በተሰናበትነው ሳምንት በቀጥታ ግንኙነት ወይም ተያያዥነት ያላቸው የማይመስሉ ለአመታት የቀጠሉ ሶስት ኩነቶች ተከናውነዋል። ነጥቦችን አገጣጥሞ ለመመልከት ለሞከረ ግን ወደ አንድ ምስል ይመራሉ። የመጀመሪያ ሽብርተኛውና ባንዳው ሕወሓት ለ3ኛ ጊዜ ከነሐሴ አጋማሽ ወዲህ እስከ ዛሬ በአገራችንና በሕዝባችን ላይ የከፈተው የክህደትና የውክልና ጦርነት ሲሆን ፤ ሁለተኛው በመንግስታቱ ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በአገራችን ላይ ያወጣው ፍርደ ገምድልና አሳፋሪ ዘገባ ነው፤ ሶስተኛው በአፋር ክልል ጠቅላይ ሚንስትሩ በኩታ ገጠም የለማ የጥጥ እርሻ መጎብኘታቸው ነው ።
ሽብርተኛውና የእናት ጡት ነካሹ ሕወሓት የጋላቢዎችን የእነ ግብጽን አገርን የማተራመስና የማፍረስ ተልዕኮና ስምሪት ተቀብሎና እኔ እንደ ብረት ቀጥቅጨ የማልገዛትና የማልዘርፋት አገር ትፍረስ ከሚል ግብዝነቱ ጋር አጃምሎ ሉዓላዊነታችንና ነጻነታችን ለመናድ በሕዝባዊ ማዕበል የከፈተብንን ወረራ፤ ጀግናው የጥምር ኃይል እና የአማራ፣ የአፋርና መላው የኢትዮጵያዊ ሕዝብ ደግሞ በአስተማማኝ ደጀንነት እየመከተው ይገኛል። ይሄን የውክልና ጦርነት ከእውነት አምላክ ጋር በቅርብ በአንጸባራቂ ድል እንደመድመዋለን ብዬ አምናለሁ።
በሉዓላዊነትና በነጻነታችን ላይ የተከፈተው ጦርነት ሌላው ግንባር በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲውና በሚዲያው የተከፈተብን የተቀናጀናና የተናበበ ጦርነት ነው። ባለፉት ሶስትና አራት አመታት አገራችን የተፈጥሮ ሀብቷን በማልማቷና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በመንቀሳቀሷ ደርዘን ጊዜ በመንግስታቱ ድርጅትና በጸጥታው ምክር የተከሳሽ ሳጥን ቆማለች። ራሱን ዓለም አቀፍ ሚዲያ ብሎ የሚጠራው ኃይልም በሀሰተኛ ወሬና ሆን ተብሎ በተዛባ መረጃ ሊፈታት ሌት ተቀን ሰርቷል። እየሰራም ነው ። ባለፈው ሳምንት በሽብርተኛው ሕወሓት ተደርሶ፤ በመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ኮሚሽን ስም የወጣው እንቶፈንቶ ዘገባ የፖለቲካዊ ዲፕሎማሲው ሌላ ቅርሻ ነው።
ይሄን አሸባሪ የማዳን መጋጋጥ መላው ዜጋ በተለይ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚገኘው ትውልደ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊ ከወዳጆቹ ጋር ሆኖ እየመከተው ይገኛል። ሆኖም በአሳዛኝ ሁኔታ በዲፕሎማሲው፣ በሚዲያውና በተግባቦቱ ዘርፍ ዛሬም እውነትንና ፍትሕን ታቅፈን ተከላካይና አስተባባይ መሆናችን ቀጥሏል። አጀንዳ ተቀባይ እንጂ አጀንዳ ቀርጸን ወደፊት ማምጣት አልቻልንም። አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም በሚል ተስፋ የመቁረጥ አባዜ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡንና ዓለም አቀፍ ሚዲያውን ለከሀዲውና ለአሸባሪው ሕወሓት በፈቃዳችን ስለ ለቀቀንለት ዛሬም ከጀርባ እየተወጋን ነው። ሰሞነኛ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ኮሚሽን ባለሙያዎች ዘገባ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
የአገር ውስጥ ሁለንተና አቅማችንን እስክንገነባ ድረስ ከሴናተሮች፣ ከኮንግረስ አባላት፣ ከአውሮፓ ሕብረት፣ ከሚዲያዎችና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የሚያግባባንና የሚያገናኝ (ሎቢ)ልንቀጥር ይገባል። በነገራችን ላይ የምዕራባውያን በተለይ የአሜሪካ ሚዲያ፣ ኮንግረስ ፣ ሴኔትና ሌሎች ተቋማት ያለ ሎቢስት አይታሰቡም። አይደለም የእኛ የንባዳዎቹ ጉዳይ የአሜሪካኖች የራሳቸው ጉዳይ ያለ አግባቢ(ሎቢስት) ስንዝር ፈቀቅ አይልም። ከእያንዳንዱ ሕግ ፣ ፖሊሲና ውሳኔ ጀርባ እልፍ አእላፍ ሎቢስቶች አሉ።
