፣ ሰኚኮ፣ የልጃችን እናት፣ ኑርልኝ፣ ቤተልሄም፣ ባለቁልፏ፣ ፊልመኞቹ፣ ፍላጎት፣ ሲመት (የተሸለመችበት ፊልም ነው) የፍቅር ሰው፣ ወርቅ በወርቅ የተሰኙ አገርኛ ፊልሞች አርቲስቷ በሙያዋ ተሳትፋባቸው የጥበብ አሻራዋን ያሳረፈችባቸው ናቸው።
ስለ ሜካፕ ሙያ እድገት
የሜካፕ ሙያ በኢትዮጵያ አሁን ያለበት ደረጃ ሲታይ ገና ብዙ የሚቀረው ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን አበረታች ለውጥ እያሳየ መሆኑን የምትገልፀው መሰረት፤ የበለጠ እድገትና ለውጥ እንዲመጣ ግን ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ ታስረዳለች::
በሌሎች አገሮች የሜካፕ አርቲስትነት ሙያ እጅግ የከበረና በስራውም ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚቻልበት መሆኑን የምትናገረው አርቲስት መሰረት፣ ይህ ልምድ እኛም አገር ላይ ሊዳብር እንደሚገባ ታምናለች።
ሙያው ትልቅና በተለያየ መስክ የተሻለ ተፅዕኖ መፍጠር የሚያስችል ነው:: ለዚህ ደግሞ የሜካፕ አርቲስቶች ትልቅ ሚና አላቸው:: እራሳቸውና ሙያውን አክብረው ሁሌም ብቁ ሆኖ መገኘትና የተሻሉ ስራዎችን መስራት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል በማለትም አስተያየትዋን ትሰጣለች:: ሙያው በራሱ ትልቅና እራስን ብቁ ማድረግ የሚፈልግ መሆኑን የምትገልፀው መሰረት፤ ባለሙያዎች ለስራው እድገትና ለውጥ የራሳቸው ትልቁን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባም ትመክራለች::
ማህበረሰቡ ስለሜካፕ ሙያ ያለው ግንዛቤ ከጊዜ ወደጊዜ እየተለወጠ መሆኑን የምትገልፀው መሰረት ሙያው በራሱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚፈጥረው በጎ አስተዋፅዖ እያደገ ይገኛል:: ሜካፕ በፊልምም ሆነ ሌሎች የስነ ውበት ስራዎች ውስጥ ትልቅ አቅም መፍጠር ይችላል:: ይህ ሙያ የሚጠበቀውን ያህል ለውጥ ማምጣት እንዲችል ደግሞ ለመስኩ ምቹ ሁኔታ ቢፈጠር መልካም ውጤት ያስገኛል የሚል እምነት አላት:: እራሷን በሙያው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለች በምትሰራቸው ስራዎች የተሻለ እድገት በማሳየት ላይ የምትገኘው አርቲስት መሰረት ወደፊትም በሙያው ላይ የተሻሉ ስራዎችን በመስራት ተፅዕኖ የመፍጠርና ስራውን ይበልጥ የማሳደግ ህልም አላት::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም