ኢትዮጵያ ለጠነሰሰችው የአፍሪካ ዋንጫ ባይተዋር ብትሆንም ዛሬ ላይ የምትኮራበት አንድ ህያው ታሪክ አላት። ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የሆነውን ይህን አኩሪ ታሪክ ከጻፉ ጀግኖች መካከል የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ደግሞ ሉቺያኖ ቫሳሎ ነው። ኢትዮጵያ 3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅታ ስታስቀር የብሔራዊ ቡድኑ አምበል የነበረው ሉቺያኖ አገሩ ዳግም ለተመሳሳይ ክብር በቅታ ሳይመለከት ባለፈው ሳምንት በ87 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የሉቺያኖ ቫሳሎ ስርዓተ ቀብር በጣልያኗ ሊዶ ከተማ ቅድስት ሞኒካ ቤተ – ክርስቲያን ተፈጽሟል። በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችንም ይህ ታላቅ የእግር ኳስ ሰው ከብቸኛው የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ድል ጋር ከብዙ በጥቂቱ እናስታውሰው።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ብቸኛውና ትልቁ ድል ሲገኝ የቡድኑ መሪ የነበረው ሉቺያኖ በ1927 በኤርትራ አስመራ ነው የተወለደው፡፡ ሉቺያኖ የተወለደው ከጣሊያናዊ ወታደር አባቱ ቪቶሪዮ ቫሳሎና ከኤርትራዊት እናቱ መብራክ አብርሃም ነው፡፡ ሉቺያኖ በኤርትራ ይኖሩ ከነበሩት በርካታ ቅይጥ ማንነት ካላቸው ዜጎችም አንዱ ነበር፡፡ የዚህ ታላቅ ሰው ታሪክ አንድም በታላቅ ስኬትና ገድል የሚጠቀስ በሌላ በኩል ደግሞ በመገለል፣ ጭቆና እና ስደት የተከበበ መሆኑን እሱን በተመለከተ የተፃፉ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡
ከምንም ነገር በላይ ቀልድና ጨዋታ አዋቂነቱ የሚነገረው ሉቺያኖ እግር ኳስን መጫወት የጀመረው በአስመራ የተጎሳቆሉ መንደሮች ውስጥ ነው፡፡ በአስመራ ከሚገኙ ኃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች አንዱ የነበረው ኮሌጂዮ ላቬላ የሉቺያኖ የእግር ኳስ ሕይወት መሰረት ነው፡፡ ይህ የካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት ስቴላ አስመሪና (የአስመራ ኮከብ) ተብሎ የሚጠራ የእግር ኳስ ቡድን ነበረው፡፡ ጥቁርና ነጩ የቡድኑ መለያ በጣልያን- ኤርትራዊ (ኢታሎ-ኤርትራ) ጥንድ-ማንነት ላይ የተመሠረ ተው ቡድን መገለጫ እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል።
ሉቺያኖ በስቴላ አስመሪና በግራ መስመር ተከላካይነት መጫወት ቢጀመርም ከቡድኑ ጋር ለረጅም ጊዜ ሳይቆይ የሌሎች ክለቦችን ትኩረት አገኘ፡፡ የአገሪቱ የምድር ባቡር ሰራተኞች ሉቺያኖ ላይ አይናቸው አረፈ፡፡ ‹ግሩፖ ስፖርቲቮ ፌሮቬሪ› በኤርትራ የባቡር ድርጅት ክለብ ሲሆን ሉቺያኖን በባቡር መንገድ ጥገና ሰራተኝነትና በተጫዋችነት ለመቅጠር ድርድር ቢያደርግም የተጫዋቹ ልብ ግን ወደ ሰማያዊ ለባሾቹ ገጀረት አደላ፡፡ ማረፊያውም ይሄው ክለብ ሆነ፡፡
ሉቺያኖ በገጀረት እ.ኤ.አ ከ1953 -1958 በነበረው የስድስት ዓመት ቆይታ ቡድኑን ወደ ከፍተኛው የሊግ እርከን እንዲያድግ አድርጓል፡፡ በዚህ ወቅት ሉቺያኖ ያሳይ የነበረው ድንቅ ብቃትም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች አይን ውስጥ አስገባው። በእርግጥ ሉቺያኖ ከድሬዳዋ ጥጥ ማህበር እስከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድረስ በበርካታ ክለቦች ተነገረው የማያልቁ ብዙ ታሪኮች አሉት። እኛ ግን ለዛሬ ወደ ታላቅነት የተንደረደረበትንና በብሔራዊ ቡድን የነበረውን ቆይታ ብቻ እየተመለከትን እንቀጥል።