በዋሽንግተን ዲሲ ብቻ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ፤ በአውሮፓ ሕብረት መቀመጫ ብራስልስ ደግሞ እስከ 30ሺህ የሚደርሱ ሎቢስቶች ይርመሰመሳሉ። ከእያንዳንዱ ግዙፍ ኩባንያና ማህበራት ጀርባ ሎቢስት አለ። ከሕዳሴው ግድብና ከአሸባሪው ሕወሓት ጀርባ ያሉ ኃይላት ነገም አይተኙልንምና ሎቢስት መቅጠር ግድ ይለናል። ምንም እንኳ ለወጪ የሚዳርገን ቢሆንም፤ በፈጠራ ወሬና በተዛባ መረጃ እየተፈጠረብን ካለው ጫናና እየጠለሸ ካለው ገጽታችን ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የማይባል ነውና ሎቢስት ሊኖረን ይገባል።
ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳዬ ስመለስ፤ ዘላቂው መፍትሔ ምዕራባውያን ድህነታችንና ኋላቀርነታችንን መያዣ አድርገው ዝቅ አድርገው እንዳያዩን፤ ከፍ ሲልም በእርዳታና በብድር ሰበብ በነጻነታችንና በሉዓላዊነታችን ላይ እንድንደራደር እጃችን ለመጠምዘዝ የሚደረገውን ጥረትና ጫና ለመቋቋም የድህነትንና የኋላቀርነትን ቀንበር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መስበር አለብን። የግብርናውን ፣ የኢንዱስትሪው ፣ የአገልግሎት ዘርፉን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የድህነትንና የኋላቀርነትን ቀለበት ሰብረን የመውጣት ጉዳይ ለነገ የሚተው ጉዳይ አይደለም ።
አስተማማኝ የስራ ዕድል መፍጠር ፤ የዋጋ ግሽበትንና የኑሮ ውድነትን ከመቀነስ ጎን ለጎን ደግሞ የዴሞክራሲ፣ የደህንነትና የጸጥታ ተቋማትን መገንባት፤ የሕዝብን አንድነት የሚሸረሽሩ ፖለቲካዊ ሴራዎችንና ደባዎችን ተቆራርጦ መታገል፤ ብልሹ አሰራሮችንና ሙስናን ፤ ጽንፍ የረገጠ ብሔርተኝነትን ፤ ወዘተረፈ ማስወገድ ፤ ውስጣዊ ለቀውስ ተጋላጭነትን ከመቀነስ ባሻገር እንዳለፉት ሶስትና አራት አመታት ያሉ ያላባሩ ጫናዎችን ለመመከት ጉልበት ይሆናሉ። ከውጭው ጫና ይልቅ እነዚህን የቤት ስራዎቻችንን አበክረን ባለመከወናችንና ባለመስራታችን የሚመጣብን አደጋ የከፋ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዶ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ይበል የሚያሰኙ ናቸው። መንግስት ምንም እንኳ ወደ ስልጣን ከመጣበት የመጀመሪያ ቀን አንስቶ በየአቅጣጫው ዘርፈ ብዙ የጥቃት ግንባሮች ተከፍቶበት ፋታ ባያገኝም ተስፋ የሚጣልባቸውን ተግባራት አከናውኗል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን በአፋር ክልል እየለማ ያለ የጥጥ እርሻን በጎበኙበት ወቅት፤ “ አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው ፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ያጎናጸፉንን ሉዓላዊነትና ነጻነት በላባችን ማስከበር ካልቻልን ልናጣው እንችላለን። “ በማለት ድሀና ተመጽዋች አገር ነጻና ሉዓላዊ ሊሆን እንደማይችል አጽንኦት ሰጥተዋል። አመቱን ሙሉ የሚገማሸሩ ወንዞችን ፣ ሊታረስ የሚችል ሰፊ ለም መሬትንና አምራች የሰው ኃይሉን አቀናጅተን በአመት ሁለትና ሶስት ጊዜ በማምረት በምግብ እህል ራሳችንን ችለን ለፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚተርፍና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ አምርተን ከድህነትና ከኋላቀርነት ካልተላቀቅን አያት ቅድመ አያቶቻችን መስዋዕት ሆነው ያቆዩን ነጻነትና ሉዓላዊነት ሙሉ ሊሆን አይችልም ።
ለዚህ ነው የለውጥ ኃይሉም ሆነ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግስት ወደ ኃላፊነት እንደመጣ ድፍረት የተስተዋለባቸውን ማሻሻያዎችን ያደረገው በተለይ የሕዳሴው ግድብ ላይ ተደቅኖበት የነበረን አደጋ የመቀልበስ ፤ የአረንጓዴ አሻራ ፣ የኩታ ገጠም እርሻ ፣ የበጋ ስንዴ ፣ የሜካናይዜሽን ግብርናን ፣ ወዘተረፈ በመተግበር የሚጨበጥ ለውጥ ያመጣው። ሕዳሴውን ከለየለት ክሽፈት ታድጎ ለዚህ ስኬት የበቃው። ከባለፈው አመት ጀምሮ ስንዴን ከውጭ ማስገባት አቁሞ ራሱን የቻለው ፤ በዚህ አመት ደግሞ ወደ ውጭ ለመላክ ያቀደው። ይህ ስኬት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን አካልና መደላድል ነው ። ውስጣዊ ድሎቻችን ለውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን አቅም ናቸው። ከፍ ብዬ የጠቀስኋቸው ሶስቱ ኩነቶች ወደዚህ የሚያደርሱ ናቸው ።
አንድ ምስል ይከስታሉ ያልሁትም ይሄን ነው። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጉምቱ አሜሪካዊ ሪቻርድ ሀስ፤ “ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከአገር ቤት ይጀምራል ፤ “/ FOREIGN POLICY BEGINS AT HOME :…”በሚል መጽሐፉ ይሄን ይተነትናል። ጠቅላይ ሚንስትሩና መንግስታቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከአገር ውስጥ እንደሚጀምር አበክረው ተገንዝበው እየሰሩ ያሉት ለዚህ ነው። ለዛሬ መጣጥፌ መግፍኤ ወደ ሆነው ወቅታዊ ጉዳይ ስመለስ፤ አበውና እማው ነገርን ከስሩ ፣ ውሃን ከጥሩ እንደሚሉት ፤ የመንግስታቱ ድርጅት ሰሞነኛ አሳፋሪና ወራዳ ተግባር የሚጀምረው ኢፍትሐዊና በእኩልነት ላይ ካልቆመው አመሠራረቱ ነው። የCNN የGPS አዘጋጅና የ”ዋሽንግተን ፖስት”አምደኛ የሆነው ፋሪድ ዘካሪያ ፤”THE FUTURE OF FREEDOM: ILLIBERAL DEMOCRACY AT HOME AND ABROAD” በሚል ባደረሰን ማለፊያ በተሰኘው መጽሐፉ፤ “የተባበሩት መንግስታት አሰራር የጨረር የኃይል አሰላለፍ ወካይ ነው።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት ከ70 አመታት በፊት የ2ኛውን የዓለም ጦርነት በአሸናፊነት የደመደሙ አገራት ናቸው ። አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ራሽያና ቻይና። ምክር ቤቱ በአለማችን በኢኮኖሚያቸው 3ኛና 4ኛ ደረጃ የሚገኙትን ጃፓንና ጀርመንን፣ ባለትልቁ ዴሞክራሲ የሆነችውን ሕንድ፣ ላቲን አሜሪካንና አፍሪካን ያገለለ ነው። “ይለናል ። “እንስሳት ሁሉ እኩል ናቸው፤ ግን አንዳንድ እንስሳት ከሌሎች ይበልጥ እኩል ናቸው።”እንደሚባለው የጸጥታው ምክር ቤትም በእነ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ብርቱ ተጽዕኖ ስር የወደቀ ነው። ስለሆነም በመንግስታቱ ድርጅት ስር የሚንቀሳቀሱ ተቋማት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱን ጨምሮ የእነዚህን አገራት ፍላጎት ማስፈጸሚያ እንጂ ገለልተኛና ነጻ ተቋማት አይደሉም። የሰሞኑን በአገራችን ላይ የወጣው ፈራጅና ወንጃይ ሪፖርት የዚህ ፍላጎት ነጸብራቅ ነው። ከዚህ ጀርባ ደግሞ አይደለም ዛሬ አባይን ገድበን ምንጊዜም ተኝታልን የማታውቀው የግብጽ እጅም አለበት።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በስሚ ስሚና የጌቶቻቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም አካሄድሁት ባለው “ምርመራ”፤ ከሽብርተኛው ሕወሓት ጭፍራዎች ባገኘው ሀሰተኛና የተዛባ መረጃ ተመስርቶ በጅምላ የጦር ወንጀል ፈጽማችኋል እያለን ነው። በሰሜን ዕዝ ላይ ትውልድም ታሪክም ይቅር የማይሉት ክህደት የፈጸመው፤ ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ጦርነት የከፈተው፤ በቀደሙት 27 አመታት ደግሞ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና ሰቆቃ የፈጸመው ዘራፊ ከሀዲና አሸባሪው ሕወሓት ተቀምጦ የፌዴራል መንግሥት ኃይሎች በሰብዕና ላይ የተፈጸመ ወንጀል አከናውነዋል ብሎ ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት አግኝቻለሁ ሲል ይሄው ኮሚሽን ተብዬ ልግጫ ይዟል፡፡ ከጅምሩ ገለልተኛ ያልሆነውና አበክሮ ድምዳሜ ላይ ደርሶና ወስኖ አካሄድሁት ያለው ምርመራ እንደጠበቅነው ነጻና ገለልተኛ ያለሆነ ሪፖርት በመፈብረክ ከሽብርተኛው ጎን ቆሟል።