ሉቺያኖ ለግሩፖ ዲፖርቲቮ አስመራ ክለብ መጫወት ሲጀምር እድሜው ገና በ20ዎቹ አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ በተከላካይ መስመር ተጫዋችነት ጀምሮም ክህሎቱን በማሳደግ የጨዋታ አቀጣጣይ ለመሆንም ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ጨዋታን የመምራት ብቃቱ እየጎለበተ የሄደው ሉቺያኖ በጠንካራ ምቶቹ ይታወቅም ጀመር፡፡
እ.ኤ.አ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከኤርትራ የተገኙ ነበሩ፡፡ ከነዚህ ተጫዋቾች አንዱ ሉቺያኖ ቫሳሎ ነው፡፡ የመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ የደረሰውም እ.ኤ.አ በ1956 ነበር። 3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአራት ቡድኖች መካከል በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ሲካሄድ ታሪካዊው ተጫዋች መንግስቱ ወርቁ ሉቺያኖ የቡድኑ አምበል እንዲሆን ትልቁን ሚና ተወጥቷል። የአፍሪካ ዋንጫው በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ስታዲየም ሲጀመር ሉቺያኖ የእግር ኳስ ታምራቱን ማሳየት የቻለው ገና በመጀመሪያው ግጥሚያ ነበር። የመጀመሪያ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በሉቺያኖ 2 ግቦች፣ በመንግስቱ 1 ጎልና በተክሌ ኪዳኔ ተጨማሪ 1 ጎል አማካኝነት ኢትዮጵያ ቱኒዝያን 4-2 ረታች፡፡
በፍፃሜው ጨዋታ ግብጾች ገና በ35ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ላይ ባስቆጠሯት ግብ እስከ 75ኛው ደቂቃ ድረስ መምራት ቻሉ። 75ኛው ደቂቃ ላይ ግን ተክሌ ኪዳኔ ኢትዮጵያን አቻ አደረገ፡፡ ግብጽም መልሳ መሪነቷን ለማግኘት ጊዜ አልፈጀባትም። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 6 ደቂቃዎች ሲቀሩ ግን ሉቺያኖ ያስቆጠራት ግብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ወደ ዳግም አቻነት መለሰች፡፡ ይህች ጎል የግብጾችን ሞራል አወረደች፡፡ በጭማሪው ሰዓት ኢትዮጵያውያኖች በተዳከሙት ግብጾች ላይ ከፍተኛ ብልጫን ወሰዱ፡፡ የሉቺያኖ ወንድም ኢታሎና መንግሥቱ አከታትለው ያስቆጠሯቸው ግቦችም ኢትዮጵያን 4ለ2 አሸናፊ አደረጓት። ኢትዮጵያም የመጀመሪያውንና ብቸኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አሸነፈች፡፡ በአስመራ ከጣሊያናዊ አባትና ከኤርትራዊት እናት የተወለደው ሉቺያኖም ከአፄ ኃይለሥላሴ እጅ ዋንጫ ተቀብሎ ወደ
ላይ ከፍ አደረገ፡፡
በኢትዮጵያ የንጉሳዊው ስርዓት ሲያበቃና ደርግ ስልጣን ሲይዝ ሉቺያኖ ኳስ መጫወት አቁሞ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በጣሊያን ታዋቂ በሆነው የእግር ኳስ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ማዕከል ኮቨርሲያኖ ከአርማንዶ ፒቺ ፣ ሴዛሬ ማልዲኒና ሉዊስ ቪንሲዮ ጋር በመማር በአሰልጣኝነት ብቅ አለ። ግን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ብዙም ስኬታማ አልነበረም። በብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነትም ብዙም ሳይዘልቅ 1976 ላይ ከአሰልጣኝነቱ ተነስቶ በጀርመናዊው ፒተር ሺንግተር ተተካ። ከጊዜያት በኋላም የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች “አምፊታሚን ካፕታጎን” የተባለ አነቃቂ፣ ጉልበት ሰጪና የምግብ ፍላጎት የሚቀንስ መድሀኒት መጠቀማቸውን ማውገዙና መንቀፉ በአዲሱ መንግሥት በጠላትነት እንዲፈረጅ አደረገው፡፡ በእርግጥ ብሔራዊ ቡድኑን በድጋሚ እንዲያሰለጥን ጥያቄ ቀርቦለት በ1978 በአሰልጣኝነት የመጨረሻ ጨዋታው ምስራቅ ጀርመንን ታሪካዊ በሆነ ሁኔታ አሸነፈ፡፡ ከጨዋታው ሁለት ሳምንት በኋላም በጠዋት ወደ በጅቡቲ አድርጎ በካይሮ በኩል አሁን ሕይወቱ ወዳለፈባት ጣሊያን እንዳመራ ተጽፏል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2015 ዓ.ም