መች በዚህ ያቆምና ኮሚሽኑ በሁለት ወራት ውስጥ በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ባደረግሁት ምርመራ፤ በጦርነቱ ውስጥ የተሳተፉት የፌዴራል መንግሥት፣ የትግራይ ኃይልና የኤርትራ መንግሥት የንፁሃን ግድያ፣ ወሲባዊ ጥቃትና ሰብዓዊነትን የማዋረድ ወንጀሎችን እንደፈጸሙ አምኛለሁ ይለንና ወረድ ብሎ ደግሞ ሕወሓት ነጻ ያወጣና ውንጀላውን መንግስትና ኤርትራ ላይ ይደፈድፋል። ይሄ ነውር ጌጡ የሆነ ኮሚሽን ወረድ ብሎ ደግሞ፤ ራሱ የመንግስታቱ ድርጅትና ሌሎች ተቋማትን በሚጻረር መልኩ፤ የፌዴራል መንግሥት ‹‹የዜጎችን ረሃብ እንደ ጦርነት መሣሪያ›› ተጠቅሟል ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት እንዳገኘ በሀሰት ይወነጅላል። ይሄን ሁሉ የውንጀላ ዶፍ የሚያዘንብብን እንግዲህ በሁለት ወር ለብለብና በሁለት ባለሙያዎች ነው። የምርመራው ሒደት ተቀባይነት ካላቸው ስነ ዘዴዎች ጋር የሚጣረስ፤ በመንግስታቱ ድርጅት ቻርተር ከተቀመጠው የገለልተኝነት መርሕ ጋር የሚቃረን ነው።
ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ላይ አካሂጄዋለሁ ያለው “የምርምራ ሪፖርት” የተሟላ እንዳልሆነ ፤ ከመረጃ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን ተግዳሮት እንደሚገነዘበው ኮሚሽኑ በመጥቀስ “ሪፖርቱ” ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን እና የጦር ወንጀሎች ተፈጽመዋል ለማለት ፍጹም የተሟላ እንዳልሆነ እቅጩን ነግሮታል ። በ“ሪፖርቱ” በአፋር ክልል ላይ ተፈጽሟል ስለሚባለው የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ወንጀል ምንም አለማለቱ አንዱና ትልቁ የሪፖርቱ ጉድለት መሆኑን ፤ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመሆን በጥምረት ያካሄዱት ምርመራ ውጤት የተሟላና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤትም ተቀባይነት ያገኘ፤ ምርመራው ገለልተኛና ግልጽነትን ባሰፈነ መልኩ የተሰራ መሆኑን በመጥቀስ ምስጋና ያተረፈ እንደሆነ ያስታውሳል ።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ በተሰራው የምርመራ ውጤት ላይ ለተደረሰባቸው ግኝቶች የተቀመጡ ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማሳወቅ በዘወርዋራ ይህን የጨረባ ሪፖርት እንደማይቀበለው ይፋ አድርጓል። በቀደመው ሪፖርቱ መሰረት በሁሉም ወገኖች ያሉ ሃይሎች ምክረ ሀሳቡን ተቀብለው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥረ ያቀረበው ኮሚሽኑ ፤ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሚኒስትሮች የተካተቱበት ግብረ ሃይል በማቋቋም የሄደበትን ርቀት እንዲያጠናክር ጠይቋል። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽንም የጋራ ምርመራ ውጤቱ ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ እንዲደግፍና ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በተቀመጠው የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ ለመተባባር ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ ገልጿል። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በሰሜኑ ኢትዮጵያ ያለውን ጉዳይ በጥንቃቄ ሊያይና ሊመረምር እንደሚገባው በማሳሰብ፤ ሁሉንም ተጎጂ የህብረተሰብ ክፍሎችና ክልሎች ፍትሀዊ ሆኖ ሳያዳላ ሊመለከት እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክረ ሀሳብ ሰጥቷል ።
ሕዳሴያችንን የሚያቆም ምንም አይነት የምድር ኃይል የለም !!!
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም